በቅርቡ የንግድ ሒደቱን ለማሳለጥ በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የሆነውን መርሀ ግብር ታሳቢ በማድረግ የጉምሩክ አዋጁን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን አስታቀ።
በኢትዮጵያ ያለውን የወጪ እና ገቢ ንግድ ከማሳለጥ ባለፈ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የጉሙሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 መሻሻል አይነተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመታመኑ አዋጁ ሊሻሻል መሆኑን አዲስ ማለዳ ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የጉምሩክ አዋጁ ማሻሻያ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበሩትን አካሔዶች በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንደሚቀይር ተጠብቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎችና ከአገር በሚወጡ ምርቶች ላይ ይጠየቅ የነበረውን የሰነዶች ብዛት በ40 በመቶ እንደሚቀንስ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ አስመጪዎች የሚያስገቧቸውን ምርቶች አገር ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድመው የጉምሩክ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ዕቃዎች በገቡ ሰዓት ወዲያው ለገበያ የሚበቁበትን ሒደት እንደሚያፋጥን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስመጪዎች ከባንክ ጋር ስምምነት በማድረግ ኮንቴነሮቻቸውን አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅመው ማውጣት የሚችሉበት አግባብ በአዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ተካቷል። ይህ ደግሞ አስመጪዎች በሚያጋጥማቸው የገንዘብ እጥረት የተነሳ በደረቅ ወደቦች ላይ የሚከሰተውን የኮንቴነር ክምችት ከመቀነሱም በላይ በአገር ውስጥ የሚያጋጥመውን የዕቃ መጥፋት ችግር እና የዋጋ ንረት በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
የፍተሻ ጣቢያዎችን ቁጥር በመቀነስ ለወጪ እና ገቢ ንግዱ መሳለጥ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ አዋጅ፣ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው ብዙ ጊዜ የሚፈጀው የፍተሻ ዓይነት በ25 በመቶ የሚቀንስ ነው። በሰው ኃይል ይተገበር የነበረው የፍተሻ ስርዓትንም በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ያደርጋል ተብሏል። ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ጭነቶች እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የደረቅ ወደብ አገልግሎት በሚሰጠው ሞጆ ደረቅ ወደቦችም ይሁን በሌሎች ሥፍራዎች ፍተሻ የሚከወነው በሰው ኃይል በመሆኑ ረጅም ጊዜን እየፈጀ ነው። አዲሱ አዋጅ ይህን መሰሉን አሰራር በመጠኑም ቢሆን የሚያስቀር በመሆኑ በዕቃዎች ላይ የሚደርሰውን የመሰበርና የመበላሸት ችግር ይቀርፋል ተብሏል። ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ ደግሞ የፍተሻ ጣቢያዎች ቁጥር መቀነስ ምርቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለዓለም ዐቀፍ ገበያ የሚቀርቡበትን እድል ይፈጠራል።
አዲሱ አዋጅ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ደረቅ ወደቦች የአሰራር ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በዚህም መሰረት በመደበኛ የሥራ ሰዓት ብቻ ተገድቦ የነበረው የደረቅ ወደቦች የአገልግሎት መስጫ ጊዜን ሳምንቱን ሙሉና በየቀኑ 24 ሰዓት እንደሚያደርግ ታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011