ናይል ኢንሹራንስ በካሳ በተፈጠረ አለመግባባት ሰራተኞቹ ታግተውበት ነበር

0
699

– የኩባንያው ተሽከርካሪ አሁንም በአጋቾች እጅ ይገኛል

በመድን ካሳ ክፍያ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ የናይል ኢንሹራንሰ ኹለት ሰራተኞቹ የካሳ ይገባናል ጥያቄ ባነሱ ሰዎች ከታገቱ በኋላ የያዙት ተሽርካሪ ተነጥቆ መለቀቃቸውን ኩባንያው አስታወቀ።

የኢንሹራንስ ኩባንያው ደንበኛ የነበሩት ከድር ደኒስ የተባሉ ግለሰብ ለጠፋው ንብረታቸው ካሳ እንዲከፈላቸው ከአንድ ዓመት በላይ ሲደራደሩ ቢቆዩም መስማማት ስላልቻሉ እገታውን ማከናወናቸውን አምነዋል።

የኩባንያው አሽከርካሪ ቴዎድሮስ ደስታና ባልደረባቸው ሳሙኤል ካሳዬ የተባሉ ግለሰቦች ታግተው የነበረው በአፋር ሎጊያ አካባቢ ሲሆን በ24 ሰዓታት ውስጥ ቢለቀቁም እገታውን ባከናወኑት ከድር፣ ማንነታቸው ባልታወቁ እና ሌሎች ተሸከርካሪ በያዙ ሰዎች የናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ ንብረት የሆነ ተሸከርካሪ እንደተወሰደ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ኩባንያውም ይህንኑ አምኗል።

ይህ ዓይነቱ ድርጊት የማይገባና ሕገ ወጥ ነው በሚል የኮነነው ኩባያው ሰራተኞቹና ንብረቱ ላይ የተፈፀመው ድርጊት ያልተገባና በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው ብሏል።
ይሁን እንጂ እገታውን ከግብረ አበሮቻቸው ጋር መፈፀማቸውን ለአዲስ ማለዳ ያመኑት ከድር ባጋጠማቸው ያልታሰበ አደጋ ምክንያት መኪናቸው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ካሳ ቢጠይቁም በፍላጎታቸው መሰረት መልስ ስላልተሰጣቸውና ጉዳዩም ከአንድ ዓመት በላይ ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩ ወዳልተገባ ደረጃ ሄዷል ብለዋል።
የተሸከርካሪያቸው ዋጋ ‹‹750 ሺሕ ብር ቢሆንም ድርጅቱ ከብዙ ቅሬታዎች በኋላ 450 ሺሕ ብር ሊከፍለኝ ቢስማማም ይህ ሌሎች የኢንሹራንስ ድርጀቶች ከሚከፈሉት አንፃር ያነሰ መሆኑን ብገልፅም መልስ ሊሰጠኝ አልቻለም›› ሲሉ ከድር አማረዋል።

በመጨረሻም ጉዳዩ በሽማግሌ እልባት እንዲያገኝ ከድርጅቱ የሚሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም ቃል የተገባው ነገር ባለመፈፀሙ ንብረቱን ለማገት መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በተቃራኒው ተሸከርካሪያቸው ላይ ጉዳት ደረሰበኝ የሚሉት ግለሰብ ሊከፈላቸው የሚገባው የካሳ መጠን ላይ ካልተስማሙ ፍርድ ቤት በሚያቀርቡት ክስ መጠየቅ እየቻሉ እገታ ማከናወናቸውን ድርጅቱ ኮንኗል። ይህም መደረጉ ሕጋዊ ስላልሆነ የሚሌ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንዲያጣራ ቢጠይቁም አቤቱታቸው መልስ እንዳላገኘ ለአፋር ብሔራዊ ክልል የካቲት 11/2011 ኩባንያው በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

አሁንም መፍትሔ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የገለፁት የኢንሹራንስ ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ንጉስ አንተነህ በአፋር ክልል ይህ አይነቱ ችግር ሲገጥማቸው የመጀመሪያ እንዳልሆነና ሥራቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት አንዳንድ ሰዎች በመድን ካሳ ክፍያ ምክንያት ቅርንጫፋቸውን አስከማዘጋት ደርሰው እንደነበር ያስታወሱት ንጉስ ችግሩን በሕግ መፍታት እየተቻለ ኃይል መጠቀም ተገቢ አይደለም ብለዋል። ‹‹ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የወረዳው ፖሊስ ከአጋቾች ጎን መቆሙ›› አንዳሳዘናቸውም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ናይል ኢንሹራንስ በአገሪቷ ከሚገኙ 16 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን 42 ቅርንጫፎች አሉት። በባለፈው በጀት ወደ 63 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር አካባቢ ያልተጣራ ትርፍም አግኝቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here