አርበኞች ግንቦት ሰባት በኮንሶ ባደረገው ስብሰባ ተሳታፊዎቹ ሲዋከቡበት ነበር ተባለ

0
506

• ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉም ሐሳብ ገበያ ላይ ቀርቦ አሸናፊው ሊወሰድ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል

አርበኞች ግንቦት ሰባት ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመሆን በኮንሶ ከሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አባላቱ ጋር ያደረገው ውይይት በተሳታፊዎች ላይ ማዋከብ ተከስቶበት እንደነበር ታወቀ።

እሁድ መጋቢት 1/2011 በተካሔደው ውይይት ለመሳተፍ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ሲመጡ የነበሩ ተሳታፊዎች ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ የአካባቢው ወጣቶች ጫና ሲፈጥሩና ሲያዋክቧቸው እንደነበር አዲስ ማለዳ ከአካባቢው የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ‹‹በአካባቢው ስብሰባ እንዳይካሔድ የፈለጉትን አካላት እናውቃቸዋለን፣ በዚያው በኮንሶ ዞን አብረን የኖርን ነን፤ እነዚህ ሰዎች ስለፖለቲካ ያላቸው እውቀት ዝቅተኛ ነው፤ ይህንን ነገር ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያትም የለም፤ ምናልባት ይህንን እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው የወረዳ ወይም የዞን አመራር ሊኖር ይችላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አርበኞች ግንቦት ሰባትና ሰማያዊን ጨምሮ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመዋኃድ አዲስ ፓርቲ ሊመሰርቱ መሆኑ ይታወቃል። በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸውና በዕለቱ በስፍራው የነበሩት ፖለቲከኛው የሸዋስ አሰፋ፣ ‹‹እዚያ ያለው አመራር ነገሮችን በሰፊው የሚያይ፣ ምኅዳሩን የሚያሰፋ አይደለም። በኮንሶ አምስትና ስድስት መግቢያዎች ይገቡ የነበሩ ደጋፊዎቻችን እንዳይገቡ የተደረገበት ሁኔታ ነበር፤ ይሁን እንጂ ማስቀረት አልቻሉም፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን ችግሩን በመቅረፍ ስብሰባውን አድርገናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በአካባቢው ብዙ መታየትና መታረም ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን አመላካች ስለመሆኑም አክለዋል።

መዋቅሮችን ስለመፍተራቸውና ቢሮዎችንም በመከፈት ላይ እንዳሉ የገለጹት የሸዋስ፣ በኮንሶ ሽማግሌዎች ፕሮግራሙ መጀመሩን ተናግረው ‹‹ሕዝቡ የዜግነት ፖለቲካን እንደሚደግፉ ነግረውናል፤ እኛም ፓርቲው በትክከል የዜግነት ፖለቲካን የሚራምድ መሆኑን ነግረናቸዋል›› ሲሉ ስለነበረው የውይይት ድባብ ተናግረዋል። በነበረው የጥያቄና መልስ መርሀ ግብር የአስተዳደር በደሎች መኖራቸውን ነዋሪዎቹ የገለጹ ሲሆን በፌደራል መንግሥቱ ያለው የለውጥ መንፈስ እነሱ ጋር አለመድረሱን በማንሳት አማረዋልም ተብሏል።

በእለቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች ንግግር ያደረጉት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ‹‹በውስጣችን ያሉ ልዩነቶችን አቻችለን፤ በተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶችና የመንግሥት አይነቶች ውስጥ አልፈን፤ በቅርብ ታሪካችን የፖለቲካ ህይወታችንንና ማህበራዊ ኑሮአችንን ለመቀየር ታግለናል፤ ወድቀናል ተነስተናል፤ ይህን ሥርዓት ለመፍጠር ጀማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ይህን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት በጥሩ መደላድል ላይ ለማስቀመጥ በጣም ብዙ ተግዳሮቶች ይገጥሙናል›› ሲሉ ተደምጠዋል።
ብርሃኑ የፖለቲካ ኃይሎች ዋነኛ ዓላማ የሕዝብን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚሞክር የፖለቲካ ሥርዓት መመስረት መሆኑን በማስታወስ ሥርዓቱን ከሁሉም ፍላጎት ጋር የሚስማማ አድርጎ የመቅረጹን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በተያያዘ ዜና ሐሙስ መጋቢት 5 በሂልተን ሆቴል በተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ፊርማ ስነ ስርዓት ላይ 107 የፖለቲካ ማኅበራት በሰላማዊና በትብብር መንፈስ ለመስራት ቃል በመግባት ፊርማቸውን አኑረዋል። በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባርን (ኢሕአዴግ) በመወከል ፊርማቸውን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚንስትርና የግንባሩ ሊቀመንበር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ሁሉም ሀሳብ ገበያ ላይ በነጻነት ቀርቦና ተሞግቶ አሸናፊው የበላይ እንዲሆን መሥራትን በተለይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ማመን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በተለይም በክልሎችና የተወሰኑ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ተወስነው የሚመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ‹‹ወደ እኛ አትምጡብን›› ከሚል ኋላ ቀር አተያይ መውጣት እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ ሕዝብን ስለርዕዮቱና ፕሮግራሙ ማስረዳት እንዲችል የጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀሳቦች በነጻነት ገበያ ላይ ቀርበው ብዙው ሰው የተስማማባቸው በምርጫ ገዥ እንዲሆኑና የብዙሃኑን ሀሳብም ማክበር እንዲለመድ ተማጽነዋል። ለዚህም የፖለቲካ ማኅራቱ ለፈረሙት ባለ 20 አንቀጽ የቃል ኪዳን ሰነድ በተግባር ተገዥ መሆን እንዳለባቸው ተሰምሮበታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘውም በተለይም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አውታሮች ለሁሉም ሀሳብና የፖለቲካ ድርጅቶች ሀሳብ እኩል ቦታ እንዲሰጡና ከአግላይነት አካሔድ ራሳቸውን እንዲቆጥቡ አሳስበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here