6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከግብር ጋር የተያያዘ ውዝፍ ዕዳ አልተሰበሰበም

0
559

በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ጥር 30 ድረስ ባለው ጊዜ ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ ውዝፍ የግብር ዕዳ መመዝገቡን በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የ30 ቀናት የመክፈያ ጊዜ የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች፣ በቀነ ገደቡ ሳይጠቀሙ ካለፈ በኋላ ያለአግባብ ግብር ተወስኖብናል በሚል አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜም እንደ ውዝፍ ዕዳ ይቆጠራል።

ግብር ከፋዮች ያለአግባብ ተወስኖብኛል በሚል አቤቱታቸውን ፍርድ ቤት ድረስ በመክሰስ ማሰማት እንደሚችሉ የሚታወቅ ሲሆን፤ በአሁን ላይ ግን የቅርንጫፍ ቢሮው መረጃ እንደሚያመለክተው አቤቱታቸው ውድቅ የተደረገና የፍርድ ቤት ጉዳያቸው ተጠናቆ እግድ ላይ የደረሱ 128 ግብር ከፋዮች አሉ። ይህንም ተከትሎ፣ በመንግሥት በኩል ሊሰበሰብ የሚገባው ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር እስከ ጥር 30/2011 ድረስ አለመሰብሰቡን በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ቢሮ የታክስ ኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ማህሌት አምዴ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ግብራቸውን ሳይከፍሉ 30 ቀናት ካለፈባቸው ድርጅቶች እስካሁን 45 ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን ማህሌት ለአዲስ ማለዳ የገለፁ ሲሆን፤ ወደ አቤቱታ ባለመሄዳቸውና የእግድ ደረጃ ላይ ስላልደረሱ፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ተሰብሳቢ ገቢ ነው ተብሎ እንደሚታሰብ አመልክተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ 30 ቀናት ያልሞላቸው ግን እስካሁን ግብራቸውን ያልከፈሉ 52 ድርጅቶች ሲኖሩ ተሰብሳቢ ግብርም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ይጠበቅባቸዋል።

በሌላ በኩል እገዳ ላይ ሳይደርሱ አቤቱታቸውን እያሰሙ ያሉ ግብር ከፋይ ድርጅቶች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ውስጥ በቅርንጫፍ ቢሮው አቤቱታ ላይ ያሉት 61 ግብር ከፋዮች ናቸው። ውዝፍ ዕዳቸውም አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ደርሷል።

በተያያዘ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ውዝፍ ዕዳ እያለባቸው የግብር ይግባኝ ሒደት ላይ ያሉ 66 ግብር ከፋይ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን፤ በዋና መስሪያ ቤት አቤቱታ ላይ ያሉ 10 ድርጅቶች ደግሞ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ውዝፍ ዕዳ እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ከቢሮው ያገኘቸው መረጃ ያመለክታል።

ከግብር አከፋፈልና አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የገቢዎች ሚኒስቴር የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት አድማ በሚመስል መልኩ ግብር የማይከፍሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖራቸውን አሳውቆ፣ አንዳንዶቹ ጭራሽ ‹እሰሩን እንጂ አንከፍልም› እስከማለት የደረሱበት ሁኔታ እንዳለ የገቢዎች ሚኒስቴር አዳነች አቤቤ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here