የክልሎች ደኅንነት እና የፌዴራል መንግሥቱ ሚና

0
985

ፌዴራሊዝም በጥቅሉ የወል እና የተናጠል አስተዳደር መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በተግባር ደካማ በመሆኑ ማዕከላዊ (የፌዴራል) መንግሥቱ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ከርሟል። በቅርቡ የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ግን የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎች ውስጥ የፀጥታ እና ሕግ ማስከበር ፈተናዎች ከክልሎች ሲገጥመው እየተስተዋለ ነው። ገመቹ መረራ ይህንን መነሻ በማድረግ፥ ክልሎች የፌዴራሉን ጣልቃ ገብነት መከላከል የሚችሉት እስከየት ድረስ እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ ይፈትሻል።

 

ከበርካታ ሳምንታት በፊት ለግል ጉዳይ ወደ መቐለ ተጉዤ ነበር። ከተማዋ ከዚህ ቀደም እንደማውቃትና ፈረንጆች እንደሚሉት “full of life” ብትሆንም፥ በአንድ በኩል የታዘብኩት ድባብ ግን ደስ የሚል አልነበረም። አንዳንድ ሸቀጣ ሸቀጦች በሱቆች ውስጥ የሉም፤ አሊያም ዋጋቸው ጨምሯል። ለዚህ የዋጋ መናር እና የሸቀጦች አለመገኘት መነሻ ተብሎ የተነገረኝ ደግሞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ የዘረፋ ተግባር እየተፈፀመባቸው በመሆኑ ሳቢያ የከተማው ነጋዴዎች በከፊል ዕቃ ማስመጣት በማቆማቸው ነበር። በርግጥ የትኛውም ሕጋዊ ነጋዴ ሊዘረፍ እንደሚችል እያወቀ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ኪሣራ ውስጥ መውደቅ አይፈልግም።

ስለጉዳዩ ያወራኋቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የክልሉ መንግሥት ይሄንን የዘረፋ ተግባር እያየ ሆነ ብሎ ነው ያላስቆመው ወይም ለማስቆም ያልሞከረው ብለው ያምናሉ። የክልላቸው መንግሥትም ሌላ ክልል ውስጥ ሔዶ መብታቸውን ሊያስከብርላቸው እንደማይችል ይገነዘባሉ። በመሆኑም ወቀሳቸውን ያዞሩት ወደ ፌዴራል መንግሥቱ ነበር። የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሉ መንግሥት ቸልተኝነት እና ከዘራፊዎቹ የወንጀል ተግባር ጋር ወግኗል፤ አሊያም ድጋፋቸውን ላለማጣት ሆነ ብሎ የሕግ ጥሰቱን አልፎታል ብለው ያምናሉ። የፌዴራል መንግሥቱ ከዚህ ዓይነት አደጋዎች የማይከላከለን ከሆነ በፌዴራል ስርዓቱ ሥር መተዳደራችን ምን ትርጉም አለው? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

አንድ
መቐለ ከመሔዴ በፊት በነበረው ሰሞን አንድ ወዳጄ አጭር ቪዲዮ በሜሴንጀር በኩል ልኮልኝ ተመልክቼው ነበር። ቪዲዮው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) “ከሰብኣዊ መብት ጥሰትና ሙስና ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በቂ ሆኖ ሳለ ከላይ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል በሚል የመከላከያ ሠራዊት መግባቱ ትክክለኛና ተገቢ አለመሆኑ” በመግለጽ በትግራይ ቲቪ በተላለፈ የዜና ፕሮግራም ያደረጉትን ንግግር ነው የሚያሳየው። ንግግሩ በዚያው ቪዲዮ በአማርኛ እንዲህ ተተርጉሟል፦

“የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ምን ለማድረግ ነው የገባው ስንል ትዕዛዝ ካላይ እንደመጣ ነው የተነገረው። ይህ ተገቢ አይደለም። ሊታረም ይገባዋል። እኛ በማናውቀው ነው ሥራ እየተሠራ ያለው። ይሁን እንጂ በላይ የሚታወቅ ነው። ይህንን ጉዳይ አቁሙ ነው እያልን ያለነው። የፖሊስ ሥራዎችም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ቢሆን ክልሉ ላይ በሚደረገው ማንኛውም ጉዳይ ሊገባ አይገባም ምክንያቱም የክልሉ ሥራ ስለሆነ። ክልሉ አቅም የለኝም ካለ አግዘኝ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ እኛ ይኼንን አላልንም። በመሆኑም የትግራይ ክልል መንግሥት ሳይጠየቅ ከላይ ታዘናል የሚል ጉዳይ ተቀባይነት የለውም። ይህ ጉዳይ አይደገምም የሚል እምነት አለኝ። የሚደገም ከሆነ ግን ሌላ ነገር ተፈልጓል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ጤናማ አይደለም። የተደረገው ጉዳይ ግን እንዳይደገም ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል።”

ኹለት
ከላይ በቀረበው ንግግራቸው ደብረፅዮን የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ ለማስከበር ዓላማ ወደ ክልል መግባቱን “ነገር ፍለጋ” አድርገው እንደተመለከቱት ነው የገለጹት። ይኼንን ንግግራቸውን ወይም አቋማቸውን በርካቶች ይጋሩታል። በሌላ በኩል ግን እሳቸው የሚያስተዳድሩት ክልል ነዋሪዎች በትግራይ ነጋዴዎች ንብረት ላይ እየተፈፀመ ለነበረው ዘረፋ በክልል የፀጥታ ኃይሎች ተገቢው ጥበቃና ምላሽ ስላልተሰጠው የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባና በንብረታቸው ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት እንዲያስቆም ይፈልጋሉ። የነዋሪዎቹ ፍላጎት ምክንያታዊ ቢሆንም የክልሉ አስተዳዳሪ ከያዙት አቋም ጋር ግን የሚጋጭ ነው፤ የፌዴራል መንግሥቱ አማራ ክልል ገብቶ ዘረፋውን ቢያስቆም አሊያም በጠቅላላ አገላለጽ ሕግ ቢያስከብር “ነገር ፍለጋ” የማይሆንበት ምክንያት የለምና። የፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ ክልሎችን በእኩል ሁኔታ የመመልከት እና የማስተናገድ ኃላፊነት አለበት። አንዱ ክልል ላይ የማያደርገውን ወይም የተከለከለውን ነገር ሌላው ክልል ላይ የሚፈፅምበት አንዳችም ምክንያት የለም።

ከላይ የተገለጹትና በኹለቱም ክልሎች የፌዴራል መንግሥቱን ጣልቃ ገብነት የሚፈልጉት ጉዳዮች የወንጀል ጉዳዮች ናቸው። ዘረፋም ሆነ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትና ሙስና ወንጀሎች ናቸው። ኹለቱ ክልሎች ከጊዜው ቅርበት እና ከጉዳዩ መጦዝ አንፃር በምሳሌነት ተነሱ እንጂ በኦሮሚያ፣ በሱማሌ፣ በደቡብ እና ሌሎች ክልሎችም የሚያጋጥም ጉዳይ ነው። የዚህ ጊዜ ነበር ቆም ብዬ ከዚህ ቀደም የክልል መንግሥታትን ሰላም እና ደኅንነትን አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥቱ ሚና ምን እንደሆነ ከአንድ ወዳጄ ጋር ያደረግነውን ውይይት ያስታወስኩት። ሐሳቡን በጽሑፍ አስፍሮት ስለነበርና ውይይታችን የተደረገውም ጽሑፉን ካነበብኩ በኋላ ስለነበር ለማስታወስ ጽሑፉን እንዲልክልኝ ጠየቅኩት።

 

የፌዴራሉን መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥልጣን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንደተወሰነ አድርጎ ማቅረብ፥ የፌዴራሉን መንግሥት ዓለም ዐቀፍ ድርጅት፣ ክልሎችን ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ አገራት አድርጎ መቁጠር ነው

 

ሦስት
የወንጀል ሕግ ተከባሪነትን ለማረጋገጥ ኹለት ዓይነት ዋና ሥራዎች ይሠራሉ። አንደኛው ሥራ፥ ሕግ ተጥሶ ሲገኝ ሕግ ተላላፊውን የመለየት፣ የመመርመር፣ የመያዝ፣ የመክሰስ፣ የመዳኘት፣ ቅጣት የተጣለበት እንደሆነም ቅጣት የማስፈፀም፣ የማረምና የማነፅ ሠራዎች ናቸው። እነዚህ ሥራዎች በጠቅላላው የሕግን ማስከበር ሥራዎች ሊባሉ ይችላሉ።

ሕግ ተላላፊዎችን በመቅጣት አጥፊው ብቻ ሳይሆና ሌላውም ሕጉን እንዲያከብር ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። በመሆኑም የወንጀል ሕግ ተከባሪነትን ለማረጋገጥ የሚሠራውን ኹለተኛውን ሥራ አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን። ይኸውም መጀመሪያውኑ ሕጉ እንዳይጣስ የመከላከልና የጥበቃ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ያለበለዚያ ግለሰቦችና ቡድኖች ወንጀሉን ፈፅመን በሕግ አስከባሪው አካል የመያዝ ዕድላችን ዝቅተኛ ነው በሚል እምነት ሕጉን ሊጥሱ ይችላሉ። እንዲሁም ሕግ መጣሱንም ለማወቅ የመከላከልና የጥበቃ ሥራዎች መሠራት አለባቸው።

በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ኹለት ዓይነት መንግሥታት እናገኛለን። የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት። ሥልጣን በኹለቱ ዓይነት መንግሥታት በሕገ መንግሥቱ ተከፋፍሏል፦

  • ለፌዴራሉ መንግሥት ለብቻው የተሰጡ፣
  • ለፌዴራሉና ለክልል መንግሥታት በጋራ የተሰጡ እና
  • ከኹለቱ ውጭ ያሉት ሥልጣኖች ደግሞ ለክልሎች የተተዉ ናቸው።

ሕገ መንግሥቱ የፌዴራሉ መንግሥት የክልሎችን ሥልጣን እንዲያከብር፣ የክልል መንግሥታት ደግሞ የፌዴራሉን መንግሥት ሥልጣን እንዲያከብሩ ይጠብቃል። በዚህ ረገድ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 50 (8) “ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት። ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት” ሲል ይደነግጋል። የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት በተሰጣቸው የሥልጣን ወሰን ሆነው ሕግ ያወጣሉ፣ ሕጉን ይፈጽማሉ፣ ያስከብራሉ፣ በሕጉ መሠረት ይዳኛሉ። ለዛ ነው ኹለቱም መንግሥታት በሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ ክፍሎች የተደራጁት።

በመሆኑም አንድ የክልል መንግሥት ያወጣውን ሕግ በክልሉ ወሰን ውስጥ የማስከበር ሥልጣን አለው። እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ያወጣውን ሕግ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የማስከበር ሥራ መሥራት ይችላል። ለዚህ ሥራው ከክልሎች ትብብር ለማግኘት ጥያቄ ያቀርብ እንደሆን እንጂ፥ የክልሎች ፈቃድ አያስፈልገውም። የፌዴራሉ መንግሥት የሥልጣን ወሰን የኢትዮጵያ ወሰን ነው። ስለዚህ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ ሲጣስ፥ ይህን የመመርመር፣ ሕግ ተላላፊውን የመክሰስና የመሳሰሉት ሥልጣኖች አሉት። የፌዴራሉን መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥልጣን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንደተወሰነ አድርጎ ማቅረብ፥ የፌዴራሉን መንግሥት ዓለም ዐቀፍ ድርጅት፣ ክልሎችን ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ አገራት አድርጎ መቁጠር ነው። እነዚህን ኹለት ተግባራት በዝርዝር እና በምሣሌ እንያቸው።

ሕግ የማስከበር ሥራ
የክልል ምክር ቤት አባላት አሊያም የክልል አስተዳዳሪዎች በፌዴራል ወንጀል ተጠያቂነትን እናንሳ። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት አላቸው። ይህ ያለመከሰስ መብት በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተቀመጠ ነው። በመሆኑም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሕግ አስከባሪዎች በዚህ መብት ይገዛሉ። በሕጉ አግባብ ይህ መብት እስካልተነሳ ድረስ፥ እነዚህ ሰዎች ሊከሰሱ አይችሉም። ይሁን እንጂ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ለክልል ምክር ቤት አባላትና ባላሥልጣናት ያለመከሰስ መብት አይሰጥም። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በክልሉ ሕገ መንግሥትና በክልሉ ሕጎች ያለመከሰስ መብት ሊሰጣቸው ይችላል። ጥያቄዉ ይኼ በክልል ሕገ መንግሥት እና በክልል ሕጎች ዕውቅና ያገኘ ያለመከሰስ መብት የፌዴራል መንግሥቱን በምን መልኩ ያስገድደዋል የሚለው ነው።

መነሳት ያለበት ጥያቄ “ሰውየው የሚከሰሰው በምንድን ነው?” የሚለው ነው። የሚከሰሰው የክልሉን ሕጎች በመጣስ ከሆነ የሰውየው ያለመከሰስ መብት ተቀባይነት አለው። ሰውየው የጣሰው የክልል ሕግ ከሆነ፥ የፌዴራል መንግሥቱን የሚያገባው ጉዳይ ላይኖር ይችላል። ነገር ግን ሰውየው የሚከሰሰው የፌዴራል ሕጉን በመጣሱ ከሆነ፥ የሰውየው በክልል ሕጎች ያለመከሰስ መብት የፌዴራል መንግሥቱን አያስገድድም። ዋናው ጉዳይ “ከሳሹ ማን ነው?” ሳይሆን “የተከሰሰው የትኛውን ሕግ በመጣሱ ነው?” የሚለው በመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ የሰውየውን በክልል ሕጎች ያለመከሰስ መብት እንዲያከብር አይገደድም።

ባጭሩ፣ የፌዴራሉን ሕግ ለማስከበር የፌዴራሉ መንግሥት የሥልጣን ወሰን የአገሪቱ ወሰን ነው። በመላው አገሪቱ የፌዴራል ሕጉን የጣሱ ሰዎች ፈልጎ በሕጉ አግባብ የመያዝ መብት አለው። ለዚህም የፖሊስ ሠራዊቱን ወይም መከላከያ ሠራዊቱን እንደ አግባብነቱ ሊያሠማራ ይችላል። የክልሎችን ፈቃድ ማግኘት አይጠበቅበትም። የክልሎችን ድጋፍ ግን ሊጠይቅ ይችላል። የፌዴራሉ መንግሥት የፌዴራሉን ሕግ የማስከበር ሥራ ሲሠራ ክልሎች ድጋፍ መስጠት ባይችሉ አሊያም ባይፈልጉ፣ እንቅፋት መሆን ግን አይችሉም።

የመከላከልና የመጠበቅ ሥራ
የመከላከልና የመጠበቅ ሥራ ለፌዴራል እና ለክልል መንግሥታት በጋራ የተሰጠ ሥልጣን ነው። ክልሎች በክልላቸው ወሰን ውስጥ ሆነው የመከላከልና የጥበቃ ሥራ ያከናውናሉ። የመከላከልና የመጠበቅ ሥራ በባሕሪው ጠቅላላ ሥራ ነው። አንድን ሕግ ለብቻው ለይቶ የመከላከልና የመጠበቅ ሥራ መሥራት አይቻልም። በአገራችን ለብቻ ተለይተው የሚሠሩ እንደ ኮንትሮባንድ ያሉ የመከላከልና የመጠበቅ ሥራዎች ቢኖሩም፥ ውሱን እና ሁሉንም የሚያመላክቱ አይደሉም። በመሆኑም ክልሎች የመከላከልና ጥበቃ ሥራ ሲያከናውኑ፥ የሚጠበቀው የክልሉ ሕግ ብቻ ሳይሆን የፌዴራሉም ሕግ ጭምር ነው።

በዚህ ሁኔታ የፌዴራሉ መንግሥት የመከላከልና የጥበቃ ሥራን ክልሎች ጋር በሁሉም ሁኔታዎች ገብቶ ቢሠራ ኹለት ችግሮች ይኖሩታል። አንደኛዉ የሀብት መባከን ነው። ኹለተኛው፣ በአንድ ቦታ ላይ ክልሎችም የፌዴራሉም መንግሥት የጥበቃና የመከላከል ሥራ ቢሠሩ፣ ዜጎች ደኅንነት ሳይሆን ፍርሐት ሊሰማቸው ይችላል። ባጭሩ የመከላከልና የጥበቃ ሥራ ከሚገባው በታችም ከሚገባውም በላይም ከሆነ፣ ዜጎች እንዲሰጉ ያደርጋል። ለዛ ነው ሕገ መንግሥቱ ሥልጣኑን በጋራ ከሰጠ በኋላ፣ የፌዴራሉን መንግሥት ሚና ግን በልዩ ሁኔታ ያስቀመጠው። ይህ ሁኔታ በክልል መንግሥታት የመከላከልና የጥበቃ ሥራ ለመሥራት የአቅምና የፍላጎት ማነስ ሲኖር የሚለው ነው።

አንደኛ፣ ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲኖር በክልሉ ጥያቄ የፌዴራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊቱን ሊያሰማራ እንደሚችል ተገልጿል። ይህ የአቅም ማነስን ያሳያል። ኹለተኛ፣ በአንድ ክልል የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ሲያጋጥሙ እና ሲደጋገሙ፥ ያለክልሉ ፈቃድ፣ በኹለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ፣ ለክልሉ መመሪያ ሊሰጥ እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ያሳያል። ይኼ የሚመነጨው ከፍላጎት ማነስ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በዚህ አግባብ የተሰጠን መመሪያ የክልሉ ባለሥልጣናት ካላከበሩት፥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን አለመወጣት ይሆናል።

ከዚህ በላይ ባሉት ኹለት አግባቦች የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ውስጥ ሠራዊት ሲያሰማራ ወይም መመሪያ ሲሰጥ፥ በክልሎች ጣልቃ እየገባ ወይም “ነገር እየፈለገ” ሳይሆን በጋራ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ነው።

መደምደሚያ
ሥልጣንና ተግባራቸውን ጠንቅቀው ከሚያውቁ፣ ነጻ፣ ገለልተኛና ሕዝብን ማገልገልን ዋነኛ ዓላማቸው ካደረጉ ተቋማት ቀጥሎ ለነዋሪዎች ደኅንነት ዋስትና የሚሆነው በጥንቃቄ እና በዕውቀት የተደገፈ አመራር መኖር ነው። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ባለሥልጣናት እና አመራሮች ከፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ከሌሎች ክልሎች አመራሮች እንዲሁም ከግለሰቦች ጋር እልህ በመጋባት የሚያደርጓቸው ንግግሮችም ሆኑ የሚወስዷቸው እርምጃዎች በስተመጨረሻ ዋጋ የሚያስከፍሉት ሕዝቡን ነው። የነሱን ንግግር እና እርምጃ ተከትሎ አላስፈላጊ ጥላቻ፣ ፉክክር እና ድርጊት ውስጥ የሚገባና በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ሊተካ የማይችል ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የሕዝብ ክፍል መኖሩን ልብ ማለት ይገባቸዋል።

የፌዴራል መንግሥቱም በተገቢው ጊዜ እና ቦታ ሥልጣኑ በሚፈቅድለት ልክ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የሕግ ማስከበርን ሥራ የማይሠራ ከሆነ የአገር አንድነት ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን የማስወገድ ግዴታውን አልተወጣም፤ መጠኑ ከሰፋና ከተደጋገመ ደግሞ ከሽፏል ማለት እንችላለን። ክልሎችም ለራሳቸው በማንም የማይደፈር ልዩና ሉዓላዊ ድንበር በሐሳብ ደረጃ እንኳ ያሠመሩ ዕለት የአንድ አገርነትን እውነታ ጥያቄ ላይ ከመጣል ባለፈ መሠረታዊ የፌዴራሊዝም ዕሳቤዎችንም ይነቀንቃሉ። በመሆኑም፣ በቅድሚያ ክልሎች ራሳቸው ማናቸውንም ዓይነት ለሕዝቦች በአንድነት ለመኖር እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ተገቢውን የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት ሊያስወግዱ ይገባል። በተለያየ ምክንያት ከነርሱ ቁጥጥር እና አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ባጋጠሟቸው ጊዜያት ሁሉ ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት በሕግ አግባብ የሚያደርገውን የሕግ ማስከበር ሥራ መቃወም ሳይሆን በተቻለ መጠን ማበረታታት እና ግዴታውን እንዲወጣ መወትወት ይገባቸዋል። በዚህ ጽሑፍ ኹለቱ ክልሎች ተጠቀሱ እንጂ ይህ እውነታ ሁሉም ጋር ያጋጠመ አሊያም ሊያጋጥም የሚችል ከመሆኑም ባሻገር ውጤቱ የአገራዊ አንድነትን መሠረት በፅኑ የሚያናጋ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠውና ሊታሰብበት ይገባል።

ገመቹ መረራ የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው fana@ethiopianlawgroup.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here