‘የጀግንነት አርአያዎች’ በሚል ርዕስ በጆን ኤፍ ኬኔዲ ተጽፎ የነበረው የተሻገር ውቤ ትርጉም መጽሐፍ የአሜሪካን ፌዴሬሽን አንድ ላይ ለመጠበቅ ስለተደረጉ ተጋድሎዎች እንደሚተርክ የሚነግሩን ብርሃኑ ሰሙ፥ እኛም እየገጠመን ያለው ፈተና እነርሱ ከኹለት ምዕተ ዓመታት በፊት የገጠማቸው ፈተና ነው ይላሉ።
አሜሪካዊያን ሕገ መንግሥታቸውን አፅድቀው በፌዴራል አደረጃጀት በጋራ ለመኖር በወሰኑ ማግስት ጀምሮ፥ አንድነታቸውን በመፈታተን ዓመታት ባስቆጠረ ብዙ ውጣ ውድ ውስጥ ማለፋቸውን የሚያመለክት መጽሐፍ ነው። ‘Profiles in Courage’ በሚል ርዕስ በጆን ኤፍ ኬነዲ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ “የጀግንነት አርአያዎች” በሚል በተሻገር ውቤ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በ1958 ለኢትዮጵያ አንባቢያን ቀርቧል፤ አስተርጓሚው የአሜሪካ ማስታወቂያ ክፍል ነበር።
“አሜሪካ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝቧ ዘንድ የሐሳብ መከፋፈልና ልዩነትን፣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ያልተወደዱትን አስተያየቶች በጥሞና መንገድ መያዝንና ማስተዋልን፣ እንዲሁም የንግግር ነጻነትን በሥራ መምሪያ ፖሊሲዎቿ ውስጥ አስገብታ እንደ አንድ ትልቅ ጉዳይ ባትቆጥራቸው ኖሮ” ዛሬ የምትገኝበት ደረጃ ባልደረሰች ነበር የሚለውን ምስክርነት የያዘው መጽሐፍ፥ ከ200 ዓመታት በፊት አሜሪካንንና አሜሪካዊያንን የተፈታተኑ በርካታ ታሪኮች ቀርቦበታል።
የአሜሪካ ዋና ከተማ የት ይሁን? በሚል የተነሳው ሙግት ብዙ አታግሏል፤ የአሜሪካ ግዛቶች ከፌደራሉ ስርዓት ተገንጥለው ራሳቸውን ይቻሉ፣ አይቻሉ የሚለው በአያሌው አጨቃጭቋል። ሴቶችን የሴኔት አባል ቢሆኑ ምን ጥቅም፣ ባይሆኑስ ምን ጉዳት ያስከትላል የሚለውም አነታርኳል። ባለሥልጣናትን ተጠግተው ለብልፅግናቸው የሚሠሩ ባለሀብቶች ለአገርና ሕዝብ ውድቀት ምክንያት መሆናቸው አወያይቷል። ጎሳ ተኮር ፖለቲካ ሥሩን አስፋፍቶ እንዳይበቅል ጥረት ተደርጎ ተሳክቷል።…
ከ62 ዓመታት በፊት በ254 ገጾች ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለኢትዮጵያዊያን የቀረበው “የጀግንነት አርአያዎች” መጽሐፍ፥ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲካን ማዕከል አድርጎ የገጠመንና ችግር መስሎ የሚታየን ክስተት፣ አያያዙ ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል እንጂ፣ መልካም ዕድል መሆኑን ያመለክታል። እንዴት ቢሉ፣ ነገ ነጥሮና ጠርቶ የሚወጣው ሕዝባዊና አገራዊ አንድነት በዛሬው ቀውስ እና ሥጋት ውስጥ ማለፉ የ“ለውጥ” አንዱ ተፈጥሯዊ ባሕሪ መሆኑን ስለሚያሳይ ነው።
ኹለተኛው፣ በመጽሐፉ ማስተላለፍ ከተፈለገው አንኳር ጭብጥ ጋር የሚያያዝ ነው። አንድ ቅንጣት የስንዴ ፍሬ አፈር ውስጥ ገብቶ ራሱን መስዋዕት በማድረጉ ምክንያት 30፣ 60 እና 100 ፍሬ እንደሚያፈራው ሁሉ፥ ተዘርቶ ለበቀለ፣ ላሸተና ለጎመራ ነገር ሁሉ የሚታይና የማይታይ፣ ሊመሰገን የቻለና ያልቻለ፣ የተወገዘ ወይም የተመሰገነ… አካል ይኖራል።
በ“የጀግንነት አርአያዎች” መጽሐፍ ታሪክና ገድላቸው የተተረከላቸው “የአሜሪካ ሴኔቶች” ዛሬ በዲሞክራሲ፣ በነጻነትና ብልጽግና ሁሉም በአርአያነት እንዲያነሳት፣ አገሪቱም አሁን የምትገኝበትንና ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ ዋናውን ሚና ተጫውተዋል። ትግልና መስዋዕትነታቸው ምን ይመስል እንደነበር ማሳያዎችን መጽሐፉ አቀርቧል።
“በዚህ ዓለም ላይ ማናቸውም ጉዳይ ጥሩና መጥፎ ነገሮችን ቀላቅሎ የያዘ ነው እንጂ አንድ ነገር ብቻ ይዞ የሚገኝ ነገር የለም። በተለይ በመንግሥት አስተዳደር መምሪያና በፖለቲካ ሥራ ውስጥ እነዚህ ኹለቱ ጉዳዮች ተደበላልቀው ሲሠራባቸው ይታያሉ። አንደኛውን ከሌላኛው ለይቶ ለማወቅ ግን የእያንዳንዳችንን አስተዋይነትና ፍርድ ይጠይቃል” የሚለው የጆን ኤፍ ኬነዲ መጽሐፍ፣ “በተደበላለቀው” ጉዳይ ውስጥ ያለው አደጋ፣ አገርና ሕዝባቸውን ለጉዳት አሳልፎ እንዳይሰጥ ከታገሉት ሴናተሮች አንዱ የኪንታኪ ተወካይ የነበሩት ሀምፍሪ ማርሻል ናቸው።
እ.ኤ.አ. በ1795 ፕሬዚዳንት ዋሽንግተን ከእንግሊዝ ጋር ለአገሬ ይጠቅማል ያሉትን ውል ለመፈራረም ወስነው፣ ኮንግሬስ እንዲመክርበት ወደ ምክር ቤቱ ላኩት። ውሉ እንዳይፀድቅ ሴናተሮች ሕዝቡን ለአመፅ አነሳሱት። የፕሬዚዳንቱን ሐሳብ የደገፉ ብቸኛው ሴናተር ሀምፍሪ ማርሻል ከወከላቸው ሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው። ሴናተሩም ለሕዝቡ እኔን መቃወማችሁ “የሚያመለክተው ድንቁርናን፣ ምቀኝነትንና የጎሳ ልዩነት ተግባርን እንጂ ቁም ነገርን ያዘለ አይደለም። እናንተ የምትፈልጉት እርስ በእርሳችን ተበጣብጠን የውጭ ጠላት ያለድካም ገብቶ በደኅና ጊዜ የመሠረትነውን የመልካም ኑሮ መመሪያችን እንዲበዘበዝብን ለመርዳት ነው” በማለት በድፍረት መልስ በመስጠታቸው በድንጋይ ተወግረዋል። ታፍነው ወደ ገደል የመጣል አደጋም ገጥሟቸው ነበር።
ለአሜሪካ ሕዝብና አገር ይጠቅማል ያሉትን እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በመወሰናቸው ምክንያት ብዙ የተንገላቱና የተሰቃዩ የበርካታ ሴናተሮችን ታሪክ ያቀረበው “የጀግንነት አርአያዎች” መጽሐፍ፣ ፍጡር ሁሉ ከፈጣሪው ጋር እንዴት ይጣላል? ሎሌስ ጌታውን እንዴት አልታዘዝም ይላል? አንድ ሴናትርም መርጦ ለላከው ሕዝብ ካላገለገለ እውነተኛ የሕዝብ እንደራሴ ነው ለመባል እንዴት ይችላል? የሕዝቡንስ ፍላጎት ካልተከታተለ የራሱ እንደራሴ ብቻ መሆኑ አይደለምን? የሚሉ ጥያቄዎችንም ያነሳል።
የፖለቲካ ንትርክ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ስለሆነ ውጤቱ የሚገኘው በኹለት የተሳሳቱ አስተያየቶች መካከል መሆኑን፣ ሕግና ደንብ በሚወጣበት ጊዜ የሁሉም ሰው አስተያየት የማካተት አስፈላጊነትና የሌሎችን ፍላጎት ወርውሮ የኔ ብቻ ይፅደቅ ማለት መጨረሻው እንደማያምር፣ በፖለቲካ ሥራ ውስጥ ያለ ሰው ራሱ የሚያምንበትን ነገር ትቶ ሕዝቡ እንደሚፈልገው የመሆን ግዴታ ቢኖርበትም እንደ ሴናተር ሀምፍሪ ማርሻል ያሉ “ከሣጥኑ ወጥተው” የሚያስቡ፣ የሚወስኑና የሚሠሩ፣ የዛሬዋን አሜሪካ ማስገኘት እንደቻለ በመጽሐፉ አፅንዖት ተሰጥቶበት ከቀረቡ በርካታ ማሳያዎች ሌላኛው የቦስተኑ ሴናተሩ ሚስተር አዳምስ ነበሩ።
አዳምስ አገራቸውን በተለያየ ኃላፊነት በብዙ ቦታዎች አገልግለውም “ምንም እንዳልሠሩ” የሚሰማቸው ሥራ ወዳድ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብና አገራቸውን አፍቃሪም ነበሩ። አገርና ሕዝባቸውን ይጠቅማሉ ብለው በአቋማቸው በመፅናታቸው ግን በርካታ ውግዘት ገጥማቸዋል። “ከዳተኛ ጠባዩ ከማኪያቬሊ የማያንስ!” ተብለው ተተችተዋል። በጋዜጦችና በየአደባባዩም “ወላዋይ! እወደድ ባይ! ከሐዲ!” የሚሉ የስድብ ናዳ ወርዶባቸዋል። ትውልድ አገሩንና ወገኖቹን የሸጠ ተብለዋል። “በቦስተን ይኖር የነበረው ሰው ሀብታሙም ሆነ ደሀው ሁሉም ሚስተር አዳምስን ጠላቸው። ከእሳቸው ጋር ከአንድ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብሎ የሚበላ ሰው ጠፋ” የተባለላቸው ባለታሪክ፥ ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለመጪው አገርና ሕዝብ ያመንኩበትን መልካም ነገር ለማበርከት በማሰቤ ነው ብለው ለእናታቸው ይህን ደብዳቤ ጽፈው ነበር፦
“እኔ አሜሪካን አገራችን በውጭ ጠላት ተጠቃች ብዬ የአገር ፍቅር አንገብግቦኝ እስዋን ለማገልገል ብነሳ፥ ጠቅላላውን የአገር ጥቅም ረስቶ ለአንድ ክፍለ አገር ጥቅም ብቻ ለምን አይቆረቆርም በማለት የቦስተን ሰዎች ከመካከላቸው አሽቀንጥረው ጥለው ሁሉም እንደ አንድ ከዳተኛ ቆጥረውኛል።”
እ.ኤ.አ. በ1813 ዋሽንግተን ከተማ ትንሽ የገጠር መንደር ታክል ነበር። ወደዚች ከተማ የተላከ አንድ የፈረንሳይ መንግሥት መልዕክተኛ “በዚች ጠፍ መንደር ውስጥ እንድኖር መላኬን እንደግዞተኛ እቆጥረዋለሁ” ብሎ ነበር የሚል መረጃ የሚሰጠው “የጀግንነት አርአያዎች” መጽሐፍ፥ እ.ኤ.አ. በ1850 የአሜሪካን ፌደሬሽን በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ እንደ ነበርና ይህንና ሌሎችንም በሕዝብና አገር ላይ የመጣን አደጋ በመከላከል ረገድ ታላቅ ገድል ከፈፀሙት መሐል እንዳንዶቹ ድካማቸው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሆኗል።
እ.ኤ.አ. በ1861 በአሜሪካዊያን መካከል ከተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ፣ የአሜሪካ ፌዴሬሽኑ እንዲጠነክር ትልቅ አስተዋፅዖ ካደረጉት መካከል፥ የቴክሳሱ ሴናትር ሳም ሒውስተን፣ የሚዙሪያው ሴናተር ቶማስ ሀርት ቤንተንና የማሳቹሰትሱ ዳንኤል ዌብስተር… የመሳሰሉት “ጀግኖች” የአሜሪካ ፌዴሬሽን እንዲቋቋም ስለደከሙበት ዋጋ ከክብር ይልቅ ውርደት የተሸለሙ፣ በዚህ አቋማቸውም ለሞት የተዳረጉም ነበሩ። ጆን ኤፍ ኬነዲ እነዚህን ለመዘከር በማሰባቸው ነበር መጽሐፉን ለማሰናዳት ምክንያት የሆናቸው።
ከአቋማቸው ጠንካራነት የተነሳ “ፌዴሬሽኑ ከሚፈርስና የአሜሪካ አንድነት ከሚጠፋ የራሴ የግል ምኞትና እንጀራዬም ቢዘጋ ግድ የለኝም” የሚሉ፣ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ሳይለያዩ በፌዴሬሽን አብረው ሊቀጥሉ ስሚችሉበት ሁኔታ ንግግር በማድረጋቸው ምክንያት በወገኖቻቸው ዘንድ ጥላቻን በማትረፋቸው፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የነበራቸውን ተስፋ “በፍላጎታቸው ቀበሩት” የተባለላቸው፣ አገራችን ጠቃሚ ባልሆኑ ምክንያቶች መከፋፈል የለባትም፣ አሁንም ሆነ ወደፊት ጠንክረን መቆም የምንችለውና የምንበለፅገው በአንድነት ገመድ የታሰርንና የተባበርን ከሆነ ነው። “አንለያይ! አንነጣጠል!” በሚሉ ንግግሮቻቸው ታዋቂ ብቻ ሳይሆን አገርና ሕዝብን ከመከፋፈል ያዳኑ በርካታ ሴናተሮች ታሪክ የያዘው መጽሐፍ ካቀረባቸው አስደማሚ ታሪኮች መሐል፥ ሙስናንና ሙሰኝነትን “የተፀየፉት” ሲናተር ቤንተንና ውሳኔያቸው ነው።
አንድ የመርከብ ነጋዴ ቤንተን ዘንድ ሔዶ ንግዱን ሊያስፋፋ የሚችልበትን ዕቅድና ዘዴ ካስረዳቸው በኋላ፣ ለዚህ ዓላማው እገዛና ትብብር የሚያደርጉለት ከሆነ የትርፉ ባለድርሻ የሚያደርጋቸው መሆኑን በገለጸላቸው ጊዜ ሴናተሩ “አንተ በጠየከኝ መንገድ ልረዳህ የምችለው መርከቦቹ ተሰርተው ካለቁ በኋላ እንዳተ ያለውን ደደብ ሁሉ ከዚህ አገር ጠርገው እንዲያወጡ የተሥማማን እንደሆነ ነው” ብለውታል።
ዛሬ በአንድነቷ ፀንታ በመቆሟ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህም ተጠቃሚም በመሆኗ ጭምር የምትታወቀው አሜሪካ፥ ከመነሻው የመከፋፈል አደጋ በከፋ መልኩ ገጥሟት እንደነበር በርካታ መረጃዎችን ያቀረበው “የጀግንነት አርአያዎች”፥ ሴናተር ሒውስተን የመሳሰሉ አርቆ አሳቢዎች “የአገር ፍቅር ስሜት ያልገባቸው የአገር ዕድገትና ልማት ምን እንደሆነ የማያውቁ ቴክሳስን ነጥለው ብቻዋን ለማስቀረት ይፈልጋሉ። እኔ የምከራከረው ለኅብረት፣ ለአንድነትና ለሕገ መንግሥታችን ክብር” እንስጥ በሚል አቋምና ፅናት ያደረጉት ትግል፣ መልካም ፍሬው ለልጅ ልጆቻቸው እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።
ሴናተሮቹ ምኞታቸውን ለማሳካት ቡጢ ተሰናዝረዋል። ሽጉጥ ተማዘዋል። በጋዜጦችና በየአደባባዩ ተሰዳድበዋል። መጽሐፍ አሳትመው አንዳቸው ሌላኛቸውን አንቋሸዋል። እንዲህም ሆኖ የአፍራሽ ኃይሎች ምኞት እውን አልሆነም። ‘የአንድነት ኃይሎች አሸንፈው የወጡት ለምን፣ እንዴትና በምን ምክንያት ነው?’ ቢባል አሜሪካ ለማሰብ፣ ለመናገርና ለመቻቻል የሰጠችው ዕውቅና ዋነኛው ከለላና ጥላ ስለሆናቸው ይመስላል። ኢትዮጵያዊያንም ከ200 ዓመታት በኋላ አሜሪካዊያኑ በነበሩበት አደባባይ ላይ ደርሰናል። ከ62 ዓመት በፊት ተተርጉሞ የቀረበልን “የጀግንነት አርአያዎች” መጽሐፍ፥ ቀውስና ስጋታችንን ለመቅረፍ አንዱን ዘዴና ብልሐት የሚያመላክት ይመስላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011