ዕጣ የወጣባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች የጋዜጣ ሕትመት ተቋረጠ

0
1052

ባለፈው ረቡዕ የካቲት 27/2011 እጣ የወጣባቸው ከ52 ሺሕ የሚጠጉ የ20/80 እና 40/60 መኖሪያ ቤቶች ዝርዝር በጋዜጣ እንዳይታተም ታገደ።

ለወትሮው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሲተላለፉ የእድለኞችን ዝርዝር ይዞ የሚጣውና በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ስር የሚታተመው አዲሰ ልሳን ጋዜጣ እንደሆነ ይታወቃል። ጋዜጣው የባለፈውን ሳምንት የኮንዶሚኒየም እጣ እድለኞች ዝርዝርም በማግሥቱ ሐሙስ የካቲት 28 አትሞ እንዲያወጣ ረቡዕ አመሻሽ የዕድለኞቹ ዝርዝር ደርሶት ነበር። በከተማው ቤቶችና አስተዳደር በኩል በተገባ የሕትመት ጥያቄ ውል መሰረት ጋዜጣው ተዘጋጅቶ ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ቢቀርብም ሕትመቱ እንደተጀመረ እንዲቋረጥ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

ከ32 ሺሕ በላይ የ20/80 የቤት ዕድለኞችን ዝርዝር ይዞ በ12 ሺሕ የጋዜጣ ቅጅ ሊወጣ መታተም ጀምሮ የነበረው አዲስ ልሳን በማን ትዕዛዝ እንዲቋረጥ እንደተላላፈ ባይታወቅም እንዲቆም መደረጉን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከ18 ሺሕ በላይ የ40/60 ዕድለኞችን ዝርዝር በማዘጋጀት ከስድስት ሺሕ በላይ ቅጅ እንዲታተም ታቅዶ የነበረው የጋዜጣው ተጨማሪ ቅፅም እንዳይታተም ሆኗል። በዚህም ጋዜጣው የሐሙስ እትሙን በተለመደው መደበኛ እትሙ እንደገና አዘጋጅቶ ለመውጣት መገደዱ ታውቋል።

ቤቶች ዕጣ ከወጣባቸው በኋላ ዝርዝራቸውን በጋዜጣ አሳትሞ ከዕድለኞች ጋር የመዋዋሉና ቤቶቹን በዘላቂነት የማስተዳደሩ ኃላፊነት ያለበት የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ሕትመቱ የተቋረጠበትንና የዕድለኞቹን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠን ተደጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ሊፈቅድ አልቻለም። ወደ ኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ተረፈ የእጅ ሥልክ ለሦስት ቀናት ተደጋጋሚ ጥሪንና የመልዕክት ጥያቄን ብንልክም ሊመልሱልን አልፈቀዱም። ኤጀንሲውን ከሚቆጣጠረው የከተማዋ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች መካከል አዲሰ ማለዳ ስለጉዳዩ ብትጠይቅም የሚመለከተው ኤጀንሲውን እንደሆነ ገልፀዋል።

ስለ ጉዳዩ ከአዲስ አበባ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊ የተገኘው መረጃ ግን የጋዜጣው ሕትመት እንዲቋረጥ የተደረገው እጣ በወጣባቸው ቤቶች ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተቃውሞ በማሰማቱ እንደሆነ አመልክቷል። በመሆኑም በጉዳዩ የኦሮሚና የአዲስ አበባ ባለሥልጣናት እስኪደራደሩና ስምምነት ላይ እስኪደርሱ በሚል ዝርዝሩ በጋዜጣ እንዳይወጣ መታገዱን ነው ኃላፊዎች የነገሩን። ስምምነት ላይ ሳይደረስ ጋዜጣው ቢታተምም ትርጉም የለውም በሚል የሕትመቱ ትዕዛዝ መሰረዙን ሰምተናል።

አሁን ላይ አስተዳደሩ እያደረገ ስላለው ነገር የጠየቅናቸው የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር አለመግባባቱ በተነሳባቸው ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ጥረት እያደረገ እንደሆነ ነግረውናል። አለመግባባቱን በሥምምነት ይፈቱታል ብለው ተስፋ የሰነቁት ኃላፊዎቹ ጠቅላይ ሚኒንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የኹለቱን ወገኖች ውይይት በቅርበት እንደሚከታተሉትም አክለዋል። ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን ወሰን ጉዳይ በጥናት እልባት ለመስጠት ይሰራሉ የተባለ ኮሚቴ ከፌደራል፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት በጠቅላይ ሚንስትሩ አማካኝነት መዋቀሩ ይታወሳል። ሆኖም የኮሚቴው አባላት ስብጥር ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

አዲስ አበባ ለዓመታት ከአፋቸው ከፍለው እየቆጠቡ ቤታቸውን ሲያስገነቡ ከነበሩት ከ900 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች መካከል 52 ሺሕ ለሚጠጉ ነዋሪዎቿ ቤት ለማስተላለፍ እጣ ማውጣቷን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሔድ መሰንበቱ ይታወሳል። ተቃውሞው በዋናነትም እጣ ከወጣባቸው ቤቶች መካከል በኦሮሚያ ክልል ይዞታ ውስጥ ገብተው የተገነቡ ቤቶች በመኖራቸው ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች አይገቡም የሚል ነው። ለቀናት በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በክልሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች ሳይቀሩ የተሳተፉ ሲሆን በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቤቶቹ ላይ ዕጣ መውጣቱን በይፋ ተቃውሟል። በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ዕጣ ማውጣት ተገቢ አይደለም ሲልም አቋሙን ገልጿል። ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ቤቶቹ ሲሰሩ ከእርሻ ማሳቸው ተፈናቅለው ለምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግር ተዳርገዋል ላሏቸው ቤተሰቦች ያለ እጣ የኮንዶሚኒየም ቤት እንዲሰጥ መደረጉን ቢያበስሩም ተቃውሞው አልቀረም። የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባነት እያስተዳደሩ ያሉት ታከለ የኦዴፓ ከፍተኛ ባለሥልጣን መሆን ደግሞ በኹለቱ መካከል የተነሳውን ውዝግበ አነጋጋሪ አድርጎታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here