የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ግኝቶች – በሴቶች

0
1067

በአውሮጳውያን ቀነ ቀመር፣ ‘ማርች ኤይት’ የሴቶች ቀን እየተባለ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ይከበራል። ይህንንም ተከትሎ በዚህ ወር በርካታ ሴቶችን የሚመለከቱ ዝግጅቶች በኢትዮጵያም በዓለም ዐቀፍ መድረኮችም ተዘጋጅተዋል። ቤተልሔም ነጋሽ አንዱን እንደመነሻ በማድረግ የሴቶችን የፈጠራ አበርክቶ በጨረፍታ ያስቃኙናል።

 

በዚሁ በፈረንጆቹ ‘ማርች’ ወር በተሳተፍኩበት “ሚዲያና ስርዓተ ፆታ፦ የሴቶች ውክልና (ቀረፃ) በኢትዮጵያ” የሚል ይዘት ያለው መድረክ አንዲት ከአንዱ የቢራ ፋብሪካ የመጣች ተሳታፊ “ፋብሪካችን ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት ፕሮጀክት ቀርፆ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ነው። ለሚዲያ ፕሮግራም ለማሠራት በተደጋጋሚ ብንሔድም ሊሠሩልን አልቻሉም። ምን ትመክሩናላችሁ?” አለች። ከሐሳብ አቅራቢዎች አንዷ የነበረች ተናጋሪ ምን አለች “በመጀመሪያ የምትሠሩትን ማስታወቂያ ሴቶችን ያካተተ እንዲሆን አድርጉ። ለምሣሌ “ያዝ” ብቻ አትበሉ”።

እውነት ለመናገር አሁን በቴሌቪዥን ጨርሶ እንዳይተዋወቅ ታግዶ እፎይ አልን እንጂ ቢራው ሁሉ እኔ እበልጥ መከራ ነበር። በዚሁ መሐል አስተዋዋቂውም፣ ተጠቃሚውም ቃላቱም ሁሉም ለወንዱ ነው። ይህንን ለምን አልኩ? ቢራን የፈለሰፉት ሴቶች መሆናቸውን ሰምቼ! አዎን ዛሬ የወንድ መጠጥ ሊሆን የበቃው የቢራ ፈጣሪዎች ሴቶች ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍረካዊው ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ “ዴይሊ ሾው ዊዝ ትሬቮር ኖህ” ላይ በተለመደ ቀልድ የተመላበት አቀራረብ አንዲት ኮሜዲያን ሲጋብዝ የዚያ የዕለቱ ፕሮግራም አንድ ክፍል ርዕስ “ወንዶች የሚወዷቸው በሴቶች የተፈለሰፉ ነገሮች” የሚል ነበር። የመጀመሪያው ምሣሌ ደግሞ ቢራ ነው። ቢራ ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት በሜሶፖታሚያ በሴቶች የተፈለሰፈ መጠጥ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት “የሴት መጠጥ” ተብሎ ይታወቅ ነበር። የሱሚሪያ የጠመቃና የቢራ አማልክት ኒንካሲ በሴት መጠራቷም ለዚሁ ይመስላል። እንደምታውቁት በአገራችንም የጠመቃ ንግሥቶች በአብዛኛው ሴቶች ናቸው። ከጠላ መጥመቅ እስከ ጠጅ መጣልና አረቄ ማውጣት አያቶቻችን ተክነውበታል። ዘመናዊነት እያስቀረው የእዝን ሳይቀር ጠጅ ወደ ቢራ ዞሯል።

የዚህ ዓመት የሴቶች ቀን መሪ ቃል ከሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ፈጠራ (innovation) ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወንዶችን ያስደሰተ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ በሴቶች የተበረከቱ ግኝቶችን እንደምሳሌ እንይ፦

የመስታወት መጥረጊያ እና የመኪና ማሞቂያ
በዝናብ ወቅት በኒውዮርክ ጎዳና ለማየት የተቸገሩ አሽከርካሪዎች አንገታቸውን ብቅ በማድረግ ጭጋጉ ሲብስም ከመኪና ወርደው የፊት መስታወቱን በመጥረግ ሲቸገሩ ያየችው አሜሪካዊቷ ሜሪ አንደርሰን የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ ብላ አሰበች። በወቅቱ መኪና የማትነዳ ቢሆንም ከመኪናው ውስጥ የሚታዘዝ የመስታወት መጥረጊያ ከመፈልሰፍ አላገዳትም። ዓመቱ እንደ አውሮፓውያኑ 1903 ነበር። ሌላው ግኝት ከመኪና ሞተር የሚወጣ የሞቀ አየር መኪና ውስጥ ሙቀት እንዲሰጥ የሚያደርገው ግኝት ማርጋሬት ዊልኮክስ በተባለች ሴት እኤአ በ1893 ተፈለሰፈ።

ገመድ አልባ የቴሌኮም መሣሪያዎች
ሄዲ ላማር የተሰኘች የሆሊውድ አክረትረስ በኹለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ሥራ ላይ የዋለውን አየር ሞገዶችን በመዝለል የሬዲዮ ግንኙነቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ምስጢራዊ የሬዲዮ መገናኛ ቴክኖሎጂ ስትፈለስፍ ለጂፒ ኤስ እና ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ መገኘት ምክንያት የሆነ የቴክኖሎጂ ግኝት መሠረት ጥላለች። ከዝነኛው የማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ተቋም (MIT) እኤአ በ1973 የዶክትሬት ዲግሪ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር የሆነችው ሼርሊ ጃክሰን ቤል (ዶ/ር) ላቦራቶሪስ በሚባል ተቋም ተቀጥራ ስትሠራ በሠራችው መሠረታዊ ሳይንቲፊክ ጥናት ተንቀሳቃሽ ፋክስ፣ ሶላር ሴሎች፣ ፋይበር ኦፕቲክስ ኬብል፣ የስልክ ጥሪ ማሳያ (caller ID) እና መሥመር ላይ የመጠበቅ (call waiting) ተግባራዊ ሊሆኑ ችለዋል።

የኮምፒውተር ቀመርና ፕሮግራም ሥራ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተሠማሩ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም (30 በመቶ) ተሠማርተው ግኝት ያበረከቱና በማበርከት ላይ ያሉ ሴቶች ግን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። አዳ ላቭሌስ የተባለች እንግሊዛዊት በሳይንቲስት እናቷ ከልጅነቷ ጀምሮ በተደረገላት እገዛና ማበረታታት ቻርለስ ባቤጅ ከተባለው የለንደን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ጋር በመሆን በሒሳብ ቀመር የሚሠራ ማሽን በመፈልሰፍ “የመጀመሪያዋ የኮምፒውተር ፕሮግራመር” የሚል ሥያሜ አትርፋለች። ሌላዋ የአሜሪካ ባሕር ኀይል ባልደረባና ሳይንቲስት ግሬስ ሆፐር “ሃርቫርድ ማርክ ዋን” የሚባለውን የኮምፒውተር ፕሮግራም መሥሪያ ሲስተም በመፈልሰፍ “የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ፋና ወጊ” ተብላለች። ቀጥላም በእንግሊዝኛ የተጻፉ ትዕዛዞችን ሰብስቦ ኮምፒውተር ሊረዳው ወደሚችለው ቋንቋ መለወጥ የሚችል “ኮምፕላየር” ለመሥራት በቅታለች።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሴቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ በዚህ የሚወሰን ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋና የሚባሉ በምሳሌነት የሚቀርቡ በመሆናቸው ተጠቅሰዋል።

የአገራችን ሴት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች
በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ወይም ቀደምት የምንላቸውን ስኬታማ ሴቶች መዘከር ዓላማው ያደረገው “ተምሣሌት” የተሰኘ ገጽ በተከታታይ ካወጣቸው ታሪኮች፣ በተለይ የሴቶች ወርን ለመዘከር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያሳትመው ሰላምታ መጽሔት ያወጣቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለም ዐቀፍ ዕውቅናን ያተረፉ ሦስት ሴቶችን ታሪክ በአጭሩ በማንሳት ጽሑፌን አበቃለሁ።

ሰገነት ቀለሙ (ዶ/ር)
እኤአ በ1957 በጎጃም ፍኖተሰላም የተወለደችው ሰገነት የቤተሰቦቿን የግብርና ምርት አካባቢው በሚገኝ ቅርብ ገበያ እየወሰደች ትሸጥ ነበር። በዚያን ጊዜም ሰብሎቹን ለማምረት ከፍተኛ ጉልበት እንደሚያስፈልግና በአዝዕርቱ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች በትርፋማነቱ ላይ ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመገንዘብ በቃች። የሕይወት ዘመን ምርምሯን በእፅዋት ሞሎኪዩላር ፓቶሎጂ እንድትጀምር ያደረጋት አጋጣሚ የተፈጠረው ግን የአንበጣ መንጋ በመንደሯ ያለውን አዝርእት ሙሉ በሙሉ በማውደሙ ምክንያት ርሐብ በተከሰተ ወቅት ነበር። ከዚያን ወቅት ጀምሮ ሰገነት ሕይወቷን ሙሉ ርሐብን በመዋጋት፣ የሰብል ምርታማነት በማሳደግ እና ኋላ ቀር የግብርና ስርዓተ ምርትን በማሻሻል ላይ አትኩሮት እና ምርምር ላይ አደረገች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በመከታተል በ1979 ተመርቃለች። ትምህርቷን በመቀጠልም ከሞንታና ስቴት ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ፓቶሎጂ እና ዘረመል ጥናት ማስተር ኦቭ ሳይንስ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪዋን በእፅዋት ፓቶሎጂ እና ሞሎኪዩላር ባዮሎጂ ከካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለማግኘት በቅታለች። ሰገነት የድኅረ ዶክትሬት ምርምሯን በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ “ሞሎኪዩላር ዲተረንትስ ኦፍ ፓቶጀነሲስ” ላይ ትኩረት በማድረግ አጥንታለች።

እኤአ በሕዳር 2013 ሰገነት የዓለም ዐቀፉ ነፍሳት ፊዚዮሎጂና ኢኮሎጂ ማዕከል የመጀመሪያዋ ሴት ዳይሬክተር ጄነራል ሆና ተሾማለች። ሰገነት ለአመርቂ ሥራዎቿና ስኬቷ በርካታ ሽልማቶችን እና ዕውቅናን ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በ2013 የዓመቱ ምርጥ ሳይንቲስት ዝናን ስትጎናጸፍ፣ በ2014 የፎርብስ ምርጥ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካዊያት ዝርዝር ውስጥ ለመካተት በቅታለች። በመስከረም 2018 በሴቶች የኢኮኖሚ ፎረም ከፍተኛ የሆነውን የዐሥርት ዓመታቱ ምርጥ ሴት ሽልማትን በማግኘት በስኬት ማማ ላይ ትገኛለች።

ሶስና ኃይሌ (ዶ/ር)
ሶስና ኃይሌ (ዶ/ር) የመጀመሪያውን ጠንካራ አሲድ ነዳጅ ሕዋሳት በማዳበር የታወቀች ትውልደ ኢትዮጵያዊት የኬሚስትሪ ባለሙያ ናት። ይህ ምርምሯም በዘርፉ ያለ አዲስ ፈጠራ ሲሆን ብክለት ለመቀነስ እንዲሁም በጣም ውድ የሆነውን የውሃ ሀብት ሊሰጠን የሚችል ነው። በአሁኑ ወቅት ችካጎ አካባቢ በሚገኘው ኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ማክኮርሚክ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት ውስጥ ፕሮፌሰር ስትሆን የነዳጅ ዘይት ሕዋስ ፈጠራ ምርምር ሥራዋንም በመኖሪያና ንግድ ተቋማት ተግባር ላይ ለማዋል እየሠራች ትገኛለች። ይህ ምርምር ለመኪናዎች፣ ለመብራት፣ ለቤቶች፣ ለንግድ ተቋማት ኀይል በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን የፎሲል ፊውልና የተረፈ ምርትን ብክለትንም ይቀንሳል።

ሶስና በቁሳዊ የምርምር ማኅበረሰብ ውስጥ ጀግኒት ከሚባሉት አንዷ ስትሆን ለዘርፉ መዘመን በዓለማቀፍ ደረጃ ላበረከተቻቸው የምርምር ስኬቶትም የዘርፉን የላቀ ሽልማት ለመቀዳጀት በቅታለች።

ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር)
ትምኒት ገብሩ የኮምፒውተር ሳይንቲስት ስትሆን በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ አልጎሪዝም ባያዝና ዳታ ማይኒንግ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ትምኒት የቴክኖሎጂ ብዝኀነት አራማጅ ስትሆን ጥቁር ተመራማሪዎች የሚሳተፉበት እና በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ የሚያተኩረው የ”Black in AI” ተባባሪ መሥራችም ናት። በኢትዮጵያ ተወልዳ ያደገችው ትምኒት ወደ አሜሪካን አገር በማቅናት በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የባችለርና ማስተርስ ዲግሪዋን በኤሌክትሪካል ምሕንድስና አግኝታለች።

ትምኒት እኤአ በ2017 የዶክትሬት ዲግሪዋን ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለሕዝብ ይፋ የሆኑ ምሥሎችን ዳታ ማይኒንግ ለመሥራት በቅታለች። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከኅብረተሰቡ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያፈሱት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ትኩረቷን ይስባታል። አማራጮችን ለማጥናትም በአሜሪካ ጉግልን በመጠቀም ጎዳናዎችን በጥልቅ በመመርመር የሥነ ሕዝብ ስብጥር ያጠናች ሲሆን በዚሁም የማኅበረ ኢኮኖሚ ጠቋሚ የሆኑ እንደ የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ፣ የገቢ መጠን፣ የዘር ግንድ፣ እና የትምህርት ደረጃን የመሣሠሉትን ከሚያሽከረክሯቸው መኪናዎች በመነሳት መገመት እንደሚቻል አጥንታለች። ትምኒት በአሁኑ ወቅት በጉግል ካምፓኒ ውስጥ በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሥነ ምግባር ላይ እየሠራች ሲሆን ቴክኖሎጂ ለማኅበረሰብ መልካም ነገርን እንዲያበርክትም እየጣረች ትገኛለች። ከኤምአይቲ ፆታዊ ምርምር ጥላ ቡድን ጋርም በትብብር ትሠራለች።

የማርች “የሴቶች ወር”ን ፕሬዚዳንታችን ሣሕለ ወርቅ ዘውዴ እንዳሉት ካሁን በኋላ ‘ማርች 8’ ብቻ ሳይሆን ወሩን ሙሉ ለማክበር ተስፋ እያደረግን በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ የዓመት ሰው ይበለን እንላለን።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here