ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከጥላቻ ንግግር መታደግ

0
504

[ይህ ጽሑፍ ‘ኦፕንዴሞክራሲ’ ላይ በቼሪያን ጆርጅ ተጽፎ ለዚህ ዐምድ እንዲሥማማ ተቀነጫጭቦ የተተረጎመ ነው።]

ሕዝባዊ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው የመቻቻል እና እርስበርስ መከባበር ዕሴት ሲኖር ነው። ነገር ግን አንዳንድ ቡድኖች አንድ አገር በየት አቅጣጫ ትሒድ የሚለው ላይ ለብቻቸው ለመወሰን ይስገበገባሉ። የነዚህ ቡድኖች የጥላቻ ንግግር እንደ ማይናማር ያሉ ጅምር ዴሞክራሲዎች የሮሂንግያ አናሳ ቡድኖችን ለዘር ጭፍጨፋ አጋልጧል፤ ረዥም የዴሞክራሲ ልምድ ያላትን አሜሪካ ደግሞ እንደ ትራምፕ ያሉ መሪ በማምጣት የዴሞክራሲ ባሕሏን በክሎባታል።

በዚህ ኹኔታ የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሳይጎዱ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የእኩልነት መብታቸውን እና ደኅንነታቸውን ሊነፍጉ ከሚፈልጉ የጥላቻ ቡድኖች መጠበቅ ያስፈልጋል። ኹለት በቦታ የተራራቁ ምሣሌዎችን እንውሰድ። እ.አ.አ. በ2009 ቴኔሲ (አሜሪካ) ውስጥ መስኪድ ሊሠሩ የፈለጉ ሙስሊሞች በፅንፈኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፤ በዚያው ዓመት ቦጎር (ኢንዶኔዥያ) ውስጥ በአዲስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያመልኩ የፈለጉ ክርስቲያኖች በፅንፈኛ ሙስሊሞች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። የአሜሪካዎቹ ሙስሊሞች ሼሪያን አሜሪካ ላይ በመጫን ፍላጎት ሲወቀሱ፥ የኢንዶኔዥያዎቹ ክርስቲያኖች ኢንዶኔዥያን ክርስቲያናዊ ለማድረግ በሚል ተወቅሰዋል።
ይህን ተከትሎ ይለቀቁ የነበሩት የተሳሳቱ መረጃዎች የእነዚህን ንፁህ ቡድኖች የማምለክ ቅን ፍላጎት ለማስተጓጎል በሚችል ደረጃ ነጻ የሐሳብ ገበያውን ተጠቅሞ ፍረጃ እንዲጎለብት መንሥኤ ሆነዋል።

የመጀመሪያው ነጥብ፣ ተጋላጭ አናሳ ቡድኖች ከጥላቻ ንግግር እና በተለይም ለመገለል እና ጥቃት ከሚያጋልጣቸው ኹኔታ መጠበቅ አለባቸው። የጥላቻ ንግግር በሐሳብ ገበያ ውስጥ ውድቀት ያስከትላል። በተለይ ዒላማ የኾኑት አናሳ ቡድኖች የጥላቻ ንግግር ከሚነዙባቸው ቡድኖች እኩል መወዳደር የሚያስችል ባሕላዊም ይሁን ታሪካዊ አቅም ስለሌላቸው በሐሳብ ገበያው መወዳደር አይችሉም። ስለዚህ ለጥበቃ ሲባል በሕግ መከልከል ሊያስፈልግ ይችላል።

ኹለተኛው ነጥብ፣ አናሳ ቡድኖችን ከጥቃት ለመጠበቅ ሕጋዊ ክልከላ ቢደረግም እስከ ማበሳጨት የሚደርስ ሐሳብ መፈቀድ አለበት። ያለዚያ ነጻነት ሊባል አይችልም። ይህ ‘ሊበራል’ የነጻ ንግግር መርሕ በሃይማኖት ላይ ለመቀለድ የተሰጠ አድርገው የሚወስዱት አሉ፤ ስህተት ነው። ለምሳሌ ያክል በአሜሪካ በሐሳብ ሃይማኖተኞችን ሊያበሳጭ የሚችል ንግግር ቢፈቀደም፥ የእምነት እኩልነታቸው ግን በፍርድ ቤት ተረጋግጦላቸዋል። በኢንዶኔዥያ ፍርድ ቤቱ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሠራ ቢያዝም፥ መንግሥት ግን ተግባራዊነቱን አላስቻለም። ኢንዶኔዥያ በሃይማኖት መቀለድን ወንጀል በማድረጓ ያተረፈችው ፅንፈኝነት እና የሃይማኖት እኩልነትን ማረጋገጥ አለመቻል ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here