የፊት ቆዳ ውበት አጠባበቅ

0
2366

ጥቂት ነጥቦች

  • ሰዎች ጊዜው ያለፈበትን የውበት መጠበቂያ ሲጠቀሙ ፊታቸው ወዲያው ይቆጣል። ለዚህም ውሃ ጨው ጨምሮ በማፍላት ፎጣን በመጠቀም ወደ በፊቱ ቆዳቸው እንዲመለስ ይረዳል።
  • ቆዳችን በተፈጥሮው በየ28ኛው ቀን ስለሚቀያየር አላስፈላጊ ቆዳዎችን በማስወገድና ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ለቀጣዩ የውበት አጠባበቅ ዝግጁ ማድረግ ይቻላል።
  • ፊታቸው በተፈጥሮ ደረቅ የሆኑ ማር፣ እርጎ፣ እርድ እና ሎሚ በማዋሐድ ከ20 እስከ 40 ደቂቃ በማቆየት በመታጠብ ድርቀትን የሚከላከል ሲሆን በተጨማሪ ብጉርን ባለበት እንዲደርቅ ያደርጋል።

̋በአገራችን የሜካፕ ሥራ ገና እየተጀመረ እንጂ አላደገም፤ ምክንያቱ ደግሞ እንደ ቅንጦት መቆጠሩ ነው ̋ ትላለች የጉንጉን የጸጉርና የሜካፕ ባለቤትና የሥነ ውበት ባለሙያ ራሔል ነጋሽ። አንዳንዶች እንደ የፊት ማስዋብንም ሆነ የፀጉር ሥራን እንደ ቅንጦት ቢመለከቱትም ራሔል ግን ቅንጦት አለመሆኑን ትናገራለች፤ ̋ፀጉርና ፊት ማስዋብ እንዴት ቅንጦት ሊባል ይችላል? ̋ ስትል በመገረም ትጠይቃለች።

ቀደምት እናቶቻችን ራሳቸውን በተለያዩ ባሕላዊ የቤት ውስጥ መዋቢያዎችን በመጠቀም ጸጉራቸውን ሹሩባ፣ ጉንጉን፣ እሽም፣ ግልብጥ፣ አልባሶ በማለት በተለያየ መልክ ይሠሩ ነበር። የፊት ውበት መጠበቂያም ቢሆን እንዲሁ በባሕላዊ ማስዋቢያዎች እንደ ቅቤ፣ አደስ፣ ስርኩል እና ፍራፍሬዎች ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች የፊት መዋቢያ መጠቀም መሰረታዊ የዘወትር ተግባር ከመሆንም ባሻገር እንደመዝናኛነት ማለትም ከድብርትና ሐዘን ስሜት ለመውጣትም ይጠቀሙበታል።

ራሔል ወደዚህ ሥራ ከተቀላቀለች 15 ዓመታትን ብታስቆጥርም ከድሮ ይልቅ አሁን ላይ ጫናዎች እንዳሉ ትገልፃለች። አንድ ተገልጋይ ሲመጣ ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ ባለሙያው ላይ ትቶ በእርግጠኝነት ነበር የሚመጣው፤ አሁን ላይ ግን በታዋቂ ሰዎች ላይ ያዩትን የፀጉር አሰራር፣ የፊት ውበት አጠባበቅ እና ሌሎች አገልግሎቶች ታዋቂዎችን ለመምሰል ይፈልጋሉ ̋ የምትለው ራሔል፤ አንዲት ሴት የፊት ማስዋቢያዎችን በባለሙያ ከተሰራች በኋላ ማንነቷን መለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ሳይሆን ያላትን ውበት ማጉላት ላይ ትኩረት እናደርጋለን በማለት ታስረዳለች። ይህ ግን አንዱ ላይ ያማረ ሌላው ላይም ያምራል ማለት አይደለም ምክንያቱም የፊት ቅርፅ፣ የቆዳ ቀለምና የፀጉር አሰራር ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ። ስለሆነም ፊታቸውን የሚሰሩ ደንበኞች የፈለጉትን ብቻ ሳይሆን ከፊት ቆዳና ቅርፅ ጋር አብሮ የሚሔድ የፊት ማስዋቢያ እንዲጠቀሙ ይመከራል።

ሌላው የፊት ቆዳ ውበት መጠበቂያ ለመጠቀም የቆዳው ዓይነትም የራሱ ሚና አለው፤ የሁሉም ሰው ቆዳ ተመሳሳይ አለመሆኑን ልብ ይሏል። በፊት አስዋቢዎቹ አጠራር ሰዎች ያሏቸው የፊት ቆዳ ደረቅ፣ ወዛማ እና በደረቀና ወዛማ መካከል የሚገኝ ብለው ይከፍሏቸዋል። ስለሆነም ደንበኞች ለእያንዳንዳቸው ቆዳ ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ይመከራሉ።

በተለይ ሙሽሮች ወይም ሌላ ትልቅ ፕሮግራም ላለባቸው ሜካፕ ከመሰራታቸው በፊት ቆዳቸው በአቧራ ስለሚሸፈን ʻበሞሮኮባዝʼ ወይንም ʻፋሻልʼ መጠቀም ያለባቸው ሲሆን ማድረግ የሌለባቸው ደግሞ የፀጉር ቀለም መቀባትና በዘፈቀደ የፊት ቆዳ ላይ ምንም ዓይነት ሜካፕ መጠቀም የለባቸውም። ለቆዳችን እንክብካቤ በማድረግ ከፊት ማስዋቢያ ቅባቶች ጋር ተያይዞ ሊመጣ ለሚችል ማንኛውም ዓይነት የቆዳ ሕመም ተጋላጭነትን ከመቀነስ እና ቆዳውንም ከጉዳት ከመከላከል ባሻገር ለስላሳ ቆዳ እንዲኖረን እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የፊት ቆዳ አጠባበቅ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍትና ጥናቶች የፊት ቆዳ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ስስ የሰውነት ክፍል እንደሆነ ነው። ሊደረግ ስለሚገባውም ጥንቃቄ ከተጠቀሱት መካከል የፊት ቆዳን ሊያበላሹ የሚችሉት የጸሐይ መከላከያ ምርቶችን አለመጠቀም፣ የመዋቢያ ብሩሾቻችንን ንጽሕና አለመጠበቅ፣ እንደብጉር ያሉ በቆዳ ላይ የሚታዩ ቁስል መሰል ነገሮችን በመነካካት ቁስለቱን እንዲባባስ ማድረግ፣ ሲጋራ ማጤስ፣ የቆዳችንን ወዝ አለመጠበቅ፣ የተቀባነውን የውበት መጠበቂያ(በተለይ ሜካፕ) ሳንታጠብ መተኛት፣ በቂ ውሃ አለመጠጣት፣ ረዘም ላለ ጊዜ በሙቅ ውሃ መታጠብ፣ ፊታችንን ከኬሚካሎች አለመጠበቅ፣ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት፣ የፊት ቆዳችንን በእጅ መነካካት፣ ለቆዳችን ዓይነት ትኩረት መንፈግን የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ፊትን በአግባቡ በንጹሕ ውሃ መታጠብ፣ ጫና በሌለው መልኩ መጠራረግና ማጽዳት ደግሞ የፊትን ቆዳ ጤንነት ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ተጠቅሷል።
ሰዎች ዘመናዊ የፊት ማስዋቢያዎችን በቤታቸው ሲጠቀሙ መጠንቀቅ አለባቸው የምትለው ራሔል፤ ለዚህም ጊዜው ያለፈበት የመዋቢያ እቃዎችን ከመጠቀም መቆጠብ እና የፊት ቆዳ ዓይነቱን መለየትና ማወቅ መቻል አለብን ስትል ትመክራለች። ይህ ካልሆነ ግን የፊት ቆዳ ለሕመም የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆንም ጠቅሳለች።

አብዛኛዎቹ የመዋቢያ እቃዎች በአገር ውስጥ ትክክለኛው ምርታቸው ስለማይገኙ ተመሳስለው የሚሰሩትን ሲጠቀሙ ፊታቸው ላይ የሚያመጣው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ራሔል የሜካፕ ተጠቃሚዎችን በተመለከተ ̋እንደ እኔ ሜካፕ እንዲጠቀሙ የምመክረው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቢሆኑ እመርጣለሁ ምክንያቱም የቆዳ መርገብ ስለሚያጋጥማቸው ነው ̋ ትላለች። ብዙዎች ʻወጣትነት በራሱ ውበት ነውʼ መሆኑን እንደሚስማሙት ሁሉ የፊት ገጽን በመዋቢያ ቅባቶች በብዛት መጠቀም የቆዳን ተፈጥሯዊነት ያጠፋል ትላለች። ሌሎቹም የውበት አጠባበቆች ለምሳሌ ብዙዎች የሚጠቀሙት ʻሂውማንሄርʼ እና ጥፍር መሞላት በተከታታይ መሰራት የራሳቸው ተፈጥሯዊ ውበትን እንደሚያሳጡ የውበት ሥራ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here