ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብር አስተባባሪና መምህር ናቸው። ኹለት የመጀመሪያ ዲግሪዎች በፍልስፍና እና በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት አላቸው። የማስተርስ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ተግባቦት የሠሩት ተሻገር፥ በ2009 የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሥነ ልሳንና ተግባቦት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በሥራው ዓለም በአጠቃላይ 22 ዓመታት ልምድ ያላቸው ሲሆን 12ቱን ዓመታት በመንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ባልሆኑና በግል ተቋማት ውስጥ በመምህርነት፣ በጋዜጠኝነትና በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት ሠርተዋል።
ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው በልምድ ሲሠራ እንደነበር የሚናገሩት ተሻገር፥ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ተቋም ከ15 ዓመታት በፊት ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት የፈር ቀዳጅነት ሚና በመጫወቱ በአሁኑ ወቅት በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችና በግል ተቋማት ውስጥ የጋዜጠኝነት ሙያ በሰፊው እንዲሰጥ መሰረት ጥሏል ይላሉ።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ አጠቃለይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምህዳር እንዲሁም ከወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከተሻገር ሽፈራው ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ችግሮች ምንድን ናቸው? ምክንያታቸውስ?
ይሔ ጥያቄ ከብዙ አቅጣጫዎች ሊታይ ይችላል። አንዱ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ባሕል አለመዳበሩ ነው። ከዴሞክራሲ ባሕል ጋር ከሚያያዙት መካከል አንዱ መገናኛ ብዙኀን እንደሆኑ ይታወቃል። ሌላው የመገናኛ ብዙኀን በደረጃ እየተለኩ የመሥራት አጠቃላይ ሁኔታ አልዳበረም። በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ገለልተኛ ሆኖ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን በማሳየት የጋራ ሐሳብ እንዲኖር የማደረግ ዝንባሌ ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ ወገንተኝነት በኢትየጵያ መገናኛ ብዙኀን በጣም ጎልቶ የሚወጣ ነው። ብዙ ጥናቶችም እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ቅርፅ ጽንፈኛ መሆኑን ነው። በርግጥ ይሔ ሐሳብ አከራካሪ ሊሆን ይችላል።
አሁን በርግጥ ቅርፁ እየተለወጠ ያለ ይመስላል። ነገር ግን ባለፉት 20 ዓመታት መገናኛ ብዙኀን የሚሰሩትን ስናይ አማካኝ ቦታ እየሠሩ ያሉ አሉ፤ በዚህም ምክንያት ረጅም ዕድሜ የቆዩ ጋዜጦችና ሌሎች መገናኛ ብዙኀን እናገኛለን። ዞሮ ዞሮ ጽንፈኝነት ወገንተኝነትን ያሳያል። ይሔ ደግሞ አንድ ትልቅ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ድክመት ነው።
አንዱ የሚደግፈውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ይዞ የዛን ሐሳብ እያራመደ፥ ሌላውን እየተቸ መንቀሳቀስ ማለት ነው። ይሔ ሌላው ትልቁ የመገናኛ ብዙኀን ድክመት ነው። መገናኛ ብዙኀን ለሕዝቡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት አንዱን ወገን እየደገፉ ሌላውን እየተቃወሙ ሳይሆን ተፃራሪ የሆኑ አስተሳሰቦችን ወደ አንድ በማምጣትና በማወያየት የጋራ ትርጉም (shared meaning) እንዲኖር በማድረግ ነው።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የዜግነት እና የብሔር ፖለቲካ የሚባሉ ሐሳቦች አሉ። እነዚህ ኹለቱ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ተቀራርበው የሚወያዩበት መድረክ መፍጠር ይገባል። አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን ኹለቱንም ወገን ሰብስበው ለየብቻቸው የሚያወያዩ፥ በመሆኑ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውይይት አይኖርመም፤ አዲስ ሐሳብም አይመጣም። በተግባቦት ጥናት እንደዚህ ዓይነት ነገር የገደል ማሚቶ (echo chamber) ይባላል።
እውነተኛ የፖለቲካ ውይይት የሚመጣው ሚዛናዊ አቋም ባላቸው፣ ገለልተኛ በሆኑ እና የሙያ ሥነ ምግባር በሚከተሉ መገናኛ ብዙኀን ነው።
ሌላው አሳሰቢ ችግር አብዛኛዎቹ የእኛ መገናኛ ብዙኀን ለዴሞክራሲ እንታገላለን ብለው ያምናሉ፤ ነገር ግን ራሳቸው የውስጥ ዴሞክራሲ የላቸውም።
ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሌላው ችግር ሕዝብ መገናኛ ብዙኀንን የማጣጣም ወይም አረዳድ (media literacy) ዝንባዘሌው ደካማ መሆኑ ነው። የተከፈተ ሬዲዮ ሁሉ መገናኘ ብዙኀን ነው ብሎ ያምናል፤ የሚታተም ጋዜጣ ሁሉ ጋዜጣ ነው ብሎ ያምናል። በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አያውቅም።
የመገናኛ ብዙኀን የሙያ ነፃነት እየተከበረ አይደለም። ለምሳሌ ጋዜጠኞች ይታሰሩ ነበር፣ በሚጽፉት ይጠየቁ ነበር፣ ተሰደዋል፣ ጋዜጦች ዛሬ ይከፈታሉ፥ ነገ ይዘጋሉ። ይህ በመሆኑ ዘላቂነት ያላቸው ሚዲያዎች እንዳይኖሩ አድርጓል።
በዘርፉ ላይ መዋዕለ ነዋይ አይፈስም።
በአጭሩ ሚዲያ በአገራችን በችግር የተሞላ ነው ማለት ይቻላል።
ሌላው ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ተቺዎች የሚያነሱት፥ ጋዜጠኝነትና የመብት ተሟጋችነት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ምኅዳር ተቀላቀለዋል የሚል ሐሳብ ነው። የኹለቱ መቀላቀል በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ምን አንድምታ አለው?
የመብት ተሟጋችና ጋዜጠኝነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መለያየት ብቻ ሳይሆን ተፃራሪም ናቸው። ጋዜጠኛ በሙያ ሥነ ምግባር የሚሠራ ሲሆን ሚዛናዊነት ትልቁ ነገር ነው።
ገለልተኝነት የተፈጠረው በዚህ በገበያ ኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ ነው። ለዚህ ወይም ለዛ የወገነ ከሆነ ለገበያ የሚመች ፀባይ አይሆንም። ብዙ ጊዜ ወገንተኛ የሚሆኑት የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ወይም የአንድ የፍላጎት ቡድን ተቀጽላ የሆኑ መገናኛ ብዙኀን ናቸው። በገበያ ውስጥ ከልዩ ልዩ ተቋማት የማስታወቂያ ገቢ የሚሰበስቡ፣ በሙያ የሚመሩ ከሆኑ አጠቃላይ አዝማሚያቸው ሚዛናዊነት፣ አለመወገንና ነፃ መሆን ነው።
በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ የጥብቅና (ʻአድቮኬሲʼ) ኃላፊነትም አለበት። ለምሳሌ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚታዩ ህፀፆችን ሲያይ እንዲህ ዓይነት ችግር ተፈጥሯል ብሎ ያንን መረጃ መስጠት አንዱ የጋዜጠኝነት ሥራ ነው።
ለሕዝብ ጥብቅና መቆም ማለት ለዚህ ወይም ለዛ ወገን መጮህ ሳይሆን ለሰብኣዊነት፣ ለፍትሕ፣ ለዲሞክራሲ እና ለእኩልነት መብት መታገል ማለት ነው። ይሔ በመርኅ ደረጃ ያለ ውግንና ነው። እነዚህን ጉዳዮች ማንም የማይፃረራቸው በረጅም ጊዜ የተፈተኑ ናቸው። ነገር ግን ለዚህ ወይም ለዛ የፖለቲካ ቡድን፣ እምነት፣ ብሔር መታገል ለመብት ተሟጋች ጋር የሚያያዝ እንጂ ከጋዜጠኝነት ጋር አይገናኝም።
በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቁ ችግር መገናኛ ብዙኀንና የመብት ተሟጋችን የመለየት ጉዳይ ነው። ጋዜጠኞች የጥብቅና ሥራ የሚሠሩበት የተመሰከረለትና የተረጋገጠ ሙያዊ የሆነ መስመር አላቸው። ለአንድ የተለየ እምነት፣ ፍልስፍናና ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ ወገን ቆሞ መታገል ከመገናኛ ብዙኀን ኃላፊነት ጋር አብሮ የሚሔድ አይደለም። ይሁንና የመብት ተሟጋችነት በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለት ይቻላል።
በመንግሥት ስርዓት ሽግግር ወቅት ሚዲያው ምን ዓይነት ሚና መጫወት ይጠበቅበታል? ሚዲያ ነፃ መሆን አለበት ይባላል። ነፃ መሆን ይቻላል? ገለልተኛ ከመሆን አንጻርስ ምን ማለት ይቻላል?
ለመገናኛ ብዙኀን ነፃ መሆን እጅግ በጣም ትልቁ ፈተና ነው፤ በመርኅ ደረጃ ግን ይቻላል። በመርኅ ደረጃ ያለንበት ቦታ ስንፈትሽ ʻከምን ጋር ነው የምናነጻጽረው? ከዛስ ምን ያክል ርቀት ላይ ነን?ʼ የሚለውን ነገር ለማየት ይጠቅማል።
በሙያ ጋዜጠኝነት የሥራ ደረጃ ውስጥ ወገንተኛ ያልሆነ ዘገባ (objective reporting) የሚባል ሐሳብ አለ። ብዙ መገናኛ ብዙኀን ወገንተኛ ያልሆነ ዘገባ ሐሳባዊ (ideal) ነው፤ እውናዊ (real) አይደለም ይላሉ። በተግባር ሊደረግ አይቻልም ስለዚህ እንተወው ይላሉ። ብዙዎቹ ደግሞ መተው የለብንም ምክንያቱም ያለንበት ቦታ የምንለካው ምናባዊ ከሆነው ምን ያክል እንደምንርቅ የምናውቀው ወገንተኛ ያልሆነ ዘገባ ስንሰራ ነው የሚል መከራከሪያ አላቸው።
በዓለም ላይ ያሉ ትላልቅ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀሩ በወገንተኘነት ይታማሉ። ግን አጥንተና ፈትሸን የምናየው ነው እንጂ ግልጽ ወይም ይፋ የሆነ ነገር አይደለም። ነገር ግን እኛ አገር ያለው ወገንተኝነት ʻእከሌ ጠላት ነውʼ ብሎ ፈርጆ፥ ʻያንን ጠላትʼ እስኪወድቅ ድረስ በግልጽ መታገል ነው።
የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ጭራ፣ ጭፍራ፣ ተከታይ ባስ ሲልም አሸርጋጅ ናቸው ተብለው ይተቻሉ። ሚዲያ የራሱን አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ አለበት ሲባል ምን ማለት ነው? በዚህ ረገደ መገናኛ ብዙኀኖች እንዴት ይመዘናሉ?
ይሔ ጉዳይ በኹለት ዓይነት መንገድ የሚታይ ነው። አባባሉ ትክክል የሆነም ትክክል ያልሆነም ነገር አለው። መገናኛ ብዙኀን የሚያስተላልፏቸውን መልዕክቶች የሚያገኙት ከኅብረተሰቡ የላይኛውን የሥልጣን እርከን ከሚገኙ አካላት ነው። እንዲሁም በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ነው። ይሁንና ይሔንን ብቻ የሚያቀርቡ ከሆነ እንደ መገናኛ ብዙኀን ሊያበረክቱ የሚችሉትን ሙያዊ አስተዋፅዎ ሳያበረክቱ ይቀራሉ።
የተሳሳቱ ፖሊሲዎች፣ ትክክል ያልሆኑ አሰራሮች ላይ በመዘገብ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ፣ አቅጣጫ እንዲለውጥ የሚያደርጉ ከሆነ መገናኛ ብዙኀን ተከታይ ብቻ ሳይሆኑ መሪም ይሆናሉ ማለት ነው።
አብዛኛውን ጊዜ የመገናኛ ብዙኀን ሚናቸውን ተቺ አለመሆናቸው ነው። ኹነቶችን መዘገብ፣ ትርጉማቸውን መሳየት፣ ትክክል ካልሆኑ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ማድረግ ላይ ትንሽ ደከም የማለት ነገር አለ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን አጀንዳ ፈጥረው፣ በዛ አጀንዳ መሰረት ለውጥ በመምራት ረገድ ገና ብዙ ይቀራቸዋል። ወደፊት ቀደም ብሎ የመሔድ፣ ኅበረተሰቡን የመምራት፣ ሕይወቱን የመተርጎም፣ ሕዝብን በማስተማር ረገድ በተወሰነ ደረጃ ውስንነት አለባቸው።
ሙያዊ ሥነ ምግባር በጋዜጠኝነት ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው? ከሙያዊ ሥነ ምግባር አንጻር የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እንዴት ይታያሉ?
ቀደም ብለን የዘረዘርናቸው ችግሮች በሙሉ ሥነ ምግባር ላይ ነው የሚያርፉት። ለምሳሌ ከሥነ ምግባር መመዘኛዎች አንዱ የሙያ ነፃነት ነው። የሙያ ነፃነት ማለት አንድ ጋዜጠኛ ሙያው በሚፈቅድለት ልክ የማይሠራ ከሆነ የሙያውን ሥነ ምግባር እንዳልተከተለ ይቆጠራል።
ለምሳሌ ከተወሰኑ የፍላጎት ቡድኖች በመሳት የመገናኛ ብዙኀን ይዘት የሚወሰን ከሆነ፥ ይሔ ነፃ ጋዜጠኝት አይደለም፤ የሙያ ነፃነትም የለውም ማለት ነው። በአጠቃላይ ግን በእኛ መገናኛ ብዙኀን ውስጥ አንዱ ትልቁ ችግር የሙያ ነፃነት ማጣት ነው።
ሌላው እውነት መናገር ነው። የጋዜጠኝት ዋና ዓላማ እውነትን ለራሱ ሲባል የሚዘግብ ሳይሆን እውነት የጋዜጠኝነት ጥራት መመዘኛ ነው። እውነት በብዙ ነገሮች ላይ ይመሰረታል። ለምሳሌ መሠረታዊ ጭብጦች የተሟሉ መሆን አለባቸው። እነዛ ምንጮች የሚያስገኙት አጠቃላይ መረጃ ደግሞ እውነት መሆን መቻል አለበት። በዚህ ደረጃ ሲታይ የእኛ አገር መገናኛ ብዙኀን በርካታ ድክመት አለባቸው። ያልተሟላ ዘገባ እና የሌሎቹን ሐሳብ አጉድሎ ማቅረብ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባን ይፈጥራል። ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ደግሞ እውነት ያልሆነ ዘገባን ይፈጥራል። ስለዚህ እነዚህ ደረጃዎች እርስ በእርስ የተሳሰሩ ነገሮች ናቸው። በእነዚህ ሁሉ መመዘኛዎች ሲታይ በጣም ከጥቂቶች በስተቀር የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የሙያ ሥነ ምግባር ደረጃው ዝቅ ያለ ነው ማለት ይቻላል።
በአገር ዐቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የሚዲያ ፖሊሲ አለመኖር በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። የሚዲያ ፖሊሲ መኖር ለሙያው የሚያበረክተው ፋይዳ ምንድን ነው? ባለመኖሩስ ምን ይታጣል?
ኢትዮጵያ ውስጥ የብሮድካስት ሕግና ሌሎች የመገናኛ ብዙኀንን የሚመለከቱ ሕጎች አሉ። ለምሳሌ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ የመገናኛ ብዙሃንን ይመለከታል። የሙያ ሥነ ምግባር ዓለም ዐቀፍ ደንቦች አሉ። መገናኛ ብዙኀን ሙያዊ ተቋም ነን ብለው ሲሠሩ ሊከተሏቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። በተጨማሪ እያንዳንዱ የመገናኛ ብዙኀን ተቋም የራሱ ፖሊሲ አለው። የብሮድካስት ባለሥልጣን የየተቋማቱ የአርትኦት ፖሊሲ አለው። የብሮድካስት ባለሥልጣን ጥያቄው በስርዓት በሕግ ቢሰሩ የሚለው ነው።
ምናልባት የፖሊሲ ክፍተት አለ የሚባለው ነገር አሁን የመገናኛ ብዙኀን ሥራ ትልቅ ʻኢንቨስትመንትʼ ነው። ቴሌቪዥንና ሬድዮ ለመክፈት ከፈለክ ያንን የሚሠራ ዝርዝር ፖሊሲ የለም የሚለውን ነገር ልናነሳ እንችላለን። ሆቴል ሲከፈት ለባለሆቴሎች የሚሰጥ የቀረጥ መብት አለ። እነዚህ መብቶች ለቴሌቪዥንና ሬድዮ ወይም ለሌላ መገናኛ ብዙኀን ቴክኖሎጂ ማስገቢያ ሲሆን የለም። በጣም ከፍተኛ ቀረጥ አለ። ሚዲያውን የሚያበረታታ አይደለም። መገናኛ ብዙኀን የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ፣ እምነት፣ እውቀት ከፍ ከማድረግ አንፃር ያላቸው አስተዋፅኦ ግዙፍ ስለሆነ ተመሳሳይ መብት ሊሰጣቸው ይገባል። እንዲያውም ከመንግሥት ውጪም ከሌላ ተቋም ፈንድ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህን ጉዳዮች ካየን በትክክል ያሉት ሕጎችና ፖሊሲዎች በቂ አይደሉም ማለት እንችላለን።
ሁሉንም ችግሮች ግን ከፖሊሲ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፤ መገናኛ ብዙኀን በውስጣቸው ያሉትን ችግሮች መመልከት አለባቸው።
ለምሳሌ ባለፉት ኻያ ሰባ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ተከፍተው ተዘግተዋል። የመፍረሳቸውም ምክንያት አብዛኛው ጊዜ ከውስጣቸው ነው ማለት ይቻላል። ጋዜጣ ማተሙ ብቻ በቂ አይደለም፤ የኢኮኖሚ መሠረት ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ጋዜጦች ሲወድቁ ውጫዊ ነው ወይስ ውስጣዊ ምክንያት ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በቂ ሀብት (ʻካፒታልʼ) ብቻ ሳይሆን በቂ እውቀት ሳይኖራቸው የሚጀምሩም አሉ። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በውስጥ አሉ። ስለዚህ በአጠቃላይ ከፖሊሲ ውጪ ሲነሱ የሚገባቸው የተለያዩ ውስጣዊ ምክንያቶች ጭምር አሉ። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ችግር ከተለያየ አቅጣጫ የሚታይ ነው።
ከሙያው ጋር በተያያዘም ንቁ የጋዜጠኞች ማኅበራት እና የሚዲያ መማክርት (ሚዲያ ካውንስል) አለመኖሩ ወይም ተጠናክሮ አለመውጣቱ በጋዜጠኝነት ሙያ እድገት ላይ ምን ተጽዕኖ ፈጥሯል?
የጋዜጠኞች ሙያዊ ማኅበርን ስንወስድ፥ አንዱ ትልቁ እኛ አገር የነበረው አለመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢጋማ) የሚባል ለረዥም ጊዜ የቆየ ማኅበር አለ። የግል ጋዜጠኞች ማኅበር የሚባልም አለ። አሁን ትልቁ ጥያቄ ʻእነዚህ ማኅበራት ምን ያህል ነፃ ናቸው? በጋዜጠኞች በነፃ ፍላጎት ተመስርተው ሙያቸውን ለማዳበር እየሠሩ ነበር ወይ?ʼ የሚለው ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ኢጋማ በአብዛኛው የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ውስጥ ያሉ ጋዜጦች ነው የሚያሳትፈው። እያንዳንዱ ተቋም ውስጥ የሌለውን ነፃነት የሙያ ማኅበሩ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ እንዲሁ አለ ለማለት ካልሆነ ሙያውን ከማሳደግና የጋዜጠኞችን የሙያ መብት ከማክበር አንፃር ሠራ ለማለት አይቻልም። ተቋማቱ በነፃነት ቢሠሩ ይዘትና የጋዜጠኞችን አቅም ከማጎልበት አንፃር የተሸለ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል።
የሚዲያ ምክር ቤት ከማኅበራት በጣም ሰፋ ያለ ሆኖ መገናኛ ብዙኀን ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ችግሮች ሲነሱ ለመፍታ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ናቸው። ጋዜጠኝነት በዚህ ምክንያት ነው ተቋም የሚሆነው። የጋዜጠኝነት ተቋማት፣ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ የመገናኛ ብዙኀን ምክር ቤቶች፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች የመሳሰሉት አንድ ላይ ሆነው የጋዜጠኝነት ተቋም የሚሠሩት። እነዚህ ተቋሞች ነፃ አለመሆናቸውና እርስ በርሳቸው አለመተሳሰራቸው መገናኛ ብዙሃንን ወይም ጋዜጠኝነትን እንደ ተቋም በማሳደግ ደረጃ ተገቢ አስተዋፅኦ አላደረጉም። የሥነ ምግባር ጥሰት ሲኖር ማስተካከል፣ ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተካክሉ፣ ተዓማኒ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል እነዚህ ተቋማት ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ አላደረጉም። በዚህም ትልቁ ምክንያት ሙያዊ ነፃነት አለመኖር ነው።
ኢትዮጵያ አሁን በሽግግር ላይ ነች ይባላል። በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሚዲያው ምን ዓይነት ሚና መጫወት አለበት?
በዚህ ወቅት መገናኛ ብዙኀን ትልቅ ሚና አላቸው። አንዱ ትልቁ ነገር የሐሳብ ልዩነቶች ወደ ጠላትነትና ቅራኔ የሚያመሩበት ሁኔታ በጣም ይታያል። ግጭቶች ይታያሉ። ልዩ ልዩ ተቀብረው የነበሩ ፍላጎቶች እየታዩ ነው። ብዙ ጫጫታ አለ። ይሔንን ከምንቆጣጠርበትና ወደ አዎንታዊ ደረጃ ከምናሳድግበት መንገዶች አንዱ ጋዜጠኝነት ነው። የሐሳብ ልዩነት ያላቸው ተቋማት ወደ ሕዝብ ቀርበው ተወያይተው ችግራቸውን ሊፈቱ የሚችሉበት መንገድ መገናኛ ብዙኀን ሊሠሩ ይገባል።
ቀደም ሲል እንዳየነው [በመገናኛ ብዙኀን ላይ] ወገንተኝነት በጣም ይበዛል። ልዩ ልዩ የፖለቲካ ተቋማትና የፍላጎት ቡድኖች በመገናኛ ብዙኀን የመጠቀም ፍላጎታቸው ይታያል። በኅቡዕ ሲሠሩ የነበሩ መገናኛ ብዙኀን ከመደበኛ መገናኛ ብዙኀን የበለጠ ተዓማኒነት እያተረፉ ነው። አዝማሚያው የኅብረተሰቡ አማካይ ነጥብ ላይ ቆሞ ግራ ቀኝ ማየትና ተደራድሮ የጋራ ትርጉም (shared meaning) ከማግኘት ይልቅ ወደ አንድ ወገን የማዘንበል ነገር ይታይበታል። ቅራኔዎችን ከመፍታት ይልቅ የማባባስ ነገር ይታያል።
መገናኛ ብዙኀን ግን ሚናቸው መሆን ያለበት ለሕዝብ ጥብቅና መቆም፣ ለፍትሕ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለሰብኣዊ መብት መታገል ነው። እንደዚህ የሚያደርጉት ደግሞ ልዩ ልዩ ቡድኖች ወደ አንድ ለማምጣት ማወያየትና ማነጋገር ያስፈልጋል። አሁን የማወያየት ሥራ በብቃተ እየተካሔደ ነው ማለት አይቻልም።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የመገናኛ ብዙኀን አቅም ደካማ ስለሆነ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ራቅ ብለው መረጃ ሰብስበው በማቅረብ በኩል በጣም ድክመት አለ። አንድ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተም ጋዜጣ አገር ዐቀፍ መረጃ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ራቅ ያለ ቦታዎችን አይቶ መሥራት የማይችል ከሆነ፥ በጠባብ አካባቢ ይወስናል ማለት ነው። ስለዚህ ይሔም ሌላ ችግር ነው። ነገር ግን ሁሉም በየአካባቢያቸው ያሉ ተፃራሪ ወይም ልዩ ልዩ ሐሳቦችን በሰከነ ሁኔታ የማወያየት፣ ቅራኔዎችን ለማባባስ ሳይሆን ለመፍታት የሚያሠሩ ከሆነ ሠላም ሲፈጠር ይችላል። በውይይቱ ውስጥ ደግሞ ለዲሞክራሲ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሊሟሉ ይችላሉ። በዚህ ወቅት ብዙ ይጠበቅባቸዋል።
ከውጭ የመጡትን ጨምሮ አገር ውስጥ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር እንዴት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል?
ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን በሙያዊና ንግድ የተቋቋሙ መሆን አለባቸው። አሁንም ግን በጣም ተሰሚ የሆኑት በኅቡዕ ሲንቀሳቀሱና ሕዝቡንም ለትግል ሊያነሳሱ የነበሩ የመገናኛ ብዙኀን ናቸው።
ሌላው የተሻለው አማራጭ ላለፉት ኻያ ሰባት ዓመታት የዴሞክራሲያና የሰላም ድምጽ ተብሎ የተቋቋመው የፓርቲ ልሰን የነበረው ፋና አሁን ቀስ እያለ ወደ ንግድ የመጣ ይመስላል። እንደሚታየው ከአዲሱ የለውጥ አስተሳሰብ ጋር እየተራመደ ያለ ይመስላል። በተመሳሳይ ሁኔታ ዋልታንም ማየት እንችላለን። እነኚህ መገናኛ ብዙኀን አሁን ከውጪ ከመጡት መገናኛ ብዙኀን ጋር ተመሳሳይ አይደሉም።
ከውጪ የመጡትም መገናኛ ብዙኀን ፖሊሲያቸውን መቀየር አለባቸው። ሁሉንም የአስተሳሰብ ዘርፎች የሚያስተናግዱ፣ ሚዛናዊነታቸው የማያጠራጥር ሙያዊ ጋዜጠኝነት ራሳቸውን በፍጥነት መለወጥ መቻል አለባቸው። ይህንንም ለሕዝቡ ማሳየት መቻል አለባቸው። አሁን ባሉበት ደረጃ ለሕዝብ መረጃ መስጠት፣ ሕዝብን ማወያየት፣ ዴሞክራሲ ማጎልበት፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ነው የምንሰራው የሚለውን ሐሳብ በሚያሳምን ሁኔታ በተግባር ማሳየት አለባቸው።
የተገለሉ የሚመስሉት መደበኛ መገናኛ ብዙኀንም ተሰሚነታቸውን ከፍ ማድረግ አለባቸው። ለምሳሌ የዜግነት ፖለቲካና የብሔር ፖለቲካ ማዶና ማዶ ቆመው የሚታኮሱ ሳይሆኑ በጋራ ሊሰሩ የሚችሉባቸውን ነገሮች ለይተው መራመድ የሚችሉበትንና የጠላትነት ስሜትን ማጥፋት አለባቸው።
በተጨማሪም በአንድ አገር ሰዎች እስከኖሩ ድረስ የፖለቲካ ተቋማትም የመገናኛ ብዙኀንም የጋራ አጀንዳ ሊኖራቸው ይገባል፤ በጋራ የሚያገለግሉበት ያንን የጋራ አጀንዳ ለይተው በጋራ መሥራት የሚችሉበት ነገር ቢፈጠር ጥሩ ሊሆን ይችላል።
ጋዜጠኛ እውነትን ይዘግባል ተብሏል። እውነቱ ግን አገርን የሚጎዳ ቢሆንስ?
መገናኛ ብዙኀን ሁል ጊዜ በአሻሚ ውሳኔዎች ውስጥ ይገኛሉ። እውነትን መዘገብ ይፈልጋሉ፤ እውነቱ ከተዘገበ ደግሞ የሚያስከትለው ጉዳት ሊኖር ይችላል።
ግጭትን ከሃይማኖት፣ ከብሔር ወይም ከፖለቲካ ፍላጎት አንፃር ማየት አለ። በተለይ ይህንን በክልል መገናኛ ብዙኀን ልናየው እንችላለን። በአንድ ክልል ያለ የመንግሥት ብዙኀን መገናኛ ሌላኛውም ክልል የራሴ ወገን ነው ብሎ የማይታገል ከሆነ ግጭት ይመጣል። የምናይበትን መስኮት ከክልላችን ውጪ ከፍ ማድረግ አለብን። የተወሰኑ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ብቻ ከማተኮር ዘላቂ ጥቅም ላይ ማተኮር፤ አጠቃላይ የኅብረተሰቡ ፍላጎት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። የሙያ ነፃነት አሰራራችን እዚህ ላይ ነው፥ ምክንያቱም የሙያው ነፃነት ካለ ኹለቱም ወገኖች አነጋግሮ ሚዛናዊ ዘገባ ለማስተላለፍ ይቻላል።
የግለሰብ ጋዜጣና ባለቤት በመገናኛ ብዙኀን ውስጥ እንደ ሕዝብ ፍላጎት ተደርጎ የሚቀርብበት ሁኔታ አለ። ይህ የሆነበት ምክንያት የሙያ ደረጃ ሥነ ምግባር ዝቅ ሰላለ ነው።
ሌላው ስሜታዊነት ነው። ወደ ጥላቻ የሚቀርቡ ነገሮች መዘገብ፣ ግጭቶች በፈጠሩት ጉዳት ላይ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠት፣ በችግሮች ላይ ማተኮር እንጂ ለመፍትሔዎች ልዩ ትኩረት አለመስጠት፣ ተከታታይና ወጥነት ያለው ዘገባ አለመዘገብ፣ እነዚህ ነገሮች በጣም በሰፊው ይታያሉ።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ይህንን የሚመጥን ሥራ ለመሥራት እያንዳንዱን ተቋም እንደገና ራሱን መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል።
የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጠንካራ የመገናኛ ብዙኀን ኢንዱስትሪ ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ አለ?
ይፈጠራሉ! በየትኛውም ዓለም ጠንካራ መገናኛ ብዙኀን የሚኖሩት ጠንካራ ኢኮኖሚ ሲኖር ነው። ምክንያቱም የገቢ ምንጫቸው ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የልማት ተቋማት ናቸው። ማስታወቂያ የሚገኘው የንግድና የአገልግሎት ሰጪዎች ሲስፋፉና ሲጠናከሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢኮኖሚው ማደግ አለበት። አሁን እንደምናየው ኢኮኖሚው በጣም በደካማ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የማመንጨት አቅሟ በጣም ደካማ ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጠንካራ ብዙኀን መገናኛ ይኖራል ማለት ያስቸግራል ምክንያቱም መገናኛ ብዙኀን እሴት ፈጣሪ አይደሉም፤ የውጭ ምንዛሬ ሊያመጡ አይችሉም። ስለሆነም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተሻለ ደረጃ መገኘት ለመገናኛ ብዙኀን እድገት አንዱ መሰረት ነው።
ሌላው ዴሞክራሲ መኖር አለበት። የመገናኛ ብዙኀን ጋዜጠኞች የሙያ መብታቸው መከበር አለበት፤ የሕግ የበላይነት መጠበቅ አለበት። አንድ ዘገባ ሲዘግቡ የፍላጎት ቡድኖች ነውጠኛ የሆነ እርምጃ የማይወስዱበት መሆን አለበት። እርግጠኝነትና መተማመን ሲኖራቸው፣ የሙያ ነጻነት ሲኖር የሥራ መሰረት የሆነው ʻካፒታልʼ ኢኮኖሚው ውስጥ በደንብ ሲፈጠር ጋዜጦች እየሰፉ፣ እየተስፋፉ ይሔዳሉ።
በአገር ውስጥ ብቻ ሳንወሰን በጎረቤት አገሮች የሚደመጡ መገናኛ ብዙኀን ሊኖረን ይችላሉ፣ ራቅ ባለበት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገሮችም የሚታዩ ቴሌቪዥኖች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እኛ አገር ታትመው ሩቅ ቦታ የሚሰራጩ ጋዜጦች ሊኖሩን ይችላሉ፤ ዘርፉ ሊያድግ ይችላል፤ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሊኖሩን ይችላሉ። የቻይናው ዥንዋ የዜና ወኪል ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።
ስለዚህ የኢኮኖሚ ማደግ፣ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም መስፈን፣ የዴሞክራሲ መስፋፋትና የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎች ነጻነት መኖር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ከአነስተኛና ጥቃቅን ወጥቶ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ እንዲያድግ የሚያደርጉ ናቸው።
ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011