ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የጥላቻ ንግግርን መግራት

0
1117

“የጥላቻ ንግግር” ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የናዚ ጀርመን እና የሩዋንዳ ዘር ማጥፋቶች ሳይጠቀሱ አይታለፉም። ኹለቱም ‘የጥላቻ ንግግር’ን ወንጀል የሚያደርጉ ሕግጋት አሏቸው። በተለይ ከማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች መከሰት ጋር ተከትሎ የጥላቻ ንግግር በአዲስ መልኩ እንደተጧጧፈ በሥጋት የሚገልጹ ምሁራን ያሉትን ያክል የጥላቻ ንግግርን በሕግ መከልከል ንግግሩን ባያስቆመውም ነጻነትን ግን ያፍናል እያሉ የሚከራከሩም አሉ። በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር በአሥጊ ኹኔታ እያደገ ነው በሚል ብዙኀን ተጨንቀዋል። መንግሥትም ይህን ለመቆጣጠር ሕግ አወጣለሁ ብሏል። በፍቃዱ ኃይሉ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያሉትን ክርክሮችን በመቃኘት ለሐተታ ዘ ማለዳ እንዲሆን አድርጎ አዘጋጅቶታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጥቅምት ወር መጨረሻ 2011 ባወጣው የአንድ ገጽ የኹለት ዓመት ዕቅድ መግለጫ ነበር። መግለጫው በ2011 ይከናወናሉ ካላቸው ዕቅዶች ውስጥ “ግጭትና የዜጎች መፈናቀልን ለመከላከል ‘የፀረ ጥላቻ ንግግር’ የወንጀል ሕግ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ” በግምባር ቀደምትነት ከተዘረዘሩት ውስጥ ይመደባል። ይህ አጭር የዕቅድ መግለጫ ዓረፍተ ነገር በአገር ውስጥ በአሳሳቢ ኹኔታ ለተከሰተው የዜጎች መፈናቀል የጥላቻ ንግግር መንሥኤ ነው ብሎ ከማሰቡም በተጨማሪ፥ እንደመፍትሔ የመሚቆጥረው ‘የፀረ ጥላቻ ንግግር’ ሕግ አውጥቶ መተግበር ነው።

የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግ የሰብኣዊ መብቶች አንዱና “ዋነኛው” መብት የሆነው የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የሚገደብበት አዋጅ እንደመሆኑ ብዙዎች ዜናው ከወጣ ጀምሮ በአንክሮ ሲከታተሉት ከርመዋል። ሌላው ቀርቶ ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተቆርቋሪ ‘ሂዩማን ራይትስ ዋች’ በዲሴምበር 3 ባወጣው መግለጫው ‘ንግግርን ወንጀል ማድረግ ችግሩን አይፈታም’ በማለት ከዚህ በፊት መንግሥት የንግግርን ነጻነት ሲገድብ መኖሩን በማስታወስ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።

ለመሆኑ የጥላቻ ንግግር ምንድን ነው? የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ገደብ አልፏል የምንለው መቼ ነው? የጥላቻ ንግግርን ለመግራት ምን ይደረግ? በሰበቡ መንግሥት መጠቀሚያ እንዳያደርገውስ ምን ማድረግ ይቻላል? ለመሆኑ በሕግ ከመከልከል የተሻለ የመፍትሔ አማራጭስ አለ?
ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ለምን?

ሁሉም የሰብኣዊ መብቶች ተነጣጥለው የማይታዩ፣ ዓለማቀፋዊ፣ ሊገፈፉ የማይችሉ፣ ያለ ፍረጃ መከበር ያለባቸው እና አንዱ በሌላው ላይ የተመረኮዙ ናቸው። እንደምሳሌም የእኩልነት መብት እና ሐሳብን የመግለጽ መብት ኹለቱም ሳይበላለጡ መከበር ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን በተለየ ትኩረት ሲመለከቱት ይታያል። ይህም የሆነበት ምክንያት የንግግር ነጻነት ለሌሎች መብቶች መከበር መሟገቻ መሣሪያም ስለሆነ ጭምር ነው።

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አራት ዐቢይ ዒላማዎች አሉት። አንደኛ፣ ግለሰቦች ምሉዕነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ ኹለተኛ፣ እውነቱን ለመለየት ከማስቻሉም ባሻገር ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ተሳትፎ ማድረግ ያስችላል፤ ሦስተኛ፣ ግለሰቦች በውሳኔ ሰጭነት ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉበትን አቅም ያጎናፅፋቸዋል፤ እንዲሁም አራተኛ፣ መረጋጋት ሳይታጣ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን መንገድ ያመቻቻል። ስለሆነም የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት በራሱ ሰዎች እንዲናገሩ ካልተፈቀደላቸው በኀይል ለማድረግ የሚሞክሩትን ነገር በመነጋገር እና ሰላም ሳያናጉ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን መንገድ ያመቻቻል። ስለዚህ የነጻነቱ መከበር ለአንድ አገር ሰላም እና ደኅንነት በጣም አስፈላጊ ነው።

እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው
መብቶች የመንግሥታት ችሮታ አይደሉም፤ በሕገ መንግሥታት ጥበቃ የሚደረግላቸው ተፈጥሯዊ ፀጋዎች እንጂ። ይሁንና ሁሉም መብቶች የሌሎችን መብት የሚጥሱ ሲኾን፣ የወል ደኅንነትን ለማስከበር ወይም ለሌላ ዓላማ ሲባል የሚገደቡባቸው ኹኔታዎች አሉ። የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎችም ይሁኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መብቶቹ ስለሚገደቡባቸው ኹኔታዎች ያስቀመጧቸው መሥፈርቶች አሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 2 ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት “በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት፣ በቃልም ይሁን በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ እና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል” ይላል። በንዑስ አንቀፅ 6 ደግሞ “እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሐሳብ እና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት” ሊሆን አይገባውም ይላል፤ ይልቁንም ሊገደቡ የሚገባበትን መርሕ ሲያስቀምጥ እንዲህ ይላል፦ “የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ሥም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦችን በነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ። የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብኣዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናሉ።” በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከዚህ ውጪም መብቶች የሚገደቡባቸው ድንጋጌዎች አሉ፤ ዋነኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው።

መብቶች የሚገደቡባቸው ኹኔታዎች
መብቶች የሚገደቡባቸው ኹኔታዎች ሁሌም አወዛጋቢ ናቸው። በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ኹኔታዎቹን በመለጠጥ የዜጎችን ሰብኣዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች በማፈን መጥፎ ታሪክ አለው። በዚህም የተነሳ እንደ “ፀረ ጥላቻ ንግግር” ያሉ ሕጎችን አወጣለሁ ሲል በጥርጣሬ የሚመለከቱት በርካቶች ናቸው። ይህንን ሥጋት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች ሁሉ ይሥማሙበታል። ሕግን ለጥጦ የመንግሥት ሥልጣን ለተቆጣጠረው አስፈፃሚ አካል ጥቅም ማዋል የታሪክ አካል በኾነበት፣ በመንግሥት የተለያዩ ቅርንጫፎች ቁጥጥር እና ሚዛን በሌለበት እንዲሁም የፍትሕ አካላቱ ነጻ እና ገለልተኛ መሆናቸውን ባላረጋገጡበት ኹኔታ “ፀረ ጥላቻ ንግግር” አዋጅ አውጥቶ ለመተግበር መሞከር የንግግርን ነጻነት ከመንፈጉም ባሻገር፣ የዜጎችን እምነት ስለሚያጎድል የፍርሐት ድባብ ይፈጥራል የሚል ሥጋት አላቸው።

ይህንን ሥጋት ያነሳንላቸው የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) “መንግሥት የዜጎችን ነጻነት ለማፈን የፀረ ጥላቻን ንግግርን ይመርጠዋል የሚል መከራከሪያ አያሳምነኝም” ይላሉ፤ ምክንያታቸውም ደግሞ “በፀረ ጥላቻ አዋጅ ሊወሰድ የሚችለው ሕጋዊ እርምጃ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል ትልቅ ቅጣት አይደለም” የሚለው ነው። የኾነ ኾኖ አዋጁ የሚወጣ ከሆነ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን አላግባብ እንዳይገድብ በጥንቃቄ እንደሚደረግ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አገዳደብ
ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ላይ ገደብ ማስቀመጥ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም በርካታ ምሁራንን አስማሚ ሆኖ የተገኘው ባለ ሦስት እርከን ፍተሻ (three-part test) የሚባለው መሥፈርት ነው። ይኸውም የንግግር መብት የሚገደበው አንደኛ በሕግ በተቀመጠ አግባብ ብቻ ሲሆን፥ ኹለተኛ መብቱን ለመገደብ አሳማኝ/ቅቡልነት ያለው ግብ ሲኖር እንዲሁም ሦስተኛ ለዚያ ቅቡልነት ላለው ግብ ንግግሩን መገደብ የግድ አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘ እና ሦስቱም እርከኖች ተፈትሸው ከተሟሉ መሆን አለበት። ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮንም ይህ ሊወጣ ለታሰበው የሕግ ገደብ መሥፈርት እንደሚሆን ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ “ዳኞችን ሕጉን በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንዲተረጉሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት በእኛ በኩል የሚታሰብ ነገር ነው” ብለዋል።

የጥላቻ ንግግር ምንድን ነው?
የጥላቻ ንግግርን ለመገደብ ፈታኝ ኹኔታ ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ ሁሉንም አሥማሚ ብያኔ አለመኖሩ ነው። ለአንድ ሰው የጥላቻ ንግግር የሆነው ለሌላ ሰው ላይሆን ይችላል። ብዙዎች በሚተረጉሙበት ግርድፍ ብያኔ ስንመለከተው የጥላቻ ንግግር ማለት “የግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ዘር፣ ሃይማኖት፣ የዘውግ ምንጭ፣ ብሔር፣ ፆታ፣ አካላዊ ጉዳት፣ የወሲብ ምርጫ፣ ወይም ስርዓተ ፆታዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ ኾኖ፥ በግለሰቦቹ ወይም ቡድኖቹ ላይ የአካላዊ ጥቃት፣ የመገለል ወይም ሌላ ተፅዕኖ የሚያሳድር የንግግር፣ የጽሑፍ፣ የምልክት ወይም መሠል ጥቃት ነው።”

“መቻቻል” በሚል ርዕስ በኦክስፎርድ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ ከምርጫ 2007 በፊት የነበረውን ተፅዕኖ እና የንግግሮቹን ይዘት ለመገምገም የተሠራ ጥናት አለ። ጥናቱ 13 ሺሕ የተመረጡ የፌስቡክ ጽሑፎችን በመመልከት የተሠራ ጥናት ሲሆን የጥላቻ ንግግር፣ አደገኛ ንግግር (‘ዴንጀረስ ስፒች’) እና አብሻቂ ንግግር (‘ኦፌንሲቭ ስፒች) ሊባሉ የሚችሉ ጽሑፎችን ለመለየት ያስቀመጠው ስሌት (‘ኢኩዌሽን’) ነበር። ስሌቱ አንድን መልዕክት የጥላቻ ንግግር ነው ወይስ አይደለም ብሎ ለመመርመር ሁነኛ ዘዴ ነው። በስሌቱ መሠረት፥ አንድ ንግግር የጥላቻ የሚባለው “መጀመሪያ ዘውግ፣ ሃይማኖት ወይም ስርዓተ ፆታን መሠረት ያደረገ ከሆነ ነው፤ ቀጥሎም አስነዋሪ ሥያሜዎችን ከተጠቀመ፣ ወይም የአመፃዊ ጥቃት ማስፈራሪያ ከያዘ፣ ወይም ለተግባራዊ እርምጃ ግልጽ ጥሪ ካደረገ፣ ወይም ሐሜት/አሉባልታ የሚያሰራጭ ከሆነ፤ እና በመጨረሻም ንግግሩ ተደራሲዎቹ ዒላማዎቹን እንዲሳደቡ፣ ወይም ክብራቸውን እንዲያዋርዱ፣ ወይም እንዲያገልሉ የሚያበረታታ ከሆነ (ሦስቱንም መገምገሚያዎች ካለፈ) “የጥላቻ ንግግር” ሊባል ይችላል።

ንጉሥ ሰለሞን የኑቢያ ኮሙኒኬሽን የጋራ መሥራች እና ኀላፊ ናቸው። በጥላቻ ንግግር ላይ ተከታታይ ‘ወርክሾፖችን’ አዘጋጅተዋል። እንደ እርሳቸው የጥላቻ ንግግሮች ከአደገኛ እና አብሻቂ ንግግሮች የሚለዩት በውጤታቸው ነው፤ “የጥላቻ ንግግሮች በባሕሪያቸው የጥቃት ድርጊት ጋባዦች ወይም ቆስቋሾች ናቸው።”

የጥላቻ ንግግር አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል?
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር ደረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷልም፣ አልደረሰምም የሚሉ ሰዎች አሉ። አዲስ ማለዳ ለማኅበራዊ ድረገጿ ተከታዮች “በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ ‘የጥላቻ ንግግር’ ሕጋዊ ክልከላ ሊደረግበት የሚገባው ደረጃ ደርሷል ብለው ያስባሉ?” በሚል ላቀረበችው ጥያቄ ከ1812 መልስ ሰጪዎች መካከል፥ 92 በመቶዎቹ “አዎን፣ በሕግ መከልከል አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ንጉሥ ሰለሞንም በዚህ ይሥማማሉ። “መቶ ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ፥ 10 በመቶዎቹ ፌስቡክ ተጠቃሚ ቢሆኑ እንኳን፣ ጠንካራ መደበኛ ሚዲያ እና ‘የሚዲያ ሊትሬሲ’ (አረዳድ) በቂ ዕውቀት በተደራሲዎቹ ዘንድ ባለመኖሩ ፌስቡክ ላይ አንድ የተሳሳተም ይሁን የጥላቻ መረጃ ያነበበ ሰው በመኖሪያ አካባቢው ወይም ገበያ ውስጥ ቢያወራው መልዕክቱ በስማ በለው ይሰራጫል፤ ሰዉ ደግሞ ያምናል” በማለት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ መልዕክቶች መሬት ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ ይተነትናሉ።
መንግሥትም “ግጭትን እና መፈናቀልን ለመከላከል የፀረ ጥላቻ ሕግ ያስፈልጋል” ሲል፥ የጥላቻ ንግግሮች በተግባር የግጭት እና መፈናቀል መንሥኤ መሆኑን እንዳመነ ያመላክታል። ብርሃን ታዬ አክሰስናው የተባለ ዓለም ዐቀፍ የበይነመረብ ነጻነት ተሟጋች ድርጅት ሠራተኛ ናቸው። በዓለማችን የበይነመረብ ነጻነት እንዲከበር የሚደረገው #KeepItOn ዘመቻ መሪ ናቸው። እንደ እርሳቸው “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮች መሬት ላይ ላሉ ግጭቶች እና መፈናቀሎች ቀጥተኛ መንሥኤ መሆኑን በእርግጠኝነት ለመናገር ጥናት ማድረግ ያሻል” ይላሉ። ንጉሥ “አሁንም ማስተካከል የሚቻልበት ደረጃ ላይ ቢሆንም፥ የጥላቻ ንግግር ደረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በአሳሳቢ ደረጃ እያደገ ነው” ብለዋል።

የአክሰስናው ባለሙያዋ ብርሃን በበኩላቸው “በጉጂ እና በጌዲኦ መካከል ላለው ግጭት እና መፈናቀል የማኅበራዊ ሚዲያ መንሥኤነት እምብዛም አይታየኝም” ይላሉ። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ እናነባቸው የነበሩ አንዳንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጸሐፊዎች አሁን በመደበኛው ብዙኀን መገናኛም ጽሑፎቻቸውን እያተሙ እና ፕሮግራማቸውን እያቀረቡ መሆኑንም ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ “አሁን ባለው ኹኔታ ማኅበራዊ ሚዲያ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ውጥረት እያራገበ ነው” ማለታቸውም አልቀረም።

“መቻቻል” በሚል ርዕስ ከ2007 ምርጫ በፊት የተደረገው ጥናት በኹለት ዓመት ውስጥ ካጠኗቸው 13 ሺሕ የፌስቡክ ጽሑፎች ውስጥ “የጥላቻ ንግግር” ሊባሉ የሚችሉት 0.4 በመቶዎቹን (52ቱን) ብቻ ነው። ከዚያ ይልቅ 0.3 በመቶ የሚሆኑት “አደገኛ ንግግር” (አንድ ቡድን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲደረግ አስተዋፅዖ ሊያደርግ የሚችል ንግግር) ውስጥ ይመደባሉ። ነገር ግን ይህ ጥናት የተደረገው ከምርጫ 2007 በፊት በመሆኑ ከዚያ በኋላ ለዓመታት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ የተፈጠረውን እውነታ እና የማኅበራዊ ሚድያ ተፅዕኖ አያሳይም።

የዩሮ-አሜሪካ ሙግት
የአውሮፓ ኅብረት የጥላቻ ንግግርን ወንጀል አድርጎታል፤ የአሜሪካ ሕግ ግን ወንጀል አላደረገውም። በአንድ በኩል የአውሮፓ ኅብረትን እንደምሣሌ ቆጥረው ኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ ያስፈልጋታል የሚሉ እና በተቃራኒው ደግሞ አሜሪካን ጠቅሰው አያስፈልጋትም የሚሉ አሉ። እነዚሁኑ ኹለት ምሣሌዎች በተቃራኒው ጠቅሰው የአውሮፓ ኅብረት ያለው የሕግ የበላይነት ስርዓት በሌላት ኢትዮጵያ “የፀረ ጥላቻ ንግግር” አዋጅ ማውጣት መንግሥት አላግባብ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ማፈኛ መሣሪያ እንዲያደርገው ነጻ ፈቃድ መስጠት ነው የሚሉት በአንድ ወገን እና አሜሪካ የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ልቅ ማድረጓ በብዙ ሲቪል ማኅበራት እና ኃላፊነት በሚሰማቸው እና ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ብዙኃን መገናኛዎች ያሏት አገር ስለሆነች ነው በሚል ኢትዮጵያ ሕጉ እንደሚያስፈልጓት የሚከራከሩ ብዙ ናቸው።

ውብሸት ታደለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ናቸው። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ‘አቢሲኒያሎው’ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት መጣጥፍ ላይ የኢትዮጵያንም ሕገ መንግሥት ስናጤነው “የዜጎችን ነጻነት ሳይሆን፥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖርን የመረጠ ስለሆነ፥ ነጻ ንግግር ወይንም ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ለእነዚህ ዕሴቶች ተገዥ መሆኗ ግድ ነው፡፡ የአውሮፓውያኑም መንገድ ይኼው ነው” ይላሉ። ሆኖም አውሮፓውያን የናዚ ጭፍጨፋ ያስከተለው ድንጋጤ አስገድዷቸው የጥላቻ ንግግርን በወንጀላቸው ቢያስቀምጡም አሁን አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆኑን ያመለክታሉ። ዛሬ ዛሬ “አውሮፓውያን አሜሪካውያንን የፀረ ጥላቻ ሕግ እንዲያወጡ መምከራቸው ቀርቶ፥ አሜሪካውያን አውሮፓውያንን የፀረ ጥላቻ ሕጋችሁን ሰርዙ እያሉ መምከር ጀምረዋል” በማለት ሮበርት ካን “Why Do Europeans Ban Hate Speech?” በሚል ርዕስ በጻፉት ጥናታዊ መጣጥፍ ገልጸዋል። ምክንያቱ ደግሞ የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕጎች የንግግርን ነጻነት የሚገድቡትን ያክል የጥላቻ ንግግርን መቆጣጠር አልቻሉም የሚል ነው።

ጌዲዮን በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ጥላቻ ሕጉን በተመለከተ ጥናት ተሠርቶ መጠናቀቁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጥናቱ ውጤት የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ ሕግ ይውጣ የሚለው በአመዛኙ ድጋፍ ቢያገኝም፥ አማራጭ መንገዶችንም እየፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል። እርሳቸው እንደሚሉት “ያለን ሌላ አማራጭ በሌላ ‘ሬሌቫንት’ (ተሥማሚ) ሕግ ውስጥ አንቀፆችን በማካተት የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር መሞከር ነው” ብለዋል። ሌሎች ተሥማሚ ሕግጋት የሚሏቸው በክለሳ ላይ ያሉ የብዙኃን መገናኛዎች እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ የሚባለውን ይጨምራል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ድንጋጌዎች እንዳሉት የሚናገሩ አሉ። የሥም ማጥፋት፣ የአመፅ ማነሳሳትን የሚከለክሉት ሕግጋት ከዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ። ሆኖም፣ ጌዲዮን በዚህ አይሥማሙም። “የጥላቻ ንግግር ከሥም ማጥፋትም፣ ከአመፅ ማነሳሳትም የተለየ በመሆኑ በነዚህ ድንጋጌዎች ቁጥጥር ሊደረግበት አይችልም።”

ሌላ ምን አማራጭ አለ?
ንጉሥ “ኢትዮጵያ እንደአገር ጥላቻ የሚዘራባቸውን ፌስቡክና ሌሎችንም ማኅበራዊ መድረኮች መቆጣጠር አቅሟ ምን ያህል ነው?” የሚለው ያሳስባቸዋል። “ሕግ በጥቅሉ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፤ ግን የኢትዮጵያን የማስፈፀም አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት” ባይ ናቸው። “የንግግርን ነጻነት አፋኝ ያልሆነ ሕግ ማውጣት በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የነጻነት አፈናን ከዚህ በኋላ አይቀበሉም። ስለዚህ ከሕግ ይልቅ ‘ሚዲያ ሊትሬሲ’ [የመገናኛ ብዙኃን ተደራሲዎች የአረዳድ ግንዛቤያቸውን መጨመር] ላይ የበለጠ ‘ኢንቨስት’ ብናደርግ ወጪ የሚቀንስ እና የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለን” ብለዋል። የብዙኃን መገናኛዎች አረዳድ ዕውቀቱ (‘ሚዲያ ሊትሬሲ’) ያላቸው ተደራሲዎች የሚሰሙትን/የሚያነቡትን የብዙኀን መገናኛዎች ውጤት በሒሳዊ መንገድ ተመልክተው የሚበጃቸውን የመምረጥ ክኅሎቱ ያላቸው ተደራሲዎች ናቸው።
የጥላቻ ንግግርን ወንጀል ያላደረጉት አገራት መከራከሪያ፥ ውብሸት (በጠቀስነው የ‘አቢሲኒያሎው’ መጣጥፋቸው) እንደሚሉት “ንግግርን ወንጀል በማድረግ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ፣ ጥላቻ ባለው ንግግር የሚፈጠረውን ጉዳት መታገስ የሚያስገኘው ጥቅም ይበልጣል” የሚለውን ነው።

ብርሃን ታዬ ከሁሉም በላይ ችግሩን በቅጡ መረዳት እንደሚቀድም ያሳስባሉ። ባለሙያዋ እንደሚሉት “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ችግር ምንድን ነው? ሕጉ የሚፈታውስ የትኛውን ችግር ነው? እንዴት?” የሚለው መጠናት አለበት። “ባለን ልምድ እኛ አገር በሕግ ሥም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚነካ ሕግ ሲወጣ ነው የምናውቀው። ጋዜጣ ላይ አንድ ሰው የሐሰት ጽሑፍ ቢጽፍ፣ ወይም የጥላቻ ንግግር ቢያትም ስለሚታወቅ፥ በቀላሉ ተጠያቂ ይሆናል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ግን እንዴት ነው ተናጋሪው የሚታወቀው? ሕጉ ስላለ ብቻ ችግሩ ይቀረፋል የሚለው አሳማኝ አይደለም።”

ብርሃን እንደ መፍትሔ የሚጠቁሙት ችግሩን አጥንቶ አማራጭ መፍትሔዎችን መፈለግ እና ሰዎችን ማስተማርን ነው። ማኅበረሰባችንን ከሥነ ኅብረተሰብ፣ ከሥነ ባሕል እና ሌሎችም መስኮች አንፃር በማጥናት ለምን እንዲህ ያለ ንግግር መረጠ የሚለውን ለመረዳት መሞከር እና ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ያዋጣል ብለዋል።

ንጉሥ ተደራሲውን ስለ ብዙኀን መገናኛዎች አረዳድ ከማስተማር በተጨማሪ፥ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ የጥላቻ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ከሕግ ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የማስተባበል፣ የማሳጣት ወይም ሌላ የተሻለ ውጤታማ ሊሆን የሚችል መፍትሔ መፈለግም ሊታሰብበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here