መንግሥትና ሕዝብ መካከል ዳግም መተማመን እየጠፋ ነውና ይታሰብበት!

0
350

ለአገር ሰላም፣ ለዜጎች ደኅንነት እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የተመቻቸ ሁኔታ ይኖር ዘንድ በመንግሥት እና ዜጎች መካከል መተማመን መኖር አለበት። ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲመሩ የነበሩት የፖለቲካ ልኂቃን ከፍተኛ ተቀባይነት የማጣት ተግዳሮት የገጠማቸው የሕዝብን እምነት በማጉደላቸው ነበር። በበርካታ የፖለቲካ ውሳኔዎቻቸው ጥፋቶችን ያጠፉ ቢሆንም እንኳን ከዚያ በኋላ “የመታረም ፍላጎት አለን” በማለት በተደጋጋሚ በአደባባይ እየማሉ ቢገዘቱም፥ ሕዝባዊ አመኔታን ማግኘት ባለመቻላቸው አገር በሰላም ማስተዳደር የማይችሉበት ሁኔታ ተከስቶ ቦታውን ለተተኪዎች ለመልቀቅ መገደዳቸው ይታወሳል።

አዲሱ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር፥ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በመጀመሪያ ለማግኘት የሞከረው የዜጎችን እምነት ነበር። ይህንን ለማግኘት የዜጎችን መበደል እና የፖለቲካ ልዩነቶችን ባለመታገስ መንግሥት ጭቆናን የመግዢያ መሣሪያ ማድረጉን በአደባባይ ማመናቸው አዳዲሶቹን አመራሮች የዜጎችን እምነት እንዲያገኙ ካስቻላቸው ምክንያቶች አንዱ ነው። ይሁንና አዲሱ አመራር ሙሉ ሥልጣን ከተቆጣጠረ አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ከፍተኛ የእምነት ማጣት ፈተና እየተገዳደረው እንደሆነ ለመመስከር ትንሽ ዘወርወር ብሎ ተራ ዜጎችን ማነጋገር ብቻ ይበቃል።

የኻያኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ፍልስፍና ልኂቃን (ቶማስ ሆብስ፣ ጆን ሎክ እና ሩሶ) “ማኅበራዊ ውል” ሲሉ የጠሩት እና መንግሥት እና ሕዝቦችን ያስተሳስራል በሚል ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ሥምምነት ያልተጻፈ የሚመሥለው ነገር ግን በሁሉም አዕምሮ ውስጥ ተቀባይነት ያለው አስተሳሰብ ነው። ያለ መተማመን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ሊኖር አይችልም። ‘ማኅበራዊ ውል’ ዜጎች ከመብቶቻቸው እና ነጻነታቸው እንዲሁም ሠርተው ካፈሩት ሀብትና ንብረት (በቀረጥ መልክ) ቆንጥረው ለመንግሥት በመስጠት፣ በምላሹ ደግሞ የመንግሥትን ጥበቃ ለደኅንነታቸው እና ጠቅላላውን ስርዓት (‘order’) ለማስከበር ዋስትና እንዲሰጣቸው የሚጠብቁበት የመተማመኛ ውል ነው።

‘ማኅበራዊ ውል’ ልክ በተራ ግብይት ወቅት ለከፈልነው ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት ወይም ምርት እንደምንጠብቀው ሁሉ፥ ከመንግሥት የደኅንነት ማረጋገጫ፣ የሕግ የበላይነትን ማስረገጫ እና ትክክለኛ መመሪያ እና መልካም አስተዳደር ማስፈንን ዜጎች እንዲጠብቁ ያደርጋል። መንግሥት ይህንን ማድረግ ባልቻለ ጊዜ ልክ ገበያተኞች ሌላ አማራጭ እንደሚፈልጉት ሁሉ ዜጎችም አንድም ወደ ስርዓተ አልበኝነት እና ሁከት ሊያመሩ ይችላሉ፤ አልያም መንግሥትን ስለሚጠራጠሩት ለፖሊሲዎቹ እና ዕቅዶቹ አፈፃፀም ተባባሪ በመሆን ፈንታ እንቅፋት ይሆኑበታል። በአዲስ ማለዳ እምነት አሁን ኢትዮጵያውያን ያሉበት ሁኔታ አለመተማመኑ እየጨመረ በመሆኑ በዚህ አፋፍ ላይ ነው።

ባለፉት ዐሥራ አንድ የአዲሱ አመራር የሥራ ጊዜያት፦
የደቦ ፍርዶች እዚህም እዚያም ተፈፅመዋል፤ ሆኖም መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋጥ የወሰደው እርምጃ ስለመኖሩ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

ማንነት ተኮር ግጭቶች ተቀስቅሰው ዜጎች ከቀያቸው በገፍ ተፈናቅለዋል፤ በዚህ ሳቢያም ለረሀብ የተዳረጉም አሉ። ይሁንና መንግሥት ነገሩን ከማድበስበስ እና የእሳት ማጥፋት እርምጃ ከመውሰድ በቀር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያደረገው ግልጽ ሙከራ የለም። የግጭት ቀስቃሾችም ላይ የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ የለም።

የፖለቲካ ሹም ሽረቶች በብዛት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ናቸው እንጂ ብቃት ላይ ያልተመሠረቱ ናቸው በሚል ብዙ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው፤ ይሁንና ለዚህም መንግሥት ግልጽ መልስ የለውም።
በክልል መንግሥታት መካከል ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ውጥረቶች ተከስተዋል። ይሁን እንጂ የክልል መንግሥቱ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ የፌዴራል መንግሥቱ በቃችሁ አላላቸውም፤ ለማለት ፍላጎት ያለውም አይመስልም።

የዜጎችን ነጻ እንቅስቃሴ እና የንግድ ስርዓቱን የሚያናጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እዚህም እዚያም ይከሰታሉ፤ ነገር ግን መንግሥት እና የፀጥታ ኃይሎቹ አይተው እንዳላዩ እየሆኑ ነው።

እነዚህ እና ሌሎችም እየተከሰቱ ቢሆንም ቅሉ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያልቻለ እና የአመፃ የበላይነቱን (monopoly of violence) ያጣ መሥሏል። ከዚህም በላይ የሚያሳስበው ግን የዜጎችን ድምፅ እና አቤቱታ ለማስከበር ያለውን ቀና መግፍኤ (honest motive) ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚነሱትን ውዝግቦች እንደ አንድ ማሣያ መቁጠር ይቻላል። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መኖሪያ እና ቤት መሆኗ ቢታወቅም ነዋሪዎቿን እንደባይተዋር እና መጤ የሚቆጥሩ የፖለቲካ ቡድኖች ያላቸውን ተፅዕኖ በመፍጠር ሲያስፈራሩ እና ግጭት እና ደም መፋሰስ ሊያስከትል በሚችል ደረጃ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መንግሥት በቸልታ በማለፍ ነዋሪዎቹ መንግሥት ለደኅንነት ጥበቃ እንዳማያደርግላቸው እንዲሰማቸው አድርጓል። ይልቁንም መንግሥት የተለየ አጀንዳ ላላቸው የፖለቲካ ቡድኖች የተደረበ እስከሚመስላቸው ድረስ ጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል። ይህ ያለመተማመን እና የጥርጣሬ መንፈስ በዋና ከተማዋ እና በፖለቲካ እምብርቷ አዲስ አበባ ውስጥ ከተንሰራፋ ወደ ሌሎች ክልሎችም መዳረሱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ስለሆነም መንግሥት ቃል ኪዳኑን ማደስ እና በተግባር እርምጃዎች የመተማመን መንፈሱን እንዲያጠናክር አዲስ ማለዳ መልዕከቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here