ከ800 በላይ ቤት አልሚ ማኅበሮች ሕጋዊነታቸው እየተጣራ በመሆኑ የግንባታ ፈቃድ ተከለከሉ

0
412

በአዲስ አበባ ከተማ ከተንሰራፋ ሰንበትበት ያለውን የመሬት ወረራን ለመከላከል በአራት ክፍለ ከተሞች ቤቶችን በመገንባት ላይ የነበሩ ከ800 በላይ ቤት አልሚ ማኅበሮች የያዙት የመሬት ይዘታዎቸ ሕጋዊነታቸው ማጣራት መጀመሩን ተከትሎ የግንባታ ፈቃድ ተከለከሉ።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በአቃቂ፣ ንፋስ ስልከ፣ ቦሌ እና ኮልፌ ክፍለ ከተማ የተቋረጠው የአልሚዎች የግንባታ ፍቃድ ከኹለት ሳምንት በፊት በነበሩት ወራት እየተሰጠ የነበረ ቢሆንም የይዞታቸው ሕጋዊነት ባለመረጋገጡ ድጋሚ እንዲከለከሉ ተወስኗል።

የማኅበራቱ ይዞታ ሕጋዊነት ተጣርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ የግንባታ ፍቃድ መከልከሉ ጋር ተያይዞ በአቃቂ ክፍለ ከተማ የግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ለማ ጅግሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ድርጊቱ የተወሰደው አጠቃላይ ካሉት 844 ቤት አልሚ ማኅበራት ውስጥ በማጭበርበር የተሠማሩ ሕጋዊ ያልሆኑ ማኅበራትን ተለይተው እስኪታወቁ እና ከዚህ ቀደም የነበሩትን ነባር ማኅበራት ላይ ሲሠራ የነበረውን ሕጋዊ ያልሆኑ አሰራሮችን መሉ በሙሉ ለማስቀረት እንደሆነ ገልፀዋል።

̋የተቋረጠው የቤት አልሚ ማኅበራት የግንባታ ፍቃድ የሚጀመረው የማጣራቱ ሥራ ተጠናቆ ሕገ ወጦችን ለፍርድ ስናቀርብ ነው ̋ ለማ ብለዋል። ይሁንና እስከአሁን ባለው አሰራር ግን ሕጋዊ ያልሆኑትን ቤት አልሚ ማኅበራት ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል።

የማኅበራት ቤት አልሚዎች በበኩላቸው እስከአሁን እየተሠራ ያለው አሰራር ግልፅ እንዳልሆነላቸውና ምንም ዓይነት ደብዳቤም ሆነ በቂ መረጃ ሳይሰጣቸው ግንባታውን እንደተከለከሉ ተናግረዋል። ሆኖም ግንባታውን ባለፉት ሰባት ወራት በተለያዩ ጊዜያት በተከለከሉበት ወቅት እንደተጉላሉና ምንም ዓይነት መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው፤ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ በሚደረገው የሊዝ ውል የተነሳ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል መሬት ልማት ማኔጅመንት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኤልያስ ዘርጋ እንደተናገሩት ከ1996 እስከ 1997 ድረስ የታገዱት ቤት አልሚ ማኅበራት በወቅቱ በነበረው አሰራር ሕገ ወጥ የሆኑትን ለመለየት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ማጣራት ሲደርግባቸው ቆይቷል። በ2008 ሕጋዊ ያልሆኑት ማኅበራት ተለይተው ተጠያቂ እንዲሆኑ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ጉዳዩ ለሕግ አስፈፃሚ አካላት ተልኮ የነበረ ቢሆንም እርምጃ አልተወሰደም።

በዚህ የተነሳ በአሁኑ ሰዓት በአራቱ ክፍለ ከተሞች ላይ እየተጣራ ባለው የማኅበራት የመሬት ባለቤትነት እስካሁን 25 ማኅበራት ብቻ ሕጋዊ መሆናቸው ተረጋግጦ ካርታቸው ወደ ክፍለ ከተማቸው ተልኳል። ቀሪ ማኅበራቶችንም ለማጣራት ከፀረ ሙስና ኮሚሽን እና ከወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ እየሰራን ነው ያሉት ኤልያስ በቢሮ በኩል አጣሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የማጣራት ሥራው የዘገየበት ምክንያት የቢሮው ሠራተኞች ሌላ ወቅታዊና አጣዳፊ የሆነ ሥራ ስለነበረባቸው ነው ብለዋል። ይሁንና የማኅበራቱ የመሬት ይዞታዎች ሕጋዊነታቸው ተጣርቶ በቅርቡ ይፋ ይሆናል ብለዋል።

 

ማስታወሻ፡ በመጀመሪያ ታትሞ በወጣው ዜና ላይ  ከ600 በላይ ቤት አልሚ ማኅበሮች ሕጋዊነታቸው እየተጣራ መሆኑን አውጥተን የነበረ ሲሆን ቁጥሩ ላይ ማስተካከያ ተደርጎአል። 

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here