ሀዋ እደሪስ – እየጨመረ የመጣው የአረብ አገር ተመላሽ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ዝርፊያ ማሳያ

0
888

በህድአት አማረ እና በመሠረት አበጀ

ሥሟ ሀዋ እንድሪስ ሰዒድ ትባላለች። የትውልድ ቦታዋ ከደሴ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ሐይቅ የሚባል ቦታ ነው። ሀዋ ቤተሰቦቿን አታውቅም። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች ሦስት ወር ሆኗታል። ወደ አረብ ሐገር ʻበሕገ ወጥʼ መንገድ ከመሔዷ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ትሠራ ነበር።

ኩዌት ከገባች በኋላ በስምንት ዓመት ቆይታዋ በቤት ሠራተኝነት በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ከሃምሳ እስከ መቶ ሃምሳ ዲናር እየተከፈለኝ ሰርቻለው የምትለው ሃዋ ወደ ስደት ለመሔድ ስታስብ ˝ሰርቼ፣ አልፎልኝ፤ ከእኔ አልፎ ተርፎ ደሃ እረዳለው˝ የሚል ዓላማ እንደነበራት ለአዲስ ማለዳ ትናግራለች።

ሀዋ፣ በኑሮ ፈተና ምክንያት የልጅነት ወዟን ያጣች የ23 ዓመት ወጣት ናት። ጠይም ፊቷ፣ ኑሮ ያጎበጠው ለግላጋ ቁመቷ፣ የጠመጠመችው ሂጃብ፣ የንግግር ዘዬዋ ማንነቷን ይናገራል። ወደ ዝግጅት ክፍላችን ስትመጣ የነበራት ሁኔታ ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ እና አሁን ያለችበትን ሁኔታ ሳትናገር ያሳብቅባታል። ስትናገር እንባ ይቀድማታል።
ከስደት ስትመለስ ፓስፖርቷ ባለመታደሱ ምክንያት በይለፍ ወረቀት ነው አገሯ የገባችው። ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣች በቀጥታ ወደ ትውልድ ቀዬዋ በማቅናት ተከራይታ ኑሮዋን ቀጠለች። በኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ በኩል ፓስፖርቷ ታድሶ ለመውሰድ ወደ አዲስ አበባ መጣች።

አዲስ አበባ መጥታ ፓስፖርቷን በመውሰድ በትውልድ አካባቢዋ በደላላነት ሲሠራ በዓይን ታውቀው ከነበረ፣ በኋላም ኩዌት በድለላ ሲሠራ በሴት ጓደኛዋ በኩል በደንብ የተዋወቀችው ፈድሩ ሰዒድ ካሚሉ የሚባል ግለሰብ ጋር መደዋወል ጀመሩ። እሱ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ኹለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ሐይቅ ሔጄ እንደዋወል ነበር የምትለው ሀዋ፣ አዲስ አበባ ለፓስፖርት ስትመጣ ደውላለት ሽሮሜዳ ይቀጥራትና ይገናኛሉ።

ግለሰቡም ˝እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአረብ አገር ለሚመጡ ቦታ የሚሰጥ ድርጅት ስላለ አራት ፎቶግራፍ፣ የቀበሌ መታወቂያ እና የባንክ የገንዘብ መጠን (ይህ ብሩ ወጥቶ ይቆጠራል)˝ ይላታል። እሷም መሬት ተሰጥቶኝ እሠራበታለው በማለት በጉጉት እሺታዋን በመስጠት ንግድ ባንክ ሽሮ ሜዳ ቅርንጫፍ ያመራሉ።

ያልታደሰ መታወቂያ አንቀበልም ብለው የተቋሙ ሠራተኛ ቢመልሷቸውም፣ ፈድሩ ሰዒድ ካሚሉ ዘዴ በመዘየድ በእስክርቢቶ መታወቂያው ላይ አስተካክሎ ኹለት ቁጥርን በመጨመር 2011 በማድረግ ወደ መርካቶ ንግድ ባንክ ምዕራብ ቅርንጫፍ ይልካትና ከጓደኛው ጋር 500 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር ወጪ እንድታደርግ ያደርጋል።

መኪናውን ያሽከረክር የነበረው ግለሠብ (ጓደኛው) ˝መታወቂያሽን ኮፒ አድርገሽ ነይ˝ በማለት ከመኪናው እንድትወርድ ካደረገ በኋላ ገንዘቡን ይዞ ይሰወራል። ስትመለስ መኪናው 500 ሺሕ ብሩን ይዞ ጠፍቷል። የስምንት ዓመት ልፋቷ በደቂቃዎች ውስጥ ገደል ገባ። ˝ወደ አገሬ ስመለስ አሁን አገሪቷ ሰላም ስለሆነች ምንም ችግር ይገጥመኛል ብዬ አላሰብኩም˝ ትላለች ሀዋ።

የሰው የዓመታት ሐሳቡና ህልሙ እንደጉም በንኖ፣ በአንድ ጀምበር ሲጠፋ ሕይወት ትርጉም አልባ ትሆናለች። በዚህም ሳቢያ ለአዕምሮ እክል፣ ባስ ሲልም ራሳቸውን ከማጥፋት አይቆጠቡም። ይህ የብዙዎች በተለይም ከአረብ አገር ተመላሽ ሴት እህቶቻችን እንግልት ላባቸው ሲመክን የመጨረሻ ውሳኔያቸው ነው። በብዛት በአገር ልጅ ሰበብ በውጭ አገር ሲገናኙ የአገራቸውን ትዝታ ያወጋሉ። በአረብ አገራት ሴት እህቶቻችን ብቸኝነት ስለሚያጠቃቸው አጠገባቸው ያለውን የሚያውቁትን ሰው ይወዳጃሉ።

በዚህም ሳቢያ የጊዜ ጉዳይ ይሆንና አንድ ይሆናሉ፤ ወይ ደግሞ የባለ ታሪኳ ዓይነት ዕጣ ፋንታ ይገጥማቸዋል። በርግጥ ይህ ዓይነቱ ችግር ለአዲስ አበባ አዲሰ አይደለም። ተዘርፈው በመንገድ ላይ የመንግሥት ያለ እያሉ የሚጮሁ ከአረብ አገር የመጡ ሴቶች ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል። ይበልጥ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ነገር ድግሞ ሴቶች ከመዘረፋቸው ባሻገር ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ የሚደርስባቸው እንግልት ነው።

˝በድን ሆኜ ከመርካቶ ጨርቆስ ተገኘሁ፤ የተገኘሁትም የሚያውቁኝ ፖሊሶች በአፋልጉኝ ማስታወቂያ ፎቶዬን ለጥፈው ስለነበር ከአራት ቀናት በኋላ ነበር˝ የምትለው ሀዋ፣ መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውኝ ቃል ሰጥቻለው፤ በወቅቱ አዕምሮዬ ትክክል ስላልነበረ የሠጠሁት ቃል ትክክል አልነበረም። ˝የመኪናውን ታርጋ እያወኩኝ፣ ልጁንም እያወኩኝ አላውቀውም አልኩኝ˝ ትላለች።

ከቀናት በኋላ ትክክለኛ ቃሏን በመስጠት ድርጊቱ በተፈፀመ በ21ኛው ቀን ተከሳሽ ፈድሩ ሰዒድ ካሚሉ ከመኖሪያ ቤቱ ሊያመልጥ ሲል በፖሊስ ርብርብ ተይዞ ከነመኪናው ቢታሰርም፣ ነገር ግን መኪናዋን በኹለተኛው ቀን ለቀዋታል። ተከሳሽ ˝እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም እሷንም አላውቃትም˝ የሚል ቃሉን ቢሰጥም የተጎጂዋ ፎቶ በመኪናው ውስጥ ሊገኝ ችሏል።

የካቲት 20/2011 ወደ ዝግጅት ክፍላችን የመጣችው ሀዋ፣ በዕለት ጠዋት ካደረችበት ጎጃም በረንዳ አስፋልት ላይ ˝ክሴን አንስቻለው ብለሽ ፈርሚ˝ ብለው የማታውቃቸው ሰዎች ቤተል አካባቢ በሚገኝ ጫካ ወስደው ከግንድ ጋር በማሠር ማስፈራራትና ድብደባ እንዳደረሱባት ነግራናለች።

የተረፍኩት በጫካው ውስጥ ፀሎት ያደርግ የነበረ ሰውዬ ጩኸቴን ሰምቶ በመምጣቱ ነው የምትለው ሃዋ፣ እሱ ሲመጣ እኔን አስረውኝ ሮጡ። በአካባቢ የነበሩ የፓርኪንግ ሠራተኞች ቀድመው መጥተው ፈተው ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። ለኤግዚቢትነት ፎቶ አንስተውኛል። ቤተል አካባቢ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የነበረውን ሁኔታ ካስረዳሁኝ በኋላ፣ የቤተል ፖሊስ ጣቢያ ዐቃቤ ሕግ ሴት በመሆኗ ክሱ ወደእሷ እንዲዞር ለመጠየቅ መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ (መርካቶ) ኮማንደሩ ስልክ ባለማንሳቱ ሌሎች የፖሊስ አባላት ስለ ክሱ እኛን አይመለከትም የሚል ምላሽ እንደሰጧት ታስታውሳለች።

የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አድነው አበራ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት እንደ ሀዋ ያሉ ተጎጂዎች ጊዜያዊ ማረፊያ እንድታገኝና በሕግ ዙሪያ ያለውን የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበርን በማነጋገር መፍትሔ ለማምጣት እንሠራለን ብለዋል።

በሌላ በኩል የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሰፋ ይርጋለም፣ ˝ይሄ ጉዳይ እኛን አይመለከትም፤ ከአረብ አገር ሲመለሱ የሚደርስባቸው ጉዳትና በደል ወንጀል በመሆኑ የሚመለከተው አካል እኛ አይደለንም˝ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ፤ ለሥራ ወደ ውጪ አገር ሔደው፣ የሥራ ጊዜያቸውን ጨርሰው፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ደርሶባቸው የሚመለሱ ዜጎች የተለያዩ ማቋቋሚያ ድጋፎች የሚያገኙበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ከውጪ አገር ሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ የሕግ ድጋፍ ለሚፈልጉ ደንበኞች የማስማማት እና የዳኝነት የመሳሰሉ ሙያዊ ድጋፎችን መስጠት ነው ሥራችን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አሰፋ እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ ካለባት የሙያ ወይም የክህሎት ክፍተት አኳያ በጥናትና በሥራ ገቢያ መረጃ ላይ ተመስርቶ የውጪ አገር ዜጎች ሊቀጠሩ የሚችሉበትን የሙያ መስክ በመለየት ቀጣሪዎች ተገቢውን መረጃና ግንዛቤ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅትና ትስስር ለመፍጠር በውጪ አገር ዜጎች የሥራ ፍቃድ አፈፃፀም ላይ ቁጥጥር እና ክትትል የማድረግ ሥራዎችንም እንሠራለን። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚመጡ ማንኛውም ተገልጋዮች አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚየደርጉም ኃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት መላኩ ባዩ በበኩላቸው፣ ˝በአጠቃላይ በአረብ አገራት ዙሪያ እኛ እየሠራን ያለነው ከሳኡዲ ተመላሽ ከሆኑት ሴቶች ጋር ሲሆን፣ ይህም ማለት የእነሱን ግንዛቤ መፍጠር እና ወደመጡበት አካባቢ የመመለስ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራ ነው የምንሰራው፤ ነገር ግን ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር በተየያዘ እየሠራ ያለው ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ነው፤ ይህም ማለት መልሶ የማቋቋሙን ሥራ እና በበላይነት ግብረ ኃይሉን የሚመራው ኤጀንሲው ሲሆን፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሔዱትን ግን የኛ መዋቅር ነው የሚሠራው ብለዋል።

ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ወደዚህ የሚመጡትን ሰዎች ከሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጋር እንዲገናኙ እድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግ ነው የእኛ ሥራ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ˝እኛ የምንሠራው በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካ እንዲሁም በኢኮኖሚ የተለያዩ ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ቅድመ ጥንቃቄ መስጠት እና ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር እንዲገኛኙ እድል እንዲፈጠርላቸው የማስተባበር ሥራ ነው የምንሰራው˝ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ለማጣራት ለማጣራት ይመለከተዋል የተባለውን ሚከታተለው መርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለሚገኙት ኮማንደር በተደጋጋሚ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በወንጀሉ ተጠርጥሮ ተይዞ የነበረው ፈድሩ ሰዒድ፣ በዋስ መለቀቁን ማተሚያ ቤት ከመግባታችን በፊት በደረሰን መረጃ መሰረት ለማወቅ ችለናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here