ኢሕአዴግ’ን የማዋሐድ ተልዕኮና ሥጋቶች

0
987

በቅርቡ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርና ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶች በአጭር ጊዜ ሊዋሐዱ እንደሚችሉ መግለፃቸውን ተንተርሶ የፖለቲከኞችና የአገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቀሴ የሚከታተሉትን ትኩረት ስቧል፤ ለብዙዎችም መወያያና መከራከሪያ ነጥብ ሆኗል። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ የውሕደት ሐሳቡ መቼ ተነሳ መቼስ ተግባራዊ ይደረጋል፣ የውሕደቱ ሥጋቶች ምንድን ናቸው? ወቅታዊውን የግንባሩን ውስጠ ፖለቲካ ተዋስኦ ድርሳናትን በማገላበጥ፣ ፖለቲከኞችና ባለሙያዎችን በማነጋገር የሚከተለውን ሐተታ ዘ ማለዳ አሰናድቷል።

መንደርደሪያ
የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየሩ ውጥን መነሳት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ጉዳይ በየኹለት ዓመቱ በሚካሔደው የግንባሩ ጉባኤ ወቅት በየጊዜው ሲነሳ ቆይቷል። በመስከረም 2011 በሐዋሳ በተካሔደው የድርጅቱ ጉባኤም ውሳኔው በይደር ለሌላ ጊዜ መተላለፉም ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በጽሕፈት ቤታቸው በነበረ ስብሰባ ላይ፣ ኢሕአዴግ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲነት በቅርቡ እንደሚቀየር ያሳወቁት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በተጨማሪ የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎች አዲስ በሚመሰረተው ውሕድ ፓርቲ ውስጥ እንደሚካተቱ ተናግረዋል።

 

“ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የማንኛውም ፓርቲ መሠረታዊያን የሚባሉት የፖለቲካ ፕሮግራም (ርዕዮተ ዓለም)፣ የአደረጃጀት መዋቅርና ዲሲፕሊን በኢሕአዴግ ውስጥ በተናጉበት ወቅትና ሕወሓት አኩርፎ ቁጭ ባለበት፣ በአማራና ትግራይ ክልል ፍጥጫዎቹ እየተባባሱ በመጡበት ወቅት፣ በምን መሠረት ላይ ነው ኢሕአዴግ ያውም አጋሮችን አካቶ የሚዋሐደው?››

 

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እርስ በእርሳቸው ያስተሳስራቸው የዓላማ አንድነት መሸርሽሩ በተለያየ መልክ ይንጸባረቃል። ለምሳሌነትም እስከ ቅርብ ዓመታት ከግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል “አድራጊ ፈጣሪ ነው” ይባል የነበረው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ግንባሩ ድርጅታዊ መስመሩን መሳቱን እና ከሚመራበት የማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት መርህ ማፈንገጡን በተደጋጋሚ መግለፁን በዋቢነት ማንሳት ይቻላል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ግንባሩ ለመዋሐድ ዝግጅቴን

ጨርሻለሁ ማለቱ ምን ያህል ከእውነታው ጋር የተጣጣመ ነው?
ኢሕአዴግ’ን አገር ዐቀፍ ፓርቲ የማድረግ ሥጋቶች
የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዐቢይ ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት ኢሕአዴግʻንና አጋር ፓርቲዎችን በማዋሐድ አንድ አገራዊ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመሥረት ዕቅድ፣ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን አዲስ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል። አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢሕአዴግ ላይ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመያዝ ስለተቸገሩ የመረጡት መንገድ እንደሆነ ሲገልጹ፣ የብሔረሰቦቻቸውን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ለማስከበር ቅድሚያ የሰጡ የፖለቲካ ልኂቃን ደግሞ “ለምን ዛሬ?” ሲሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

ሥጋቱ የሚጀምረው ከራሱ ከኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ነው። በ1999 የፀደቀውና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኘው መተዳደሪያ ደንብ ላይ “ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔር አገር እንደመሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን፣ በድርጅቶች በተለይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት ነው” የሚል መሠረታዊ ዘውግ አለው።

መተዳደሪያ ደንቡ፣ ምክንያቶቹንም ሲያብራራ፣ ኢሕአዴግ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች በአንድነት ያዋቀሩት ግንባር ሲሆን ብቻ፣ በፅኑ የሚታገልለትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነትና አንድነትን የማስጠበቅ ዓላማ በተግባር ሊተረጉምና ሊያረጋግጥ እንደሚያስችለው ይገልጻል።

“በመሆኑም የሕዝቦቻቸውን መብት የማስጠበቅ ዓላማን ያነገቡና በቀላሉ የሕዝባቸውን ድጋፍ የሚያገኙ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶችን ብቻ በግንባሩ ዙሪያ አሰልፎ ይንቀሳቀሳል፤›› ሲል የመተዳደሪያ ደንቡ የኢሕአዴግን ድርጅታዊ መዋቅር መርህ ይደነግጋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩበት ምክንያት ምንድን ነው?” ብለው የሚጠይቁት የፖለቲካ ተንታኙ ሙሼ ሰሙ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን ያለውን ሁኔታ ገምግመው ለአገሪቱ አይጠቅምም ብለው በማሰብ ነው ይህንን ያሉት? አንድ ፓርቲ ብድግ ብሎ ከብሔር ድርጅትነት ወደ ኅብረ ብሔራዊነት እለወጣለሁ ሲል ምክንያቱ ምንድን ነው? ያለውን የፖለቲካ ፍልስፍና ስለማይቀበለው ነው? አላዋጣ ስላለው ነው? አልገባኝም፤ መጀመሪያ ይሔ መብራራት አለበት” ሲሉ ስለጉዳዩ ግራ መጋባታቸውንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ግላዊ መሰረት ያለው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሙሼ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰረታዊ ጉዳዮችን አላብራሩም ሲሉ ይሞግታሉ። ሙሼ ካነሷቸውና ዐቢይ ሊመልሷቸው ይገባል ብለው ከጠቀሷቸው ነጥቦች መካከል የአስተሳሰብ፣ የፖለቲካ ፍልስፍና እንዲሁም የአዲሱ ፓርቲ አደረጃጀትና በብሔር የተዋቀሩት ፓርቲዎች ዕጣ ፈንታ የሚሉት ይገኙባቸዋል። ይህ በተሟለ ሁኔታ ባልተመለሰበት ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ሙሼ ተቀባይነቱን አጠራጣሪ ወይም ስሜታዊ ያደርገዋል ይላሉ።

ሙሼን ጨምሮ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ስሜት የተጫነው ወይስ በደንብ የታሰበበት ለሚለው ጥያቄ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳዳት ነሻ ለአማርኛው ቢቢሲ በሰጡት ምላሽ፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ተመሳሳይ ፕሮግራም ስላላቸው፣ በልማት፣ በዲሞክራሲና ሰላምን በማስፈን በጋራ ሲሠሩ በመቆየታቸው ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ላለመሸጋገር የሚያግዳቸው ምንም ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላው አጠራጣሪ ጉዳይ የውሕደት ሐሳቡ ኢሕአዴግ አሉኝ ከሚላቸው 6 ሚሊዮን አባላት እንዲሁም አባል ፓርቲዎቹ መክረውበታል ወይ የሚለው መሰረታዊና መመለስ የሚገባው ጥያቄ ሆኖ ወጥቷል።

የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች በተረጋጋ መስመር ላይ ያለመሆን
ኢሕአዴግ ከበፊት ጀምሮ ወደፊት ወደ ተዋሀደ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲነት እንደሚለወጥ ሲያመላክት እንደነበር፣ ነገር ግን ወደዚህ ውሕደት ለመምጣት የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና አባላት በግንባሩ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም፣ በመርኅና በአስተሳሰብ መብሰልን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጡና ይኼንን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ባለመቻሉ ውህደቱን ከዓመት ዓመት ሲገፋው እንደቆየ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህርና የፖለቲካ ተንታኝ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ያስታውሳሉ።

ሲሳይ “አሁን ምን ተገኝቶ ነው ኢሕአዴግ ወደ ውሕደት የተጣደፈው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፣ “ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የማንኛውም ፓርቲ መሠረታዊያን የሚባሉት የፖለቲካ ፕሮግራም (ርዕዮተ ዓለም)፣ የአደረጃጀት መዋቅርና ዲሲፕሊን በኢሕአዴግ ውስጥ በተናጉበት ወቅትና ሕወሓት አኩርፎ ቁጭ ባለበት፣ በአማራና ትግራይ ክልል ፍጥጫዎቹ እየተባባሱ በመጡበት ወቅት፣ በምን መሠረት ላይ ነው ኢሕአዴግ ያውም አጋሮችን አካቶ የሚዋሐደው?›› ሲሉ ተግዳሮቶቹን በጥያቄ መልክ ያቀርባሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊ የፖለቲካ ትርክቶችን አቅጣጫ ለመዘወር ፈልገው የተናገሩት እንደሆነ የሚያምኑትም በዚህ ምክንያት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

 

ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣቱ ጉዳይ ቀደም ሲል የነበረ አስተሳሰብ ነው። እናጥናው ተብሎ ሲንከባለል የቆየ ነው። በቅርብ ጊዜ ባደረግናቸው ስብሰባዎችም፣ ይሔ ነገር ለአንድነታችን ይጠቅማል በሚል ተነስቶ ነበር። ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ጥቅም አለው። ይሔ ማለት ግን የብሔር ብሔረሰብ አደረጃጀት ይጠፋል ማለት አይደለም

 

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህሩ ወንደሰን ታረቀኝ (ዶ/ር) ሲሳይ ካነሱት ነጥብ ጋር ይስማማሉ። ወንድወሰን ወደ ውሕደት ከመካሔዱ በፊት ብዙ የቤት ሥራዎች መሰራት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

ቢያንስ በዋና ዋና የፓርቲው የሕገ መንግሥት፣ የልማት ሁኔታዎች ላይ ተመሳሳይ አሊያም እጅግ ተቀራራቢ አረዳድ መኖር አለበት፤ እነዚህ ሳይሟሉ ወደ ውሕደት ለመሄድ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚመለከትም በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት እንደሌለ የአደባባይ ምስጢር ነው ሲሉም ያስረዳሉ።

“የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላት ተቀራራቢ ወይም አንድ ዓይነት አቋም እንደሌላቸው ግልፅ ነው፤ ራሳቸውም በተለያየ ጊዜ የሚናገሩት ይህንኑ ነው” የሚሉት ወንደሰን ግንባሩም እንደ ግንባር ተቀራራቢ አቋም ሳይኖረው አንዳንዶቹ የግንባሩ ፓርቲዎች ከፍተኛ የሆነ የጎራ መደበላለቅ እያለ ‘እንዋሐድ’ ስለመባሉ ያላቸው ሐሳብ ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል።

ይሁንና በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ጋዜጣ መጋቢት 2011 ያነጋገራቸው ሳዳት ነሻ፣ ውሕደቱ የሚፈጸመው የኢሕአዴግ ጉባዔ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህም መሠረት ጥናት መካሔዱንና ጥናቱ በለያቸው ጭብጦች ላይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች በቅርቡ በተናጠል ሆነው ከማኅበራዊ መሰረቶቻቸው ጋር ውይይት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል። በመሆኑም የፖለቲካ ትርክት አቅጣጫ ማስቀየሪያ ሳይሆን፣ ታቅዶና በኢሕአዴግ ጉባዔ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች ውስጥ በጋራም ይኹን በተናጠል ሊገለጹ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩም እነዚህ ችግሮች ውሕደቱን እንደማያደናቅፉ፣ እንዲያውም የውሕደቱ መምጣት ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ የራሱን ዕገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ውሕደቱ የሚፈጸመው የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባሕርያት ሳይለቅ እንደሆነ የተናገሩት ሳዳት፣ “ውሕደቱ የብሔር፣ የቋንቋ ማንነቶችንና ፌዴራሊዝሙን ይንዳል የሚሉ ሥጋቶች ያሏቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ እነዚህ የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባሕርያት በውሕደት በሚወልደው አዲስ አገር ዐቀፍ ፓርቲ ውስጥም የሚቀጥሉ መሠረታዊያን ናቸው፤” በማለት አስረድተዋል።

በውሕደቱ የማይስማማ ፓርቲ ቢኖርስ?
የፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ ኢሕአዴግ ከግንባር ወደ ፓርቲ መሸጋገር አለበት የሚል ጥያቄ ወደ ጉባዔም መጥቶ በተለይ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ አፅንኦት ተሰጥቶት አቅጣጫ ተቀምጧል። ኮሚቴም ተዋቅሮ እየተሰራበት ይገኛል፤ ጥናቱ አልቆ ለአጋር ድርጅቶቹ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት አባላቶቹም መክረው ነው ውሳኔ ሊሰጥበትና ውሕደቱ ይፋ ሊደረግ የሚገባው ብለው፣ በዚህ ውይይት ውህደቱን የማይስማሙ ድርጅቶች መኖራቸውን ያላገናዘበ ንግግር ማድረግ ውጤቱን ያበላሸዋል ባይ ናቸው።

በገዢውም በኩል ሆነ በተፎካካሪዎች በኩል ወደ ውሕደት መሔዳቸው፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለማምጣት ከተፈለገ በጣም ጥሩ ሒደት ነው ብዬ ነው የማስበው የሚሉት ፖለቲከኛው የሸዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ውሕደትን በተመለከተ መለስ ዜናዊ በነበረበት ወቅት በ2002 ይሔው ጥያቄ ተነስቶ ነበር። የኢሕአዴግ ድርጅቶች በአንድ ሳንባ በሚተነፍሱበት፣ በአንድ ልብ በሚያስቡበት ዘመን ታስቦ ግን አልሆነም፤ ሸፋፍነው ነው ያስቀሩት። ስለዚህ የመርኅ ጉዳይ ነው። አንድ ሆነህ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሆነህ ትወጣለህ ብሎ ማመን አንዱ ነው። በዚህ ውሕደት አላምንም ያለው ተለይቶ መውጣት ይችላል የሚል አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።

በኢሕአዴግ ፓርቲዎች መካከል ልዩነቶች ስለመኖራቸው በግልጽ በሚታይበተት በአሁኑ ወቅት ውሕደቱ እውን ሊሆን ይችላል እንደሆነ ሪፖርተር ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሳዳት “ኢሕአዴግ ውስጥ የተለመደ አሠራርና ልምድ አለ፤ ድርጅቱ የትግል ፓርቲ ነው፤ ስለሆነም ኢሕአዴግን የመሠረቱት ፓርቲዎች የተለያዩ ክርክሮችና ሐሳቦችን ያቀርባሉ፤ ነገር ግን ኢሕአዴግ ይህን እንደ ልዩነት አያየውም” ብለዋል።

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በገዢው ግንባር ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት ከውሕደቱ በፊት እንዲጠብ ካልተደረገ የኢሕአዴግ ዋነኛ አስኳል ሆኖ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው ሕወሓት በሚመሰረተው ውሕድ ፓርቲ ውስጥ የመዝለቁ ነገር አጠያያቂ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ሳዳት ተመሳሳይ ለሆኑ ለእንደዚህ ዓይነት ጥያቄ መላሽ ሲሰጡ ውሕድ ፓርቲ ለመሆን የአባል ድርጅቶች ፍላጎት ይጠይቃል፤ መሠረታዊ ፍላጎት አለ ብለን በማለት ግንባሩ ያስጠናው ጥናትም ያረጋገጠው እሱን መሆኑን በአነክሮ ገልጸዋል። “ይህ ከሌለ ግን ወደ ፓርቲም ሳንሸጋገር ከግንባርም መውጣት የሚፈልግ መውጣት ይችላል” ሲሉ ሳዳት በውሕደቱ የማያምኑ ካሉ አማራጩን ጠቁመዋል።

ሐሳቡ መቼ ተነሳ? በማን?
የኢሕአዴግ ውሕደቱ ሐሳብ በግልጽ ፈጥጦ የመጣው ሳዳት እንደሚሉት በዘጠነኛውና ዐሥረኛው ጉባዔን ጨምሮ በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲነሳ የቆየ መሆኑን አስታውሰው፥ ከግንባር ወደ ፓርቲ መሻገር ያስፈልጋል በሚል አፅንኦት ተሰጥቶ የተነሳው በ11ኛው መደበኛ ጉባኤ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ ሌሎች መረጃዎች ከእሳቸው የሚጣረስ ምላሽ ያቀርባሉ። ለምሳሌ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አሌክስ ደዋል (ፕሮፌሰር) በ2018 (እ.አ.አ.) “The Future of Ethiopian Developmental or Political Market Place?” በሚል ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት ላይ፣ መለስ ኢሕአዴግ ተዋሕዶ አንድ አገር ዐቀፍ ፓርቲ እንደሚሆን፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው መሟላት የሚገባቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መደላድሎች ሲረጋገጡ መሆኑን እንደ ነገሯቸው አጣቅሰው ጽፈዋል።

ነገር ግን ለዚህ ሽግግር የሚያበቁ ናቸው የሚላቸው ምቹ መደላድሎች ሳይሟሉ ከግንባርነት ወደ አገር ዐቀፍ ፓርቲነት ለመሸጋገር በማሰብ ሥራ የጀመረው በ2007 ባካሔደው የግንባሩ ጉባዔ ይኼንኑ የሚመለከት ውሳኔ በማሳለፍና ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚቴ በማቋቋም የነበረ ቢሆንም፣ ይኼው ኮሚቴ ላለፉት አምስት ዓመታት ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲያካሔድ የነበረውን ጥናት ማፋጠን የጀመረው ግን ከ2010 በኋላ መሆኑ ይነገራል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ሽኩቻና መጠላለፍ በዋናነት ይጠቀሳል። በመስከረም 2011 በተካሔደው የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይም ይኸው የውሕደት ጉዳይ ኮሚቴው ባቀረበው ያልተጠናቀቀ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ውይይት ተደርጎበታል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን (ዶ/ር) ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተጠይቀው ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ምላሻቸውን ሲሰጡ፣ ˝ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣቱ ጉዳይ ቀደም ሲል የነበረ አስተሳሰብ ነው። እናጥናው ተብሎ ሲንከባለል የቆየ ነው። በቅርብ ጊዜ ባደረግናቸው ስብሰባዎችም፣ ይሔ ነገር ለአንድነታችን ይጠቅማል በሚል ተነስቶ ነበር። ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ጥቅም አለው። ይሔ ማለት ግን የብሔር ብሔረሰብ አደረጃጀት ይጠፋል ማለት አይደለም ብለው ነበር።

መቼ ተግባራዊ ይሆናል?
ይኼንን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ በግንባሩ ጽሕፈት ቤት የጥናትና ምርምር የሥራ ክፍል ሥር ተዋቅሮ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን የሚገልጸው ሰነዱ፣ ኮሚቴው ባካሔደው ጥናትም የግንባሩን መዋቅራዊ አደረጃጀት በተመለከተ ሦስት አማራጮችን ማመላከቱን ይገልጻል።

ጥናቱ በመጀመርያ አማራጭ፣ ኢሕአዴግና አጋሮቹን አንድ ላይ ለማዋሐድ ጊዜው ገና መሆኑን፣ ይህም ማለት ኢሕአዴግና አጋሮቹን ለውሕደት የሚያበቃው ቅድመ ሁኔታ አለመሟላቱን የሚያመላክት ሲሆን፣ በኹለተኛ አማራጭነት የቀረበው ደግሞ የኢሕአዴግ መሥራች ድርጅቶችም ሆነ አጋር ድርጅቶች አሁን በሚገኙበት አቋም ላይ ሆነው አንድ የጋራ አገር ዐቀፍ ፓርቲ ይመሥርቱ የሚል ነው። በሦስተኛ አማራጭነት፣ የቀረበው ደግሞ አሁን ያሉት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች (የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች) የብሔራዊ ድርጅቶቻቸውን አባላት ይዘው አንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይመሥርቱ የሚል ነው።

በቀረቡት ሦስት አማራጮች ላይ የመከረው 11ኛው የድርጅቱ ጉባዔ የግንባሩን አደረጃጀት ፈትሾ የማስተካከል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መግባባተ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህ የመዋቅር ማስተካከያ የኢሕአዴግ የግንባር አደረጃጀት ̋አሁን ያለንበትንና ከፊታችን የሚጠበቅብንን የትግል ምዕራፍ በአግባቡ ሊያሳካ ይችላል ወይስ አይችልም?˝ የሚለውን ጉዳይ አፅንኦት በመስጠት እንዲፈጸም አቅጣጫ አስቀምጧል።

በመሆኑም በጥናቱ በቀረቡት አማራጮች ላይ ዝርዝር ውይይት በየደረጃው ጊዜ ወስዶ በማካሔድ ከተቻለ ከሚቀጥለው ጉባዔ በፊት እንዲጠናቀቅ፣ ካልተቻለ ደግሞ በሚቀጥለው ጉባዔ (የድርጅቱ ጉባዔ ከኹለት ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የጊዜ ልዩነቶች የሚካሔድ ነው) ቀርቦ እንዲወሰን አቅጣጫ አስቀምጧል።
ይህ ውሳኔ በመስከረም ከተላለፈ በኋላ ኮሚቴው ተጨማሪ የማጣራት ሥራዎችን ማከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችና ድርጅቶቹ ከሚወክሏቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ያደረጉት የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር በጥቂት ወራት ውስጥ ኢሕአዴግʼንና አጋር ድርጅቶችን በማዋሐድ አንድ አገር ዐቀፍ ፓርቲ እንደሚመሠረት ይፋ አድርገዋል።

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ አጋር ድርጅቶች ከስመው፣ በወራት ውስጥ አገር ዐቀፍ ፓርቲ እንደሚመሠረትና ኢሕአዴግ የሚለው መጠሪያም እንደሚቀየር በድፍረት መናገራቸው [ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ] አስገርሞኛል ያሉት ሲሳይ (ዶ/ር) መጀመሪያ አጋር ድርጅቶቹና ደጋፊዎቻቸውን መምከር የባቸውም ወይ ሰሉ ይጠይቃሉ። አክለውም የግለሰብ ውሳኔ የፓርቲና የደጋፊ ውሳኔ ሊሆን ስለማይችል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ግለኝነትን የተላበሰ ነው ሲሉም ተችተዋል።

ኢሕአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወዴት?
የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ አንቀጽ ˝ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም የሚመራና በፕሮግራሙ ላይ ለሰፈሩት ዓላማዎች የሚታገል ድርጅት ነው። ያነገባቸው ዓላማዎች ዴሞክራሲያዊና አብዮታዊ በመሆናቸው በተግባር ላይ ከዋሉ ኅብረተሰባችንን ከሚገኝበት ድኅነትና ኋላ ቀርነት አላቀው ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና ያበቁታል ̋ ይላል።

የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩሩ በረከት ስሞኦን በ2010 ባሳተሙት ̋ትንሳዔ ዘ ኢትዮጵያ˝ በሚል ርዕስ ባሰተሙት መጽሐፍ ላይ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በርዕዮተ ዓለምነት የተቀበለበት ምክንያት በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ዕድገትን በፍጥነት ለማረጋገጥ በመተለም መሆኑን ጠቅሰዋል። የርዕዮተ ዓለሙ ደጋፊዎች ባለፉት የኹለት ዐሥርታት ዓመቱ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጤት መሆኑን በስፍት ይናገራሉ።

ኢሕአዴግ ለፈጠረው ግንባር ዘልቆ እንዲቆይና ውጤታማ ተግባር እንዲፈጽም ያደረገው ዋናው መሣሪያ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙ እንደሆነ አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አዲስ ፈተናዎች›› በሚል ርዕስ ነሐሴ 2010 በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ ጠቅሰዋል።

ይሁንና በመጋቢት 2010 ወደ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነትና ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር የተፈናጠጡት ዐቢይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም ይዘው ለመጓዝ ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፤ ወደ ሥልጣን በመጡ በመጀመርያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች የዚህ መገለጫ ምልክቶች ተደርገው በብዙዎች ይወሰዳሉ።

̋በአገሪቱ ላይ በአንድነት ተዋሕደው የቆዩ ሌሎች ፓርቲዎች የሉም። ከእነሱ ልምድ እንቅሰም እንዳይባል ኢሕአዴግ ነው የነበረው። እሱም አንድ ውሕድ ፓርቲ ሳይሆንም በሰላም ሲሰራ ነበር። ስለዚህ ዋናው የአመራር አስተሳሰብ ጉዳይ ነው። የአመራር አስተሳሰብ ሲበላሽ ነው ዘር የሚባለው ነገር የሚመጣው። አንድ ፓርቲ ቢሆንም የዘር አስተሳሰቡ አይቀርም˝ በማለት ዘረኝነትን በአንድ ፓርቲነት ማስቀረት እንደማይቻል ጠቁመዋል።

የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት መሆን የሚቻለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማን በግልጽ በፕሮግራማቸው ላይ የቀረፁ ድርጅቶችን ብቻ መሆኑን፣ ነገር ግን ይኼንን ፕሮግራም መቀበል ብቻ ሳይሆን በተግባር ለፕሮግራሙ ተፈጻሚነት የሚታገሉ፣ አባላቱም ይኼንኑ የሚያሟሉ መሆን እንዳለባቸው በመሥፈርትነት ያስቀምጣል።

ይሁን እንጂ ቅዳሜ ነሐሴ 19/ 2010 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢሕአዴግ የፕሮግራም ለውጥ የማድረግ ሒደት ውስጥ እንደሆነ ተጠይቀው ምንም የተለወጠ ነገር አለመኖሩን በተድበሰበሰ መንገድ ገልጸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙን የመለወጥ ፍላጎት እንዳለው ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የተድበሰበስ የሚያደርገው፣ ምላሻቸው እስካሁን የተቀየረ ነገር ስላለመኖሩ ወይም አሁን ያለው ሁኔታ ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ ነው።

̋ኢሕአዴግ በጥልቅ መታደስ አለብኝ ብሎ ወስኗል። በጥልቅ መታደስ ማለት አርጅቻለሁ፣ ሻግቻለሁ ማለት ነው፤ ̋ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ̋መለወጥ ያስፈልገናል። እስካሁን ግን አይዲኦሎጂን በሚመለከት የተነሳ ነገር የለም፤˝ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

̋እኛ ቆመን ማኅበረሰቡ ከቀደመን ልንመራው አንችልም። ቢያንስ አንድ ርቀት እየቀደምን ማየት አለብን። አዳዲስ ሐሳቦችን እየጨመርን መሔድ አለብን፤˝ ሲሉ ተናግረዋል። ያልተመለሰው ጥያቄ ግን ኢሕአዴግ መለወጥ የሚፈልገው ወዴት አቅጣጫ ነው የሚለው ነው።

አንድርያስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ እየታዩ ያሉ ለውጦች ግንባሩ ወደ ሊበራላዊ ዴሞክራሲ የመሸጋገር አዝማሚያ የሚታዩበት መሆኑን ጠቁመዋል። ‹‹ይህ ኒዮ ሊብራሊዝም ከሚባለው አስተያየት የተለየ ነው። ኒዮ ሊብራሊዝም በአስተዳደር የመንግሥትን ሚና የሚያንኳስስ፣ የነፃ ገበያውንና ዋና ተጠቃሚዎቹን ለከፍተኛ ቦታ የሚዳርግና አብዮታዊም ሆነ ሊበራላዊ ዴሞክራሲን የሚቃረን ነው፤›› ሲሉም ልዩነቱን አስቀምጠዋል።

ሳዳት ኢሕአዴግ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ የአገሪቱ መሪ መሆን የሚችል ሰው የማፍራት አቅም ለማዳበር ታልሞ እንደሆነ ውሕደቱ ያስፈለገበትን ምክንያት ዘርዝረው፣ ይሁን እንጂ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ከመሆኗ ጋር ተዛምዶ በተለይም ኢትዮጵያዊነት በድርጅቱ ሊቀ መንበር ጎልቶ በሚቀነቀንበት ወቅት፣ የውሕደት ሐሳቡ ወደፊት መምጣቱ ለአንዳንዶች በብሔር አደረጃጀትና በፌዴራሊዝም ላይ ለውጥ የሚያጣ ሆኖ ታይቷቸዋል ይላሉ።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) ፌደራል ስርዓቱ፣ በብሔር ብሔረሰብ ደረጃ የሚታዩ ኅብረተሰቦች እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ነው። እራሱን ለማስተዳደር የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል። ̋ ሲሉ ከዚህ ቀደም ከፌደራል ስርዓቱ ባልተነጠለ መልኩ እንዲካሔድ መታሰቡን አስረድተዋል። ኅብረተሰቡ በራሱ ቋንቋ፣ የራሱ አካባቢ፣ የራሱ ታሪክና ባሕል ያለው ስለሆነ ልናጠፋው አንችልም።

“ሁሉም የጋራ አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት እንዲሆን የታሰበ እንጂ ኢሕአዴግ በፌደራል ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ለውጥ የለም፤ ግንባሩን ወደ አንድ ፓርቲ ማምጣት ማለት ወደ አኀዳዊ ሥርዓት ይመጣል ከሚለው ሐሳብ ጋር አይገናንኝም” ሲሉ አንድርያስን በሐሳብ ሞግተዋል።

እንደማጠቃለያ
የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ዐቢይ ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት ኢሕአዴግንና አጋር ፓርቲዎችን በማዋሐድ አንድ አገራዊ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመሥረት ዕቅድ፣ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ልኂቃን አዲስ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷ፤ ዛሬም ጉዳዩ በአወያይነቱ ቀጥሏል። የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች እርስ በርስ መተማመን ባልቻሉበት በአሁኑ ወቅት፣ በብሔር ፌደራሊዝም ለሩብ ምዕተ ዓመት የቆየን ድርጅት ወደ አገራዊ ፓርቲነት ለመቀየር መታሰቡ፤ በክልሎች መተማመን አለመተማመኑ ሥር ከመስደድ አልፎ ለጦርነት ተፋጠዋል የሚሉ ወሬዎች በሚናፈሱበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መነሳቱ የብዙዎች መነጋገሪያ አድርጎታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here