መሪ ሐሳቡ የማን ነው?

0
457

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በኢትዮጵያችን የሴቶች ቀን መከበር የጀመረው በደርግ ዘመነ መንግሥት ከ1968 ጀምሮ ነው። ታድያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ˝የኢትዮጵያ ሴቶች አስተባባሪ˝ የተባለ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ወይዘሪት ንግስት ተፈራ ነበሩ።

ሊቀ መንበሯ በንግግራቸው ˝…በማንኛውም ጨቋኝ ስርዓት የሴቷ ቦታ በቤት ውስጥ በምግብ ማብሰልና በልጅ ማሳደግ የተወሰነ ስለሆነ በፖለቲካ ጥያቄ በአገርና በነጻነት ጉዳይ ላይ ቸልተኛ ነች። ይህም ሳትከራከር፣ ሳትጠይቅና ሳታውቅ አንገቷን ደፍታ እንድትኖር የወንድ ትምክህት ስላስገደዳት፤ በዚህ ሁኔታ ዝቅ ብሎ የሚገኘውን የፖለቲካ ንቃቷን ከፍ ለማድረግ ጭቁን ሴት በጾታዋ መደራጀት አለባት» ነበር ያለት።

በዚህ ንግግር የተጀመረ ጉዞ ዛሬ 43 ዓመታትን አስቆጥሯል። የቀኑ መከበር ለውጥ አመጣ ወይስ አላመጣም? የሚለውን ለለውጥ ተጽእኖ እንደሚኖረው በማመን መልሱን ለጥናት ባለሙያዎች እንተወዋለን። እኔን ግን ግርም እያለኝ ያለው የመሪ ሐሳቡ ወይም የመሪ ቃሉ ነገር ነው። ይህ መሪ ሐሳብ የማን እንደሆነና ለማንስ እንደሆነ ተገልፆልኝ አያውቅም።

ቀኑን በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መነሻ ከሆነው ጉዳይ በመነሳት ምሁራን ትንታኔ ሊሰጡበት ይችላሉ። ምን ፋይዳ አለው የሚለው ላይም እንደዛው። ከዛ ባለፈ በአገራችን ቀኑን አስበን የምንውልበት መንገድስ እንዴት ነው? በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ʻከለር ዴይ…ዋተር ዴይʼ እያሉ ከሚያከብሩበት መንገድ በምን ይለያል? የሚለውም ላይ አስተያየት ያለው ሊናገር ይችላል።

እዚህ ላይ ይህን ሁሉ ሊጠቀልል የሚችለው መሪ ሐሳቡ ነበር ብዬ አምናለሁ። ˝ኢትዮጵያ ትቅደም˝ እንደሚለው ዓይነት መፈክር፤ መሪ ሐሳብ ከልብ የማይጠፋና ለለውጥ የሚያነሳሳ ሊሆን ያስፈልጋል። መሪ ሐሳብ እንደ ሥያሜው መሪ መሆን ያለበት ሐሳብ ነው። በአንጻሩ የሴቶች ቀንን በተመለከተ ከተሰጡ መሪ ሐሳቦች መካከል የተወሰነውን ተመልከቱ፤

˝መልካም አስተዳደርን በማስፈን የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ! በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን! ተግባራዊ ለዉጥ ለሴቶች ዕኩልነት መረጋገጥ! የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳፎና ተጠቃሚነት!…˝ እነዚህ መሪ ሐሳቦች እውነት መሪ ናቸው?

በተለይ በዚህ ዓመት፤ ሴቶች ወደ ሥልጣን መጥተው አይተናል። ምንም እንኳን ከታች ያሉ አደረጃጀቶች አሁንም በጥያቄ ውስጥ ቢሆኑም፤ ለሁሉም ነገር መጀመሪያ አለውና በዛ መጀመሪያ ላይ ነን። ታድያ ዛሬም መሪ ሃሳባችን ለምን «ትኩረት ስጡን?» ይሆናል? ለምን ትኩረት እንዲሰጡ የፈለግናቸውን አካላት ትኩረት የሚወስድ አልሆነም? የዘንድሮው የሴቶች ቀንን ስናከበር መሪ ሐሳቡ ˝የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት˝ የሚል መሆኑን ልብ ይሏል!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here