የኢኮኖሚ አማካሪዎች ካውንስል ለማቋቋም ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሐሳብ ቀረበ

0
505

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ሊረዳ የሚችል የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ካውንስል ለማቋቋም ጥያቄ መቅረቡን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።

ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በሦስት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የቀረበው ጥያቄ መልስ ባያገኝም ሐሳቡ መጀመሪያ የቀረበው በቀድሞ የአሜሪካ አምባሰደር በነበሩት ካሳ ተክለ ብርሃን እንደሆነ ታውቋል።

ካውንስሉም በአገር ውስጥ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ምሁራኖች በኢኮኖሚ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያመቻች መሆኑ በቢሮ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ተገልጿል።

በተጨማሪም በዓለም የንግድ ገበያ መልካዓ ምድራዊ ፖለቲካ ምክንያት የሚመጡ ለውጦችንና ችግሮች ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ቅድሚያ በመከላከል ረገድ ካውንስሉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል፤ አገሪቱ ለማሳካት በእቅድ ያስቀመጠቸው ግቦች ለመምታት ካውንስሉ መረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት በማድረግና አማራጮችን በማቅረቡ ሊረዳ እንደሚችል በምክረ ሐሳቡ ላይ ቀርቧል።

በኢትዮጵያና በተለያዩ የውጪ አገራት ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ምሁራኖች በማሳተፍ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል የተባለው ካውንስሉ መንግሥት በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ለመተግበር ያቀዳቸው እንደ የአክሲዮን ገብያ (ʻሰቶክ ማርኬትʼ) እና በቅርቡ ለመተግበር ያሰበው ፕራይቬታዜሽን ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማሳካት ይረዳል ተብሏል።

ምክረ ሐሳቡ ላይ እንደተገለፀው ካውንስሉ ተቀባይነት ካገኘ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አማካሪ ሆኖ የሚያገለግለው ለኹለት ዓመት ይሆናል። እንደ ሕንድ፣ አሜሪካ እና ማሌዥያ ካሉ አገራት ልምድ በመቅሰም ውጤታማነቱን ተገምግሞ ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ ካውንስል በቋሚነት ቢቋቋም የአገሪቱን ምጣኔ ኢኮኖሚያዊና ተያያዥ ተግዳሮቶች ለመፍታት ወሳኝ እንደሆነ በምክረሐሳቡ ላይ ተገልጿል።

ካውንስሉ ተቀባይነት ካገኘ በችሎታ መሰረት የሚመረጡ እና ጊዜያዊ አባላት እንደሚኖሩት ለማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ፤ ምክረ ሐሳቡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ መላኩን ብታረጋግጥም የተቋሙ ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት ንጉሱ ጥላሁን ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ፤ የቀረበው ፕሮፖዛል በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ትዕዛዝ በከፍተኛ አማካሪያቸው ማሞ ምህረቱ እንዲታይ መወሰኑን ምንጮቻችን ቢገልፁልንም ይህንን ማረጋገጥ አልቻለንም። ስለ ጉዳዩ ማሞን አዲስ ማለዳ በፅሁፍና በመልዕክት ለማግኘት ብንሞክርም መልስ ሊሰጡን አልቻሉም።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከሚያዝያ 2010 አንስቶ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደተሻለ አቅጣጫ ለማስኬድ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል። ለአብነትም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ባቡር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው አይዘነጋም ።

በተጨማሪም የቴሌኮምን፣ አቬሽን እና የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭና በትውልድ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ መንግሥት ረቂቅ አዋጆችን ማዘጋጀቱ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here