ያለፉት 3 የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አልነበሩም ሲል ማኅበሩ ወቀሰ

0
722

ያለፉት ሦስት የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አልነበሩም ሲል የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ባወጣው ሪፖርት ወቀሰ። አቤቱታውን እንደሚቀበል የገለፀው ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በማኅበሩ በኩል ቁጥሮችን ከፍ አድርጎ የማቅረብ አባዜ መኖሩን ግን አውቃለሁ ብሏል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ቆጠራዎች የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ዝቅ ብሎ መቅረቡን የሚገልጸው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር፣ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር በ1976 ቆጠራ 3 ነጥብ 6 በመቶ፣ በ1987 ደግሞ 2 ነጥብ 95 በመቶ እንዲሁም በ1999ኙ ሦስተኛ ከ1 ነጥብ አንድ በመቶ እንደማይዘል ማስቀመጡን በመጥቀስ ቅሬታ እንዳለበት አሳውቋል።

የማኅበሩን ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ ያስረዱት የማኅበሩ ሊቀ መንበር አባይነህ ታመነ፣ ይህም የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ድርሻ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዙር ባሉት የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች እየቀነሰ መሔዱን ከማመልከቱም በላይ ከዓለም ዐቀፉ ሪፖርት አንጻር ሲመዘንም የተጋነነ ልዩነት ያለበት ነው ብለዋል።

በሕዝብና ቤት ቆጠራዎቹ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየቀነሰ የሔደ ቢሆንም፣ ሌሎች ጥናቶች ግን ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል የሚለው የማኅበሩ ሪፖርት፣ በአውሮፓዊያኑ 2006 በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዓይነ ስውርነት እና ትራኮማ ላይ የተደረገው ብሔራዊ የዳሰሳ ጥናት የዓይነ ስውራን ቁጥር አንድ ሚሊዮን 200 ሺሕ 456 መሆኑን እንደሚያመለክት ለአብነት በሚል ይጠቅሳል። ዝቅተኛ ዕይታ ያላቸው ደግሞ ኹለት ሚሊዮን 776 ሺሕ 56 መሆናቸውን ያመለክታል።

የዓይነ ስውራኑን አኃዝ ብቻ የሚመለከተው ቁጥር ደግሞ በሦስተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ አሉ ከተባሉ አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በእጅጉ የላቀ እንደሆነ በመጥቀስ ነው ማኅበሩ የሚወቅሰው።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳፊ ገመዲ፣ በ1999ኙ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት የሚቀርቡትን ቅሬታዎች እንደሚጋሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ በቁጥሩ ላይ ግነት መኖሩንና አኃዞችን እያጋነኑ የመናገር አባዜዎች በማኅበሩ በኩል መኖራቸውን ጠቁመዋል።

˝በኢትዮጵያ ያለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር 17 ሚሊዮን ነው ሲባል መነሻው ምን እንደሆነ አይገባኝም˝ የሚሉት ሳፊ፣ ማንኛውም ነገር ሪፖርት ሲደረግ ጥናት እንደሚያስፈልገውና ያለጥናት የሚወጡ ሪፖርቶች መሰረት የሌላቸው እንደሆኑ ያስገነዝባሉ።

ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ባንክ መረጃ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ 15 በመቶ የሚሆነው አካል ጉዳተኛ እንደሆነ ይገልጻል። ይሔው መረጃ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ 17 ነጥብ ስድስት በመቶ አካል ጉዳተኛ እንደሆነም ያሳያል። በዚህ መሰረት 107 ሚሊዮን ከሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 18 ሚሊዮኑ የተለያዩ ዓይነት የአካል ጉዳቶች ያሉበት ነው እንደማለት ነው።

በመጀመሪያ ኅብረተሰቡ ባለው የተዛባ አመለካከት አካል ጉዳት ያለበትን የቤተሰብ አባል በተገቢው ያለማስቆጠር ክፍተት እንዳለ የነገሩን ሰፊ፣ አካል ጉዳተኞች እራሳቸውም ለመቆጠር ፍላጐት አለማሳየት፣ ለቆጣሪዎች ስለአካል ጉዳት ጽንሰ ሐሳብ በቂ ግንዛቤ አለመስጠት፣ በቅድመ ቆጠራ ወቅት ኅብረተሰቡን በሚገባ ተደራሽ ያደረገ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመሰራት፣ ለቆጠራው የተዘጋጀው መጠይቅ የተሟላ መረጃ ስለ አካል ጉዳተኝነት በመያዝ ረገድ ክፍተት ያለበት መሆኑና ሌሎችም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ነግረውናል።

የዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት በአንቀጽ 31(1) ሥር መንግሥታት ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ፣ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽና ተግባራዊ ለማድረግ የስታትስቲካዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here