የለውጡ እርምጃ ከፍፁም እምነት ወደ ጥርጣሬ ጎዳና

0
1046

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከመጋቢት እስከ መጋቢት በሚል ርዕስ ባለፈው አንድ ዓመታት የተመዘገበውን ለውጥ የመወያያ ርዕስ አድርጎታል። ስንታየሁ አባተ የተለያዩ ምሁራን ስለ ለውጡ የተናገሩትን መሠረት በማድረግ የለውጡ እርምጃ አነሳሱ ላይ ከአነገበው ተስፋ በብዙ ምክንያቶች እየተነጠለ የጥርጣሬ ጎዳና ፊቱ ተጋርጦበታል በማለት፥ ለዚህ መንሥኤ የሆኑትን ጉዳዮች በሐተታ ዘ ማለዳ በጥልቀት ዳስሷቸዋል።

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለይም ከ2008 ጀምሮ በሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ ሲናጥ ከመክረሙ ባሻገር ኹለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እስከማውጣት መገደዱ ይታወሳል። ኢሕአዴግ አንድ ጊዜ ʻተሐድሶʼ ሌላ ጊዜ ደግሞ ʻጥልቅ ተሐድሶʼ በሚል ሳምንታትን ተሰብስቦ እየመከረ ‘ታድሻለሁ’ የሚል መግለጫ ቢያወጣም፥ በሕዝቡ የተደቀነበት ተቃውሞ ሊበርድ አልቻለም። በዚህም የፖለቲካ ምኅዳርን ለማስፋትና አገራዊ መግባትን ለመፍጠር በሚል የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት፣ ማዕከላዊ እስር ቤትን ለመዝጋት ወስኖ የሕዝቡ እምቢታ ግን ሊበርድ አልቻለም ነበር። የኋላ ኋላ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ኃይለማሪያም ደሳለኝ ˝የመፍትሔው አካል ለመሆን” በሚል ከኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣናቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ አደረጉ። ይህን ተከትሎም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኃይለማሪያምን ቦታ ተኩ። መጋቢት 24/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በጠቅላይ ሚንስትርነት ተሰየሙ። እነሆ ይህ ከሆነ አንድ ዓመቱን ሊደፍን ሦስት ቀናት ብቻ ቀርተዋል። በአንድ ዓመቱ የዐቢይ አስተዳደር ሕዝቡ በኢትዮጵያ መፃዒ ዕጣ ፈንታ ላይ ብሩህ ተስፋም፣ ተስፋ የመቁረጥም ስሜቶችን እያስተናገደ ዛሬ ላይ ደርሷል።

የለውጡ መልክ በምሁራን አንደበት
የዐቢይን አስተዳደር የአንድ ዓመት ጉዞ ስኬትና ተግዳሮት የተመለከተ የኹለት ቀናት ʻአዲስ ወግʼ የሚል ሥያሜ የተሰጠው ውይይት መጋቢት 13 እና 14 በሸራተን አዲስ ሆቴል መካሔዱ ይታወሳል። በውይይቱም 17 ጽሑፍ አቅራቢዎች ʻየኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ፤ የታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ተግዳሮትʼ፣ ‘የኢትዮጵያ የውጪ ፖሊሲና የአፍሪካ ተሳትፎ አመቻችʼ፣ ʻየኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሥራ ፈጠራና ማኅበራዊ አካታችነትʼ እና ʻየዴሞክራሲ ግንባታና ማፅናት በኢትዮጵያ፤ ተግዳሮትና ቀጣይ አካሔዶችʼ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ክርክር ተደርጎበታል።

በኢትዮጵያ ከተከሰቱ የፖለቲከ ለውጦች መካከል አንዱ የዛሬ ዓመት የተከሰተው ለውጥ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አበባው፥ አያሌው ከዚህ ቀደም ከነበሩ ለውጦችም የተለየ ስለመሆኑ ያነሳሉ። መለያውን ሲያስረዱም ከዚህ ቀደም የነበሩ ለውጦች በውጪያዊ ጫና የመጡና ለውጡም በውጭ ኃይል የሚተካ እንደነበር በማስታወስ የአምናው ግን ከውስጥ የመጣ ነው ይላሉ። ይህም እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚወሰድ ያክላሉ። በበፊቶቹ ለውጦች ʻለውጥ አመጣንʼ ይበሉ እንጂ መሪዎቹ ራሳቸው ለውጥ አቀንቃኝ አልነበሩም ሲሉም ያብራራሉ። በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በነበሩ ለውጦች የነበረው አካሔድ የነበረውን ደምስሶ ወይም ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ አዲስ ስርዓት የመትከል አካሔድ አንደነበር በማስታወስ ዐቢይን ወደፊት ያመጣው ለውጥ አብዮታዊ በሚባል መንገድ ሙሉውን አፍርሶ በአዲስ የመተካት ሳይሆን ያለውን አሻሽሎ የማስቀጠልን ስልት የተከተለ መሆኑንም አበባው ይገልጻሉ።

አበባው ሲቀጥሉም የ1983ቱን ለውጥ ጨምሮ ከዚያ በፊት የነበሩ የአገዛዝ ስርዓቶች ወደ ፊት ሲመጡ የፖለቲካ አሸናፊና ተሸናፊ ነበራቸው በማለት በአሁኑ ለውጥ ግን አሸናፊና ተሸናፊ የለም ይላሉ። በዚህ ሐሳብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፌደራሊዝምና ሰብኣዊ መብቶች መምህሩ ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) አይሥማሙም። አሁንም ቢሆን የፖለቲካ ተሸናፊና አሸናፊ አለ የሚሉት ሲሳይ፥ ቀድሞ በነበሩት የኢሕአዴግ ዓመታት የበላይ የነበረው ሕወሓት በአሁኑ ለውጥ ተሸንፏል፣ ተገፍቷልም፤ ስለዚህ አሸናፊና ተሸናፊ የለም የሚለው አያስኬድም ሲሉ ይናገራሉ።

አበባው በሌላ ጎኑ የለውጡን መልክ ሲያስረዱ ከዚህ ቀደም በነበሩ ለውጦች የተሸነፈውን ወይም ቀድሞ ሥልጣን ላይ የነበረውን አካል የማሰር፣ ወይም ተሸናፊውም እንደ አዲስ ትግል ውስጥ የመግባት አካሔድ ነበር ይላሉ። የእነ ዐቢይ ለውጥ በአንፃሩ ነባሩን ከማሰርና ነባሩም ትግል ውስጥ ከመግባት ይልቅ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ የተሻለ ትኩረት አድርጎ መሥራቱም ሌላው መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ያምናሉ።

ለታሪክ ተመራማሪው አበባው ሌላው የለውጡ መልክ የፖለቲካ ተዋናዮች የበዙበት፣ ለውጡም ከራስ አልፎ የጎረቤት አገራትና ቀጣናዊ ጉዳዮችን ትኩረት የሰጠና የዳሰሰ ነው። ለአብነትም ኤርትራን ጨምሮ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጥሩ መግባባትን መፍጠር መቻሉን ያነሳሉ።

የፖለቲካ ምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ እአአ 1916፣ 1974፣ 1991 የተካሔዱ ለውጦችን በማንሳት ሁሉም ለውጦች ከዓለም ዐቀፋዊ ሁነቶች ጋር ተያያዥነት እንደነበራቸው፣ በሌላ አገላለጽ በለውጦቹ ወቅት ሌሎች ዓለም ዐቀፋዊ ጫናዎች በተቀሩ አገራትም ለውጥና አመፃ በመቀስቀስ ተመሣሣይ ዓይነት አካሔዶች አንደነበሩ ያስገነዝባሉ።

ዲማ ስለዛሬ ዓመቱ ለውጥ የተለየነት ሲናገሩም የለውጡ ፍላጎትና ስሪት አገራዊ ብቻ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ። በሌላ አባባል በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የሚያነሳሳና የሚያስገድድ ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳይ አልነበረም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያዊያን በውስጣቸው ለውጡን አምጥተዋል። በሕዝብ ግፊትና አመፅ የመጣ ቢሆንም ከውስጥ (ከኢሕአዴግ ቤት) የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ለውጡ ከውስጥ የመጣ እንደሆነ ከሚገልጹት አበባው ጋር ይስማማሉ። ቀዳሚዎቹ ለውጦች በወታደራዊ ኃይል ይደረጉ የነበረ ሲሆን የአምናው ግን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የአመራር ሽግግር የተስተዋለበት መሆኑንም ዲማ በበጎነትና በተለየ መልክነት ያነሱታል።

ሰሚር የሱፍ (ዶ/ር) የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ናቸው። እንደ እርሳቸው እምነት ለውጡ በጎ ቢሆንም አሁንም መንግሥት መራሽ ለውጥ ብቻ በመሆኑ ሥጋት እንዳለው ያነሳሉ። ይህንን ሲያስረዱ ለውጡን ሊያስቀጥሉ የሚችሉና የነበረባቸው የሲቪል ማኅበራት መክሰማቸውን በማንሳት ነው። ሌላው የለውጡ መልክ የተለመደን አምባገነናዊ ውርስ ይዞ ያለ መሆኑ ነው ይላሉ ሰሚር። ይህም ማለት ያለፈን ችግር አውልቆ ያለመሔድና ያለፈው ችግር ጥላ እያጠላ የመጓዝ ልምድ ነው ይላሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብዙ ቂም መኖሩን በመግለጽ ይሔን አራግፎ መሔድ ካልተቻለ ሽግግሩን ማሳካት አዳጋች መሆኑን በመግለጽ፥ ከኋላው ያለፈ ነገር ይልቅ የወደፊቱ ላይ ማተኮርን ይመክራሉ። ዲማ በበኩላቸው አጥፍተዋል በሚባሉት ላይ እስከመቼ ዓመታት ነው ወደኋላ ተመልሶ ተጠያቂነትና ይቅርታን መተግበር የሚቻለው የሚለው በራሱ አጨቃጫቂ ነገር መሆኑን በመግለጽ ሰክኖ ማሰብ እንደሚፈለግ ይመክራሉ።

አስተያየት ሰጪዎች፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንደሚስተዋለው፣ ቀድሞ ከነበረው ተስፈኝነት እየለዘበ መጥቶ፥ ተቺዎችና ለውጡንም በጥርጣሬ የሚመለከቱ፣ በጥቅሉ ሲታይም “የዐቢይ መንግሥት ሲሸውደን ነበር ወይ?” የሚሉ ጠያቂዎች ድምፃቸው እየጎላ ነው ይላሉ። ይህ እውነት ከሆነ ምክንያቶቹ ምን ይሆኑ?

የኢሕአዴግ ውስጥ ተቃርኖ
ለጥርጣሬዎቹ አንዱ መነሻ ደግሞ በራሱ በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለመናበብና የተቃረነ አቋም መታየት እንደሆነም የሚያነሱ አሉ። መንግሥት በሙስናና የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በመጠርጠር በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚፈልጋቸው ግለሰቦች፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ፣ በሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ወይስ አይሻሻል፣ በፌደራሊዝም ስርዓቱ ቅርፅና አተገባበር፣ በሥልጣን ቦታዎች ክፍፍል እና መሰል አጀንዳዎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እርስ በእርሳቸው የመቃረንና የተለያየ አቋም ይዞ የመገኘት አካሔድንም ለማሳያነት ያቀርባሉ።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ቧያለው ግን በዚህ አይስማሙም። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የነበረውን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት የጤነኛ ፖለቲካና አስተሳሰብ ማሳያ እንጂ የክፍፍል ማረጋገጫ እንደማይሆን አስረድተዋል። “በእርግጥ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በየፊናቸው እርስ በእርሱ የሚጣረስ የሚመስል ሐሳብ ሲሰነዝሩ ሲሰማ ቅራኔ የተጠፈጠረ ይመስላል” ያሉት ዮሐንስ፥ “በኢሕአዴግ የቀድሞ ዘመን ልምድ የተለየ ሐሳብ ስለሚታፈን ሕዝቡ አይሰማም ነበር” ይላሉ። ያ ባሕል አሁን ስለተቀየረ የልዩነት ሐሳቦች መደመጣቸው፥ የሠለጠነ የፖለቲካና የአስተሳሰብ መገለጫ እንጂ የሕዝብ መሸበሪያ ሊሆን እንደማይገባውም ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። ሐሳብን ማፈን እንደማያዋጣና ሕዝብን ለአመፅ ዳርጎ የሚያመጣው ውጤት የከፋ እንደሚሆን የሚያምኑት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራና ጤናማ መሆኑንም ያነሳሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ሳይቀር የሚለጥፏቸው ጽሑፎች በኢሕአዴግ ውስጥ ጠንካራ ትስስር አለ ለማለት እንደማያስደፍር የሚያነሱ አሉ። ይህ ዓይነት የተራራቀና ጥራዝ ነጠቅ የሆነ የአመለካከትና ግለሰባዊ አቋም ልዩነት ባለበት ኢሕአዴግ ውስጥ ዮሐንስ እንደሚሉት ጤናማ ግንኙነትና አንድነት አለ ለማለት አይቻልም የሚሉ አስተያየቶች አሉ።

አበባው “ሕዝብ ዝም ብሏል ይህ ደግሞ አደጋ ነው። ለውጡን እስከ ነሐሴ ሕዝቡ ደግፏል፣ አሁን ግን ዝም ብሏል። በፌስቡክ የሚታየው ትርምስም ‘የኤሊቶች’ እንጂ የሕዝቡ አይደለም፤ ሕዝቡ ዝም ነው ያለው። ይህ ደግሞ አደጋ አለው ትኩረት ይፈልጋል” ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።

ሰሚር (ዶ/ር) በኢሕአዴግ ውስጥ ወጥነት የለም ይላሉ። አሁን ላይ የቡድን ሽኩቻ ገኖ ስለመውጣቱም ያስረዳሉ። የተከፈተውን የፖለቲካ ነጻ መድረክ በመጠቀም የተለያዩ ቡድኖች ፅንፍ በመውጣት የግላቸውን ወይም የቡድናቸውን ጥቅም ፍላጎት ለማስከበር እየጣሩ ነው ይላሉ። ሰሚር “በዚህ ደግሞ ትልቁን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እየጎዱትና አደጋ ላይ እየጣሉት ነው” ሲሉ ያሳስባሉ። ይህ “ብሔር ላይ ያተኮረ ክፍፍል ደግሞ መጥፎ አደጋ ይዞ መጥቷል” ነው የሚሉት። ተገዳዳሪ የሚባሉት ኃይሎችም ቢሆኑ የረጅምና የወል አገራዊ ግቡን እየረሱ መሔዳቸውን የሚገልጹት ሰሚር፥ በመንግሥትም በኩል ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ አለመዘጋጀቱ ለሚታዩ ስጋቶች አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።

ዲማ በበኩላቸው፣ እርሳቸውን አገር ቤት ያመጣቸው እና ለውይይት ያበቃቸው ለውጡ መሆኑን ቢገልጹም ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ ላይ ጉድለት እንዳለ አልሸሸጉም። አበባው አያሌው ደግሞ ለውጡን የሚሸከሙና የሚስቀጥሉ ተቋማት አለመኖራቸውን ለማስታወስ “የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትም ባለፉት ዓመታት ድባቅ ተመትተዋል” ይላሉ።

በእርግጥ መንግሥት የጀመራቸውን የተቋማት ግንባታና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማብዛት ብሎም ለማጠናከር የሚያግዙ ሕጎችን ከአፋኝነት ባሕሪያቸው ለማላቀቅ በማሻሻያ ሒደት ውስጥ መሆኑን ምሁራኑ አይክዱም። የሰላም ሚንስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ለሥጋቶቹ መልስ ሲሰጡ ጊዜው ገና አንድ ዓመት ብቻ መሆኑን በማስታወስ ጊዜ እንደሚፈልግ ሲያነሱ አስተያየት ሰጭዎቹና ምሁራን በበኩላቸው በብዙ ችግር ውስጥ የሚኖርን፣ በተለይም ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ታገሱኝ ማለት ቅቡልነት እንደማይኖረውና ቅድሚያ የሚሰጣቸው እርምጃዎች ቀድመው እንዲፈፀሙ ያስገነዝባሉ። ዐቢይ ደግሞ “ብዙዎች አመራርነት አልቆ የሚጀመር ይመስላቸዋል፤ መርተው ስለማያውቁ” በማለት የፍኖተ ካርታ ጥያቄውን አጣጥለውታል።

የፖለቲካ ማኅበራት መፈልፈል
የዛሬ ዓመት በኢሕአዴግ ቤት የተደረገው ሽግግር ካሳያቸው ለውጦች መካከል አንዱ እጅግ የበዙ የፖለቲካ ማኅበራት (ፓርቲ፣ ንቅናቄ፣ ድርጅት፣ ወዘተ) እንዲፈለፈሉ ማድረጉ ነው። ከዚህ ቀደም በውጭ አገር ሆነው ይታገሉ የነበሩ፣ በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም አሸባሪ የተባሉና መሪዎቻውም በሌሉበት የሞት ፍርድ የተበየነባቸውን የፖለቲካ ኃይሎች የዐቢይ አስተዳደር በይቅርታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና ነፍጥ አውርደው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲታገሉ መፈቀዱን ብዙዎች ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት ማሳያ ያደርጉታል። በተያያዘ ያለፈው አንድ ዓመት ቁጥራቸው የበረከቱ የፖለቲካ ማኅበራት የተመሠረቱበትና አሁንም የቀጠለ ጊዜ ነው። በዚህም አሁን ኢትዮጵያ የ107 ፖለቲካ ማኅበራት ባለቤት ሆናለች። ይህን የሚያስተውሉ አስተያየት ሰጪዎች ለአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንደማለት መሆኑን በማንሳት እስከመሳለቅ ደርሰውበታል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚዴቅሳ ከወራት በፊት ለአዲስ ማለዳ አንደበት አምድ እንግዳ ሆነው በቀረቡበት ወቅት ስለፖለቲካ ማኅበራቱ መብዛትና መሥፈርት አሟይነት ተጠይቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን የሚመለከቱ ሕጎች እየተሻሻሉ መሆኑን በመጥቀስ፥ ሲጠናቀቅ (እስካሁንም ተጠናቅቆ አልፀደቀም) ምን ያህሉ መሥፈርቱን ያሟላሉ? ምን ያህሉስ አያሟሉም? የሚለው ታውቆ በሕግ የሚቀጥሉና የሚፈርሱት እንደሚታወቁ መናገራቸው ይታወሳል። በወቅቱ ግን 60 የሚጠጉ የክልልና አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛትን እንደ ትልቅ አጀንዳ የማይወስዱ ምሁራን በበኩላቸው የፓርቲዎቹን መብዛት ኢሕአዴግ (ራሱ የፈጠራቸው አሉ ብለው የሚያምኑም አሉ) አንድም ሐሳብ ለመከፋፈል ወይም ጠንካራ የፖለቲካ ተገዳዳሪ ድርጅት እንዳገጥመው፣ ኹለትም የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቷል ለሚል ሪፖርት እንደሚጠቀምበት ያስረዳሉ።

አበባው አያሌው “የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁሞ ቀር መሆናቸውን” በመግለጽ ይህም የለውጡ አንድ እንቅፋት ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ዲማ ነገዎ ደግሞ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጉናል” ካሉ በኋላ፥ አሁን ‘ፓርቲ ነን’ ብለው የሚያምኑ ድርጅቶች እውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲነትን ቁመና ወይም ስብዕና ይወክላሉ ወይ ከተባለ ከሥም የዘለለ ሚና እንደሌላቸው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ገዢው ኢሕአዴግ ራሱ ከሥልጣን ቢወርድ እንደ ፖለቲካ ኃይል ኅልው ሆኖ መቀጠሉን የሚጠራጠሩት ዲማ እንደ መፍትሔ የተደራጁና ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው የፖለቲካ አደረጃጀቶች ሊፈጠሩ ይገባል ይላሉ።

ከወራት በፊት በፍሬድሪክ ኧርበርት ሲቲፍተንግ ተዘጋጅቶ በነበረው፣ በኢትዮጵያ የለውጥ ማዕቀፍ የዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን የለተመለከተ ውይይት ላይ ሲነሱ ከነበሩ ሐሳቦች አንዱ የተቃዋሚው ጎራ ፖለቲካ አደረጃጃቶች ሲመሠረቱ ከነበሩበት ችንካር መላቀቅ አለመቻላቸው፣ ራሳቸውንም በየጊዜው ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እየቃኙ አለማሳደጋቸው ነው የሚለው ይጠቀሳል።

ብዙ የፖለቲካ ማኅበራት የጠራ ፕሮግራም፣ ከገዥው ኢሕአዴግ የሚለዩበትና ለሕዝቡ የሚያቀርቡት አማራጭ ስለሌላቸው መንግሥት የሚለውን ሁሉ መቃወም እንጂ የተሻለው አማራጭ ይህ ነው ብለው ሲናገሩ አይታዩም በሚልም ይወቀሳሉ። ለዚህም ይመስላል አሁን “የምኅዳሩን መስፋትና የሐሳብ ነጻነት መከበርን” ተከትሎ ፅንፍ በመውጣት አገርን አጣብቂኝ ውስጥ፣ ሕዝብንም ስጋት ውስጥ እያስገቡ ነው በሚል የሚተቹት። ዐቢይ ደግሞ በየአደባባዩ ያለውን ፉከራና መዛዛት ወደ አዳራሽ ውስጥ አምጥቶ በውይይት መፍታት ካልተቻለ አደጋ መሆኑን ያሳስባሉ። ርዕሰ ብሔሯ ሳሕለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ከምንም ጊዜ በላይ በውይይት፣ የሐሳብ የበላይነትና ዕውቀት (አብርኆት) ልንመራ የሚገባበት ወቅት መሆኑን በማስገንዘብ ለመታረም ያለው ዕድል ጠባብ መሆኑን አፅንዖት ይሰጡታል። ለዚህ ደግሞ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና መላው ሕዝብ መደማመጥ አንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።

የደቦ ፍርድና የዜጎች መፈናቀል
ከላይ እንደተገለጸው የቡድኖች መቃቃርና በየአቅጣጫው ባለው የራስ ፍላጎትን (የኢሕአዴግ ድርጅትና ባለሥልጣናትን ጨምሮ) ብቻ የማድመጥ አካሔድ በየአካባቢው የዜጎች ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሕጋዊና ሞራላዊ መብቶች እንዲጣስ እየሆነ ነው። በርካቶችም ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ፣ የሕግ የበላይነትም ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊነት እየራቀው ነው ሲሉ መንግሥትን የሚከሱ በዝተዋል።

ሳሕለወርቅ የጉልበት ዘመን አብቅቶ በውይይት ማመን ካልተጀመረ አደጋው ከዚህ የከፋ እንደሚሆንም ያስጠነቅቃሉ። በግጭቶች ሳቢያ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የሚገልጹት ተቺዎች የዐቢይ አስተዳደር የኀይል የበላይነቱን አጥቷል በማለት ይከራከራሉ። ዐቢይ ግን “እስር ስለሰለቸን፣ ለዚያ ነው የታገስነው” በማለት የኀይል የበላይነቱን መንግሥታቸው አለማጣቱን ይከራከራሉ። በዚህ ሐሳብ የማይሥማሙ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አገር እስኪፈርስ መታገስ ምን ይሉታል ሲሉ ይተቻሉ።

የዓረና ትግራይ ሊቀመንበሩ አብርሃ ደስታ ሕግን ከማስከበር ጋር ተያይዞ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የፌደራሉ መንግሥት ሕግ ማስከበር አለቻለም፣ መንግሥት ባለበት ነው ብዙዎች እየተፈናቀሉ፣ ክልሎችም ለእርስ በእርስ ጦርነት እየዳዳቸው ያሉት ይላሉ።

“ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚለውን አቋማቸውን ለአንድ ዓመት በተደጋጋሚ ሲገልጹ የከረሙት ዐቢይ ሲመልሱም ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አካሔድ መቆም ካልቻለ ግን መንግሥት ጥፋተኞችን ለማሰርም ቢሆን እንደማይደራደር አስጠንቅቀዋል። አገርን እያሸበረ ያለው ፌስቡክ ላይ የሚዘራው የጥላቻ ዘር ነው ለሚለውም መንግሥት የፀረ ጥላቻ ንግግር ሕግን እያረቀቀ መሆኑን በማስታወስ ጉዳዩን በሕግ ፈር ማስያዝ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ከፌስቡክ (ድርጅቱ) ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ዐቢይ ግልጽ አድርገዋል።

የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ
ጠቅላይ ሚንስትሩ በተሾሙ ወራት ውስጥ የመጀመሪያውን ማብራሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሰጡ ቁጥሩን መግለጽ አስፈላጊ ባይሆንም ወደ ሥልጣን ሲመጡ የመንግሥት ካዝና የተመናመነና የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ ጥቂት እንደነበር አንስተዋል። ይሁንና በጥቂት ወራት ውስጥ ከተለያዩ አገራት በተገኙ ድጋፎች ክምችቱን ከፍ እንዳደረጉ ሲገልጹም ከነበረው የ330 በመቶ ዕድገት እንዲኖረው ማስቻላቸውን አብራርተው እንደነበር ይታወሳል። ይህም ሆኖ አሁንም የምጣኔ ሀብት ቀውሱ ከኢትዮጵያ አናት ላይ አለመውረዱን ምሁራን ይገልጻሉ። የምጣኔ ሀብቱ ዳፋ ብዙ መዘዞች እንደሚኖሩት በመጥቀስም ለሚስተዋለው ስርዓተ አልበኝነትና የሕግ ጥሰቶችም ተጠያቂ የሚያደርጉት አሉ። ኢትዮጵያ መረጋጋት እንዲሳናትም ምጣኔ ሀብቱ መሸከም ያቃተው በርካታ የሥራ አጥ ቁጥር መኖርን የሚያነሱት ብዙዎች ናቸው።

ዐቢይ በቅርቡ ለምክር ቤት አባላት ሲገልጹ በየዓመቱ ኹለት ሚሊዮን ሥራ አጥ እንደሚፈጠር ግን ደግሞ ሥራ የሚያገኘው ግማሹ ብቻ እንደሆነ አንስተዋል። መንግሥት ከኹለት ዓመት በፊት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ የነበረ ቢሆንም በወጉ ሥራ እንዳልተፈጠረበትና ለሥራ ፈላጊዎቹም እንዳልደረሰ በተለያዩ የመንግሥት ግምገማ መድረኮች ሲተች ነበር። ይሁንና በቅርቡ ከተመደበው ገንዘብ 9 ቢሊዮን አካባቢው ለክልሎች መሰራጨቱን ሪፖርት ወጥቷል። ታዲያ ገንዘቡ ወዴት ሔዶ ነው ሥራው ያልተፈጠረው ለሚለው ክልሎች የተንዛዛ የብድር ስርዓትን በመዘርጋታቸው ወጣቶች በቀላሉ ተደራጅተው ወደ ሥራ ለመግባት ዳገት ስለሆነባቸው ነው የሚል ምላሽ ከመንግሥት ሲሰጥ ከርሟል።
እንደ ዲማ እምነት የደኅንነትና ፀጥታ (ግጭትና መፈናቀል)፣ የምጣኔ ሀብት ችግር፣ ቀጣናዊ አለመረጋጋትና ዴሞክራሲ ያልተገነባበት ቀጣና መሆኑ ተደማምሮ ኢትዮጵያንም ሆነ ቀጣናውን ውጥረት ውስጥ ከመክተቱም በላይ ዴሞክራሲን ለመገንባት ፈተና ነው።

ሰሚር የሱፍ (ዶ/ር) ደግሞ በኢትዮጵያ አሁንም ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ፣ ብዙ ድሃ ሕዝብ፣ ኢፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል በመኖሩ ለውጥና ሽግግርን ማሳካት ይከብዳል የሚል እምነት አላቸው።

ተስፋ ሰጪው ዲፕሎማሲ
በመግቢያው እንደተነሳው ለውጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤትንም የመቃኘት፣ ዲፕሎማሲንም የማጠጠናከር ሒደትን በመተግባር ስኬታማ መሆኑ ተመስክሮለታል። በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረው የ20 ዓመታት ፍጥጫና መወቃቀስ በሰላም መተካቱ ትልቁ እመርታ ሆኖ ይነሳል። ዐቢይ ላይ የተንተለጠለ ቢሆንም የአፍሪካን ቀንድ አንድ ለማድረግ የተኬደው ጉዞና የተገኙ የለውጥ ጭላንጭሎችም ለዐቢይ አስተዳደር በአንድ ዓመት የተገኙ ስኬቶች ተደርገው በዲፕሎማሲና የመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ ተንታኞች ይነሳሉ።

ይህም ሆኖ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ግለሰባዊ (የኹለቱ መሪዎች) ሆኗል የሚል ትችት እንደሚነሳ የገለጹት ዐቢይ ለዐሥርት ዓመታት ያልተሳካን ዕርቅ በማሳካታቸው ውዳሴ ሲገባቸው ከንቱ አቅላይነት የተሞላበት ትችት መሰንዘሩን መልሰው ይተቻሉ። ከሱዳንም ጋር ቢሆን ተመሳሳይና የተቀራረበ ግንኙነት መፈጠሩን በመግለጽ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ ከሁሉም ጎረቤቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ስለተፈጠረ ብቻ በአንድ ጊዜ የማካለሉ ተግባር ይከናወናል ብሎ ማሰብ እንደማያስፈልግም ይገልጻሉ።

ምሁራን ኢትዮጵያ አካባቢዋ ሰላም ካልሆነ እሷ ብቻ ሰላም ብትሆን ምን ይረባታል በማለት ይጠይቁና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ዐቢይ የሔዱበት ፍጥነትና ትጋት ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን ያነሳሉ። ግን ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገራት እርስ በእርስ የድንበር፣ የግዛትና የተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የያዙ መንግሥታት የሌሉባቸው መሆኑን በማንሳትም ትብብርና ቀጠናዊ ውኅደትን በቀላሉ ለማሳካት እንደሚቸግር ያስረዳሉ።

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተመራማሪው ማርቲን ፕላውት ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው የጽሑፍ ምልልስ በቀጣናው ብዙ ያልተፈቱ የፍላጎት ተቃርኖዎች መኖራቸውን በማስታወስ ፈተናዎች የበዙበት ቀጣና እንደሆነ አስገንዝበዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ትብብርርን ለመፍጠር የምታደርገው ጥድፊያ ከምዕራባዊያኑ ያደጉ አገራት እጅ ምን ያክል የፀዳ ነው የሚለውም ትኩረት እንደሚሻ ይገልጻሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የጻፉ ምሁራን አዲሱን ትብብር ማድነቅ ተገቢ ቢሆንም ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካና በእሷ ከሚዘወሩ (ወዳጆቿ ከሆኑ) የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሪነትና ፍላጎት የፀዳ ነው የሚል የዋኅነት እንደማያዋጣም ያሠምሩበታል። በተለይም ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ያላት የጠበቀ ወዳጅነት ከጀርባው በእጀ ረጅሟ አሜሪካ ላለመዘወሩ ምን ዋስትና አለ ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ በርካታ ገንዘብ አበዳሪዋ ቻይናስ (የበላይ ለመሆን በሚደረግ ፍትጊያ የአሜሪካ ባላንጣ መሆኗን ልብ ይሏል) ምን አቋም ይኖራት ይሆን ሲሉ ኢትዮጵያ ውስብስቡ ቀጣና ውስጥ ስለመሆኗ ያስገነዝባሉ።

ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር ጋር በሚኖራት ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የምትሰጥበትና በሉኣላዊነቷ የምትደራደርበት አንዳችም ምክንያት እንደማኖር የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው እየተከለሰ መሆኑን በመጠቆምም ጥልቅ ምክክር ተደርጎበት ሲያበቃ ፀድቆ የአገሪቱ የዲፕሎማሲ መመሪያ እንደሚሆን አክለዋል።

ለኢትዮጵያዊያን ምን ይሻላል?
በጉልበት ለማሸነፍ ከመሮጥ መደማመጥና በውይይት ማመን ከመቼው ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ መሆኑ ይነሳል። በተለያዩ ወገኖች የአመለካከትና የሕልም መራራቅ መኖሩን የሚያነሱት ሰሚር የሚያቀራርቡ ስርዓቶችን መፍጠር፣ ቡድኖችንም እኩል ውክልናና ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። አበባው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እርሾ የተጣለው በ150 ዓመት በፊት መሆኑን በማስታወስ ዛሬም ግን ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ጥያቄ መሆኑን ይገልጻሉ። ስለሆነም ሰክኖ ማሰብ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ዲማም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፣ ከ50 ዓመት በፊት ይነሱ የነበሩ የዴሞክራሲ፣ የቋንቋ፣ የብሔርና ሌሎች ጥያቄዎች ዛሬም እየተነሱ መሆኑን በመግለጽ ዛሬም እዚያው ላይ ነን ሲሉ ቁጭታቸውን ያጋራሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያ እስካሁን ለምን የሰከነ የመንግሥት ስርዓት አልተገነባም፣ ልማትና ዕድገትስ ስለምን አልመጣም የሚለውን በአንክሮ እየጠየቁ በስክነት ለመፍትሔ መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ሰሚር ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ስርዓት የምናገኘው ከውጭ በመቅዳት ሳይሆን በጥሞና እሳቤና ምክክር ከራስ ጋር ሰምሮ ሊሔድ የሚችልን የራስ ተሥማሚ ስልት በመቀመር ነው ሲሉ ይመክራሉ።

የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁሯ ኢክራም መሐመድ እንደ ሕዝብ አንዳንድ ጊዜ ጥያቄያችን ምን እንደሆነ አናውቅም ይላሉ። ግላዊ ማዕከልነትን የሚያጠነጥኑ ጥያቄዎች ከመብዛታቸው ባሻገር የጋራውን እየተው የራስን ብቻ ይዞ የመጮህ አባዜ በዝቷል ሲሉም ያክላሉ። ለራሳችን የምንጠነቀቀውን ያህል ለሌሎች ወይም ለጋራ ጉዳዮች ቦታ ያለመስጠት ብልሽት መኖሩንም ያነሳሉ። ኢክራም የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት እንዲቻል እንዲፋጭና እንዲያሸንፍ ሊፈቀድለት የሚገባው ሐሳብ ብቻ ነው የሚለውን ያሠምሩበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here