የቤተ መንግሥቱ ጉብኝት “ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ በአዲስ አበባ ጉዳይምሥጋት አይግባችሁ” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

0
829

ብርሃኑ ሰሙ መጋቢት 5፣ 2011 ከጥበብ ሰዎች እና ደራሲያን ጋር ቤተ መንግሥት ተጋብዘው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የመወያየት እና “ግቢውን” የመጎብኘት ዕድል አግኝተው ነበር። በዕለቱ ያዩትን እና የሰሙትን እንሚከተለው በአጭሩ ተርከውታል።

 

 

 

የኢሕአዴግ ኹለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው፣ ሕልፈታቸው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙኀንን ትኩረት የሚስብ ታላቅ ዜና በነበረበት ወቅት፥ ቪ.ኦ.ኤ. የአማርኛው ፕሮግራም ክፍል፣ በወቅቱ በአሜሪካ ይገኙ ለነበሩት ብርቱካን ሚደቅሳ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምን ተሰማዎ?” የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው። በአምስት ቃላት የቀረበው ጥያቄ ቀላል ቢመስልም፣ ጋዜጠኛው ይህን ጥያቄ ለተጠያቂዋ እንዲያቀርብ ምክንያትና መነሻ የሆነ ሰፊ ታሪክ በውስጡ ነበረበት። ጥያቄውን ለሰማ የሬዲዮ አድማጭም “ብርቱካን ምላሻቸው ምን ይሆን?” በሚል ስሜት ጉጉት ፈጣሪ ነበር።

የብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ ከቂምና በቀል የፀዳ፣ ፍቅርና ሰብኣዊነት የሚታይበት፣ ለነገው አገርና ትውልድ ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት እንደሚጨነቁ የሚያመለክት ነበር። ለሟቹ አንቱታን ሳትነፍግ የሰጠችው ምላሽ “ሞታቸውን ስሰማ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ሞት አሳዝኖኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለልጆቻቸው አባት፣ ለሚስታቸው ባል፣ ለቤታቸው አባወራ ስለሆኑ ሕልፈታቸው እነዚህን ስለሚጎዳ ይህም ያሳዝናል። ምንም ይሁኑ ምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሬ መሪ ስለሆኑ ሕልፈታቸው አሳዛኝ ነው። በጣም የሚቆጨው ግን ማስተካከል የሚችሉት ብዙ ነገር በእጃቸው እያለ ያንን ሳይሠሩ ማለፋቸው ነው።”

 

“መለመን በምንም መመዘኛ አሳፋሪ ተግባር ቢሆንም፥ ቡቱቶ ለብሰን፣ በዝቅተኝነት መንፈስ በመለመንና አምረን፣ በራስ መተማመን ስሜት ተሞልተን በመለመን መሐል ሰፊ ልዩነት አለ።

 

መለስ ዜናዊ (ዐፈሩ ይቅለላቸው) ብርቱካን ሚደቅሳ ስለ እርሳቸው የሰጡትን ምስክርነት የመሥማት ዕድሉ ቢኖራቸው፣ አገርና ሕዝብ ለመምራት ይከተሉት በነበረው አቋም፥ በተለይ ማስተካከል በሚችሏቸው ነገሮች፣ ላይ ምን ለውጥ ያደርጉ ነበር ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት ቢቻልም መልስ ማግኘቱ ግን የሚታሰብ አይደለም። ከጋዜጠኛው ጥያቄና ከተጠያቂዋ ምላሽ ዛሬ በሕይወት ያሉ ሕያዋን ምን ልማሩ ይችላሉ? የሚለው ግን ሊያነጋግር ይችላል። ታሪክን መሠረት አድርጎ ለመግባባት የመወያየት አስፈላጊነትና ፋይዳም ይኸው ነው። ታሪክን መሠረት አድርገው ለመለያየት መሥራት እንደሚቻልም በተግባር ለማሳየት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አካላት መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
ያለፈ ታሪካችንን አንስቶ መወያያት በእጅጉ አስፈላጊ በሆነ ጊዜና ዘመን ላይ መገኘታችን እሙን ነው። ታሪካችን በነጭና ጥቁር የተጻፈ ነው። በግራጫው ጥምረት ውስጥ ሐዘንና ደስታ ተቀላቅሎ ነው የሚገኘው። ከግራጫው ታሪካችን፤ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ለጥሩና መልካሙ ዕውቅና እየሰጡ “ስህተቱ እንዲታረም” በብልሐት የሚያመላክቱን አሉ። በተቃራኒው በነጭ ነጠላ ላይ ያገኙትን ጥቁር ነጥብ እያጎሉ፣ አገርና ሕዝብን የሚያስጨንቁም አሉ።

የብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ በአንድ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ያየሁትንም ስዕል ያስታውሰኛል። “የሳይንስ ርዕይ” በሚል ርዕስ በ1980ዎች ለአንባቢያን የቀረበ መጽሐፍ ነው። በስዕሉ የዓለምን ገጽታ የሚያሳይ ሉል፣ በአራት አቅጣጫ በአራት እጆች ተከቧል። ከአራቱ አንዱና በጡንቻ የዳበረው እጅ፣ ቡጢ ጨብጦ ዓለምን ሊነርታት፣ ድራሽ አባቷን ሊያጠፋት ሰንዝሯል። በተቃራኒው ሦስት ሰላማዊ እጆች በዓለም ሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ተዘርግተው ምድር በቡጢኛው ጥቃት እንዳትረበሽ ሲከላከሏት ያሳያል።

ይህን የመጽሐፋ ላይ ሽፋን ባየሁበት 1980ዎቹ፤ በአገራችን ይካሔድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በምን መልኩ ይቋጭ ይሆን የሚለው ስጋት የተጋሩ ይመስሉ የነበሩት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፥ በብሔራዊ ሙዚየም ለሕዝብ ባቀረቧቸው ሦስት ተራኪ የስዕል ሥራዎቻቸው በአንደኛው ወንድማማቾቹ አቤልና ቃየል ሲጋደሉ ያሳያል። ኹለተኛው ስዕል ትንሹ ዳዊት ትልቁን ጎልያድ እንዳሸነፈው ይተርካል። በሦስተኛው ስዕል ወንድማማቾችም ሆኑ ኀያልነት የሚሰማቸው ጡንቸኞች በሚጭሩት ፀብ፣ በሚያስነሱት ጦርነት፣ ዋነኛው ሰለባ እናቶች በመሆናቸው፥ የእናቶችና የምድርን ሐዘንና መከራ ለመቀነስ ሙከራ ይደረግ የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

አሁንም ዓይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ በአደባባይ የሚታየው የአገራችን እውነታ ኀላፊነት የሚሰማቸው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ “የዚህች አገር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? ወዴትስ እያመራን ነው?” የሚያስብል ሆኗል። ዜጎች ከሚያዩትና ከሚሰሙት ተነስተው እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ቢያቀርቡና ሥጋታቸውንም ቢገልጹ ሟርተኛ የሚያስብላቸው አይመስልም። ባይሆን የሥጋቱ ተጋሪዎችን ቁጥር መቀነሻና ተደጋግመው የሚሰሙ አሉታዊ አስተሳሰብና ድርጊቶችን ማቆሚያ ጊዜና ብልሐት አመልካች ናፋቂው ቢበዛ ነው ትክክል የሚሆነው።

እያየንና እየሰማን ባለው፣ ብዙ ሰዎችንም ስለሚያሠጋው ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተለየ አቋም ያላቸው ይመስላሉ። ይህን እንድል ምክንያቴ እኔም ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተወከሉት አንዱ በሆንኩበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 5 ቀን 2011 አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን እንዲጎበኙ ለተጠሩ የጥበብ ሰዎች “አትስጉ ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ በአዲስ አበባ ጉዳይም ምንም ሥጋት አይግባችሁ” ብለዋል። ይህን በልበ ሙሉነት የማበረታቻ ቃል ሲናገሩ መስማቴ አንዱ ምክንያቴ ሲሆን፣ በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ እየሠሩት ያለው የልማት ሥራ፥ በአገርና ሕዝቡ ላይ ተስፋና እምነት ባለው መሪ ካልሆነ በስተቀር የሚሞከር ተግባር አለመሆኑን ማስተዋሌ ሌላኛው ነው።

ጉብኝቱ ሦስት ዓላማዎች ነበሩት። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ባለፉት ወራት ያከናወናቸውና ተግባራዊ ለማድረግ በዕቅድ ስለያዛቸው ጉዳዮች ማብራሪያ ማቅረብ ቀዳሚው ነበር። በቅርቡ ይፋ የተደረገው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ተፋሰስ ልማት በምን መልኩ ሊተገበር እንደታቀደ ገለጻ መስጠት ኹለተኛው ሲሆን፥ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኙ ሕንፃዎች፣ ታሪካዊ ቤቶችንና ግቢውን ለማስዋብና ለቱሪስት ክፍት ማድረግን በተመለከተ ለተያዘው ዕቅድ ባለፉት 10 ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን ማስጎብኘት ሦስተኛው ነበር።

በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን አባት አርበኞች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች… የመሳሰሉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በመጋበዝ የማስጎብኘት ዕቅድ መያዙን ያመለከቱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች፥ “በግቢው ውስጥ ምን እንዳለ፣ ምን እየተሠራበት እንደሆነ ለሕዝብ ለማሳየት፣ በየሳምንቱ ቢያንስ 200 ሰዎችን እየጠራን እናስጎበኛለን የሚል ዕቅድ አለን” ብለዋል።

በ46 ሔክታር ላይ የሚገኘው 4 ኪሎ ቤተ መንግሥት በከ1980ዎቹ አንስቶ ግቢው ውስጥ ገብተው አገሪቱንና ሕዝቧን የመሩ አካላት ሁሉም የየራሳቸውን አሻራ አኑረው ማለፋቸው በተገለጸበት መድረክ፥ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የአስተዳደር ዘመን በግቢው ከተሠሩ ሕንፃዎች አንዱ የሆነውና አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሆኖ እያገለገለ ያለው (የቀድሞው ኢሕዴሪ አዳራሽ) ሕንፃን እና የተወሰኑ ውስጣዊ ክፍሎቹን ለማደስ የተቻለው በተባባሪ አካላት በተገኘ የገንዘብ ዕርዳታ መሆኑም ተገለጸ።

መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ለኅብረተሰቡ ማድረስ ያለመቻል ክፍተት እንዳለባቸው ያልካዱት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት (ሰክሬቴሪያት) ሠራተኞች፣ ይህን ማሻሻል የሚያስችል የቢሮና የአሠራር ዘዴዎችን እያስተካከሉ መሆኑን አመለከቱ። በመቀጠል በቪዲዮ ፊልም በመታገዝ ስለ አዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻዎች አረንጓዴ መናፈሻ ልማት ዕቅድ ማብራሪያ አቀረቡ። ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የእራት ግብዣ መድረክ መዘጋጀቱን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ትብብር የሚያደርጉ አካላት በማፈላለግ ላይ መሆኑንና ፕሮጀክቱን በተለያየ መንገድ ለማገዝ ከወዲሁ ፈቃደኛ ሆነው፣ ቃል የገቡ የተለያዩ አካላት መገኘታቸውም ተነገረ።

“ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት ሲቀበሉ፥ ለመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈል ደሞዝና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ብቻ ሳይሆን ቻይናና ጨምሮ የብዙ አገራት ያልተከፈለ ብድር ጣራ ደርሶ ነበር” የሚለውም ተገልጿል። ለጎብኚዎች የቀረበው ይህ መረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመን ብቻ የታየ አዲስ ክስተት አይደለም። በ1928 ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር፣ በ1933 ዐፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ወደ አገራቸው ሲመለሱ፥ በ1967 ደርግ፣ በ1983 ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸዋል። አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን አልላቀቀው ያለው ይህን አዙሪት ለመቅረፍ አሁን መላ የተዘየደለት ይመስላል። ከግቢው የሚወጣው ሐሳብ አገርና ሕዝብን እንዲለውጥ ቤተ መንግሥቱም መልማት አለበት በሚል አቋም ተያዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ጀምሮ 4 ኪሎ ቤተ መንግሥትን የቱሪስቶች አንዱ መዳረሻ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ገልጸው ነበር። ከመቶ ዓመት በላይ አገሪቷን ያስተዳደሩ መንግሥታት መቀመጫ ሆኖ ያገለገለው “ግቢ” እንዲህ ዓይነት አገልግሎት በመስጠት በአፍሪካ ብቸኛው ቤተ መንግሥት መሆኑንም በአፅንዖት ምስክርነት ሰጥተውለታል። ይህ ግቢ በዋነኛነት ለኢትዮጵያዊያን ክፍት ሆኖ ዜጎች ታሪካቸውን ሊማሩበት ይገባል በማለት፥ ሰኔ 20 ቀን 2010 በርካታ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲጎበኙት ያደረጉትም በዚህ ምክንያት ነበር።

ሲነገር የማይቻል ይመስል የነበረው አራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን አድሶ ለሕዝብ ክፍት የማድረግ ሐሳብ፣ አሁን ዕቅዱ መሬት ወርዶ ብዙ ሥራዎች ወደ ማጠናቀቂያቸው እየተቃረቡ ነው። በዐፄ ምኒልክ እና በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተሠሩ ጥንታዊ ቤቶች እድሳት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ከፊት በር እስከ ግብር አዳራሽ፣ ጎብኚዎች በእግር ጉዞ የሚገቡበት ጠመዝማዘው የእግር መንገድ ሥራውም አልቋል። ለሕፃናት መዝናኛና መጫወቻ እንዲሆን የተከለለው ቦታ ሥራ ተጠናቋል። የእንስሳት ማቆያ ሥፍራ በመገንባት ላይ ሲሆን ግቢው ውስጥ 10 ሺሕ ተመልካቾችን መያዝ የሚችል አምፊ ቴአትር የመገንባት ዕቅድም ተይዟል።

በአገሪቱ የነበረው ቀውስ እየተባባሰ መጥቶ፥ ለመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈል ደሞዝና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ሰዓት ነበር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡት ከመባሉ አንጻር የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ግቢንና ሕንፃዎች ለማደስ የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ያስቻለው የገንዘብ ምንጭ ከየት ተገኘ? ለሚለው፦

“መለመን በምንም መመዘኛ አሳፋሪ ተግባር ቢሆንም፥ ቡቱቶ ለብሰን፣ በዝቅተኝነት መንፈስ በመለመንና አምረን፣ በራስ መተማመን ስሜት ተሞልተን በመለመን መሐል ሰፊ ልዩነት አለ። ለጋሹ ለኹለተኛው አቀራረብ የሚኖረው ስሜት ከመጀመሪያው በተሻለና አወንታዊ ነው የሚሆነው። ቢያንስ ኹለተኛው ሰው እየለመነ ያለው ቸግሮት ነው አይልም። ልግስናውም ለመጀመሪያው ለማኝ ከሚሰጠው በብዙ እጥፍ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። ይህ ዘዴ በአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተግባራዊ እየሆነ ላለው ልማት ገንዘብ የተገኘበት” አዲስ ዘዴ መሆኑን በምላሽነት ቀርቧል።

በጉብኝቱ ማጠቃለያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መሐል፣ ሕዝቡ ለተደቀነበት ወቅታዊ “አገር ትፈርሳለች” ለሚለው ሥጋት ምላሽዎ ምንድነው? የሚል ነበር። “ኢትዮጵያ በአንድ ቀን አልተሠራችም። በአንድ የግርግር ዘመንም አትፈርስም። ዛሬ ከሚታየው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ በዐፄ ኃይለሥላሴ፣ በደርግና ኢሕአዴግ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናት ታይቶ ነበር” ያሉት ዐቢይ በአገሪቷም ሆነ ከዋና ከተማዋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ግርግር ሕዝባዊ መሠረት የሌለውና ጥቂት ግለሰቦች የሚመሩት ነው ብለዋል።

ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛወች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን የመጻሐፍትም ደራሲም ናቸዉ። በኢሜይል አድራሻቸዉ ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here