የኦሮሞ ብሔርተኞች በኬኛ ሲንድሮም መለከፋቸውን በአዲስ አበባ፣ በድሬድዋና በሐረር እያየን ነው የሚሉት መላኩ አዳል በአዲስ አበባ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም አንስቶ ወደ ባለቤትነት ጥያቄ ማሸጋገር እየተሞከረ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባን ቻርተር አለአግባብ ለውጠው ታከለ ኡማን የሾሙበት ዋና ምክንያት ይኸው የብቸኛ ባለቤትነት አጀንዳ መሆኑ ግልጽ ነው በማለት በአንድ አገር እየኖርን፣ የራሳችን ትርክቶች ይዘን በተለያየ አገር እንደሚኖሩ የማይተዋወቁ ሕዝቦች እየሆንን ነው በማለት በጉዳዩ ዙሪያ መሰረታዊ ችግሮችን የሚሏቸውን ለይተዋል፤ ለችግሮቹም መፍትሔ የሚሉትንም ሐሳብ አቅርበዋል ።
የዘር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ዋናው ማጠንጠኛውም የብሔር ጭቆና ነበር የሚል የሐሰት የታሪክ ትርክት ነው። ʻበእኛ-እነሱʼ ከፋፍለህ ግዛ ሀብትን ለራስ ለመዝረፍና በስሜት ሕዝብን ለመንዳት ይጠቀሙበታል። የዘር ፖለቲካ በሰጥቶ መቀበል ላይ የማይመሰረት፣ በስሜት የሚመራ መንጋነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተግዳሮት ነው። የዘር ፖለቲከኞች መደበቂያ ብሔር የሚባል ዋሻ ስላላቸው የሞራል ገደብ የላቸውም። የዘር ፖለቲካችን ሕዝባችንን አስተባብረን ድኅነትን፣ ኋላ ቀርነትንና ችጋርን መታገል የምንችልበትን የሰው ሀብት እያባከነ ነው። ፖለቲከኞቻችን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ሲኖርባቸው፣ በፈጠሩት የፈጠራ ትርክቶች የአገራችንን ታሪክ በጎ ጎኖች ወደ ጎን በመተው ደካማ ጎኖች ላይ ብቻ በማተኮር፣ ሕዝብን በማሳሳት አገርንና የአገር አንድነትን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው። በዘር መሰረት የተዋቀረ ፌዴራሊዝም አቋቁመው አገራችንን አደጋ ላይ ጥለዋታል።
አዲስ አበባ እና ‘ኬኛ ሲንድሮም’
አዲስ አበባ በመጀመሪያ የነዋሪዎቿ፣ በመቀጠልም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ የኦሮሞ ብቻ የምትሆንበት ምንም ሕጋዊም፣ ታሪካዊም ዳራ የለም። አዲስ አበባ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል የተደረገ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና የጠንካራ ሥራ ውጤት ናት። ይህም የአዲስ አበባን ጉዳይ የሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሆን ያደርገዋል። አዲስ አበባ በዙሪያዋ ላሉ ኑዋሪዎች ትልቅ ጥቅም ትሰጣለች። ይህም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ጥያቄን መሠረት የሌለው ያደርገዋል። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን ማልማት እና የአካባቢው ነዋሪም የልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻል ነበር፤ ይቻላልም። አሁንም የከተማዋ መስፋት አይቀሬ ነውና፣ ከመሬታቸው የሚነሱ ገበሬዎች ተገቢው ካሣ የሚያገኙበትና ወደ ከተማ ሕይወት ለመግባት ተገቢ ሥልጠና የሚያገኙበት መንገድ መታሰብና ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጾች የሚገልጹት፣ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ እንደሆነች፣ የከተማ አስተዳደሩ እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፣ መስተዳድሩም ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥቱ እንደሆነ እና የከተማዋ ነዋሪዎችም በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወከሉና እራሷን የቻለች አስተዳደራዊ ግዛት መሆንዋንም ይደነግጋል። የከተማዋ አቀማመጥ በኦሮሚያ ክልል የታጠረ ስለሆነ የተለያዩ አገልግሎቶች፣ በከተማዋ እድገትም ሆነ መስፋፋት ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጋር አብሮ እንዲሰራ ይጠይቃል። ከዚህ ውጭ ኦሮሞው ከሌላው ብሔር ተወላጅ ጋር በአዲስ አበባ ላይ ያለው የልዩ ጥቅም ተጠቃሚነት እኩል ነው። ምክንያቱም የልዩ ጥቅሙ ዋናው መስፈርት አካባቢያዊ አቀማመጥ እና አስተዳደራዊ ግንኙነት እንጂ የብሔር ማንነት አይደለም።
የኦሮሞ ብሔርተኞች በኬኛ ሲንድሮም መለከፋቸውን በአዲስ አበባ፣ በድሬድዋና በሐረር እያየን ነው። ከአዲሱ አረጋና ለማ መገርሳ የሰማነው “500 ሺሕ ተፈናቃዮችን አዲስ አበባ ዙሪያ አሰፈርን፣ 6 ሺሕ ኦሮሞዎችን ከኦሮሚያ የተለያየ ቦታ በዝውውር አምጠተን አዲስ አበባ አስገብተን ሥልጣን ሰጠን፣ መሬትና የቀበሌ ቤቶችን እንዲታደሉ አደረግን፣ ሕገ ወጥ የመታወቂያ እደላ እያደረግን ነው” የሚል ነው። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም አንስቶ ወደ ባለቤትነት ጥያቄ ማሸጋገር እየተሞከረ መሆኑን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባን ቻርተር አለአግባብ ለውጠው ታከለ ኡማን የሾሙበት ዋና ምክንያት ይኸው የብቸኛ ባለቤትነት አጀንዳ መሆኑ ግልጽ ነው። የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ መውጣት ተከትሎ በጃዋርና የቄሮ የተቃዋውሞ ሰልፍ በመነሳት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 1) የክልሉን ወሰን አልፈው የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ ለባለ አድለኞች መተላለፋቸውና የማስተላለፍ ሒደቱ ተገቢ አይደለም፤ ይህ ውሳኔ እንዳይተገበር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዟል፣ 2) በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ተያይዘው የሚከናወኑ ሥራዎች ከክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ዕውቅና ውጪ ለመሥራት መታቀዳቸው ሕጋዊ አይደለም፣ እና 3) በአዲስ አበባ ጉዳይ ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይህ መግለጫ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 40 (3) መሰረት የሁሉም ክልል መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ንብረት እንጂ የአንድ ክልል የግል ንብረት አይደለም የሚለውን የሳተና መሬት የግሌ ነው ብሎ ሊወስን የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንና መብት እንደሌለ መሆኑን ያላገናዘበ ነው።
የልዩ ጥቅሙ ዋናው መስፈርት አካባቢያዊ አቀማመጥ እና አስተዳደራዊ ግንኙነት እንጂ የብሔር ማንነት አይደለም
የአዲስ አበባ ጉዳይ አሁን መታየት ካለበትም፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተቋቋመው በወሰንና አስተዳደር ጥናት አቅራቢ ቡድን መሆን ይገባው ነበር። ኦዴፓ በፌዴራል፣ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ላይ ባለው ሥልጣን፣ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ብቻ ለማድረግ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አመላካች ነው። ለዚህም እንዲያግዛቸው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልልን የድንበር ጉዳይንና ችግሮች ለመፍታት ሙፈሪያት ካሚል ከደኢሕዴን፣ ጠይባ ሀሰን ከኦዴፓ፣ ግርማ አመንቴ ከኦዴፓ፣ አሕመድ ቱሳ ከኦዴፓ፣ ታከለ ኡማ ከኦዴፓ፣ እንዳወቅ አብጤ ከአዴፓ፣ ሰለሞን ኪዳኔ ከሕወሓት እና ተስፋዬ በልጂጌ ከደኢሕዴን የያዘ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስተሩ አቋቁመዋል። የኦሮሚያ ክልልና ኢሕአዴግ ከተሳተፉ፣ አዲስ አበባ የሁሉም እንደመሆኗ መጠን በኮሚቴው ውስጥ አዲስ አበባን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች እንዲሁም ሁሉም ፓርቲዎች ሊወከሉ ይገባ ነበር። ስለዚህም፣ እንዳወቅ አብጤ፣ የደሕዴንና ሕወሓት ሰዎች፣ አሁኑኑ ከኮሚቴው ራሳቸውን ማግለልና የታሪካዊው ስህተት አካል እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ይህንንም ተከተሎ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ስለ አዲስ አበባ ምን እናድርግ ውይይት ጠርቶ ብዙ ሕዝብ በተገኘበት ከውይይት በኋላ በድጋፍ የፀደቀ የአቋም መግለጫ አውጥቶአል፡- 1) አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ እና የኢትዮጵያ እንጅ ማንኛውም ክልል ልዩ ጥቅም ሊጭንባት የማይችል ከተማ ነች፣ 2) የአዲስ አበባ ወሰን፣ በከተሞች የሚደረጉ ሰፈራዎች ላይ በምርጫ የተመረጠ አስተዳደር እስኪኖር ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ፣ 3) የአዲስ አበባ ሕዝብ በሚቀጥለው ምርጫ ልዩ ጥቅም ለሚል አካል አንድ ድምፅ እንዳይሰጥ፣ ይህን ለማድረግ ስብሰባውን የጠራው አካል በሕዝብ የተሰየመ መሆኑና 4) እንቅስቃሴያችን ሰላማዊ መሆኑን የወሰንን መሆኑን በሙሉ ድምፅ ተስማምተናል በማለት ተቁዋሞውን ሕዝቡ አሰምቷል።
መሰረታዊ የችግሩ መንስዔዎች
የችግሩ መንስዔዎች ድንቁርና፣ ኋላ ቀርነት፣ ደካማ ባሕል፣ ብሎም የልኂቃን ጠባብ የሆነ የዘር ፖለቲካና የዘር ፌዴራሊዝም ናቸው። ሕገ መንግሥቱ ከፌደሬሽኑ አወቃቀር ጋር ተዳምሮ ዋናው የግጭት መሠረት ሆኗል። የጋራ እሴትና ርዕዮት እንዳይኖርና ኢትዮጵያዊነት ማንነት ከዘውግ ማንነት እንዲያንስ መሠራቱ በኢትዮጵያ ኅልውናና በዜጎች የትም የመኖር መብት ላይ ችግር አስከትሏል። የየክልሎቹ ሕገ መንግሥቶች በየክልሉ ያሉ ሕዝቦችን ነባርና መጤ ብለው በመከፋፈልና ነባር ለሚሏቸው የክልሉ መሬትም ሆነ ሀብት ላይ ሌላው ዜጋ የሌለውን የልዩ ባለቤትነት መብት ይሰጣሉ። አገራዊ አንድነታችን የሸረሸረውና ልዩነት የሚያባብሰው፣ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ይበልጥ እንዳናበለጽግ ተግዳሮት የሆነን ይኸው ሕገ መንግሥትና አስተዳደራዊ መዋቅር ነው። የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ሕዝብ በመረጠው ከንቲባ ለመተዳደር አለመቻልም በዚሁ ምክንያት ነው። በኦሮምያ ያለው የሀይል ሚዛን በኦዴፓ፣ በኦነግና በቄሮ መካከል መበተኑ እና በመንግሥት ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ኦነግነት ማመዘን ሌሎቹ ችግሮች ናቸው።
ለችግሮቻችን መፍትሔዎች
ሕገ መንግስቱን ማሻሻል፣ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም መሰረት ማዋሐድና በዘርና በቋንቋ ላይ መሰረት ያላደረጉና የርዕዮት መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረት ያስፈልጋል። በዘርና ቋንቋ ብቻ የተዋቀረውን ፌዴራሊዝም ማስተካከል፣ የክልል ሕገ መንግሥቶች ከፌዴራል ዋናው ሕገ መንግሥት ጋር ያለውን መጣርስና ከብሄሩ ውጭ ለሆኑ ዜጎች ተንቀሳቅሰው የመስራት መብት መጣስ መንስዔ መሆኑን ማስተካከል ያስፈልጋል። ሚዲያዎችና አክቲቪስቶችም በሕጉ መሠረት እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ባሕልንና ቋንቋን ማሳደግ፣ ለእኩል ተጠቃሚነት መሥራት፣ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ፍትሓዊነትን ማረጋገጥ ያሰፈልጋል። የታሪክ ትርክቶችን ወጥ በማድረግና በኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ በመኖር ውስጥ የቡድን መብት እንደሚከበር ማሳየት ይገባል።
ማጠቃለያ
ይህንንም ʻዲሞግራፊክ ኢንጂኔሪንግʼና ሁሉን የኛ አጥብቀን እንቃወመዋለን፣ ለነገ አገርን ወደ እርስ በርስ ጦርነት የሚገፋ ነውና። በአንድ አገር እየኖርን፣ የራሳችን ትርክቶች ይዘን በተለያየ አገር እንደሚኖሩ የማይተዋወቁ ሕዝቦች እየሆንን ነው። ይህ የሚያሳየን የጋራ የሆነ ርዕዮት እንዲኖረን በበቂ እንዳልሰራን፣ በብሔረ-ምስረታው እንዳልገፋን፣ የታሪክና የጥቅም ሽሚያው ላይ መሆናችንን ነው። ችግሩ የአስተሳሰብ ልዮነትን በማክበር እና ልዮነትን በሐሳብ ተግባብቶ መፍታት አለመቻል ነው። እናም ከታሪክና ሥልጣን ሽሚያው ወጥተን፤ አገራዊ ነጻ ተቋማትን ገንብተን፤ በጠራ ርዕዮተ ዓለም ብቻ የምትመራ የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ። ለዚህም ግፊት እናድርግ። ያለዚያ ግን በጊዜያዊ ጉልበት ብቻ ሥልጣን የሚያዝባት፣ የተወሰነ ቡድን የሚጠቀምባት እና ብዙኀኑ የሚጎዳባት ኢትዮጵያ እንዳትሆን አሁንም እሰጋለው።
መላኩ አዳል ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በመሥራት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011