108ኛው ፓርቲ ነገ የመሥራች ጉባኤውን ያካሒዳል

0
700
  • 109ኛውም በምሥረታ ሒደት ላይ ይገኛል

በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደረጃጀት 108ኛ ፓርቲ ሆኖ ብቅ ያለው ‘ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ’ (ነእፓ) የመሥራች ጉባኤውን ለማካሔድ ነገ እሁድ፣ መጋቢት 15 በካፒታል ሆቴል ስብሰባ የጠራ ሲሆን ፓርቲውን በይፋ እንደሚመሰረት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ ፓርቲው የኢትዮጵያን ነባራዊና ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቆች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አሕጉራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመዘን፣ የአገሪቱን መልከዓ ምድራዊ ፖለቲካና ስትራቴጂያዊ መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም ሥጋቶች በመተንተን ፕሮግራሞቹንና ፖሊሲዎቹን አሰናድቷል ብለዋል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ “ኢትዮጵያ ያሉባት ውስብስብ ችግሮች እንዲወገዱ በጠንካራ አገራዊና የሕዝብ ፍቅር ተሞልቶ፣ በጥናትና በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞችን ቀርጾ የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የተቋቋመ” የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን የፓርቲው ፕሮግራም መግቢያ ያትታል።

ፓርቲው “በአገሪቱ የሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች እንዲተገበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የፖለቲካ ሥልጣን ከሕዝብ የሚመነጭበት የፖለቲካ ባሕል እንዲሰርጽ፣ ዜጎች ሐሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ መብታቸው እንዲከበር፣ የሚዲያና የሲቪል ማኅበራት በአገር ግንባታ ውስጥ ሰፊ ሚና እንዲኖራቸው ይታገላል” ሲሉም አብዱልቃድር ተናግረዋል።

በአንድ በኩል የግዛት አንድነቷ የተከበረ ጠንካራ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሀብት ማኅበረሰብ እንዲገነባ በሌላ በኩል የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የባሕል ልዩነቶች እንዲከበሩ እንደሚሰራም የፓርቲው ፕሮግራም ያስረዳል።

“በመግባባት ላይ የተመሰረተ ከፍጥጫ፣ ከሴራና መጠላለፍ የራቀ የፖለቲካ ትግል አካሒዳለሁ” ያለው ፓርቲው፣ አገሪቱንና እና ሕዝቡን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ ማንኛውምን ዓይነት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ካለው የፖለቲካ ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ከወዲሁ አቋም መያዙን ዘርዝሯል።

በተያያዘ ዜና፣ 109ኛው ፓርቲ በይፋ ሊመሰረት ዝግጅቱን እያደረገ ነው። የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ “አሁን በአገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ ስላሳሰበኝ አማራጭ ሆኜ መጥቻለሁ” ሲል ለአዲስ ማለዳ አሳቀውቋል።

“የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና የፖለቲካ ቡድኖች የፈጠሩት ፍጥጫ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማወቅ አይቻልም” የሚሉት የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ የአደራጆች አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢው መሐመድ አሊ መሐመድ፣ “በዚህ ሁኔታ አማካይ ቦታ ያለው ሁሉን ዐቀፍና በአንጻራዊነት ሁሉም ወገን የኔ ነው ሊለው የሚችል አንድ የተደራጀ ኃይል መኖር አለበት ብለን ስላመንን ከአንድ ዓመት በላይ ተከታታይ ውይይቶች ተደርገው አገራዊ መፍትሔ ያመጣል” በሚል ፓርቲው በመመስረት ላይ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

በዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት የተጀመረው የለውጥ ሒደት ብዙ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑን የሚናገሩት መሐመድ፣ “ሁሉንም ነገር ጠቅለን የለውጥ አመራሩ ላይ ጥለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አደጋ አለው” ሲሉም አክለዋል።

“በቁጥር ብዙ ፓርቲዎች አሉ ቢባልም እንደ አማራጭ ግን ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት ያለው፣ ግልጽ የሆነ አጀንዳና ስትራቴጂ ያላቸውን ፓርቲዎች ብዙ መዘርዘርና መቁጠር ባለመቻሉ አማራጭ ኃይል ሆነን መጥተናል” ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።

ከቀናት በፊት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት የተዘጋጀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ 107 የፖለቲካ ድርጅቶች መፈረማቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 20 መጋቢት 14 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here