የሕግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም! ሕግ የሰውን ልጅ መብት ማስከበሪያና ነፃነቱን ማረጋገጫ ነው!

0
731

መነሻቸውን በቅርቡ በለገዳዲና ለገጣፎ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው በሚል ቤቶች እንዲፈርሱ በማድረግ ነዋሪዎችን ስላፈናቀለው ድርጊት ያደረጉት ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)፥ ማፈናቀል የሕግ ተጠያቂነት እንደሚያመጣ በየአካባቢው ያሉ አስተዳዳሪዎችን ማወቅ እንዳለባቸው ያስጠነቅቃሉ። ለአስረጂነት የሰሜን አሜሪካንና አውሮፓን ተመክሮ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ካለው ጋር በማሰናሰል በየትኛውም ደረጃ ያሉ አስተዳደሪዎች እውነተኛ የሕዝብ አገልጋዮች ለመሆን የተዘጋጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ሲሉ ይሞግታሉ።

 

የሕግ የበላይነት መከበር (The Rule of Law) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በማዕከለኛው አውሮፓ ዘመን በዚያን ጊዜ የፍጹም ነገሥታቶችና የመሬት ከበርቴዎች በአርሶ አደሩ ላይ የፈለጋቸውን ነገር ያደርጉ ስለነበርና፣ በዚህም የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች መብቱ የተገፈፈው አርሶ አደር ለመብቱ ትግል ሲያደርግ የተመለከቱና የተመራመሩ የእንግሊዝ ሊኂቃን፣ አንድ ኅብረተሰብ በዚህ ዓይነት ስርዓት አልባ ሁኔታ እንደማኅበረሰብ ሊኖርና ኑሮውንም ለማሻሻል እንደማይችል በመረዳት የሕግ ስርዓት መከበር እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ።

ይህም ማለት፣ ማንኛውም ዜጋ በአምላክ አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ የመንግሥታት ኃላፊነትና ግዴታ የማንኛውንም ዜጋ መብት ማስከበር ነው። በዚህ ዓይነቱ የመብትን ማወቅ ሒደት ውስጥ የግል ሀብት ወሳኝ ሚናን ቢጫወትምና፣ የግል ሀብት መኖር እንደ ተፈጥሮአዊ ነገር ተቆጥሮ ቢወሰድም፣ መንግሥትም ሆነ ሕግ ከማንኛውም ዜጋ በላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ፤ በተለይም ጆን ሚልተን የተባለው ʻዘ ፓራዳይዝ ሎስትʼ በሚለው መጽሐፉ ውስጥ በደንብ አስቀምጦታል። በእሱ እምነትም ማንኛውም አገዛዝም ሆነ እራሱ ንጉሡም ቢሆን የሕዝብ አለኝታና መብቱን የሚያስከብሩ እንደመሆናቸው መጠን የፈለጋቸውን ነገር ማድረግ አይችሉም። የሕዝብን መብት የሚጥስና በሆነው ባልሆነው ነገር የሚያሰቃይ አገዛዝና ንጉሥ መቀጣት እንዳለበት ለሚልተን ግልጽ ነበር።

በጊዜው ይህ ዓይነቱ በእነ ጆን ሎክና ሆብስ እንዲሁም በሚልተንና የኋላ ኋላ ደግሞ በእነ አዳም ስሚዝ ከገበያ ኢኮኖሚና ከሀብት ክምችት ጋር እያደገና እየዳበረ የመጣው አስተሳሰብ፣ በጊዜው የከበርቴውን የበላይነት የሚያንፀባርቅና ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በፊዩዳሉ ስርዓት ላይ ድልን መቀዳጀቱን የሚያበስር ሁኔታ ነበር። የአውሮፓው ማኅበረሰብ በካቶሊክ የወግ አጥባቂ ሃይማኖት መሪዎችና በመሬት ከበርቴው መደብ መሰቃየቱ ማቆም እንዳለበትና ዘመኑም የአብርኆት (Enlightenment) የሐሳብ የበላይነት ዘመን የታወጀበት ጊዜ ነበር።

በዚህ ዓይነቱ እልክ አስጨራሽና የኋላ ቀር ኃይሎችን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አስወግዶ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተገነባ አገር መመስረቱ የጊዜው አዋጅ በመሆን ይህ ዓይነቱ የነፃነት ብርሃንና እየዳበረ የመጣው ዕውቀት በተለያየ ፍጥነት የብዙ አውሮፓ አገሮችን ቀስ በቀስ በማዳረስ ለኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት ጣለ። በዚህም አማካይነት ጥበብና ክላሲካል ሙዚቃ እንዲሁም ሥነ ጽሁፍ ሲያብቡ፣ እያንዳንዱ ግለሰብም እውነተኛ ነፃነት የማግኘት ዕድል አጋጠመው። ቀስ ቀስ እያለም የማቴሬያል ሁኔታዎች ሲሻሻሉና በአገር ደረጃም የባቡር ሃዲድ ሲዘረጋ ማንኛውም ዜጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር ኑሮውን ማሸነፍ እንደሚችል በመረዳት በግለሰብ ታታሪነትና በመንግሥት ጣልቃ ገብነት አዲስ የኢኮኖሚ ስርዓትና ልዩ ዓይነት ኅብረተሰብአዊ ግኑኝነትና እሴት በመፈጠር ሕዝቡን ማዳረስ ቻለ። ኅብረተሰቡም በጎሳ የተከፋፈለና በተለያየ ቋንቋ በመነጋገር የማይግባባ ሳይሆን፣ አንድ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ በመዳበርና ተቀባይነት በማግኘት ኅብረተሰብአዊ ዕድገትን ማምጣት ተቻለ።

 

‘ዘ ሩል ኦፍ ሎው’ ማለት የሕግ ስርዓት መከበር አለበት፤ ማንኛውም ዜጋ መብቱንና ግዴታውን ይወቅ ማለት እንጂ፣ የሕግ ተገዢ በመሆን እየተሸማቀቀ ይኑር ማለት አይደለም

 

ከዚህ አጭር ሐተታ ስንነሳ በአውሮፓ የኅብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ውስጥ የሕግ ስርዓት መኖርና መከበር አለበት ብለው በተነሱና በሰበኩ፣ የአውሮፓውያን ምሁራን ዘንድ ሕግ ከሰዎች በላይ በመሆን ሥልጣንን በአጋጣሚም ሆነ በምርጫ የያዘ አገዛዝ ወይም ግለሰብ እያንዳንዱን ዜጋ እንደፈለገው ሊያሽከረክር ይችላል ብለው ያስተማሩበት ጊዜና ቦታ የለም። ሕግም የሚጣስ ከሆነ እንደየሁኔታው ከሕግ አንፃር በማጣራት ሚዛናዊ ፍርድና እርምጃ የሚወሰድ እንጂ ዝም ብሎ የሕግ የበላይነት ተጥሷል ተብሎ በደካማ ዜጋ ላይ የሚጣል የዱብ ዕዳ የለም። ፅንሰ ሐሳቡም ቃል በቃል ሲተረጎም የሕግ የበላይነት የሚል ሳይሆን፣ ʻዘ ሩል ኦፍ ሎውʼ ማለት የሕግ ስርዓት መከበር አለበት፤ ማንኛውም ዜጋ መብቱንና ግዴታውን ይወቅ ማለት እንጂ፣ የሕግ ተገዢ በመሆን እየተሸማቀቀ ይኑር ማለት አይደለም።

ይሁንና ግን እንደነዚህ የመሳሰሉ ፅንሰ ሐሳቦች ከትርጉማቸው እየተዛነፉና ሌላ ትርጉም እየተሰጣቸው፣ አንዳንድ የበላይነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎችና አገዛዞች የሰውን መብት የሚጥሱበትና፣ አንዳንዶች ደግሞ ጠብመንጃ በማንገት ተራውን ሕዝብ የሚያስፈራሩበትና እንዲያም ሲል የሚገድሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአገራችን ምድር የተስፋፋው ጥራዝ ነጠቅነትና የኅብረተሰብን አገነባብ ታሪክ ያላገናዘበ አተረጓጎም -ለምሳሌ የማንነት ጥያቄ ወይም ደግሞ አዲስ አበባ ድሮ ፍንፍኔ ተብላ ነበር የምትጠራው- እያሉ ማውራትና ማስፈራራት ሰፊው ሕዝብ ተንሳፎና ተሳቆ እንዲኖር የሚያደርገው አደገኛ የጥራዝ ነጠቆችና የወጣት ፋሽስቶች ዘመቻ ነው። ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ጥራዝ ነጠቅነትና አምባገነንነት ወይም የጥቂቱ ንዑስ ከበርቴ ፋሺስታዊ ድርጊት እልባት እስካላገኘ ድረስ ከፍተኛ የሆነ ኅብረተሰብአዊ ውዝግብ መፈጠሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ዛሬ እጠቀማለሁ፣ የበላይነትንም በመቀዳጀት የሕዝባችንን ዕድል እንደፈለጉት አሽከረክራለሁ የሚለው ኃይል እራሱም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባና፣ እወክለዋለሁ የሚለውን ብሔረሰብ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው።
የለገጣፎና የለገዳዲ ጉዳይ! ሕዝብን የማፈናቀሉ ሁኔታ!

የአውሮፓውን የከተማ አገነባብ ታሪክ ስንመለከት፣ በተለይም ከዐሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተካሔደውን የከተማ አገነባብ ታሪክ ለተመለከተ በብዙ ምርምርና ጥናት በዕቅድ ከተማዎች እንደተቆረቆሩና ቤቶችም እንደተገነቡ መገንዘብ እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ንቃተ ሕሊና የነበራቸው ምሁራንና ሳይንቲስቶች ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ የአገርንና የሕዝብን ጉዳይ አስቀድመው በማየታቸውና ሳይታክቱ በመሥራታቸው ውብ ውብ ከተማዎችን ገንብተው አልፈዋል። ስለሆነም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያደገ አዳዲስ ትውልድ የሕንፃ አሰራር ተቋማት በመክፈትና በመመራመር በቁጥር እየጨመረ ለሚመጣው ህዝብ ቤቶች በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ተሰርቶ ሊቀርብ የሚችልበትን ሁኔታ ማጥናትና ተግባራዊም በማድረግ ኅብረተሰቡ የተስተካከለ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ችሏል። እኛም ከአገራችን ወጥተን በየአገሩ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የዚህ ዓይነቱ የሰለጠኑ ኑሮ ተካፋይ በመሆን አነሰም በዛም ደልቶን እንኖራለን። በደንብ የተጠና ከተማና የቤቶችና የሕንፃዎች አሰራር እንደባሕል በመውሰዱ ማንኛውም ዜጋ ኅብረተሰቡን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች እንዳይሰራ ይቆጠባል። ግለሰቦችም ቤት ለመስራት በሚፈልጉበት ጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥናት በሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች አማካይነት እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ ቤት የመሥራት ፈቃድ ይሰጣቸዋል። መሬትም በማጭበርበር አንዱ ለሌላው የሚሸጠው ሳይሆን አንድ ቤት ከመሰራቱ በፊት ቤት ለመሥራት የሚፈልገው ሰው መሬቱ የራሱ ለመሆኑ የሚያረጋግጥ ካርታ ማቅረብ አለበት።

ወደ አገራችን፣ በተለይም ደግሞ ወደ ለገጣፎና ለገዳዲ ስንመጣ ችግሩን የፈጠሩት ራሳቸው ቤት ሰርተው መኖር የጀመሩትና፣ ቤታቸው እንዲፈራርስ የተደረገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ፣ ዋናው ተጠያቂዎች በየአካባቢው ያሉትና አካባቢውን የሚያስተዳድሩት አንዳንድ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ በአሁኑ አጠራር ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ካድሬዎች ናቸው። አንዳንድ ካድሬዎች ሥልጣናቸውን በመጠቀም መሬት ለመከራየት ወይም ለመግዛት ለሚፈልግ ሰው መሬትን በብዙ ሺሕ ገንዘብ በመሸጥና ቤት እንዲሠራበት በማድረግ ቤት ካለዕቅድ እንደተሠራ ይታወቃል። በሌላ አነጋገር ለዚህ ዓይነቱ ዕቅድ አልባ የቤት አሠረራ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው በብዙ ሺሕ ገንዘብ አውጥተው መሬት ተመርተውና ሠርተው የሚኖሩት ሰዎች ሳይሆኑ የከተማዎቹ አስተዳዳሪዎች ናቸው። ይህ መሆኑ እየታወቀ የተሠሩት ቤቶች ከሕግ ውጭ የተሠሩ ናቸው እያሉ ቤቶችን ማፍረስና ነዋሪውን ሰው ከነልጆቹ በየሜዳው እንዲጣል ማድረግ ምን ዓይነት ፈሊጥ ነው?

እዚህ ላይ በግልጽ መታወቅ ያለበት ነገር ከአንድ ብሔረሰብ የተውጣጣና ተከልሎ የሚኖር ጎሣ በባሕል፣ በምጣኔ ሀብት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በፍጹም ሊያድግ አይችልም። የሥልጣኔና የኅብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ላጠናና ለተከታታለ አንድ አገር ሊያድግና ሕዝቡም ንቃተ ሕሊናው ሊጎለምስ የሚችለው የተለያዩ ሐሳቦች ከውጭ መጥተው አገር ውስጥ ካለው ጋር ሲቀላቀሉና ሲዋሐዱ ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካን ጎልቶ የሚታይ ነው። ምዕራብ አውሮፓ ከግሪክ በመጣ ሳይንስና ፍልስፍና አማካይነት ነው ከጨለማው ዘመን በመላቀቅ ቀስ በቀስ የሥልጣኔን ብርሃንን ማየት የቻለውና በቴክኖሎጂ ያደገው።

ከዚህም በላይ በየአንዳንዱ የምዕራብ አውሮፓ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ዕድገት ሊመጣ የቻለው ከሌላ ቦታ ፈልሰው የመጡ ሕዝቦች ከአገሬው ሕዝብ ጋር በመጋባትና በመዋለዳቸው ነው። አሜሪካም እንደዚሁ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው ከውጭ በመጣ ዕውቀት አማካይነት ነው። ዛሬም ቢሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከየአገሩ በመምጣትና እዚያው በመኖር የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆን ችለዋል። እዚህ እኛ የምንኖርበት በርሊን ከተማ ብቻ ከ150 አገሮች የመጡ ሰዎች በመኖር ለኢኮኖሚው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን የባሕል እመርታን ሰጥተውታል። የኢጣሊያ፣ የቱርክ፣ የስፔይን፣ የኢትዮጵያና የሌሎች አገሮች የምግብ ቤቶች በብዛት ይገኛሉ።

በመንግሥት መስሪያ ቤትም ሆነ በግል ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ አገር ሰዎች ይገኛሉ። አብዛኛዎችም የመምረጥና የመመረጥ መብትና ዕድል አላቸው። ከዚህ ስንነሳ ከተማን ከተማ የሚያደርገው የተለያየ ሕዝብና የተለያየ ባሕል ሲኖሩና ሲዳብሩ ብቻ ነው። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ሲቪክ ማኅበረሰብ ሊዳብርና ተከታታይነት የሚኖረው ሥራ ሊሠራ የሚችለው። በአንፃሩ በዚህ መልክ የማይደራጅና የማይታቀድ ከተማ የድንቁርናና የድኅነት ሰለባ ይሆናል። ይህንን ነው የለገጣፎና የለገዳዲ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን የሚመኙት። ብርሃንን ሳይሆን ጨለማን ነው የሚሹትና እየተደናበሩ ወደ ገደል ለመግባት የሚፈልጉት።

ስለሆነም ከእንደዚህ ዓይነቱ ያልሰለጠነ አሠራርና አስተዳደር መላቀቁ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የማንነት መብት ወይም ራስን በራስ ማስተዳደር በሚል ሰበብ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ሕዝብ በጥቂት ዘመናዊ ካድሬዎች መረበሽና ፍዳውን ማየት አይገባውም።

መታወቅ ያለበትም ጉዳይ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የሁሉም ዜጋ እንደመሆኗ መጠን እያንዳንዱ ዜጋ የፈለገበት ክፍለ ሀገር ወይም ክልል ሔዶ የመሥራትና ሀብት የማፍራት፣ እንዲሁም በአስተዳደር ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው። ማንኛውም የየክፍለ ሀገሩ አስተዳደር ወይም መስሪያ ቤት ለሁሉም ዜጋ ክፍት መሆን አለበት።
ፖሊሶችም ከሁሉም ብሔረሰብ በመውጣጣት ፀጥታን የሚያስከብሩ መሆን ያለባቸው እንጂ ከአንድ ጎሳ በመመልመል ብቻ ሌላውን ጎሳ የሚያምሱበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም። በመሆኑም ስለለውጥ በሚወራበት ጊዜ እነዚህ ሁሉ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ በተረፈ ግን የተራው ሕዝብ ቤቶች ካለአግባብ እንዲፈርሱና ሰዎችም በየቦታው እንዲጣሉ ያደረጉ የከተማዎቹ ከንቲባዎችና የአስተዳደር አባላት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።

በሕግ የበላይነት ሥም በማሳበብ እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ሰርተው እጃቸውን አጣጥፈው ሊቀመጡ በፍጹም አይገባቸውም። ይህ ብቻ ሳይሆን ቤታቸው የፈረሰባቸው ካሳ ማግኘት አለባቸው። ቤት ተሰርቶ እንዲሰጣቸው የክልሉ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን መንግሥትም አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለበት። ከዚህ በተረፈ እንደዚህ ዓይነት ነገር ወደፊት እንዳይደገምና የሰፊው ሕዝብ መብት እንዳይጣስ በአስተዳደር ውስጥ ተቀጥረው ለመሥራት የሚፈልጉ ወደ ተግባር የሚመነዘርና በየአካባቢው እውነተኛ ኅብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር የሚችል እውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።

የሕዝብ አገልጋይ ለመሆን ብቃት ይኖራቸው እንደሆን ልዩ ዓይነት የጭንቅላት ምርምር ፈተናዎችን ማለፍ አለባቸው። እውነተኛ የሕዝብ አገልጋዮች ለመሆን የተዘጋጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here