የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሪር ቀናት

0
1062

ኮሞሮስ፣ ሕንድ ውቅያኖስ
በወርሃ ጥቅምት፣ ከወሩም በ13ኛው ቀን 1989 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 767-200 ER ወይም በቅፅል ስሙ ‹‹ዙሉ›› የበረራ ቁጥር ኢቲ 961 አፍንጫውን ወደ ፀሐይ መውጫ አዙሮ ነፋሻውን የጥቅምት ወር ከአደይ አበባ መአዛ ጋር እየተነፈሰ ግዳጁን ይጠብቃል።

በዋና አብራሪው ካፒቴን ልዑል አባተ እና በረዳት አብራሪው ዮናስ መኩሪያ ከሌሎች የበረራ አስተናጋጆች ጋር በመሆን 175 መንገደኞችን አሳፍሮ መዳረሻውን ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ጎረቤት አገር ኬንያ አድርጎ ጉዞ ጀምሯል። ምድር ላይ ባሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚሰጠውን መረጃ እየተቀበለ ዋና አብራሪው ልዑል አባተ ʻየሰማዩን ጋሪʼ ከደመና በላይ እያስወነጨፈው ነው የተፈቀደለትን ከፍታ ለመያዝ። አሁን ከፍታውን ተቆጣጥሯል፣ 21 ሺሕ ጫማ (6,400.8 ሜትር ከመሬት ወደ ሰማይ ያለው ርቀት) ከመሬት ርቆ፤ የለመዳቸውን የአፍሪካን ተራሮች ቁልቁል በኩራት እየገረመመ 200 ማይል በሰዓት መወንጨፍ ጀምሯል።

አውሮፕላኑ የተፈቀደለትን ከፍታ ይዞ በረራውን ማድረግ ከጀመረ ከቆይታዎች በኋላ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ። በፀጥታና በአርምሞ የተሞላው የአውሮፕላኑ ክፍል ትልቅ መደናገጥና መረበሽ ተሞላ። ˝ማንም ሰው የተለየ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ይህን አውሮፕላን እናጋየዋለን˝ የሚል ማስጠንቀቂያ መርዶ ቢባል የሚቀል ድምፅ ከሦስት ወጣቶች ተሰማ። ወጣቶቹ ወደ ዋናው አብራሪ እና ረዳቱ በመሔድ አውሮፕላኑ መጠለፉንና ከፍታውን ጨምሮ ወደ ምድር ዳርቻዋ አሕጉር አውስትራሊያ እንዲያቀና ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ። ከዋና አብራሪው በኩል በቂ ነዳጅ እንዳልያዘ እና ወደ ተባለው ቦታ መድረስ እንደማይችል ቢነገራቸውም በጀ አላሉም ጫናው ሲበዛ ግን ለተሳፋሪዎች ደህንነት ሲባል ወደተባለው ሥፍራ ማቅናት ግድ ሆነ ።

ነገር ግን የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት አስበው ጠለፋውን የፈፀሙት ወጣቶች እንዳሰቡት አልሆነም። ከፍታውን ጨምሮ ወደ አውስትራሊያ የሚገሰግሰው ʻዙሉʼ ነዳጅ ጨረሰ፣ ከግስጋሴው ተገታ፤ በዚህ ጊዜ ካፒቴን ልዑል አባተ ፈጣን ውሳኔ ወሰኑ እናም ውሃ ላይ ለማሳረፍ ተገደዱ ። ውሳኔው ʻየተሻለውን ሰይጣንʼ መምረጥ ቢሆንም ምርጫ አልነበረም ። የዋና አብራሪውን ውሳኔ ተከትሎ በሕንድ ውቅያኖስ በኮሞሮስ ደሴት አቅራቢያ ወደቀ።

ለወትሮውም አዳዲስ እና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት ፋሽን ተከታይ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በጊዜው የመጨረሻው ሞዴል የሆነውን ቦይንግ 767-200ኢ አር ወይም ʻዙሉʼ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ነግሶበት ነበር። በዚያን ቀን ግን 175 መንገደኞችን ይዞ እንደወጣ ዳግመኛ ላይመለስ ʻዙሉʼ ከ125 መንገደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች ጋር እስከወዲያኛው ተሰናበተ።

ቤሩት፣ ሜዲትራኒያን ባሕር
ዓመታት ተቆጠሩ፤ አየር መንገዱም መርዶን በሩቁ እያለ የዕለት ተዕለት ሥራውን የአፍሪካ ኩራት ሆኖ ቀጥሏል። በጥር 2002 ግን ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ ። ከመካከለኛው ምሥራቅ ከሊባኖስ፤ ቤሩት ራፊክ ሃሪሪ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ የተነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8ኤኤስ የበረራ ቁጥር ኢቲ 409 መዳረሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በማድረግ 82 መንገደኞችንና 8 የአውሮፕላን ሠራተኞችን ይዞ ጉዞ ጀመረ።
ነገር ግን ከመንደርደሪያው ተነስቶ ምድርን እንደለቀቀ ከአምስት ደቂቃ በኋላ የሬዲዮ ግንኙነቱ መቋረጡ ይነገራል በኋላም በሜዲትራኒያን ባሕር ግብዓተ መሬቱ ሆነ። በአደጋው ለወሬ ነጋሪ እንኳን አልተረፈም የ90 ሰዎች ሕይወት ከዚህ ዓለም እንደዋዛ ተቀነሰ። ለአደጋው መንስዔ ይሆናል የተባሉ ብዙ መላምቶች ቢኖሩም እስካሁን ድረስ በእርግጠኛነት ለመናገር የሚያስችል መረጃ ሳይገኝ ቀርቶ ʻየውሾን ያነሳ ውሾʼ በሚል በዝምታ ታለፈ።

ቢሾፍቱ፣ ኢጀሬ መንደር
መጋቢት 1/2011 ከደቡብ አፍሪካ ቆይታው በሰላም የገባው ቄንጠኛው ቦይንግ 737-ማክስ 8 ለሚቀጥለው ግዳጁ ዝግጁ ለመሆን የሦስት ሰዓታት እረፍትና የሞተር ምርመራ አድርጎ ጨርሶ የበረራ ቁጥር ኢቲ302 ተሰቶታል። 149 መንገደኞቹን በጉያው ሸክፎ፤ ለደንበኞቹ ያስለመደውን እንክብካቤ ሊከውን ደግሞ 8 የበረራ ሠራተኞቹን ጨምሮ ጉዞውን ወደ ጆሞ ኬንያታ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ናይሮቢ፤ ኬንያ አድርጓል። ከጥዋቱ 2 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ሲል የተጀመረው ጉዞ ግን ከ6 ደቂቃ በላይ መዝለቅ አልቻለም። ዋና አብራሪው ያሬድ ጌታቸው ምድር ላይ ላሉ የአየር ʻትራፊክʼ ተቆጣጣሪዎች የአውሮፕላኑ የኮምፒውተር መቆጣጠሪያ ሰሌዳው እምቢ ማለቱን ካስተላለፈ እና እንዲመለስ ትዕዛዝ ከተሰጠው በኋላ ግንኙነቱ እስከ ወዲያኛው ተቋረጠ።

ለአራት ወራት ብቻ በሥራ ላይ የቆየው የዚህ ዘመን የቴክኖሎጂ እድገት አምጦ የወለደው ቦይንግ 737-ማክስ 8 ʻሞቴን በአገሬʼ ያለ ይመስላል፤ በቢሾፍቱ ሰማይ ላይ ጨሰ፣ ከዋና አብራሪው ቁጥጥር ውጭ ሆነ፣ በመጨረሻም የተፈቀደለትን ከፍታ እንኳን በአግባቡ ሳይቆናጠጥ ወደ መሬት ተመዝገዘገ ከዛም ወደ ፍርስራሽ ተቀየረ። የ33 አገራት ዜጎችን አሳፍሮ እንደነበር የሚነገርለት ቦይንግ 737-ማክስ 8 ዳግመኛ ይቺን ምድር ላይመለሱባት ወደ ወዲያኛው ዓለም አሻግሯቸዋል።
አምነው የተሳፈሩትን መንገደኞች አደራ በመብላት የሚታወቀው ቅንጡው አውሮፕላን ቦይንግ 737-ማክስ 8 የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ ንብረት ከአምስት ወራት በፊት በጥቅምት 189 መንገደኞችን አሳፍሮ በጉዞ ላይ ሳለ ተከስክሶ ሁሉም መንገደኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው 737-ማክስ 8 መከስከስን ተከትሎ በርካታ አዳዲስ መረጃዎች በየቀኑ እየተሰሙ ሲሆን፤ በአቪየሽን ደንብ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሲያጋጥሙ እንደሚደረገው ሁሉ፥ የመረጃ ማጠራቀሚያ ሳጥኑ በአፋጣኝ ፍለጋ ከተደረገበት በኋላ በአሁኑ ሰዓት ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ አገር መላኩ ተጠቃሽ ነው ። የምርመራ ሒደቱም በመጀመሪያ ዙር ውጤቱን ለማወቅ ሦስት ወር የሚፈጅ ሲሆን፤ ምርመራው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ የአንድ ዓመት ዕድሜ ይፈልጋል።

አደጋው የሰሚን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነበር፤ 157 ሰዎች ሕይወት በቅፅበት ይህቺን ምድር ተሰናብተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የባልደረቦቻቸውን በድንገት መለየት በተሰበረ ልብ ነበር በአብራሪዎች ማኅበር አዳራሽ እርማቸውን ያወጡት። ˝የምንወዳቸው ሰዎች ተሰባስበው ጥለውን የሔዱ ነው የመሰለኝ˝ የሚል በእንባ የታጀበ ንግግር ተሰምቷል።

የዘር ሐረጋቸው ከሕንድ ከሚመዘዘው ኬንያዊት እናቱ እና ከኢትዮጵያዊ አባቱ የተወለደው ዋና አብራሪ ያሬድ ጌታቸው የ8 ሺሕ ሰዓት የበረራ ልምድ ነበረው፤ አሁን ላይ በነበር ቢቀርም። አሜሪካ ሰሜናዊ ቨርጂንያ ግዛት መኖሪያቸውን ያደረጉት ጌታቸው ተሰማ (ዶ/ር) የያሬድ አባት ሐዘናቸውን እያስታመሙ ይህን ተናገሩ፤ ˝አንድ ልጅ እንኳን ላበርክት ብዬ ነው ኢትዮጵያ ያስተማርኩት˝ ይላሉ በተሰበረ ድምፅ። ጌታቸው የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር በመጥቀስ ˝ልጄ ሲኖር ኢትዮጵያዊ ነበር፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሆኗል ። እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ˝ ሲሉ የልጅ ሐዘን ባደቀቀው ድምፅ ተናግረዋል።

የድሬድዋው ፈርጥ አሕመድኑር ሞሐመድ በቦይንግ 737-ማክስ 8 ላይ ብቻ የ200 ሰዓታት የበረራ ልምድ ነበረው። ነገር ግን ልምዱ ሕይወቱን ሊታደጋት አልቻለም። ለግላጋው ወጣት ረዳት አብራሪ ቅርብ ወዳጁ ረዳት አብራሪ ዘሩባቤል ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንዲህ ብሎ ተናጋሯል፤ ˝አሕመድ ካለ ሳቅ አለ። ከፍተኛ የሥራ ጫና ስላለብን እሱን ለማግኘት እንፈልጋለን ምክንያቱም በሳቅ መንፈሳችንን ስለሚያድስልን።˝ አሕመድኑር አሁን አጠገባቸው የለም፣ የቅርብ ወዳጁ ዘሩባቤል ከፍተኛ ሐዘን ላይ ነው። ዓይኑን እያየሁ ለመጨረሻ ጊዜ መፅናናቱን ተመኘሁለት።

ሩብ ምዕት ዓመት እንኳን በአግባቡ በዚህ ምድር ላይ ያልኖረቸው የበረራ አስተናጋጇ አያንቱ ግርማ በመጪው ግንቦት 25 ዓመት ይሞላታል። ለኹለት ዓመታት ያለመታከት ከደመና በላይ እየበረረች ውቂያኖሶችን አቋርጣለች። የአፍሪካን መልከዓ ምድርን ከታች አድርጋ ፍልቅልቅ ገፅታዋን በማስቀደም መንገደኞችን በማስተናገድ ˝እንዲህ ነው ኢትዮጵያዊነት˝ ተብላለች ። መጋቢት 1/ 2011 ግን ከወትሮው የተለየ ነበር፤ ዕቅዶቿ በሙሉ ከቢሾፍቱ ሰማይ ወዲያ ስንዝር ሊራመዱ አልቻሉም። ሮጣባት ያልጠገበቻትን ምድር እየበረረች ተሰናበተቻት።

ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘቸው አማ ተስፋማሪያም ባደጋው ሕይወታቸውን ካጡ የበረራ አስተናጋጆች አንዷ ናት። አማ ደስ በሚል የሕይወት ምዕራፍ ላይ ነበረች። ዓይኗን በዓይኗ ካየች ገና ስምንተኛ ወሯን በቅጡ አልሞላችም ። የነገ ተስፋዋን፣ የመኖሯን ምስጢር ልጇን ዳግመኛ ላታገኝ እስከ ወዲያኛው በድንገት አሸለበች። ስለ አማ ለማናገር ወደ ባልንጀራዋ ቤተልሔም ይርጋ አዲስ ማለዳ ያደረገችው የሥልክ ቆይታ በለቅሶ ብዛት ከተዘጋ ጉሮሮ የሚወጣ ድምፅ ተቀብሏታል። በለቅሶ የታጀበ ነበር ንግግራችን ˝ከዚህ በላይ መጎዳት ሊደርስብኝ አይችልም˝ አለች በተዳከመ ድምፅ። እኔም ለማፅናናት የተጠቀምኳቸው ቃላት ቀለሉብኝ።

ሌላኛዋ አዲስ ሙሽራ እና አንድ ዓመት ያልሞላው ሕፃን እናት ኤልሳቤጥ ምንውየለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተመርቃለች። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ በመሆን በቅርቡ ነበር ሥራ የጀመረችው። ʻሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪʼ ሆነችና ባልታሰበ አደጋ ቢሾፍቱ ሰማይ ላይ መክና ቀረች። ዘመድ ወዳጆቿን ቦሌ ከአየር መንገድ አቅራቢያ በቀጠሮ ተገናኘን፤ ለቅሶ እንደሰነበተባቸው ያስታውቃሉ፣ የበለጠ ደግሞ ያሳሰባቸው አንድ ዓመት ያልሞላት አንዲት ፍሬ ሕፃን ነገር ነው። ፈጣሪ ያጽናናቸው!

የሦስት ልጆች እናትና ከፍተኛ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችው ሳራ ገብረሚካኤል ረጅም ጊዜ ባገለገለችበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የከፋ መንገጫገጭ እንኳን በምትበርበት አውሮፕላን አጋጥሟት አያውቅም ነበር። የመጋቢት 1/2011 አጋጣሚው ግን የእስከዛሬውን የሚያካክስ ይመስላል። ሳራ የሦስቱን ልጆቿንም ሆነ የወዳጆቿን ዓይን ዳግመኛ ወደማታይበት ሔዳለች። ̋ስላልቀበርኳት እውነት እየመሰለኝ አይደለም ̋ ይላል የሳራ ወንድም ዳዊት ገብረሚካኤል። አስከሬን ማግኘት ካልተቻለም ቦታው ተከልሎ እየሔድን የምንጎበኝበት ሁኔታ ቢመቻችልን ይላል ዳዊት ግራ በተጋባ እና ሐዘን ባጠላበት መንፈስ።

ከአየር መንገድ ሠራተኞች በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን መንገድኞችም ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት ሠራተኞች ይገኙበታል ። ሳራ ቻላቸው፣ ጌትነት አለማየሁ፣ ስንታየሁ አይመኩ እና መልሰው ዓለሙ ይባላሉ።

ከቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋን ተከትሎ በርካታ አገራት ይህን ዓይነት አውሮፕላን ወደ አየር ክልላቸው እንዳይገባ ከማገድ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ገዝተዋቸው የነበሩትንም ከበረራ ውጪ እስከማድረግ ደርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ አገራዊ ግዙፍ ኩባንያዋን በመደገፍ ስትከራከር የነበረቸው ኃያሏ አገር ሰሜን አሜሪካ ቦይንግ 737-ማክስ 8 በስተመጨረሻ እገዳ ጥላበታለች። አሁን ላይ ቦይንግ ኩባንያ በመላው ዓለም ያሉ የ737-ማክስ 8 ሞዴል ምርቶቹን ሥራ ላይ እንዳይውሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም አደጋው በተከሰተ ማግሥት የቀሩትን አራት 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን ከአገልግሎት እንዲገለሉ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መፃኢ ሁኔታ
‹‹በአለም ላይ ባሉ የአየር መጓጓዣ ድርጅቶች ላይ ስጋት ከገባህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብረር›› ይላል ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠንካራ የደህንነት ሁኔታ ሲናገር የCNN ጋዜጠኛው ሪቻርድ ኩዌስት። ይህ ግን አሁንም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲህ በቀላሉ የገነባውን ስም ጠብቆ እንዲቀጥል ስለ ማስቻሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

አየር መንገዱ ስለሚኖርበት ጫና በአቢሲኒያ የበረራ አግልግሎት ምክትል ስራ አስኪያጅ ካፒቴን አማረ ገብረሐና ምላሽ አላቸው ።‹‹ ጫናውን የሚፈጥረው አየር መንገዱ በአንድ ጊዜ አራት አውሮፕላኖችን ከበረራ ማገዱ ነው ›› ሲሉ ይጀምራሉ ። በአቪየሽን ዘርፍ የረጅም አመታት ልምድ ያላቻው ካፒቴን አማረ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ በዚህ ሁኔታ በረራዎችን ማከናወን አደጋው የከፋ ስለሚሆን አየር መንገዱ የወሰደው እርምጃ ተገቢ እንደሆነም ያብራራሉ። ‹‹ይሁን እንጂ›› ይላሉ ካፒቴኑ‹‹ ቦይንግ 737-ማክስ8 በጣም ዘመናዊ አውሮፕላን ነው በቀላሉ ታግዶ የሚቀር አይደለም አስፈላጊው ስራ ተሰርቶ እንደሚመለስ እምነት አለኝ ›› ብለዋል። በሌላ በኩል ግን ይላሉ ካፒቴን አማረ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አውሮፕላን የተከሰተውን አደጋ ትኩረት ቢሰጥበት ኖሮ አሁን ላይ የተከሰተውን ከባድ ሀዘን መከላከል ይቻል እንደነበር ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ ከካፒቴን አማረ ሙያዊ ገለፃ መረዳት እንደተቻለው አሁን ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ በቴክኒክ ችግር የሚከሰቱ የአውሮፕላን አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ እሙን እንደሆነና የአውሮፕላን አደጋ ደግሞ በየትኛውም አየር መንገድ ላይ ሊያጋጥም እንደሚችል ይናገራሉ። ካፒቴን አማረ ይህን ብለው ሲያበቁ በሰው ስህተት የሚፈጠሩ የአውሮፕላን አደጋዎች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ምንም አይነት መሻሻል ማሳየት እንዳልቻሉ አለም አቀፍ ጥናቶችን ተመርኩዘው በመናገር ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here