ለምን የደካማ ውይይት ባሕል ባለቤቶች ሆንን?

0
539

በአገራችን በአሁኑ ወቅት በግልጽ የሚታየው ደካማ የፖለቲካ ተዋስኦ አንደኛው አጠቀቃላይ የውይይትና የመደማመጥ ባሕላችን ደካማነት ማሳያ መሆኑን የሚገልጹት መላኩ አዳል፥ መሰረታዊ መንስዔዎች ናቸውን ያሏቸውን በማስቀደም እንደመፍትሔ ሊወሰዱ የሚችሉትንም ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

 

 

የውይይትና የመደማመጥ ባሕላችን እንደ አገርና ሕዝብ በጣም ደካማ እንደሆነ ለሁላችንም ግልፅ ነው። በፖለቲከኞቻችን መካከልም የምናየው ተመሳሳይ ነው። ይህም ላለንበት የፖለቲካ ምስቅልቅል፣ ለአገራችን ኅልውናና አንድነት ተግዳሮት ፈጥሮአል። እናም፣ ለዚህ ደካማ የውይይት ባሕላችን መንሳዔዎች ምንድን ናቸው ብሎ መጠየቅና ለመፍትሔው መሥራትን ይጠይቃል። እንደኔ የደካማው የውይይት ባሕላችን መንስዔዎች ብዙና እርስ በርሳቸው የተገናኙ ናቸው ብዬ አምናለሁ። እስኪ ጎላ ብሎው የሚታዩትን አንድ በአንድ እያነሳን እንያቸው።

አንዱና ዋናው የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፤ የተፈጥሮ ሀብት ውስን መሆን። ይህም ውስንነት ሰውን ከʻጀነቲክʼ ራስ ወዳድነቱ በተጨማሪ፣ የበለጠ ራስ ወዳድና ተወዳዳሪ አድረጎታል። ይህም ደካማው እንዳይጎዳ የሚያደርግ በጣም ተወዳዳሪዎችንና ኀይለኞችን ከማኅበረሰቡ የሚያጠፋ የዝግመተ ለውጥ (ʻኢቮሊሽንʼ) ሒደት እንድንከተል አድርጎናል።

በተጨማሪም ሕግና ደንብ ተበጅቶለት፣ ከሕዝብ ውል ወስዶ፣ ደኅንነቱን የሚጠብቅለት፣ የሀብት ክፍፍልን ተመጣጣኝነት የሚጠብቅለት መንግሥት የሚባል ተቋም በማቋቋም ደካሞች በጠንካሮች እንዳይበሉ ጥበቃ ለማድለግ ጥሯል። ይህም በጊዜ ሒደት በብዙ አገሮች የወል ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችል ሁኔታን ፈጠሯል፣ ለአገሮች እድገትም የራሱን ተፅዕኖ አበርክቷል። እና ለሌሎች የውይይት መድረክ ከፈጠረና ከሠራ ለምን ለእኛ አይሠራም?

ለአንድ ኅብረተሰብ ሥልጣኔ ኋላቀርነትና ተወያይቶ ችግሩን አለመፍታት ዋናው ምክንያት የእውቀት ማነስ ነው፣ ድንቁርና። የሥልጡን ማኅበረሰብ አንዱ መገለጫው፣ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብና መደማመጥ ብሎም የተሻለውን መምረጥ መቻሉ ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ ዋናው ተግዳሮት ደግሞ እኛ ዜጎችዋ ይህን ማድረግ አለመቻላችን ነው። አማራጮቻችን በደንብ አጢነን ጥሩውን ከመውሰድ ይልቅ በኹለት ተቃራኒ ፅንፎች መቆምንና ከመካከል ባሉት ላይ ከሁለቱም ጎን የጥፋት ፍላፃ መወርወር እንመርጣለን። ለዚህም በኦርቶዶክስና እስልምና፣ በኦርቶዶክስና ካቶሊክ ዕምነት ተከታዮች፤ የአፄ ዮሃንስና አፄ ቴዎድሮስ ሞት፤ እንዲሁም በ1960ዎቹና 1970ዎቹ ወጣቶች መካከል በፖለቲካ ርዕዮት ልዩነት የተደረጉት የእርስ በርስ መጠፋፋቶች ቋሚ ማስረጃዎች ናቸው። የአሁኑም ፖለቲካችን አንዱ ማሳያ ነው።

ከመንግሥት እንደ ተቋም ልንጠቀም ያልቻልነው ለውይይትና መግባባት የሚያስችል እውቀት ስለሚያንሰንና የባሕል መደላድልም ስለሌለን ነው። እስኪ የእያንዳዳችን አስተዳደግ በሕሊናችን እንፈትሽ። ምን ያህሎቻችን ነን ከወላጅና ከቤተሰቦቻችን ጋር በግልጽ ተወያይተን ያደግነው? ምን ያህሎቻችንስ ነን ከልጆች ጋር በግልጽ የምንወያየው? ምን ያክሎቻችንስ የሰው ሥነ ልቦና ምን እንደሚመስል እናውቃለን? ኅብረተሰባችን አባታዊ (patriarchal society) አወቃቀር ነው ያለው። የተገነባው በተዋረድ ሙሉ በሙሉ (vertical) በሆነ ግንኙነት ነው፤ አግድም ትይዩም (horizontal) ግንኙነት መጨመር ሲገባው። በአጠቃላይ የአዛዥ እና ታዛዥ ሥልጣን ነው ያላቸው። ማንኛውም ሰው ከሌላው ጋር በመከባበር መወያየት የሚችለው ‘እኩል ነኝ’ ብሎ ሲያስብ ብቻ ነው። እናም ያለ ልምድና ተሞክሮ የውይይት አቅም ከየት ይመጣል?

ሌላው ምክንያት ጥሩ የሆነ የትምህርት ስርዓት አለመኖር ለእውቀት ማነስ ምክንያት መሆኑ ነው። የመጀመሪያ የሆኑት የአብነት ትምህርት ቤቶቻችንና መድረሳዎቻችን በአመክንዮ የማያምን፣ የሥነ ሰብ ትምህርቶችን ያላካተተ፣ ዓለምንና አካባቢውን የማያነብና የማይተነትን፤ አሳቢና አሰላሳይ ትውልድ መፍጠር አለመቻላቸው አንዱ ችግር ነው። እንዲያውም ይህ የሃይማኖት ትምህርት ለራሳችን እራሳችን ኃላፊነት እንዳንወስድ፣ ወደ ሰማዩ ጌታ ብቻ እንድናንጋጥጥ አድርጎናል። የቴዎድሮስ የባሕልና የኢንዲስትራላይዜሽን እንቅስቃሴ በሕዝብና በቤተ ክርስቲያኗ የስህተት አቋም ምክንያት አልተሳካም።

 

ችግሩ ሕዝብ እንዴት መንግሥትን መቅረፅና መግራት እንዳለበት አለማሰቡና አለማወቁ ነው

 

በአፄ ኃይለ ሥላሴ የተደረገው የዘመናዊ ትምህርት ለውጥም፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አገራዊ እውቀትን ባላገናዘበ ሁኔታ በመቀረጹና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ከማነብነብ ውጭ አሳቢና አሰላሳይ ዜጋ መፍጠር አልተቻለም። እንዲያውም ጠያቂነትንና ውይይትን የማያበረታታ፣ ባሕሉንና ምንነቱን የረሳ፣ እውቀት ማለት እንግሊዝኛ ቋንቋ መቻል የሚመስለው፣ ከሌላው ባሕል ምን መውሰድና መተው እንዳለበት መለየት የማይችል፣ ያላነበበና ያልመረመረ፣ ቢያነብም ያነበበውንና ያወቀውን ማንበርና መተግበር የማይችል፣ የምዕራባውያን ናፋቂ፣ ለወጣበት ማኅበረሰብ ምንም እውቀትና ተግባር መከወን የማይችል የተማረ ተብዬ ʻግማሽ ጥሬ ግማሽ ብስልʼ ምሁር ነው ማፍራት የተቻለው።

ነገር ግን በብዙ ጥሬዎች” ምክንያት፣ የአሰቡትን ለአገራቸው ለመሥራት ያልቻሉትን ትንሽ የበቁ ምሁራንን ሳንረሳ። ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ስርዓቱ በፖለቲካው ተፅዕኖ ሥር መውደቁ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል። እናም ያለ እውቀትና ልምድ ሰላማዊ ክርክርና ውይይት እንዴት ይኑር?

የፖለቲካ ልዮነት በየትኛውም ዓለም ያለ ቢሆንም የኔ መንገድና ሐሳብ ብቻ ትክክል የሚሉ ፖለቲከኞች መንግሥትና ሕዝብ ተስማምተው እንዳይኖሩና የሐሳብ ልዩነትን ተነጋግሮ መፍታት እንዳይችል እያደረጉ ነው። የሕዝባችን ችግር የቀድሞው የመንግሥት ስርዓት ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትና ጥንካሬውን ለማሻሻል ከማሰብና ሐሳቡን ለመተግበር ከመጣር ይልቅ አዲሱ መንግሥት የሚገባውን ቃል እያመኑ በደመነፍስ እያጨበጨቡ ተስፋ ማድረግ ነው።

ችግሩ ሕዝብ እንዴት መንግሥትን መቅረፅና መግራት እንዳለበት አለማሰቡና አለማወቁ ነው። የእውቀት ማነስ የባሕልና ልምድን መበላሸት ብሎም የአስተዳዳር ብልሹነትን ይወልዳል:: የአስተዳደር ብልሹነት ደግሞ አንኳን አዲስ ሥልጣኔ ሊፈጥር ያለውን/የነበረውን ያጠፋል። ይህም ድንቁርናን፣ ድኅነትንና ኋላቀርነት ያስከትላል። ለእነዚህ ችግሮች የመነሻ ምክንያት ደግሞ የአስተዳደር ብቃት ማነስ ነው። በተጨማሪም በተጠና ርዕዮተ ዓለም አለመመራት፣ ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ አለመኖር መገለጫዎቹ ናቸው። ይህም የራስን ጥቅም ከአገር ጥቅም ማስቀደምን ያስከትላል። መፍትሔውም በፅንሰ ሐሳብ የሚያምን፣ ራዕይ ያለው፣ ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚነድፍና የሚተገብር መንግሥት መገንባት ነው። በተጨማሪም አንድነት፣ መከባበር፣ እኩልነት፣ የጋራ የሆነ አገራዊ ራዕይ እንዲኖር ማድረግና ከራስ ይልቅ የአገርን ጥቅም ማስቀደም መቻል ነው።

የእውቀት ድኅነት ለሞራል ድኅነትም አንዱ መንስዔ ነው። የሞራል እሴቶች መጥፋት ደግሞ ዋሾነትን፣ ስግብግብነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ሌብነትን፣ አመንዝራነትንና ሲሰኝነትን፣ የእኔ ብቻ ትክክል ባይነትን፣ አለመተማመንን፣ ሰውን አለማክበር፣ ኃላፊነትን አለመወጣት፣ ተጠያቂነት አለመውሰድን፣ ቃል አባይነትን፣ የጋራ ታሪክና እሴቶችን ማጥፋትን፣ የʻጨቋኝ ተጨቋኝʼ ትርክትን፣ የʻእኛ እነሱʼ ክፍፍልን፣ ብሔርተኝነትን፣ ጎሰግነትን፣ ጎጠኝነትንና መንደርተኝነትን፣ በጠቅላላው ዘረኝነትን በኅብረተሰባችን ውስጥ እንዲዘራ፣ አብቦ እንዲያፈራ አድርጓል። በዚህ ሁኔታ እንዴት ተደማምጠን እንወያይ?

ሌላው ደግሞ የእውቀት ማነስንና የኢኮኖሚ ድኅነትን ተከትሎ የሚመጣው የኃያላን መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ተፅዕኖ ነው። ኃያላን መንግስሥታት የራሱ ባሕልና ማንነት ያለው፣ ትናንት ሥልጡን የነበረ ሕዝብ፣ ዛሬ ያለ ተፅዕኖ ትተው በእድገት ጎዳና እንዲራመድና የሁሉም ጥቁር ሕዝብ አርዕያ እንዲሆንና የነገ የጦርና የሀብት ሽምያ ተወዳዳሪ እንዲሆን አይፈልጉም። የአረብ አገራትም በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ያላቸው ፍላጎትና ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የመግብያ በር መሆን ለተፅዕኖ ተጋላጭ እንድንሆን አድርጎናል። ይህም ለተወሰነ ቡድን እርዳታ በማድረግ የውይይቱን አቅጣጫ በመቀየር ስምምነት እንዳይኖር ያደርጋሉ። ለዚህም ቢሆን ተጠያቂዎቹ እኛው ነን፣ እራሳችንን መጠበቅና ችግሮቻችን ተወያይተን መፍታት አልቻልንምና።

ሕዝባችን አእምሮውን በመጠቀም አስተሳሰቡን ሳያዳብር፣ ሐሳብን በምክንያት መረዳትና መሞገት ሳይችል የጎሳም ሆነ የዜግነት ፖለቲካን አማራጭ መምረጥ አይችልም። ለዚህ ችግር እንደ መፍትሔ፣ መሠረታዊ የሆነ፣ ባህላችንና ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት ያደረገና የሌሎችን ሀገሮች ተሞክሮ የቀመረ ሀገራዊና በግልፅ ፓሊሲ የሚመራ የባህል አብዮት የሚያስፈልገን አይመስላችሁም? እንዴት በሚለው ላይ ብንወያይበት? በኔ በኩል እንዴት ለሚለው የባሕል አብዬት ማሳያዎች ከራሺያ፣ ኩባ እና አውዳሚነቱ ቢያመዝንም የማአዎ ቻይናን ለመለወጥ የወጠናቸው ተጠቃሽ እመርታዎች ባሕላዊ አብዮትን በማንቀሳቀስ ለዛሬዋ ቻይና እድገት እርሾውን እንዳስቀመጠ ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል።

ከሩቅ ወደ ቅርብ ያለው የኛው አገር ታሪክ የኃይለ ሥላሴን የሀገሪቱን ትምህርት ስርዓት በመለወጥ ከአብነት አስተምሮት ብቻ ለማላቀቅ ብሎም ለማዘመን የተወሰዱ ብርቱ እርምጃዎችን ከፍ ባለ ሁኔታ ማየት የሚቻል ይመስለኛል። ቀጥሎ ‘መሰረተ ትምህርትን’ ለማስፋፋት እንዲሁም ፓለቲካዊ ሒሳቡ እንዳለ ሆኖ የእድገት በኅብረት ዘመቻ ጥቅል ውጤት በደርጉ ዘመን ከተወሰዱ ባሕል ነክ አብዮት በምሳሌው ማንሳት ይቻላል።

በሌላ በኩል ማስተማር አንዱ መንገድ ነው። የትምህርት ፖሊሲያችን የሥነ ሰብ ትምህርቶችን (ታሪክ፣ ጂእግራፊ፣ ፍልስፍና፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሲዮሎጂ፣ ቋንቋ፣ የንባብ ክህሎት ሥልጠና ወዘተ) እና አገራዊ እውቀቶችን እንዲጨመር ማድረግ፣ ሕፃናትን በአግባቡ መቅረፁ ላይ መሥራት፤ የቤተሰብ አስተዳደርና የዕድገት ሥነ ልቦና እውቀት እንዲኖር መስራት፣ የንባብ ባሕል እንዲያድግ መሥራት፣ ቤተ መጽሐፍት መስፋፋትን መደገፍ፣ ደራሲያንንና ተመራማሪዎችን በተለይም ፈላስፋዎቻችንና አሳቦቻቸው ለሕዝብ እንዲደርሱ መደገፍ፣ የሕትመትና የመጻሕፍት ዋጋ እንዲቀንስ መሥራትን፣ የሚዲያ ሰዎች ማስተማር ዓላማቸው መሆንን እንዲያውቁ ማገዝ፣ የሕዝብ የመወያየትና በአመክንዮ የማመንን ባህል ማዳበር ይጠይቃል።

እናም መፍትሔው ያለው በእጃችን ነውና ችግሮቻችን በመለየት ለመፍትሔው እንረባረብ!!!

መላኩ አዳል የዶክትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በመሥራት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here