እንጻፍ…እናስነብብ

0
600

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

መጽሐፍትን አንባቢ ከሆኑ አንድ ነገር በትክክል ይረዳሉ፤ በመጻሕፍቶቻችን ብዙውን ጊዜ የወንዶች ጀብዱና የሴቶች ውበት ጎልቶ ይንጸባረቃል። ቴአትሮቻችን፣ ፊልሞችና ሙዚቃዎችንም ከዚህ የተለየ ሐሳብ አይገኝባቸው። እንግዲህ ፍትሓዊ የʻርዕሰ ጉዳይʼ ክፍፍል ነው ከተባለ፥ እሰየው! ብቻ በዚህ ላይ ከአንድ ወዳጄ ጋር በአጋጣሚ ስንነጋገር ካቀበለኝ ሐሳብ ላካፍላችሁ ወደድኩ።

በእርግጥ ነገሩን የሴቶች ወይም የወንዶች ጉዳይ ብለን አልነበረም ያነሳነው። ነገርን ነገር እያነሳው፤ ˝በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻችን የወንድ ልጅ ውበት ለምንድን ነው የማይጠቀሰው? የተገለጸስ እንደሆነ አዲስ ነገር የሚሆንብን ስለምን ነው?˝ ተባባልን። በኋላ ይኸው ወዳጄ ʻሮዝʼ በተባለች መጽሔት ላይ፥ አንድን ፈላስፋ ጠቅሶ ደራሲና ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም ያስነበበውን ነገር አጫወተኝ።

እንዲህ ነው፤ ብዙ ጸሐፍት ወንዶች ናቸው። ታድያ የራሳቸውን ጀግንነት እንጂ ውበታቸው ላይ ብዙ የሚያነሱት ነገር የለም። ስለሴት ልጅ ውበት ግን ሳይታክቱ፤ በሚገርሙና ከራሳቸው ከተደናቂዎቹም በልጠው በተዋቡ ቃላት ገለጻ ማድርግን ያውቁበታል፤ ይችሉበታልም። ይሁንና ሴት ጸሐፍያት ብዙ ባለመሆናቸው የወንዶች ውበት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የመነሳቱ ነገር ጥቂት እንኳን የሚባል አይደለም።

እና ሴቶች ለምን አይጽፉም ወይም አንጽፍም? መቼም ጥበብም አድልታ ወንዶችን ብቻ ጠርታ አይደለም! እንጻፍ ስል ታድያ የወንዶችን ውበት እንግለጽላቸው ማለቴ አይደለም። ይሄ በየጉያችን ገብተው የሚበሉን እልፍ ችግሮቻችን የተቀረፉ ጊዜ፤ የቅንጦት መብት ስንጠይቅ የሚነሳ ሊሆን ይችላል። ግን ይነሳ ቢባል እንኳ ወጣትና ጥሩ ብዕር ያላቸው ሴት የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችን በየጊዜው እያየን በመሆኑ ያም የሚቸግር ሆኖ አይደለም።

ታድያ ለምን አንጽፍም? ጥሩ የሕይወትም የሙያም ልምድ ካላቸው ሴቶች ጋር በተለያየ የሥራ አጋጣሚ ለመነጋገር እድሉ ነበረኝ። ለምን አትጽፉም ብያቸው ባላውቅም በተለያየ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸው በቃለ መጠይቅ እንዲሰጡ ስጠይቅ ፈቃደኛ አይሆኑም። ጥያቄዬ ችግር ኖሮበት ወይም ትህትና ይዟቸው ነው? አይመስለኝም። የተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎችም ይህን ሲሉ እሰማለሁ፤ ባለጉዳዮቹ ራሳቸው አስተያየት መስጠት አይፈልጉም።

አሃ! እና ማን ያውራው? ማንስ ይጻፈው? የዘንድሮውን ማርች 8/የሴቶች ቀን/ ምክንያት በማድረግ ጋዜጣችን አዲስ ማለዳ የሴቶች መጽሔት ይዛልን ብቅ ብላለች። ይህ ግን ቀድሞ በራሳቸው በሴቶች ሊጀመር የሚገባ ጉዳይ አልነበረምን? ይሁን…ቢሆንም ዛሬም እንጻፍ። ችሎታውና አቅሙ አጥሮ ነው ብዬ አላምንም፤ ˝የኔም ሐሳብ ይጠቅማል!˝ ብሎ ማመን ግን ያስፈልጋል። የሚነበብ ነገር በአንባቢ ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ካወቅን እናም በንባብ ካመንን፤ ታሪካችን እና እውነታችንን መጻፍ…ከዛም ማስነበብ አለብን።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here