ቆጠራው በብቃት ለመወጣት በርካታ ሥራዎች መሰራት አለባቸው

0
352

የአንድ አገር የልማት ዕድገት አቅጣጫ የሚመራው አገሪቱ በምትቀርፃቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም እነሱን ለማስፈጸም በምታዘጋጃቸው ዕቅዶች መሆኑ ይታወቃል። የሚዘጋጁት የአገሪቱን ወቅታዊና ተጨባጭ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታዎች ከሚያንጸባርቅ ስታትስቲካዊ መረጃ በመነሳት ነው።

በሌላ አነጋገር በዕቅድ የሚመራ የትኛውም የልማት ዘርፍ ቀጣይነት ረጅም የዕድገት ጉዞ በማለም በየዕርከኖቹ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን እያስወገደ ወደ ታሰበው የዕድገት ግብ ለመሸጋገር ከፍተኛ መረጃ ሊኖር ይገባል።

ባለንበት ፈጣን ዘመን ልማትና ብልጽግና ሊረጋገጥበት የሚችልበትና ፕሮግራምና ፖሊሲ ለመንደፍ፣ የዕድገት ለማዘጋጀት በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተከትሎ ውጤቱን ለመገምገም የስታትስተክስ መረጃዎች አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20/2011 ለማካሔድ የዝግጅት ሥራዎችን የማጠናቀቅ ምዕራፍ ይፋ ሲያደርግ ቆጠራው ወቅታዊ፣ ጥራት ያለው፣ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው ለማድረግ የአሰራር ማሻሻያዎች እንዳደረገ ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም በወረቀት ይካሔድ የነበረው የመረጃ አሰባሰብ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲካሔድ፣ በአንድ ቋንቋ ይደረግ የነበረውን የቆጠራ አሰራር በአምስት ቋንቋዎች እንዲካሔድና የመረጃ ደኅንነትና የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርቷል።

ለቆጠራው በአጠቃላይ 3.5 ቢሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን በተጠባባቂነት ደግሞ 946 ሚሊዮን ተይዟል። 200 ሺሕ የቆጠራ ጣቢያዎች፣ 152 ሺሕ የቆጠራ ማዕከላት የተዘጋጁ ሲሆን ከ190 ሺሕ በላይ ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች እንደሚሰማሩ ታውቋል። በተጨማሪም 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒውተሮች እንዲሁም 126 ሺሕ ኤሌክትሪክ ቢጠፋ በሚል ተንቀሳቃሽ ችርጀሮች መዘጋጀታቸውን ታውቋል።

ሌላው የቆጠራው ሥራ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት እንዲካሔድ መደረጉ የመረጃውን ተአማኒነትና ፍጥነት እንደሚያግዝ ቢታወቅም አሁንም በሕዝብ ዘንድ የሚቀርቡ በርካታ አቤቱታዎች አሉ። ስለዚህ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች በመኖራቸው አሳማኝና ፈጣን መልስ ካልተሰጠ የሚደረገውን የቆጠራ ሒደት ውስብስብ ሊያደርገው ስለሚችል ከወዲሁ ቢታሰብበት መልካም ነው።

ይህ ትልቅ የአገር ሀብት የሚፈስበት የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚፈለገውን አገራዊ ውጤት ካላመጣ ብክነቱ በከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሊሰበሰብ የታለመው መረጃ ወደፊት ለሚታቀዱ አገራዊ ዐቅዶች ላይ ሳንካ ይሆናል። ከዚህ ቀደም የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ የአማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ የቆጠራውን ተአማኒነት ለመጨመር መሰራቱን ቢነገርም የተደረሰበት ሁኔታ ግን በግልጽ ሲነገር አይሰማም። የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለልማት የዕቅድ ዝግጅት፣ ለፖሊሲ ቀረጻ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።

የሕዝብና ቤት ቆጠራው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሔድ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች የኃይማኖት ተቋማት ሕዝቡን በማስተማርና በመቀስቀስ ለቆጠራው መሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ መደረጉ ጥሩ ነው። በተዘረጋው ዘመናዊ አሰራር ከዚህ ቀደም የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙም ይታመናል።
እስካሁን ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶችና ያልቆመው የዜጎች መፈናቀል በቆጠራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው እንደማይቀር፣ መንግሥትም ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚሰጥ መግባባት ላይ መደረስ እንዳለበት ይታመናል ።

ከዓመት ዓመት የጊዜ ሰሌዳው ሲገፋ የቆየው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተያዘለት ቀን መቆረጡ እውነት ይመስላል። ሆኖም አገሪቱ ባልተረጋጋችበት ወቅት መካሔዱ ሌላ አለመረጋጋት ይፈጥራል የሚል ሥጋት እና ከዚህ በኋላ ሊራዘም አይችልም የሚሉት አጣብቂኞች እንቆቅልሽ ፈጥረዋል። በመሆኑም መንግሥት በዚህ አገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ቁርጠኛ ተሳትፎ በማድረግ ለውጥኑ መሳካት የአንበሳውን ድርሻ ሊይዝ ይገባል።

በሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይ በመሳተፍ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚሰማሩት ባለሙያዎች ሕጋዊ ከለላ ከመስጠትም አንፃር መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here