ግለሰቦች እውነታ ማኅበረሰቦች ደግሞ ምናባዊ ናቸው የሚሉት መላኩ አዳል፥ ስንሰባሰብ የመንጋ ባሕሪ ሊኖረን ይችላልም ይላሉ። ይህ እንዳይሆን ግለሰቦችም፣ መንግሥታትም የየግል ሚናቸውን መጫወት አለባቸው ይላሉ።
ሰው ከሌሎች እንሰሳት የተለየው ለአዋቂዎች በአማካኝ 1300 ግራም የሚመዝን አዕምሮ ባለቤት መሆን በመቻሉ ነው። የአስተሳሰባችን ሁኔታ በነርቭ ሕዋሳት ብዛት፣ በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት፣ በጀነቲክስ እና በውጫዊው የዓለም ሁኔታ የሚወሰን ሲሆን የነርቭ ሕዋሳት በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት በሰው ውስጥ ከፍተኛ መሆን በተለይም “ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ” ላይ ያለው ከፍተኛ አደረጃጀትና ግንኙነት ትልቁ አሳቢ ፍጡር እንዲሆን አድርጎታል። አዕምሮአችን በመነጋገር (‘ኮሚኒኬት’) ማድረግ በሚችሉ የነርቭ ሕዋሳት መካከል ብቻ በሚደረግ “የኔትወርክ (የሞጁሎች)” ስብስብ ነው።
እነዚህ ‘ሞጂውሎች’ በተለይም በግራው የአዕምሮ ክፍል የሚገኙት ምንም እንኳን የተገናኙ ቢሆንም የራሳቸውን ሥራ ያለ ማዕከላዊ ዕዝ በራሳቸው መሥራት የሚችሉ ናቸው። እነዚህ ʻሞጂውሎችʼ ቋሚ ያልሆኑ፣ እርስ በርስ፣ ከሌላ የሰውነት አካል፣ ከአካባቢ፣ ከሌላ አዕምሮ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር የሚለዋወጥ ነው። ይህም ከተለያዩ ‘ሞጁውሎች’ የተገኘውን የተሻለ ውሳኔ መምረጥና ትክክል የመወሰን ዕድሉ እንዲሰፋ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ ዓይነት ኀይል (ንቃተ-ሕሊና) የምንመራ እንድንሆንም አስችሎናል።
ሰው ለዘገምተኛ ዕድገቱ ብዙ ወጭ የሚያስወጣ ቢሆንም እግረ መንገዱን የአዕምሮ ዕድገቱን እንዲያፋጥን፣ የባሕል ትምህርትና ክኅሎት እንዲያዳብር ረድቶታል። ይህ ከሌላው የመማር አቅም በሰው ልጅ እጅግ የአደገም ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የቋንቋ እና የማስመሰል አቅምን የጨመሩ የአዕምሮ ክፍሎች፥ ከሌሎች ቅርቦቹ እንሰሳት የበለጠ ማደጉ ነው። ይህም የሚያመለክተው ለነዚህ ወሳኝ ኹነቶች መኖር ከመማር አቅም መጎልበት በተጨማሪ ለዋናው ‘የሞጁውሉ’ መኖር ‘የጀነቲክስ’ መኖር ወሳኝ መሆኑን ነው። አስመስሎ የማድረግ አቅም በመስተዋት የነርቭ ሕዋሳት የሚከወን ነው። ይህ የአዕምሮ ሥራ ዕውቀትን በምሣሌ እንድናስተላልፍ ጠቅሞናል። ይህም ዘገምተኛ ከሆነው የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ በተነፃፃሪ ፈጣን ወደ ሆነው የባሕል ዝግመተ ለውጥ እንድንገባ አግዟል። ይህም ሁሉም ነገር ‘የጂን ሙቴሽን’ (gene mutation) ከሚወስነው የዳሪውን ʻኢቮሊሽንʼ ወደ የባሕል ለውጥ በፍጥነቱ ወደ ሚወስነው ሽግግር እንድናደርግ አድርጎናል። ይህም ከዝግመተ ለውጥ ወደ አብዮታዊ ለውጥ እንድንገባ አግዞናል። ይህ ለውጥ ጥንት በእሳት፣ መሣሪያዎች፣ አልባሳት፣ ቤት ግንባታ፣ ሥነ ጥበብ፣ በዋነኝነትም በቋንቋ መፈጠር፣ ቀጥሎም በተለያዩ አብዮቶች፣ አሁን ደግሞ በመረጃ ቴክኖሎጂ አብዮቱ ታግዞ እየፈጠነ ነው።
ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው። ኅብረተሰብ የግለሰቦች ጥርቅም ነው። ግለሰብ ተጨባጭ ሲሆን፥ ኅብረተሰብ ግን ሐሳብ ነው። የጋራ እሴት፣ አስተሳሰብና ስሜት አለው። ሁላችንም የየግላችን አእምሮ አለን። የጋራ አእምሮ ደግሞ አለን። ምንም ያህል ብልህ፣ ነጻ፣ አስተዋይ ግለሰብ ብንሆን የጋራ አዕምሮአችን ወደፊት ሊገፋን ይችላል፤ ወደ ኋላ ሊጎትተን ይችላል። ግለሰቦች ማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳርፉትን ተፅዕኖ ያህል ኅብረተሰብ ግለሰቦች ላይ ያሳርፋል፤ ተመጋጋቢ ናቸው። ከጋራ አዕምሮአችን ክፉም ሆነ በጎ ተፅዕኖ ለማምለጥ ስለማንችል ራሳችንን ለመለወጥ የምንጥረውን ያክል ማኅበረሰቡን ለመለወጥ መጣር አለብን። በየአገሩ የምናያቸው አምባገነኖች የሁሉም ሕዝብ አስተሳሰብ ድምር ውጤት ናቸው። ለዚያም ነው ሕዝብ መሪን ይፈጥረዋል እንጂ መሪ ሕዝብን አይፈጥርም የሚባለው። ኅብረተሰብ እንዲለወጥ መጀመሪያ ግለሰቦች ነጻነታችንን ማወጅና መለወጥ አለብን።
ሰዎች በመንጋ ሲገኙ የመንጋ አስተሳሰብ በሰዎች ውስጥ ይኖራል። ይህ በተለይም ደግሞ ኃይል በተቀላቀለባቸው ድርጊቶች ላይ በሰፊው ይስተዋላል። ሰዎች በአንድ ቡድን/መንጋ ውስጥ ሲቀላቀሉ የራስን ማንነት መርሳት ያጋጥማቸዋል። ይህ በሚሆንበት ወቅትም ለብቻቸው ሲሆኑ የሚኖራቸውን ራስን የመግዛት አቅም በመዘንጋት ከቡድኑ/መንጋው አስተሳሰብ ጋር የመቀላቀሉ ፍላጎታቸው እያየለ ይሔዳል። ሰዎች ቡድንን/መንጋን ሲቀላቀሉ ለብቻቸው ሲሆኑ የማያደርጉትን ድርጊት ያደርጋሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የመንጋው ቁጥር ብዙ ሲሆን እና ሰዎች በተናጠል የሚያደርጉትን ድርጊት ማንም ዱካቸውን ተከትሎ ደርሶ ተጠያቂ አንደማያደርጋቸው ከተሰማቸው የሁከት ድርጊቶችን ለማድረግ ብርታት ይሆናቸዋል።
በኢትዮጵያችን በሚያስፈራ እና በሚያስቀይም መልኩ ማኅበረሰብ የነበረውን የማረጋጋት፣ ሰላም የመጠበቅ እና የማስጠበቅ፣ ግለሰቦችን ከክፉ የመከለል አስተዋፅዖ አፈንግጦ ለግለሰቦች የሥጋት እና የአደጋ ምንጭ ሆነዋል። ሕግ ሲሰበር ሕግ በመሆን፣ ፍትሕ ሲጓደል መንገድ በመጠቆም፣ ሰው ሲረክስ የሰውነትን ክብር በማመላከት፣ ፍጅት ሲነግሥ ተያይዘው መቆም ሲሳነን እያየን ነው። የጋራ ርዕዮት እስከሌለን ድረስ በ107 ፖርቲ በጎጥ ተደራጅተን መባላታችን የማይቀር ነው። የሁሉም ችግራችን መንሥኤ ድንቁርና፣ ኋላ ቀርነት፣ ደካማ ባሕል፣ ብሎም እሱን ተከትሎ የመጣው የልኂቅ ጠባብ የሆነ የዘር ፖለቲካና የዘር ፌዴራሊዝም ነው። የምንመኘውን ዴሞክራሲና የበለፀገች አገር ለመገንባት በዕውቀት የሚያምን፣ ዴሞክራሲን መሸከም የሚችል ባሕል እንዲኖረን ያስፈልጋል። በተጨማሪም በጠቅላላው የትምህርት ጥራት መውረድ፣ በተለይም የመምህራን ጥራት መውረድ፣ ከቀደመው የጉልት ስርዓት አስተሳሰብ አለመውጣታችን ከምንመኘው ለመድረስ እንቅፋት እየሆነብን ነው።
የችግሮች ዋናው ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው። በኢትዮጵያችን ሕገ መንግሥቱን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የፌዴራል አስተዳደራዊ አወቃቀሩን፣ የትምህርት ስርዓቱን ወዘተ. በብሔር ብቻ እንዲቃኝ መደረጉ የሕወሐትና የኦነግ ጥፋት ነው። ሕገ መንግሥቱ ለአገራዊ አንድነትና ሕልውና ፀር ነው። ሕገ መንግሥቱ ለሕዝብ ግጭትና መፈናቀል፣ ለዕለት ተዕለት የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የጋራ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶቻችንን እንዳናበለጽግና ያሉንንም እንድናጣ፣ የጋራ ቋንቋ እንዳይኖረን፣ ልዩነት እንዲነግሥና አንድነታችንን እንዲዳከም አድርጓል። የየክልሎቹ ሕገ መንግሥቶች በየክልሉ ያሉ ሕዝቦችን ነባርና መጤ ብለው የሚከፍሉ፣ ነባር ለሚሏቸው ደግሞ የክልሉ መሬትም ሆነ ሀብት ላይ ሌላው ዜጋ የሌለውን የልዩ ባለቤትነት መብት የሚሰጡ ናቸው። ይህ በጠቅላላው የሚያሳየን የችግሩ ምንጮች እኛው ተማርን፣ አወቅን ባዮች፣ የተማርን ማህይሞች፣ ራሳችን የካድን ባዕድ አምላኪዎች መሆናችንን ነው። የመንጋ ፖለቲካ እንዲነግሥ አድራጊዎች እኛው ነንና።
ሕገ መንግሥት፣ መንግሥትና ሕጎች የአስፈለጉበት ምክንያት የሰው ራስ ወዳድነት ነው። እናም የታቀደላቸውን ዓላማ አንዲያሳኩ ማስተካከልንና በትክክል መተግባርም እንወቅ። የዘር ፖለቲካና የዘውጌ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ሕልውናና በዜጎች የትም የመኖር መብት ላይ ችግር አስከትሏል እና ይስተካከል እንጂ፥ ብሔርተኞች እንደሚሉት የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ይፍረስ ያለ የለም። የፖለቲካ ፓርቲ መሠረቱን በቋንቋ ላይ ካደረገ ከዕውቀት የፀዳ ርዕዮት አልባ ተከታዮቹን ወደ ጨለማ ገደል የሚመራ ነው። የብሔር ፖለቲካ የማይታረም አስከፊ ባሕርዩ ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትሕን እና የሕግ ልዕልናን በመሠረታዊነት እወክለዋለሁ ከሚለው ብሔር ጥቅም አንፃር ብቻ ማየቱ ነው። ከዘውጌነት ያተረፍነው ርሃብን፣ ስደትን፣ ወደብ ማጣትን፣ ሙስናን፣ የሞራን ድቀትን፣ አያገባኝም ባይነትን፣ የጋራ ርዕዮት ማጣትንና ዘረኝነትን መሆኑንና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ዋናው ምክንያት ነውና ሊስተካካል ይገባል። ለሁሉም መፍትሔው ያለው የሕገ መንግሥት፣ የመዋቅርና የስርዓት ለውጥ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል፣ በዘር የተማከለውን የክልል ፌደራሊዝም በማስተካከል፣ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች በርዕዮተ ዓለም መሠረት በማዋሐድ ለቀጣይ አገር ደኅንነት መሥራት ይኖርብናል። በዘርና በቋንቋ ላይ መሠረት ያላደረጉ፣ የርዕዮት መሠረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረትና ከዘር እና ቋንቋ በተጨማሪ የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት ተመጣጣኝነት፣ የመልከዓ ምድር አቀማመጥና አሰፋፈርን፣ የንግድና የኢኮኖሚ ትሥሥርን፣ የአስተዳደርና የልማት አመችነትን፣ የአኗኗር ዘይቤን፣ የታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ልቦናና የባሕል ትሥሥርን ያካተተ የፌዴራል አወቃቀር እውን መሆን የችግሮቻችን መፍትሔ ነው። የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሲቪክ ማኅበር ብቻ ሆነው የብሔራቸውን መብት ያስጠብቁ፣ ሕዝብ በቀጥታ የመከረበት እና ድምፅ የሰጠበት ሕገ መንግሥት እንዲረቅም ማድረግ ያስፈልጋል።
ከመንጋ አስተሳሰብ ራሳችንን የምንታደገው ደግሞ ራስን በማወቅና ራሳችንን ባለመዋሸት፣ ዘውትር የተሻለ እንድናስብ፣ እንድንመኝ እና ራስን ከማታለል ሕይወት እንድንነቃ የሚያደርጉንን ሰዎች ፈለጎ በመወዳጀት፣ የአስተሳሰብ ምኅዳርን በማስፋት፣ መረጃዎችን የምናገኝባቸውን ምንጮች በማስፋት፣ ዘውትር በመጠየቅና የሌሎችን ሐሳብና ድርጊቶችን በመሞገት፣ በዕውቀት በመመራትና የምንደግፋቸውንም ሆነ የምናወግዛቸውን ነገሮች የመመርመር ልምድ በማዳበር፣ የሐሳብ ግጭትን በመላመድና በውይይቶች ሐሳቦቻችን የተሞገቱ እና የጠሩ እንዲሆኑ በማድረግ ነው። መንግሥትም አራቱን መሠረታዊ የመንግሥት ግዴታወች፦ አንደኛ ሕግና ስርዓትን ማክበርና ማስከበር፣ ብሎም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ኹለተኛ፣ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ ሦስተኛ፣ ዜጎች አገራቸውን “አገራችን” ብለው ይጠሩ ዘንድ የዜግነት ስሜትን እንዲፈጥሩና እንዲያዳብሩ ማድረግ እና አራተኛ፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና አገራዊ ሀብትን በፍትሐዊነትና በእኩልነት መርሕ ለዜጎች እንዲደርስ ማድረግ ይኖርበታል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011