በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ቀንጢቻ የሚገኘው የቀንጢቻ ታንታለም ማውጫ የማምረት አቅሙን ለማሳደግና ተጨማሪ እሴቶችን በታንታለም ላይ ለመጨመር ታስቦ የግል ባላሀብቶችን የሚያሳትፍ ጨረታ አወጣ። ከፍተኛ የታንታለም ክምችት የሚገኝበት የቀንጢቻ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ ከዚህ ቀደም በመንግሥት ይዞታ የነበረ ሲሆን፤ የታንታለም ማዕድንን በማውጣት ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት እንዲውል በማድረግና ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግና በታንታለም ምርት ላይ እሴት ለመጨመር በማሰብ የግል ባለሀብቶች የሚሳተፉበትን መንገድ ለመክፈት ከፊል ይዞታውን ጨረታ ማውጣቱን መንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንዳፍራሽ አሰፋ እንደተናገሩት እስካሁን የታንታለም ማዕድንን መንግሥት ምንም ዓይነት ማቀነባበር ሳያደርግ ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ሲያቀርብ መቆየቱን ገልፀው፤ ይህም ከማዕድኑ ሊገኝ የሚችለውን ገቢ የሚያሳንስ እንደነበር ጠቁመዋል። አያይዘውም የማዕድን ማውጫው አቅሙን በማጎልበትና በምርቱ ላይ እሴት ተጨምሮበት ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገኝ ታስቧል ብለዋል። በጨረታውም ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ባለሀብቶች በቀጥታ መሳተፍ እንደሚችሉ ወንዳፍራሽ ገልፀው፤ ጨረታውም ከመጋቢት 9/2011 ጀምሮ ክፍት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የቀንጢቻ ታንታለም ማውጫ ድርጅትን በባለቤትነት የሚመራው መንግሥታዊው የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ኮርፖሬሽኑ የማዕድን ማውጫው ላልተወሰነ ጊዜ ሥራ ማቆሙን ተከትሎ 354 ሚሊዮን ዶላር እንዲያጣ መገደዱንና ለ 1 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የመበተን አደጋ እንደተጋረጠበት አዲስ ማለዳ በየካቲት 16፣ እትም 15 መዘገቧ የሚታወስ ነው። ምንጮች እንደሚያመላክቱትም የማዕድን ማውጫው ሥራውን ማቆም ተከትሎ ከኹለት ቶን በላይ የሚሆን የታንታለም ክምችት እንደተዘረፈ ታውቋል።
ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ማምረት እንዲያቆም ከኦሮሚያ ክልል ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ትዕዛዝ የደረሰው ማምረቻው፤ በየወሩ 10 ቶን የማምረት አቅም ነበረው። ለ28 ዓመታት ታንታለም በማምረት የዘለቀው እና በ5 ነጥብ 3 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለው የቀንጢቻ ማዕድን ማምረቻ ሥራ ካቆመ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን ወንዳፍራሽ ገልፀዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ጉዳዩ ከክልሉ መንግሥትና ባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተደረገበት እንደሆነና በአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘም በባለሙያዎች ጥናት እየተካሔደበት እንዳለ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ከዓመት በፊት የታንታለም ማዕድን ማውጫን በተመለከተ ግል ባለሀብቶችን ለማሳተፍ ጨረታ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም እና አራት ኩባንያዎች ፍላጎት እንደነበራቸው የሚታወስ ነው። ነገር ግን መንግሥት ጨረታውን ግልፅ ባለሆነ መንገድ እንዲታጠፍ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ። እንደ ወንዳፍራሽ ገለፃ ግን በድጋሚ የወጣው ይህ ጨረታ መንግሥት በደንብ አስቦበት እና ዘርፉን ለማጎልበት ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ስኬት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011