ባለመረጋጋት ትምህርታቸው ለተስተጓጎለባቸው ተማሪዎች የሚራዘም የአገር ዐቀፍ ፈተና የለም

0
581

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በነበረው አለመረጋጋት የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው ለወራት ርቀው ለነበሩ ተማሪዎች የሚራዘም አገር ዐቀፍ ፈተና እንደማይኖር የትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ባለሙያዎች በበኩላቸው ለወራት ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች እንዳሉ እየታወቀ ፈተናውን አለማራዘም ስህተት ነው ብለዋል።

በትምህርት ገበታቸው ላይ ለወራት ያልነበሩ ተማሪዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ተምረው የአገር ዐቀፍ ፈተናውን በተያዘለት ጊዜ እንዲወስዱ እየተሰራ ነው ሲል ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ለሦስትና ከዚያ በላይ ወራት የመማር ማስተማር ሒደቱ የተቋረጠባቸው አንድ ሺህ 200 ትምህርት ቤቶች በመላው አገሪቱ እንደነበሩ ለመረዳት ተችሏል። በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶች መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክተር ዮሐንስ ወጋሶ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የትምህርት መስተጓጎል የነበረባቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት የጊዜ ሰሌዳውን በማሻሻል የማካካሻ ትምህርት እንዲሰጡ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ሥራውም በተቀላጠፈ መንገድ እየተሰራ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ዮሐንስ ገለጻ የማካካሻ ትምህርቱ ሙሉ ቀን ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ቅዳሜ እና እሁድን በመጠቀም የሚሰጥ ሲሆን ፤ ግማሽ ቀን በሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ተጨማሪ የትምህርት ሰዓታትን በመጠቀም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በማስተማር የሚከወን ነው።

ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመግባባት ወደ ሥራ ተገብቷል የተባለው ይህ የማካካሻ ትምህርት አሰጣጥ በተገቢው መንገድ እየተሰጠ እንደሆነ ለመገምገም ከአንድ ወር በኋላ ከትምህርት ሚኒስቴር የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች የመስክ ምልከታ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና ፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸው በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርትና የባህሪ ጥናት መምህሩ ውቤ ካሳየ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አያይዘውም ‹‹የትምህርት ጥራቱ መውደቁ የታወቀ ነው›› ያሉት መምህሩ ‹‹ከዚህ በላይ ደግሞ ይህ ዓይነት አለመረጋጋት ሲፈጠር በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በመምህራንም ላይ ስነ ልቦናዊ ቀውስ ስለሚያስከትል የወደቀውን የትምህርት ጥራት ጭራሽ የሚቀብር›› እንደሆነ ያሰምሩበታል።

መምህሩ እንደመፍትሔ የሚያነሱት መንግሥት ከሁሉም አስቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚኖርበትና ቀጥሎ ደግሞ የተማረውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ የታሰበውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር በመለወጥ ከስር ጀምሮ መሥራትን ነው። ይሁንና በጸጥታው ችግር ምክንያት ተማሪዎች ለወራት ከትምህርት ርቀው እንደነበር እየታወቀ እንዲፈተኑ ማድረግ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳልሆነም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ጥርት ያለ የተፈታኞች ቁጥር እንደሌለው ለአዲስ ማለዳ ገለፆ፣ በየዓመቱ ከቀዳሚው ዓመት የ10 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ ስለሚገመት ይህ ታሳቢ ተደርጎ ፈተናዎች ማተሚያቤት መግባታቸውን አስታውቋል። ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ አንድ ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተናን የወሰዱት ደግሞ 282 ሺሕ ተማሪዎች መሆናቸውን ያስታውሳል። ዘንድሮም የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከግንቦት 21 እስከ 23 የሚሰጥ ሲሆን የ12ኛ ክፍል ደግሞ ከግንቦት 26 እስከ 30 እንደሚሰጥ መርሀ ግብር ወጥቶለታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here