˝በሰብኣዊነት መቆመሩ እስከመቼ?

0
502

የአገሪቱ መመሰቃቀል
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የወሰዳቸው የፖለቲካ ማሻሻያ እርምጃዎች በብዙኀኑ ዘንድ በአዎንታ መወሰዳቸው የሚታወቅ ነው። ይሁንና በዚያው ልክ ከአንድ ዓመት የማይሻገር ዕድሜ ያስቆጠረውን እና አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች አሁንም ጉልበቱ አልጠነከረም የሚሉትን አስተዳደር የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለታቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

የፖለቲካ እና የፀጥታ ፈተናዎች ገና ከማለዳው ጀምሮ ከትግራይ ክልል የፖለቲካ ልኂቃን የተሰነዘረውን ተቃውሞ፣ በሶማሌና በኦረሚያ ክልል የነበረው ፍጥጫና የሕዝብ መፈናቀል፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂ ቡድኖች የገጠመውን እምቢታ፣ የተፈናቃዮችን በሚሊዮኖች መቆጠር፣ የአዲስ አበባ አጨቃጫቂነት መካረር፣ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል ያለውን ፍጥጫ ማንሳት ይቻላል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ፣ በቄለም ወለጋ፣ በነቀምትና በጅማ የተቀሰቀሱትን ጨምሮ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ፣ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞኖች፣ በአፋር፣ በሶማሌ ክልሎች ካለፉት ኹለት ዓመታት ጀምሮ በተከሰቱት ግጭቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ለጉዳት ከመዳረጋቸው በላይ ለአስቸኳይ ዕርዳታ ጠባቂነት መጋለጣቸው ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ መቶ ሺሕ መጠጋቱ በርካቶችን ባሳሰበ ማግስት የተፈናቃዮቹ ቁጥር የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በአዋሳ ከተማ 11ኛ ጉባኤውን በሚያከናውንበት ወቅት በፍጥነት መጨመሩ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል።

ግጭቶችንና ግድያዉን ማስቆም፣ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፤ ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነቱን ጥሶ ባሻዉ የሚጓዘውን ባለሥልጣን፣ ግለሰብ ወይም ቡድንን አደብ ማስገዛት ያለበት መንግሥት ነዉ የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ግጭትና ሥርዓት አልበኝነቱን ማስቆም ያልቻለበት ምክንያት አጠያያቂ ነው ይላሉ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት።

አንዳዶች የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ማድረግ ያለበትን እንዳያደርግ በቅርብ ደጋፊዎቹ ʻታግቷልʼ ወይም ተቀይዷል ሲሉ፣ አቅም የለዉም ባዮችም ብዙ ናቸዉ። መንግሥት እስካሁን ትዕግሥት አብዝቷል ወይም ዳተኛ ሆኗል ባዮችም ይህን አሳባቸውን ሲገልጹ ይደመጣል።

ተከትሎ የመጣው ምጣኔ ሀብታዊ መቀዛቀዝ
ቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ መጋቢት 10/2011 ʻዘኢኮኖሚስትʼ መጽሔትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከ2015 ጀምሮ ከ8 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የዕለት ጉርስ የሚያገኙት ከዉጪ በሚለመን ምፅዋት ነዉ። በዚሕ ቁጥር ላይ 3 ሚሊዮን ተፈናቆዮች ተጨምርውበታል። በድምሩ 11 ሚሊዮን ሕዝብ ተመጽዋች ነው።

በመላው ዓለም ያሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚከታተለው IDMC የተባለው ተቋም ይፋ ባደረገው ታህሳስ 2018 (እ.አ.አ) ሰነድ መሰረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 1.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሱ ከሚገኙት ሶሪያ እና የመን ካላቸው የተፈናቃይ ብዛት የኢትዮጵያ የላቀ መሆኑን ሰነዱ ይጠቁማል። መፈናቀል ባለፉት ሦስት ወራትም እንዲሁ መቀጠሉ ይታወቃል።

ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር አባልና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ የአገርን ሰላም ማረጋጋት ካልተቻለ የመጀመሪያው ተጠቂ ኢንቨስትመንት ነው ይላሉ፤ ከዘርፎች መካከል ደግሞ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት እየመራ የነበረው የኮንስትራክሽን ዘርፍ በየአካባቢው በሚስተዋሉ ግጭቶች ሳቢያ ተቀዛቅዞ፤ ግብርናውም አምራቹ ኃይል እየተፈናቀለበት በመሆኑ ምርቱን እያገኘ አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከመዋቅራዊ ለውጥ እና ከቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያ የተወሰኑ ፓርኮች ተመርቀው መከፈት ሲጀምሩ የፖለቲካ ቀውሱ ጫፍ ላይ ስለደረሰ በሚጠበቅባቸው ፍጥነትና ደረጃ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም የሚሉት ሰይድ ከዚህ በላይ የሚጠበቀውን ሚናቸውን ለመገምገም ድኅረ መረጋጋት ወቅትን መጠበቅ ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

አነጋጋሪው የጌድዖ ሕዝብ ጉዳይ
የግጭት ሰለባዎች እና ተፈናቃዮች የሌሎችም ክልሎች ችግሮች ቢሆኑም፣ በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተጠመደውን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አካባቢ ሲስተዋል የነበረው ባስ ባለ መልኩ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል። በርግጥ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በኋላ በአካባቢው እርዳታዎች በሚፈለገው መልኩ በመግባት ላይ ናቸው። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ግለሰቦችን ጨምሮ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ ከሳምንት በፊት በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋትና የዜጎች በከፍተኛ ደረጃ ለችግር መጋለጥን ተከትሎ መንግሥት ፈጣን ምላሽ አልሰጠም በሚል በአገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙኃን፣ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች፣ በፖለቲከኞችና በምሁራኑ ትችት ተሰንዘሮበታል።

መንግሥት ለሚሰነዘሩበት ትችቶች የአጸፋ መልስ ከመስጠት ይልቅ ስህተቱን አምኖ በፍጥነት በሥፍራው መገኘት ነበረበት የሚሉት የሕግ መምህሩ ደረጀ፣ ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የገነባውን መልካም ገጽታ ዳግም እንዲነጠቅ እንዳያደርገው ያሰጋል ይላሉ።

ላለፉት ሦስት ዓመታት በሰላም ዕጦት ሲሰቃይ የከረመው የጌዴዖ ዞን፣ በተለይም ከአጎራባቹ የጉጂ ዞን ጋር በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ ባለፈው ዓመት ከኹለቱም ወገን የተመዘገው የተፈናቃዮች ብዛት ከ900 ሺሕ በላይ እንደነበር መንግሥት መግለፁ ይታወሳል።

በተለይ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በምግብ እጥረት በአስከፊ ደረጃ የተጎዱ እናቶችና ሕፃናት ምሥሎች በመሠራጨታቸው በርካቶች ቁጣቸውን በመንግሥት ላይ እንዲሰነዝሩ፣ አንዳንዶችም ̋ለጌዴኦ ሕዝብ እንድረስለት˝ የሚል ዘመቻ በመክፈት የዕርዳታ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወቃል።

የክልሎች ሥልጣንና ራሳቸውን የማስተዳደር መብት፣ አስከፊ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮች ሲከሰቱ፣ በኹለት ክልሎች መካከል በሚከሰት ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ዕርዳታ የማቅረብ ብሎም ጣልቃ የመግባት ግዴታ እንዳለበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ያዕቆብ አርሶና (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥቱ ይህንን ሥልጣኑን ሲጠቀም አላየንም ሲሉም ይወቅሳሉ።

የተፈናቃዮች እርዳታ አሰጣጥና የቁጥሮች ተቃርኖ
ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዴዖ ዞን የተጠለሉ ዜጎች ፈተና የኢትዮጵያ መንግሥትን ለብርቱ ወቀሳ ዳርጎታል። ʻዘጋርዲያንʼ በመጋቢት 16/2019 (እ.አ.አ) ዕትሙ በጌዴዖ ውስጥ ያለውን ቀውስ ሲገልጸው “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ላይ ጥቁር ነጥብ ነው” ሲል አስፍሯል። በርካቶችም መንግሥት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት በጣም ዘግይቷል ሲሉ ይተቻሉ። አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጌዴዖ በመጓዝ ጉብኝት ያደረጉት ጉዳዩ በማኅበራዊ ትስሰር መድረኮች ላይ ዋነኛ ርዕስ ከሆነ በኋላ ነው ይላሉ። በተጨማሪም የሰብኣዊ እርዳታ እንዲቋረጥ የተደረገው ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ጫና ለመፍጠር ነው ሲል ʻዘ ጋርዲያንʼ ጠቁሟል።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ለወቀሳው በሰጡት ምላሽ “ይህ የመገናኛ ብዙኀን ፕሮፓጋንዳ ነው። ሰብኣዊነትና ፖለቲካ ኹለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ብለው ነበር። አገሪቱን ለማናጋት የሚፈልጉ ኃይሎች አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት እንደሆነ በመግለጽ የወጡትንም መረጃዎች ተችተዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ ትዝአለኝ ተስፋዬ መጋቢት 14 ለጀርመን ድምጽ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ቸልተኝነት እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ማከፋፈል በማቆማቸው ተፈናቃዮች የከፋ ችግር ገጥሟቸው ነበር ሲሉ እማኝነታቸውን ገልጸዋል፤ ችግር ከገጠማቸው መካከል ሕፃናት እና እናቶች ይገኙበታል ሲሉም አክለዋል።

ደረጀ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው፣ ለምግብ እጥረት ተጋልጠው ለዐሥር ወራት እየተንከራተቱ ባለበት ወቅት መንግሥት የሚዲያዎችን ጩኸት ጠብቆ መውጣቱ እጅግ አሳፋሪና አሳሳቢ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ ˝መንግሥት አሁንስ በሥፍራው የተገኘው የመገናኛ ብዙኀኑንና ዓለም ዐቀፉን የበጎ አድራጎቶች ጩኸት ሰምቶ ነው? ወይስ ኃላፊነቱ መሆኑን አምኖ?˝ ሲሉ ይጠይቃሉ።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ግን የጌዲዖ ተፈናቃዮችን በተመለከተ በመንግሥታቸው ላይ የተነሱ ትችቶችን አጣጥለዋል። “ለስምንት ወራት እርዳታ አናገኝም ነበር የተባለው ትክክል እንዳይደለ ተግባብተናል” ሲሉ ምላሽ የሰጡት ሙፈሪየያት ከአካባቢው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የተደራጁ ቡድኖች እርዳታውን በመቀማት እክል መፍጠራቸውን መጥቀሳቸው ተቅሰዋል። በተጨማሪም በዞኑ ታችኛው መዋቅር ላይ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች የእርዳታው አቅርቦት በአግባቡ እንዲዳረስ በማድረጉ በኩል በቂ ሥራ አለመስራታቸው ሙፈሪያት ጠቅሰው አልፎ አልፎ ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ አለማግኘታቸውን አምነዋል።

የሚኒስትሯን መልስ ጉራማይሌ ነው ሲሉ የገለጹት የሕግ መምህሩ ደረጀ ሚኒስትሯ ካነጋገሯቸው ተፈናቃዮች መካከል “ለስምንት ወር ምንም አላገኘንም˝ ያሉ በተናገሩበት ሁኔታ የሚኒስትሯ ማስተባበያ ውሃ እንደማይቋጥር ገልጸው፣ ˝ተግባብተናል ሲሉስ፥ በምን መንገድ ነው የሚስማሙት?˝ ሲሉ ይጠይቃሉ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ያዕቆብም በበኩላቸው መንግሥት ለምን እሰጥ አገባ ውስጥ እንደገባ እንዳልገባቸው ጠቁመው በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳጣ ከመሆኑም ባሻገር ዋጋ እንዳያስከፍሉው መጠንቀቅ አለበት ብለዋል።

ሌላው ተቃርኖ ደግሞ የጌዲዖ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ትዕግስቱ ገዛኸኝ “ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲዖ ዞን ብቻ የተጠለሉ 198 ሺሕ 977 ሰዎች ይገኛሉ” በማለት ሲገልጹ፣ ሙፈሪያት በበኩላቸው የተፈናቃዮች ቁጥር “ግማሽ ሚሊዮን አምስት ሺሕ የሚሆን ምናምን የሚባለውም ትክክል አይደለም። ቦታው ላይ የነበሩ ተፈናቃዮች አሉ። እነሱ ላይ ደግሞ የተጨመሩ ወደ 54 ሺሕ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ። ቁጥሩ በድምሩ ወደ 96 ሺሕ ገደማ ነው” ሲሉ የጽሕፈት ቤት ኃላፊውን ምላሽ ተቃውመዋል።

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የእርዳታ አቅርቦት እንቅፋቶች
ለተፈናቃዮች እገዛ የምታቀርበው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ወልዴ አየለ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ ትዝአለኝ ተስፋዬ የሚጠቅሷቸው ችግሮችና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጣቸው ምላሾች የተለያዩ ናቸው።

በገደብ ወረዳ በገደብ ከተማ እንዲሁም ጎቲቲ፣ ባንቆራ እና ጮርሶ ማዞሪያ በተባሉ ቀበሌዎች የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ተዘዋውረው የተመለከቱት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ወልዴ አየለ ተፈናቃዮቹ “እጅግ በሚያሳዝን ኹኔታ” ላይ እንደሚገኙ የተናገሩ ሲሆን፣ “በረሐብ ብቻ በየቀኑ በአማካኝ ከሦስት እስከ አራት ሰው ይሞታል” የሚሉት ቄስ ወልዴ አየለ “ከአንድ ወር ወዲህ ጭራሽ እርዳታ የሚባል ነገር የቆመበት ኹኔታ ነው ያለው ብለው ነበር። ሰው በረሐብ የተጎዳበት ኹኔታ ነው ያለው” ሲሉ የሰላም ሚንስትሯ ከመግባታቸው ከአንድ ቀን በፊት መጋቢት 14 ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ በረሃብ የተጎዱ የሴቶችና ሕፃናትን የሚያሳዩ ፎቶዎችን በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ ለማጣራት እየተሠራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሯ ተናግረው ነበር። እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በአካባቢው ከጤና እና ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር ተያይዞ ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ በቀን እስከ አምስት ሰዎች በምግብ እጥረት ይሞታሉ የሚለው መረጃ ትክክል አይደለም። ከውሃና ከጤና ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች ለመፍታትም ከጤና እና ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴሮች የተውጣጣ ቡድን አቋቁመው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ላይ በቋሚነት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ድጋፍ እያቀረበ ያለው ʻወርልድ ቪዥንʼ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች መልሶ ማቋቋም ላይ ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል። በአካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የፌዴራል መንግሥትና በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚሠሩ ሥራዎችም በአካባቢው ነዋሪዎች በኩል ወንጀለኞችን የመደበቅ ችግር መኖሩንም አንስተዋል።

ተፈናቃዮች ለከፋ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸው የሚስማሙት የዲላ ዩኒቨርሲቲው ትዝአለኝ ግን በሚኒስትሯ ምላሽ አልተስማሙም “የሰው ምግብ አጥተው ድሮ ለከብቶቻቸው ይሰጡት የነበረውን ቀለብ መመገብ ጀምረዋል” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ይገልጻሉ። ኃላፊው እንደሚሉት ተፈናቃዮች ተጠጋግቶ በመኖር ለሚከሰቱ እንደ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ማጅራት ገትር የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጠዋል።

ትዝአለኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮቹን ቸል በማለቱ እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እንዳይሰጡ መከልከሉ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው ያምናሉ፤ “ምግብ ሲከለከሉ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ” የሚል ግምት በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ አለ ሲሉ ይወቅሳሉ።

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ትዕግስቱ ግን የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ለማቅረብ ክልከላ አልተደረገም ሲሉ አስተባብለዋል።

ኃላፊው “ምዕራብ ጉጂ አካባቢ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ከተደረሰው መግባባት የተነሳ መሔድ አለባቸው የሚል አቋም ነበረ። ነገር ግን እዚያ ምቹ ኹኔታ ባለመኖሩ መመለስ አልቻሉም። ስላልቻሉ እነዚህ ሰዎች በሚሰጠው ምግብ አልተካተቱም” ሲሉ የማይረዱ ዜጎች እንደነበሩ አምነዋል።

መንግሥት በማንኛውም ሰዓት ለዜጎቹ ደኅንነት መቆም እንዳለበት የነገሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ታደለ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ጥፋተኛ አይደለሁም የሚል ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በችግሩ ጊዜ ቀድሞ በመገኘት ለሕዝብ ደራሽ መሆኑን ማሳየት አለበት። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን የሕዝቡን እምነት ያጣል፤ ሕዝቡን የመጠበቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እንዳለበት በመጠቆም። የጌዲዖ ጉዳይ ለመንግሥት ትልቅ ትምህርት መሆኑንም አክለዋል።

የጌዲዮ ተፈናቃዮች በአሁኑ ሰዓት በርካታ እርዳታዎች እየገቡላቸው ሲሆን፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እርዳታውን ስርዓት ባለው መልኩ እየተከፋፈለ እንደሚገኝ ሕትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ለማወቅ ችለናል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here