ስለአገራችን ዝም አንበል!

0
598

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ኹለት ወንድሞቿ ተጣልተዋል፤ ልታስታርቅ ሞክራ አታውቅም። ያንንም ይሄንንም ለየብቻቸው ስታገኝ ታማክራቸዋለች። በሐሳብ አሳምናቸው ግን አታውቅም። በልጅነታቸውም በትንሽ በትልቁ ይጣሉ ስለነበር ጥላቸው ወደመጠላላት ያድጋል ብላ አላሰበችም።

በየጊዜው የሚሆነውን ጓደኛዋ ለሆነችው ለእናቴ ታጫውታታለች። እናቴም ̋አይዞሽ ፈጣሪ ያውቃል። አንቺ አትጨነቂ ̋ ትላታለች። እንዲህ እያለ ጊዜ አለፈ፤ አንዱ ወንድሟ ቤቷ ሲገኝ ሌላኛው ወንድሙን ላለማየት ብሎ ሲቀር፤ ደግሞ ሲቀያየር ፀባቸው ተለመደ። ከጊዜያት በኋላ የቤተሰባቸውን ንብረት ሸጠን ካልተካፈልን አሉ።

ይሔኔ ጉድ ፈላ፤ እርሷ ቤተሰቧን ይዛ ትኖርበት የነበረው ቤት ሊሸጥ ሆነ። ወንድሞቿ ከእርቅ ርቀዋል፤ ማንንም ከማይሰሙበት ደረጃ ደርሰዋል። እናም ̋ቤቱ ይሸጣልና ከቤቱ ውጪ፤ አንቺም የድርሻሽን ታገኛለሽ ̋ ተባለች። ቆጫት! … ̋ያኔ ጠርቼ በአንድ ላይ ባነጋገርኳቸው ኖሮ…ጫን ብዬ በተቆጣሁ ኖሮ ̋ አለች፤ ከረፈደ።
ኹለቱም ወንድሞቿ እየቀረቡ ̋…ከእርሱ ጋር የምጋራው ነገር እንዲኖር ስለማልፈል እንጂ አንቺን እህቴን ለመጉዳት አይደለም ̋ አሏት። ግን አልቀረላትም…ከኹለቱ ፀበኞች ወንድሞቿ በላይ እርሷና ልጆቿ ተጎዱ። የእናት የአባቷን ቤት ወንድሞቿ ሸጠው ቅንጣት ፍራንክ ወረወሩላት፤ ለእርሷ ካላቸው ፍቅር ይልቅ ፀባቸው በርትቷልና። አሁን ላይ ልጆችዋን ይዛ በቤት ኪራይ ትንገላታለች።

እናቴ ሰሞኑን ደጋግማ ስታስታውሳት፤ እኔም ነገሩ ከሰሞኑን የኢትዮጵያችንን ነገር ተመሳሰለብኝና አሰላሰልኩት። የእኛዋን አገር ብቻ አይደለም የዓለማችንን የጦርነትና የፀብ ወሬዎች ስመለከት ይህች በወንድሞቿ ፀብ ቤቷን ያጣች ሴት ታወሰችኝ፤ የእናቴ ጓደኛ።

̋እናት አባት ቢሞት… እህት ወንድም ቢሞት… በአገር ይቀሳል
አገር የሞተ እንደው ወዴት ይደረሳል … ̋ እንዲሉ፤ መብትን ለመጠየቅና አሳትፉኝ ለማለትም አገር ያስፈልጋል። አሁን ላይ አገራቸው ፈራርሳ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ከንፈሩን እየተመጠጠላቸው ያሉ ሕዝቦች፤ አገራቸው ዳግም ብትሠራና ለምነው ቢበሉ እንደማይጠሉ መገመት አይከብድም። ሁሉም የሚሆነው አገር ሲኖር ነዋ|
ሴቶች! በኢትዮጵያችን በየዕለት የምንሰማው መፈናቀልና ግጭት፤ ንትርክና ጭቅጭቅ ይመለከተናል፤ እንመለከተዋለን። መፈታቱ አይቀርም ብለን ችላ ያልነው ጉዳይ በኋላ በየደጃፋችን ሲደርስ መመልከታችን አይቀርም። በየትኛውም በኩል አቋም ሊኖረን ይችላል፤ ግን ወደ ሰላም የሚያቀናውን መንገድ እንደምንመርጥ አልጠራጠርም። ተው ማለት ካልጀመርን ግን በኋላ ውጤቱን የምንሸከመው እኛ ነን፤ ልጆቻችን ናቸው።

በፖለቲካ መድረክ ሙግት፣ በውይይትና በምክክሩ ወንዶች ብቻ ይታያሉ። እኛስ የት ነን? ተው ሳንል ቀርተን፣ ሐሳብ ሳናካፍል ስለኢትዮጵያችን ዝም ብለን፣ ተናጋሪዎቹን በመታዘብ ብቻ ቆይተን፤ በኋላ መከራውን የምንሸከመው እኛው ነን። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወደ ሴት ልጆቿ የምትመለከት ይመስለኛል። ብንችል ብንችል … የላክነው ሞት እንደማይፈራ ሁሉ ለሰላም ሊተጋ ይችላልና፤ ይመለከተናል ብለን ሐሳባችንን እናሰማ። ስለአገራችን ዝም አንበል!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here