ለውጡ እንዳይቀለበስ፥ ድክመቶቹ ይታረሙ!

0
722

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣነ መንበሩን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ያህል የሕዝብ ብሶት አንዳንዴ እየጋመ፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየተቀዛቀዘ እዚህ ደርሰናል። እስከ 2010 የመጀመሪያ ወራት ድረስ የሕዝብ ጥያቄዎችን ችላ በማለት ሕዝባዊ አመፆችን በፀጥታ አካላቱ ጡንቻ እየደፈቀ ዘልቋል። ለዚህም በ1980ዎቹ አጋማሽና በድኅረ 1997 ምርጫ ወቅት የነበሩትን ሕዝባዊ ተቀውሞዎች ተከትሎ የተሰጡት ምላሾች ተጠቃሾች ናቸው። ከመጋቢት 2010 ወዲህ የመጣው አመራር ግን የሕዝብን ጥያቄ ለማድመጥ ዕድል የሰጠ ይመሥላል።
ገዢው ግንባር የ2007ቱን ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፊያለው ካለበት ማግስት ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም የአማራ ክልል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የወጣቶችን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግዱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ኢሕአዴግ እነዚህን ተቃውሞዎች እንደቀድሞዎቹ ሁሉ በተለመደው በፀጥታ አካላቱ ጡንቻ ለመድፈቅ በመሞከር ከፍተኛ ሰብኣዊ ጉዳት ቢያደርስም፥ ሕዝባዊ አመፁ በተለይም የወጣቶቹ ቁጣ ዕለት በዕለት እየጨመረና እየተስፋፋ በመሔድ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ተሥፋቷል።

የሕዝባዊ አመፁ አለመቆም፣ ምናልባትም በኢሕአዴግ ውስጥ የሕዝቡን ጥያቄ ለማዳመጥና የራሳቸውንም ነጻነት ለማወጅ የለውጥ ኃይል ሆኖ የወጣ አንጃ እንዲኖር አስገድዷል። በግንባሩ ውስጠ ፖለቲካ ትግትግ በእነ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ ኃይል ድል ቀንቶት የአመራር ቦታውን ተረክቧል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ተከትሎ መጋቢት 24/2010 ዐቢይ አሕመድ ሥልጣነ መንበሩን እንዲይዙ ጥርጊያው ተመቻችቷል።

ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባሰሙት ʻየሥልጣኑን ተቀብያለሁʼ የመጀመሪያ ንግግራቸው የብዙኀኑን ተስፋን ያጫረ፣ ያነቃቃና የዕርቅና ይቅርታ መንፈስን ያዘለ ነበር። በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎችም ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣናቸውን ከተረከቡበት ዕለት አንስቶ ድፍረትና ፍጥነት የተሞላባቸው ትንፋሽ የሚያሳጥር እርምጃቸው የብዙኀንን ቀልብ ስቧል፤ ድጋፍም አስገኝቶላቸዋል። ዕረፍት የለሽ የነበረው፣ በድንገቴ የተሞላው የመጀመሪያ ወራት እንቅስቃሴያቸውና ድፍረት የተሞላበት አካሔዳቸው የሕዝቡን ቀልብ ከመያዝ ባሻገር አንዱን እርምጃ ሳያጣጥም በላይ በላይ በተወሰዱ እርምጃዎች በአገር ውስጥ ሰልፍ ያስወጣ ድጋፍ ሲያስገኝላቸው፥ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ደግሞ ዕውቅና እና ሙገሳ አስችሯቸዋል።

ይሁንና ከመጀመሪያው ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወሰዱ የነበሩ እርጃዎችንም በጥርጣሬ የሚመለከቱ፣ ድምፃቸው ግን የታፈነ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ግለሰቦች እንደነበሩም አይዘነጋም። የእነዚህኞቹ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደፋርና ፈጣን እርምጃዎች በመርሕና በግልጽ በተቀመጠ ፍኖተ ካርታ የሚመራ አይደለም በማለት ነው።
አዲስ ማለዳ የለውጡን መምጣት በአዎንታዊ መንገድ የምትወስደው ሲሆን እስካሁን የተሔደበት መንገድ ግን እንከን አልባ ነው ብላ ግን አታምንም። በመሆኑም ምንም እንኳን የረፈደ ቢመስልም፥ አሁንም በመንግሥት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች ትጠቁማለች።

አዲስ ማለዳ ካስተዋለቻቸው እና ባለፉት ኅትመቶቿ ስትዳስሳቸው ከነበሩ ችግሮች መካከል መንግሥት ሕግ የበላይነት የማስከበር ሚናውን የመወጣት ከፍተኛ ክፍተት የታየበት መኾኑ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። በዚህ ክፍተት ምክንያት ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ጠርዝ የነካ ብሔርተኝነት መንሠራፋት፣ የደቦ ፍርዶች መበራከት፣ ስርዓት አልበኝነት መስፈን እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን መፈናቀል አስከትሏል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም እንደ አገር የመቀጠል ኅልውና ፈተና ላይ ወድቋል።

በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ከሰላምና ደኅንነት መታጣት ጋር በተያያዘ ምጣኔ ሀብቱ ማለትም የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ፣ የምርታማነት መቀነስ፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት ምላሽ ማጣት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት አለመቀረፍ ምክንያት ሆነዋል።

የውጪ ግንኙነትንም በተመለከተ ዐቢይ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ፍጥጫ ማስቆማቸው እንዲሁም መልካም ጉርብትና መፍጠራቸው ያስወድሳቸዋል። ከአፍሪካ ቀንድ አገራት፣ ከግብፅ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት፣፣ ከቻይና እንዲሁም ከአውሮፓ በተለይ ከፈረንሳይና ጀርመን እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የማጠናከር ሥራ መሥራታቸውን አዲስ ማለዳ ታደንቃለች። ይሁንና እነዚህም የዲፕሎማሲ መስተጋብሮች ምን ያክል በመርሕ ላይ የተመሠረቱ ናቸው? ተቋማዊ እንዲሆኑስ ምን ተደርጓል የሚሉት ነገሮች መፈተሸ እንደለባቸው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

አዲስ ማለዳ መንግሥት ለሚወስዳቸው የማስተካከያ ወይም የማሻሻያ እርምጃዎች አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደም ብላ ታምናለች፤ በፍጥነት ግን ተግባራዊ መደረጋቸው ችግሮቹን ሥር እንዳይሰዱና ውስብስብ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በተለይ ሕግን ማስከበር መንግሥት ለድርድር የሚያቀርበው ጉዳይ መሆን እንደሌለበት አዲስ ማለዳ በአንክሮ ታሳስባለች። በሥጋት ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ እፎይታ ሊሰጠው ይገባል።

ሌላውና ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ፥ ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩና አንዳንድ ባለሥልጣኖች ለመቀበል ቢከብዳቸውም እየመሩት ያለው ለውጥ ወይም ሽግግር በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሀብቱም ሆነ በዲፕሎማሲው ረገድ ግልጽ የሆነ በጊዜ ሰሌዳ የተቀመጠ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል። ይህም ኢትዮጵያ ወዴት እያመራች እንደሆነ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ዘንድ ያለውን ብዥታ፣ መደናገርና እርግጠኝነት ማጣት ይቀንሳል በማለት አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 21 የመጋቢት 21 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here