የሞጆ ደረቅ ወደብ በፈታሽ እጥረት ምክንያት ደንበኞቹ እየተጉላሉበት ነው

0
536

በሞጆ ወደቅ ወደብ የፈታሾች እጥረት የፈጠረው መጉላላት አስመጪዎችን እያማረረ ነው ሲሉ፣ የወደቡ ደንበኞች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰሙ።

ከዚህ ቀደም በደረቅ ወደቡ በቀን እስከ 200 ኮንቴነር ይፈተሽ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ቁጥሩ ከ300 እስከ 400 ኮንቴነር ከፍ ብሏል። ፍተሻ የሚደረግባቸው ኮንቴነሮች ቁጥር ይጨምር እንጂ፣ የእቃዎቹ ብዛት እና የሰው ኃይሉ አለመመጣጠን አስመጪዎችን እንዳስመረረ ነው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በቅሬታዎቹ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ የሰጡት የሞጆ ደረቅ ወደብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አየለ ወርቁ የፈታሽ ባለሙያ እጥረት ያጋጠመው የወደቡ ሥራ (‹‹ኦፕሬሽን››) ስለጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ ኮንቴነር ዕቃን ለመፈተሽ የሚወስደው ሰዓት ቢበዛ እስከ ኹለት ሰዓት ቢሆንም በወደቡ ካለው የሥራ እንቅስቃሴ አንፃር ደንበኞች ቀናትን መጠበቅ ግድ እንደሚሆንባቸውም ገልፀዋል።

አንድ ዕቃ ለፍተሻ 10 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን በአንድ ኮንቴነር 400 ዕቃ ቢጫን ለእያንዳንዱ ዕቃ አስር ደቂቃ በመስጠት ብዙ ሰዓቶች እንዲያልፉ ያደርጋል ያሉት ስራ አሥኪያጁ በደረቅ ወደቡ ያሉት ፈታሾች ቁጥር 80 መሆኑን አሳውቀዋል። 80ዎቹ ፈታሾች ሥራ ላይ ቢሆኑም መጨናነቁ አለመቀረፉን ያመለከቱት አየለ በሰው ሀብት አስተዳደር በኩል ተጨማሪ የሰው ኃይል ለመጨመር ተቋሙ በሒደት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

በደንበኞች በኩል ‹‹ለመጉላላታችን ሌላው ምክንያት ነው›› ሲሉ የሚነሱት የ‹‹ኔትዎርክ›› መቆራረጥን ሲሆን ይህም እልባት ሊያገኝና የተቀላጠፈ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ይጠይቃሉ። ሥራ አስኪያጁ አየለ እንደሚሉት ደግሞ በደረቅ ወደቡ አስተዳደር ከበይነ መረብ ትስስር መቆራረጥ ጋር ተያይዞ መላ እንዲሰጠው ለኢትዮ ቴሌኮም የጠየቀ ሲሆን፣ መፍትሔን እየጠበቀ ነው።

በጉምሩክ አሰራር ሦስት ዓይነት የአደጋ ስጋት አይነቶች አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ በሚል ይፈረጃሉ። አረንጓዴ የአደጋ ሥጋት ላይ የተቀመጡ አስመጪዎች ፍተሻ የማይደረግባቸው፣ በሥራ ሒደታቸው ባሳዩት ሕጋዊ እንቅስቃሴዎች ተዓማኒነትን ያተረፉ በዚህም የተለየና የሚያስጠረጥር መረጃ ሲገኝ ድንገተኛ ፍተሻ የሚካሔድባቸውን የሚይዝ ነው።

ቢጫ ደረጃ ላይ የሚቀመጡት አስመጪዎች ደግሞ አስፈላጊውን ሰነድ ማሟላታቸውን በማየት እንዲያልፉ የሚደረጉ ናቸው። በቀይ የአደጋ ስጋት ውስጥ የሚፈረጁት ደግሞ አስፈላጊ ሰነድን ከማሟላት ባሻገር በእንዳንዱ ዕቃ ላይ ጥብቅ ፍተሻ የሚደረግባቸውን የሚይዝ ነው።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራራያ በሞጆ ደረቅ ወደብ አሁን ላይ የተፈጠረው መጨናነቅ ቀይ የአደጋ ስጋት ላይ የተቀመጡት አስመጪዎች በመብዛታቸው እያንዳንዱን ዕቃ ላይ ፍተሻ ማካሄድ በማስፈለጉ ነው። ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መዘግየት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል። ይህንን ጭንቅንቅ ለማስቀረትም ከሰው ኃይል ማሟላት እንቅስቃሴ ባሻገር በሞጆ የወደብ ማስፋፊያ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here