የአገራችን ችግር ማኅበራዊና ኋላ ቀርነት እንጂ አይደለም!

0
697

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት የብሔረሰብ ዕይታ እንጂ ሳይንሳዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ አላፈለቀም የሚሉት ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)፥ አንድ አፍታ ቆም ብሎ ለችግሮቻችን ሁሉ የተሻለውን መፍትሔ የሚሰጥ ንድፈ ሐሳባዊ መዋቅር ማስቀመጥ እንደሚገባ በዚህ መጣጥፍ ጠቁመዋል።

 

ያለፉትን 60 ዓመታት የአገራችንን የመንግሥት አወቃቀርና ከዚህ የሚመነጨውን ፖሊሲ ለተከታተለ፣ ሦስቱም አገዛዞች በሳይንስ የተጠና፣ ፍልስፍናን እና ንድፈ ሐሳብን መሠረት ያደረገ፣ አገራችንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደርጋት የሚችል ፖሊሲ እንዳልነበራቸው መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ሕዝባችን ኋላ ቀር ከሆነ የአኗኗር ስልት ተላቆ ምርታማነትን በማሳደግና ኑሮውን አሻሽሎ ሰፋ ያለና ጠንከራ ኅብረተሰብ እንዲመሠርትና ተከታታይነት እንዲኖረው የወሰዱት ሳይንሳዊ ፖሊሲ በፍፁም አልነበረም። የአገራችንን ኹኔታና የሕዝባችንን ፍላጎት ያላገናዘበና፣ የተከታታዩንም ትውልድ ዕድል ቁጥር ውስጥ ያላስገባ፣ በውጭ ኃይሎች የተነደፈና ተግባራዊ ያደረጉት ፖሊሲ በአገራችን ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ኅብረተሰባዊ ሀብት እንዳይፈጠር ለማድረግ በቅቷል።

በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ ዘመኖች በአገራችን ምድር ሥልጣንን የጨበጡ የገዢ መደቦች አገራችን ያላትን ተፈጥሯዊ ሀብት በሥነ ስርዓት መጠቀም ስላልቻሉና እውነተኛ የሆነ ብሔራዊ ሀብት ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጋቸው በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይፈጠር አድርገዋል። ከተማዎች እንዳይገነቡ፣ ሰፊው ሕዝብ በተለያየ ሙያ በመሠልጠን፣ በንግድ አማካይነት እንዳይተሳሰርና እንደ አንድ ሕዝብ ታሪክን እንዳይሠራ በአብዛኛው ጎኑ ሳያውቁት ከፍተኛ መሰናክል ሊፈጥሩ ችለዋል። ስለሆነም ድህነትን ለመቅረፍ ቀን ከሌሊት ደፋ የማይል አገዛዝ በመሠረቱ ጥሎ የሚያልፈው ያልተረጋጋና በሆነው ባልሆነው የሚናቆር ሕዝብ እንደሆነ የአንዳንድ አገሮችም ታሪክ ያስተምረናል። እንደዚህ ዓይነቱ በሰፊ የኢኮኖሚና የማኅበረሰብአዊ መሠረት ላይ ያልተገነባ አገር ደግሞ መጥፎ ሕልም ለሚያልሙ ጥራዝ ነጠቅ ለሆኑ የውስጥ ኃይሎችና፣ የአገራችንን መዳከምና እንዲያም ሲል መበታተን ለሚፈልጉ ኃይሎች ቀዳዳ መስጠቱ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ስለሆነም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የብሔረሰብን ጥያቄ አንግቦ ነጻ እወጣለሁ በማለት እዚህና እዚያ የሚሯሯጠው ኢትዮጵያዊ ኃይል በሙሉ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት አውጇል። በውጭ የስለላ ኃይሎችና በአካባቢው በሚገኙ የአገራችንን መጠናከርና መረጋጋት በማይፈልጉ አጎራባች አገሮች በመታገዝ አገራችንና ሕዝባችን በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። እነዚህ ለነጻነታችን እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች በራሳቸው ላይ አጉል ዝቅተኛ ስሜት በማሳደርና፣ ወጣቱን በመቀስቀስና አመፀኛ እንዲሆን በማድረግ እንዳየነውና እንደቀመስነው ለብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሰው ሕይወት መጥፋትና፣ አገራችንም አሁን ባለችበት ኹኔታ እንድትገኝ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ʻበቡሃ ላይ ጆሮ ደግፍ ተጨምሮበትʼ እንደሚሉት አነጋገር፣ ሌሎችም ከብሔረሰብ ጋር ያልተያያዙ ኃይሎች በዚህና በዚያኛው ሙያ የተሠማሩ የአገራችን ምሁሮች፣ ከሲቪሉም ሆነ ከወታደሩም የተውጣጡ፣ የውጭ የስለላ ኃይሎች የሚሰጧቸውን ምክርና የገንዘብ ድጋፍ ተገን በማድረግ አገራችንን እንደነቀርሳ በሽታ ሰርስረዋታል፤ በፊዩዳላዊ ተንኮል ክፉኛ አዳክመዋታል።

እነዚህ ኃይሎች በተለይም ቀደም ብለው ከነበሩት የገዢው መደቦች ጋር በጥብቅ የተሳሰሩና ዝምድናም የነበራቸው ሲሆኑ፥ ዋናው ዓላማቸው በተለይም አገራችንና ሕዝባችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ጠንካራ አገር እንዳይመሠርቱ ማድረግ ነው። በዚህ ዓይነቱ የአንድን አገር ኅልውና የሚያወድምና ተከታታዩ ትውልድም በየጊዜው አዳዲስ ታሪክ እንዳይሠራ የማርክሲዝምን አርማ አንግቦ እታገላለሁ ይል የነበረው ኃይል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአገራችንን ውድቀት አፋጥኗል ማለት ይቻላል።

ግራ አጋቢ የልኂቃን ፕሮፓጋንዳዎች
ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ፣ በተለይም እንደነጃዋር የመሳሰሉት አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናይ ነን ብለው የፖለቲካን ትርጉም ሳይረዱ የተሰጣቸውን የሚዲያ ዕድል በመጠቀም የሚያስፋፉት ቅጥ ያጣና የተዘበራረቀ ልፍለፋ የፖለቲካውን ትግል እየረበሸውና አብዛኛውን ሕዝብ ደግሞ ግራ እያጋባው እንደመጣ እንመለከታለን። ሕዝባችን በፍርሐት በመዋጥ ፈጣሪን እየለመነ እንዲኖር አድርገውታል። በመተባበርና በመከባበር አንድ ለሁሉም የምትሆን ነጻ አገር እንዳይገነባ አለመተማመንን አስፋፍተዋል። ጃዋርና ተከታዮቹም ሆነ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት “ተጨቁነናል፤ ነጻነታችንንም መልሰን ማግኘት አለብን” የሚለውን ከማራገብና ሕዝብን ከማወናበድ በስተቀር፥ ይህ ነው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲያችን ብለው ሲያስተምሩና ሲከራከሩ በፍፁም አይታዩም። በመሠረቱ ሳይንስን፣ ፍልስፍናንና ንድፈ ሐሳብን መሠረት አድርጎ የማይካሔድ ትግል ወደ ፋሺዝም ነው የሚያመራን። እንዳየነውና በታሪክም እንደተረጋገጠው፥ በብሔረሰብ ላይ የተመረኮዘ ብሔርተኝነት ከሌላው የተለየሁ ነኝ ብሎ ስለሚያምን ነጻነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው እሱን ያልሆኑትን በመግደል ወይም በመጨረስ ብቻ ነው። ይህም ማለት ሒትለር የመጨረሻው መፍትሔ (The final Solution) እንዳለው በአገራችን ምድርም ተግባራዊ የማይሆንበት ምክንያት የለም። ሕወሓትም እስከተቻለው ድረስ ይህንን ዓይነቱን አንድን ብሔረሰብ የማውደም ፖለቲካ ሲከተል ነበር። የአሁኖቹም ፅንፈኞች ይህንን ከማድረግ አይቆጠቡም። በየቦታው የሚካሔደው መፈናቀልና መሰደድ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። ሒትለር ለጀርመን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉትን ይሁዲዎችን በመጥላትና ዝቅተኛ ስሜትም ስላደረበት ነው ዘመቻ ያደረገባቸውና የመጨረሻ መጨረሻም ለስድስት ሚሊዮን ሰዎች ማለቅ ምክንያት የሆነውና ‘ሆሎኮስት’ የሚባለውን ዘግናኝ ድርጊት የፈፀመው። እነ ሻቢያና ሕወሓት የሚባሉትም ገዢዎች በአጀማመራቸው የማርክሲዝምን አርማ ይዘው ቢነሱም ዋናው ዓላማቸው የአማራውን ሕዝብ ቅስም ለመስበርና እነሱ በጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረፁትን የአማራውንና የኦርቶዶክስን ሃይማኖት የበላይነት ማዳከምና የራሳቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ነበር ዋና ዓላማቸው። ድርጊታቸው ከፋሺዝም የሚያንስ አይደለም ማለት ነው።

የሚያዳክሙን ትግሎች
በአገራችን ምድር ውስጥ እስካሁን ድረስ የተካሔዱት ትግሎች በሙሉ ራሳችንን የሚያዳክሙ እንጂ ለማንም የሚጠቅሙ አይደሉም። የታሪክን ሒደትና የኅብረተሰብን ዕድገት፣ ከዚህም በላይ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ያለን ምሁራዊ ድክመትና፣ ጠለቅና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖር ያላገናዘቡ በመሆናቸው እርስ በእርሳችን እንድንፋተግ ተደርገናል። የድንቁርናችን ሰለባ በመሆን ተባብረንና ተቻችለን ታሪክን ከመሥራት ይልቅ የውጭ ኃይሎች ተጠሪና ተመካሪ በመሆን የአገራችንን ውድቀትና መበታተን እያፋጠን እንገኛለን። የተማርነው ትምህርት ሁሉ ጭንቅላታችንን አንፆት የተቀደሰ ተግባር ከመሥራት ይልቅ መጥፎ ነገር የተማርን ይመስል በክፉኛ መቀናናትና መጠላላት በመወጠር መሥራት ያለብንን ነገር እንዳንሠራ ታግደናል። ይህ ዓይነቱ ታሪክን ያላገናዘበ ትግል ግን አንድ ቦታ ላይ መገታት አለበት። እያንዳንዱ ምሁር ራሱን በራሱ በማግኘት ታሪክ ሠሪነቱንም የሚያረጋግጥ መሆን አለበት እንጂ የአገራችንን ውድቀት ለማፋጠን ከውጭ ኃይሎች ጋር መሥራት የለብትም። እርስ በእርስ መመካከርና ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ እንጂ ከውጭ ኃይሎች ምንም ዓይነት ምክር የሚጠይቅበት ምክንያት የለውም።

የኦሮሚያን ሪፐብሊክ እንመሠርታለን ብለው ደፋ ቀና ለሚሉት ኃይሎች የመጨረሻ ጥሪዬ፣ በኢትዮጵያ ምድር ታሪክን ልትሠሩ የምትችሉት በዚህ ዓይነቱ አካሔድ ሳይሆን፣ ከሌላው ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር በመመካከርና ሐሳብ ለሐሳብ በመለዋወጥ ብቻ ነው። ዓላማችንም ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሥማማና፣ ተደላድሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚያስችለውን አገር መገንባት ብቻ ነው። ስለሆነም የብሔረሰብና የሃይማኖት ጥያቄዎች የኅብረተሰብ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ አይደሉም። የአንድ ኅብረተሰብ ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። የንጹሕ ውሃ ጉዳይ፣ በቂ ʻዳይትʼን የሚሰጥ ምግብ፣ በደንብ የተሠራ መጠለያ፣ ሕክምናና ጭንቅላትን ክፍት የሚያደርግና፣ ሰው መሆናችንን እንድንገነዘብ የሚያደርገው ሁለ ገብ ትምህርት የጠቅላላው ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎችና የሕዝብ ፍላጎቶች መልስ መስጠት የምንችለው በተናጠል በመታገልና የራሴ አጀንዳ አለኝ በማለት ሳይሆን፣ በአንድ የአስተሳሰብ ዙሪያ ስንሰባሰብ ብቻ ነው። ዛሬ ሠለጠኑ የሚባሉ አገሮች ቀናውን መንገድ በመከተልና በመደማመጥ ብቻ ነው ለማደግና ዓለምን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር የቻሉት። ስለዚህም ወዲህና ወዲያ ከምንሯሯጥ ይልቅ እስቲ አንድ ጊዜ ተቀምጠን የምንሠራውን ሥራ ሁሉ እናሰላስል። አስተሳሰባችንን በሙሉ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በፍልስፍና ዙሪያ እናድርገው። ለብሔረሰብ ሳይሆን ለነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እንስጣቸው።

የዛሬውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አገዛዝ የማሳስበው ውስጥ ሆነው አደገኛ ፖለቲካ ጨዋታ የሚጫውቱ ግለሰቦችን መግታት እንዳለባቸው ነው። ፖለቲካቸው ጠቅላላውን ሕዝብ የሚመለከትና ኃይሉንም የሚሰበስብ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ የውስጥ ፖለቲካ ተብሎ የሚጠራና አንድን ሕዝብ እንደማኅበረሰብ የሚያሰባስበውና የሚያጠናክረው ሰፋ ያለ ፖሊሲ አለ። የዚህም ፖሊሲ ፍልስፍናዊ መሠረት ጠቅላላው ሕዝብ ከየት እንደመጣ፣ ለምን እንደሚኖር፣ ምን ማድረግ እንዳለበትና ወዴትስ እንደሚጓዝ የሚያስገነዝበው ነው። ይህንን ለማረጋገጥና በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ደግሞ በሳይንስና በፍልስፍና የተፈተነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ብሔራዊ ሀብትን የሚፈጥር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት።

እንደማየውና እንደምከታተለው ከሆነ አሁንም አገዛዙ የውጭ ምክርንና ትዕዛዝን በመቀበል ነው ወደፊት ለመጓዝ የሚጥረው። በተለይም እየደጋገሙ የገንዘብ ቅነሳ ማድረግና በገበያ ሥም የተካሔደውና የሚካሔደው ፖሊሲ አገሪቱን የባሰ ደሀ ነው ያደረጋት፤ ህዝባችንን በኑሮ ውድነት እንዲማረር አድርጎታል። ስለሆነም አገዛዙ ከቻይናዎችና ከራሽያኖች እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ መንግሥታት መማር አለበት። በራስና በሕዝብ ላይ መተማመን ብቻ ነው አንድን ሕዝብ ነጻና የተከበረ ሊያደርገው የሚችለው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም ከአረብ መንግሥታት ጋር ያለው ግኑኝነት በጥብቅ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው። የውስጥ ለውስጥ የሚካኼድ ሳይሆን ለውይይትና ለክርክር መቅረብ አለበት። የአገራችን ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ሕዝባችንም ጉዳይ ስለሆነ አጠቃላዩ የውጭ ፖሊሲያችን ወይም ፖለቲካችን ሕዝብ ሳያውቀው በዝግ ችሎት የሚካሔድ መሆን የለበትም። በዚህ ዓይነት ፖለቲካ ብሔራዊ ነጻነታችን መደፈሩ ብቻ ሳይሆን ባሕላዊ አገር እንዳንገነባ እንታገዳለን።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው
fekadubekele@gmx.de ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here