የሥጋት ፖለቲካና ጭፍን ድጋፍ

0
488

በሐሳባዊነት “የተለወጠው”፣ በመዋቅር እና ሕጋዊ አተያይ ግን “ያልተለወጠው” የፖለቲካ ስርዓት፥ ከሁሉም ሕዝቦች የሚሰበስበውን “ጥቅም” ለጭፍን ደጋፊዎቹ በ“የእኔነት” ስሜት ማከፋፈል ከጀመረ፥ ተለወጠ ሳይሆን ማሊያ ቀየረ ነው ሊባል የሚችለው በማለት ቤተልሔም ነጋሽ ይህን መጣጥፍ አቅርበዋል።

 

 

ላለፈው አንድ ዓመትና ከዚያም ጥቂት አለፍ ለሚል ጊዜ አገራችን በለውጥና በብዙ ክስተቶች ውስጥ አልፋለች፤ በማለፍም ላይ ትገኛለች። በብዙ መልኩ የእኛ ጉዳይ ሊተነተንና ትርጉም ሊሰጠው የማይችልበት ብዙ አጋጣሚ እና እውነታ አለ። የመጀመሪያው እውነታ ምንም ለማመን ቢቸግረን ያለው “አዲስ” መንግሥት (በእርግጥ አዲስ አይደለም) የድሮ ያልነው መንግሥት አካል የነበሩ አባላት ተሐድሶ አድርገው የመጡበት ነው። ፓርቲው አሁንም ያው ፓርቲ ነው፤ መዋቅሩ ያው መዋቅር ነው፤ አሠራሩ ያው አሠራር ነው፤ ፓርላማው ያው ፓርላማ ነው። መነቃቃቱ ለየት ማለቱ እንዳለ ሲሆን በሥልጣን ላይ ያሉት መሪዎች ሳይቀሩ በአብዛኛው “በአዲስ መልክ ሥራ የጀመሩ” ናቸው።

በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ይህ ለውጥ ያመጣው መነቃቃትና ተስፋ መሟሸሽ፣ መተንፈስ ሲጀምር እያየን ነው። ይህ በይፋ ወጥቶ መናገር የጀመሩ ሲኖሩ ሌሎች አሁንም ከተስፋቸው ጋር ሆነን አሁንም የለውጡ መሐንዲሶች ካሏቸው ጎን እንደቆሙ እየተናገሩ ነው። ከመንግሥት በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኩል የሚሰጡ መረጃዎች (ቢያንስ ለማኅበረሰቡ አንገብጋቢ በሆኑ የሰዎች መፈናቀል፣ ቤት መፍረስ፣ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ውዝግብ ፣ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ጣጣ ወዘተ.) በተቀዛቀዙና ከሚጠበቀው ባነሱ (ለምሳሌ አልሰማሁም፣ አላወቅኩም) ቁጥር ቅሬታውም እየጨመረ የመጣ ይመስላል። የዛሬ ጽሑፌ ዓላማ ሙያዊ ትንተና ለማቅረብ አይደለም። ከንባቤ ካገኘኋቸው የፖለቲካ ርዕዮትና ትንተናዎች፣ ያለፍንበትን አሁንም ያለንበትን ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን ትርጉም ያስይዛሉ ያልኳቸውን ነጥቦች ከመዘርዘር እንጂ። ነጥቦቹ ወይም ምሳሌዎቹ ከአገራችን ሁኔታ የራቁ ቢመስሉ ብዙ አትገረሙ።

“የምሥራቁ ዓለም ትራምፕ”፣ “ዱተርቴ ፈጣኑ”፣ “ቅጣት አድራሹ” የፊሊፒኑ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱተርቴ ከተቸሯቸው ቅጽል ሥሞች መካከል ይጠቀሳሉ። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ባራክ ኦባማ “ደማቅ ቀለም ያለው ሰው” ተብለው ሲሞካሹ ሲጀምሩም ለየት ያለ የፖለቲካ ዘይቤ ይዘው በመምጣታቸው ነበር። ዘይቤው በኋላ “ ታላቁ የዓለም ዐቀፍ ሚዲያ ዲማጎግ” እስኪባሉ ያበቃቸው ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት እስከ ካቶሊኩ መሪ ፖፕ ፍራንሲስ በፀያፍ ቃላት በተመላው ንግግራቸው ነበር። በመንግሥት ላይ ትችት የሚያዘንቡ ተንኮለኛ ፖለቲከኛና የከተማ ከንቲባ ከመሆን ወደ ፕሬዚደንትነት ያደጉም ናቸው።

 

የሥጋትና የፍርሐት ፖለቲካ እንደ ዱተርቴ (ምናልባትም እንደ ትራምፕ) ዓይነቱ የለየለት አምባገነን ወደ የማይገባው ቦታ፣ ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል

 

የካናዳው ካንቤራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁር ኒኮል ኩራቶ (ዶ/ር) “የስጋት ፖለቲካ፣ ተስፋ የማድረግ ፖለቲካ፤ ጠንካራ ሕዝበኝነትና የዱተርቴ ወደ ሥልጣን መውጣት” በሚል ጆርናል ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ እንዳሉት የዱተርቴ ደጋፊዎች ራሳቸውን የቻሉ የሚገርሙ ዓይነት ሰዎች ናቸው። ሰውየው ኋላ ላይ መዘባረቁ ጨምሮ አምባገነንነቱን የሚያሳይ ተግባር ሲያመጣ ደጋፊዎቹ አልሸሹትም ነበር። ዘጠና በመቶው ደጋፊው እንዳለ ከነድጋፉ አጠገቡ ነበር። አብዛኛው ድጋፉ የመጣውም ቀድሞ በነበረው መንግሥት ለዓመታት ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ገሸሽ ተደርጎ የቆየውና ደስተኛ ካልነበረው ከመካከለኛ ደረጃ ነዋሪው ነበር። ዱተርቴ የዚህን ሕዝብ ቀልብ መግዛት የቻለው “እንዲህ አደርጋለሁ” በሚለው ዝርዝር ቃል ሲሆን፥ በአብዛኛው የመልካም አስተዳደርና የመንግሥት አገልግሎት ላይ የነበረውን ብልሹ አሠራር ከመጠገን ጋር የሚገናኝ ነበር።

በተለይ ዱተርቴ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት በዘመቻው ወቅት ሌሎች እሱን የማይደግፉ የአገሬው ሰዎችና ከውጪ ሆነው የሚያዩ ተመልካቾች ደጋፊዎቹን ሞራላዊ ሥነ ምግባር የሌላቸው፣ አክራሪና ደም የጠማቸው፣ በቀል የሚሹ አካላት አድርገው የመሳል አዝማሚያ ነበራቸው። ሰውየው የለየላቸው አምባገነን እንደሚሆኑ ምልክት ታይቶም መደገፋቸው ነው ለዚህ ውንጀላ የዳረጋቸው፣ የጠቀስኩት ጥናት አቅራቢ ግን ደጋፊዎቹን አረመኔዎች አድርጎ መሳሉ ረብ የለውም፥ ይልቁንም እነሱን ያፈራው ፖለቲካዊ አካሔድ ሊጤን ይገባል ባይ ናት። በጥናቱ ለማረጋገጥ የምትሞክረው መላ ምትም የሥጋትና የፍርሐት ፖለቲካ እንደ ዱተርቴ (ምናልባትም እንደ ትራምፕ) ዓይነቱ የለየለት አምባገነን ወደ የማይገባው ቦታ፣ ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል የሚል ነው።

እንደ ኒኮል ፍርሐትና ሥጋት ብቻውን ሳይሆን የማኅበራዊ ጥናት ባለሙያዎች ሥር የሰደደ ሕዝበኝነት ወይም ‘penal populism’ የሚሉት ክስተትም አለበት። ይኸውም ሥጋትና ፍርሐት ጋር አብሮ ዲሞክራሲ ሊሰፍን ይችላል፤ እንዲህ ዓይነቱ ከቀደመው ስርዓት ጋር ጠብ የነበረው ሰው ሲመጣ ስርዓቱ ተሻሽሎ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ሊተካ ይችላል የሚል “ተስፋ” የማግኘት ሁኔታ ነው። ይህ ክስተት “ሕዝበኝነት” የሚደግፉት ፖለቲከኛ ስህተት ሲፈፅም የማይባል፣ ከመሪ የማይጠበቅ፣ አንድን የማኅበረሰብ ክፍል ክብር የሚነካ፣ ቋንቋ ሲጠቀም (ትራምፕ በተደጋጋሚ ሴቶች ላይ ጥቃት ስለመፈፀምም ይሁን ፖለቲከኛ ሴቶችን ሐሳባቸውን መሞገት ትቶ አስቀያሚ ብሎ እስከመሳደብ ሲደርስ፣ ዱተርቴ በተቃዋሚ ጎራ ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለተገደለች ሴት ቀልድ ሲያወራ) ዝም ብሎ የማለፍ ጉልበት የሚሰጥ ነው። የሕዝበኝነት ምንጩ በአንድ ወገን ተግባር አለመደሰት ሲሆን፥ ዋነኛ መገለጫው በ“ሕዝብ” እና “ሌላኛው አደገኛ ቡድን” መካከል ተቃኖን መፍጠር ነው።

እንዲህ ዓይነቱ የሥጋት ፖለቲካ በአገራችንም ነበር። ኢሕአዴግ በአገራችን ታሪክ ወርቃማ በሚባለው የምርጫ 97 የፖለቲካ ክርክር ሒደት “እኔ ከሌለሁ እንደ ሩዋንዳ ልትሆኑ ነው” ብሎን ነበር። ብዙ ጊዜ በተለይ አሁን የሚታየው ውጤት እንደሚያሳየው በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦች ሌሎች ሕዝቦች እንዲህ አደረጓችሁ፣ ያደርጓችኋል በሚል በተዘራው ጥላቻ የሥጋትና የፍርሐት ፖለቲካ ገዥው ፓርቲ የሥልጣን ዕድሜውን ማራዘም ብቻ ሳይሆን፥ ግለሰቦች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው አገሪቱን የሚበዘብዙበት ዕድል ተመቻችቷል። በዘር የተከፋፈለ ፖለቲካ እና የፖለቲካዊ ተቋማት ደካማ መሆን ለዚህ አስተዋፅዖ ነበረው።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ምሁር ፓድሮ ሚጊኤል “በተከፋፈለ ሕዝብ የፖለቲከኞች የቁጥጥር ስልት፤ ሽብር የመንዛት ፖለቲካ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጣጥፍ እንደሚለው ጠንካራ የፖለቲካ ተቋማት መንግሥትና ፖለቲከኞች ባሕርይ ላይ ገደብ በማበጀት ስለ ሕዝባቸው እንዲያስቡና የሚያወጧቸውንም ፖሊሲዎች በዚያ እንዲቃኙ በማድረግ ወሳኝ ናቸው። በአንፃሩ የፖለቲካ ተቋማት ደካማ በሆኑበት ጊዜ ፖለቲከኞች ወይንም መሪዎች የሚገድባቸው አይኖርም፣ ከሥልጣንም ያልተገባ ኪራይ ይሰበስባሉ። እንደ ሚጊኤል ገለጻ እነኝሁ መሪዎች የሰበሰቡትን ኪራይ ማለትም ሀብት ባልተገባና ብቃት በሌለው መልኩ መልሶ በማከፋፈል ሥራም ተጠምደው ሊታዩ ይችላሉ። ይህ የብቃት ማነስ በሌላ ጎኑ ደግሞ ሥልጣናቸው ገደብ ያለበት መሆኑን አመላካች ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ከላይ የጥናቱ ርዕስ ጠቆም እንደሚያደርገው እንደኛዋ አገር በዘር የተከፋፈለ “divided society” ባለበት ነው። በዘር በተከፋፈለ ስርዓት ውስጥ ፖለቲከኛው የሚወስደው ከሁሉም ቢሆንም መልሶ የሚሰጠው የእኔ ለሚለው፣ በዚህም ምክንያት የተሻለ ለሚደግፈው ሕዝብ ሊሆን ይችላል።

ሟርት አድርጋችሁ ባትወስዱብኝ ይህ ገለጻ በኦሮሚያ ክልል እየሆነ ከመጣው ክስተት ጋር የሚመሳሰል ይመስለኛል። ሀብት እያሰባሰቡ ወደ ኦሮሚያ የመውሰድ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ተጠቃሚነት ወደ ከተማ አፍልሶ እስከማስፈር ድረስ በይፋ የሚደረግ በየንግግሩም የሚገለጥ ስለሆነም ይህን ማለቴ ድፍረት አይመስለኝም። ይልቁንም ጥያቄው ድሮ የነበረው “ያልተለወጠው” መንግሥት የሚታወቅበትን የኢኮኖሚ ጥቅምን ለአንድ ቡድን ብቻ መስጠት፥ ቡድኑን መለያ አስቀይሮ ለሌላው ማድረግ ምናልባት ሌላ ተቃውሞ፣ ሌላ ቀውስ ፈጥሮ አገርን ወደ ውድቀት እንዳይመራ ሊታሰብበት ይገባል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here