የተዛባው ምሥል

0
717

ማኅበረሰቦች በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ምክንያቶች ስለ አንድ የማኅበረሰብ ክፍል የተሳሳተ ምሥል ይፈጥራሉ። ሙኒራ አብድልመናን በዚህ መልኩ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተሰጣቸውን የተዛባ ምሥል አግባብ አለመሆን በመተንተን የውክልናን ፋይዳ እና የተዛባ ምሥልን ዳፋ በዚህ መጣጥፋቸው ያስረዱናል።

መግቢያ

ጓደኛዬ ነው፤ ብዙ ነገሬን ያውቃል። ብዙ እናወጋለን፣ አንድ ቀን ስለ ሥነ ውበት እያወራን እያለ፥ በጉዳዩ ዙሪያ በጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ የተጻፈ ሐሳብ ጠቀስኩለት። በብዙ የሚያውቀኝ ጓደኛዬ ከሐሳቡ ይልቅ የእኔ ኒቼን መጥቀስ አስደነገጠው። “እንዴት ኒቼን አወቅሽው?” ሲል ጠየቀኝ፤ “እንዴት አላውቀውም? የታወቀ ፈላስፋ እኮ ነው” ስል መለስኩ። ታዋቂማ ነው ግን እኔንጃ አንቺ ታውቂዋለሽ ብዬ አልጠበኩም ብሎ መለሰልኝ። ‘አንቺ ታውቂዋለሽ ብዬ አልገመትኩም’ ያለው የትኛው የአንቺነት መገለጫዬ ላይ ተሞርክዞ እንደሆነ ስላልገባኝ መልሼ ማብራሪያ ጠየቅኩ።

“የመጀመሪያ ዲግሪዬን ፍልስፍና ላይ እንደሠራሁ ታውቃለህ፤ ‘አንቺ ታውቂዋለሽ ብዬ አልጠበቅኩም’ ስትል የትኛው እኔነቴን እያልክ ነው? አልገባኝም” አልኩት።

“ስልሽ ሙስሊም ስለሆንሽ፣ ሂጃቡ ምናምን፣ ብቻ ኒቼን ታውቂያለሽ አላልኩም” አለኝ። በጊዜው ከቅርቤ ሰው እንዲህ ያለ የተዛነፈ አመለካከት መስማቴ ቢያስከፋኝም ከሱ ስህተት አሳልፌ ትልቁን ምስል ለማየት ሞከርኩ።

ሀንስ ሮስሊንግ (ዶ/ር) “Factfullness: Ten reasons we are wrong about the world” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ዕይታችንን የሚያዛቡ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ 10 ደመነፍሳዊ ባሕሪዎችን (instincts) ይጠቅሳል። ከነዚህ ደመነፍሳዊ ባሕሪያት አንዱ፣ “The Generalization Instinct” ነው። እንደ ሀንስ የሰው ልጆች ነገሮችን በመደብ (Catagory) የመረዳት ዝንባሌ አለን። በዚህም የተነሳ አንድ የሚያደርጋቸው ነገሮች ያሏቸው ግን ተመሣሣይ ያልሆኑ ሰዎችን፣ ግለሰቦችን፣ ሐሳቦችን፣ አገራትን፣ ብሎም ክስተቶችን በአንድ መደብ ውስጥ እንከታቸዋለን። ይህ ብቻም ሳይሆን እንደ ፆታ፣ ብሔር፣ ሙያ፣ ሃይማኖትና አገር ባሉ መደቦች ውስጥ ያሉ አላባውያን አንድ ዓይነት ናቸው ብለን እንረዳለን።

ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ራሳችን በእዝነ ሕሊና የፈጠርናቸው መደቦች ውስጥ ስለከተትናቸው ነገራቶች አልያም በአንድ መደብ ውስጥ ስላሉ አባላቶች የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። ይህ በመደብ አጉሮ የመረዳትና

ወደ ድምዳሜ የመድረስን ሒደት ሀንስ የማኅበራዊ ተግባቦት እንቅፋት ሲል ይገልጸዋል። በማኅበረሰብ ግንባታና ዕድገት እንዲሁም በአኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልፅግና ላይ ማነቆነቱንም በቁጥር የተደገፈ መረጃ በማቅረብ ይሞግታል።

በግለሰብ ደረጃ ጠንቅቆ የሚያውቀኝ ወዳጄ፣ ያጠናሁትን ዘርፍ እና የግል ዝንባሌዎቼን የሚያውቅ ጓደኛዬ እንኳን ሙስሊም ሴትነቴ የመረጃ አድማሴ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ካሰበ የዚህ የተዛነፈ አስተሳሰብ መነሻው የት ነው? መተላለፋችን የመነጨው ከምንድነው? ይህ አስተሳሰብ እኔን እና መሰሎቼን እንዲሁም ኢትዮጵያ አገሬን ምን እያስከፈላት ይሆን?

በመረጃ የታገዘ ዜጋ (Informed citizen) ነው የምለው ሰው እንዲህ ካሰበ፥ በየቦታው ከትናንሽ የሥልጣን እርከኖች አንስቶ እስከ ትልልቅ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ሙስሊም ሴቶችን በተሳሳተ መልኩ ቢወክሉ ወይንም ጭራሹን ባይወክሉ፣ አግባብ ያለው ግልጋሎት ለመስጠት ቢሳነፉ እና ቢያንገላቱ ምን ይገርማል?

የችግሩን መሠረት ለመፈለግ ወሰንኩ፤ ፍለጋው ገና አላለቀም። እስካሁን የደረስኩበትን ግን የዘንድሮውን ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት አድርጌ ላካፍላችሁ ወደድኩ።

የተዛባው ምሥል
ኢኮኖሚስቷ ኬት ራዎርዝ የዚህን ዘመን የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና አሰተምህሮ ጉድለቶችን በፈተሸችበት ‘Doughnut Economics’ የተሰኘ መጽሐፍ የኢኮኖሚክስ አሰተምህሮ የሰው ልጅን የሚገልጽበትን ንድፈ ሐሳብ (‘Rational Economic Man’) ከሊዬናርዶ ዳቪንቺ አስቂኝ ስዕል (‘Caricature’) ጋር ታመሳስለዋለች። እነዚህ አስቂኝ ስዕሎች የሰውን ልጅ አንድ የሰውነት ክፍል በማግዘፍ ፈገግታ የሚያጭሩ ቢሆኑም ትክክለኛውን ሰው አያሳዩም። ኢኮኖሚስቷ ኬት ‘Rational Economic Man’ የተባለው ገናና የኢኮኖሚክስ ኀልዮት እንደ አስቂኝ ስዕል ስለ ሰው ልጅ የተዛባ ምልከታ ፈጥሯል ስትል ትሞግታለች። ይህ ምሥል በቀለም፣ በሸራና ብሩሽ ወዘተ. ብቻ የተፈጠረ አይደለም። የዕሳቤና አሰተምህሮት ውጤትም ነው። በተለያየ አጋጣሚ የተላመድናቸው ስሁት ድምዳሜዎቻችንም የሚፈጥሩት ምሥል አለ፤ የተዛባ ምሥል፤ በጊዜ ሒደት መዛባቱን ረስተን እንደ ትክክለኛ ነገር የምንለምደው ምሥል።
ሙስሊም ሴቶችን አንድ ቅርጫት ውስጥ የመክተቱ ነገር መልኩን እየቀያየረ በየጊዜው ይገጥመናል፣ ጎረቤት፣ አብሮ አደግ ጓደኛ እና ዘመዳሞች አይደለንም እንዴ? እንዴት ይህን ያህል ልንተላለፍ፣ ላንተዋወቅ ቻልን ስል እብከነከናለሁ። ለጊዜው አናዶኝ ቢያልፍም ቆየት ብዬ አመለካከቱ የመጣበትን ሥር መሠረት ለመረዳት እሞክራለሁ። ተራው ሕዝብ ጋር ንፁኅ (genuine ) አለማወቅ ያመነጨው ስሁት ግንዛቤ ነው ልንል እንችል ይሆናል። አንድ ሕዝብ አብራው የምትሠራ ሙስሊም ሴት፣ በተለያዩ ሙያ ዘርፎች የተሠማራች ሙኒራ፣ በሚድያ የምትታይ ፋጡማ፣ አስተማሪዋ አይሻን ካላወቀ እኔን በለመደው ዘርፍ ብቻ ቢፈርጀኝ ምንም አይገርምም። አገሬ እንደ አገር እኔን ማብቃቱ እና ማንነቴን ጠብቄ የመማር እና መሥራት ዕድል ስለነፈገችኝ በተፈጠረ ክፍተት የተነሳ ቦታዎቹ ላይ አለመኖሬን ተንተርሶ የተገነባ የተሳሳተ ምሥል ነው።

አንዳንዴ ግን ይህ የተዛባ ምሥል በተለይም ምሁራን እና ልኂቃኑ ላይ ሲሆን ከግብዝነት የመነጨ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያዊትን በራሳቸው ፖለቲካዊ ዕሳቤ፣ ባሕል እና እምነት ዙሪያ ብቻ ይሽከረከር ዘንድ አካታች ያልሆኑ ቀለሞችን ነክረው በግብዝነት ሸራቸው ላይ የሳሉት አሰቂኝ ምስል (‘ካሪኬቸር’) አለ። ይህ የተዛባን አሰቂኝ ምሥልን ያልመለሠ አገሪቷ አትገባውም፤ አልነቃም እና ባዕድ ነው የሚል ብያኔም አላቸው። ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በጥቅሉ እንዲሁም ሙስሊሟን ሴት በተለየ ሁኔታ የማግለል ወኔ የሚቀዳውም በእነዚህ ጥቂት ግብዝ ባለጊዜዎች ከተሣለው የተዛባ ምሥል ነው።

ይህን የተሳሳተ አመለካከት የሚያግዙ ማኅበረሰባዊ ክፍተቶቻችንም በዛው ልክ ብዙ ናቸው። የሁላችንም ማንነት ላይ የግለሰብ ተፈጥሯችን፣ የቤተሰባችን ሁኔታ፣ አስተዳደግ፣ ማኅበረሰባዊ እውነታ፣ እምነት እና መሠል ነገሮች የሚያሳርፉት ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ በትምህርት ቤቶች በኩል የሚያርፍብን ተፅዕኖ ግን የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። “የሙስሊም ትምህርት ቤት” ውስጥ ከተማሩ ሰዎች ውጪ ስንቶቻችን ነን ሙስሊም ሴት አስተማሪ እያየን ያደግነው? ስንቶቹ የመማሪያ መጽሐፍትስ የሙስሊም መገለጫዎችን የምታንፀባርቅ ሴት ምስል እና ታሪኮች አሏቸው? የአገሪቷ የትምህርት ስርዓት (‘ካሪኩለም’) ውስጥ እኔን ፈልጌ ማግኘት ይቻለኛል ወይ? በገዛ አገሬ እኔነቴን ይዤ እንድኖር ተፈቅዶልኛል ወይንስ አንድ እርምጃ ለመራመድ በሞከርኩ ቁጥር ከትምህርት እና ማንነቴ መሐል የመምረጥ አጣብቂኝ አማራጭ ይቀርብልኛል? አብረውኝ የሚማሩ የክፍል ጓደኞቼስ ምን ያህል ሙስሊም ሴት መሆንን እንደተለመደ ነገር (‘ኖርማላይዝ’) ማድረግ እንዲችሉ ሆነው አድገዋል? ይህን ሁሉ ለማየት ሞከርኩ የማገኘው ውጤት ግን በብዙው እንደ አገር ሙስሊም ሴቶችን የማትወክል አገር እንዳለኝ ያሳዩኛል።

ብዝኀነት አልባ ብዙዎች
አገር ውስጥ የሚታዩ በርካታ ተከታታይ ድራማዎችን፣ ፊልሞችን፣ በየጣቢያው የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን እና የሙዚቃ ክሊፖችን በወፍ በረር ተመለከትኩ ሂጃብ ያደረገች ሴትን በስፋት ማየት የቻልኩት የባንኮች ከወለድ ነጻ መስኮት ማስታወቂያ፣ አረብ አገር ከመሔድ ጋር የተያያዙ ትርክቶች፣ የሙስሊም በዓላት ልዩ ዝግጅቶች ላይ፣ እሱም በአረብኛ ሙዚቃ ታጅቦ አልያም የተወሰኑ ክልሎችን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ነው። በብሔራዊ ጣቢያችን ብዙኀኑ ሙስሊም በሆኑባቸው ክልሎች ቋንቋ ካልሆነ በስተቀር በአገሪቷ የሥራ ቋንቋ የሚተላለፉ ዜናዎች ላይ ሂጃብ ለብሶ ዜና ማንበብ ሕልም ነው። ለዚህ ሥራ ሲባል የማንነታቸው አንድ አካል የሆነን መገለጫ ከላያቸው ላይ ማንሳት አልያም ከሥራ ገበታው መነሳት አማራጭ የሌለው ምርጫ ሆኖ ኖሯል።

በተለምዶ የአገር ኩራት ተብሎ የሚጠራው አየር መንገዳችንም ቢሆን በአገር የማስተዋወቅ ተግባሮቹ ላይ ሂጃብ የለበሰች ሙስሊም ሴትን ሲያሳትፍ አላየሁም። ለአውሮፕላን አብራሪነት፣ ለበረራ አስተናጋጅነት፣ ግራውንድ ላይ በግልጽ ለሚታዩ ኀላፊነቶች እና የመሣሠሉት ቦታዎች ላይ ለመቀጠር አንዲት ሴት በትምህርት ደረጃ ብቁ ብትሆንም እንኳን ሙስሊም ሴትን መሥሎ መገኘት ግን ክልክል የሆነ ይመሥላል። እነዚህን ነገሮች ባስተዋልኩ ግዜ ስለምን በገዛ አገሬ ምሥል ውስጥ ራሴን ፈልጌ እንዳላገኝ ተፈረደብኝ እላለሁ። እርግጥ ነው በየትኛውም የሕይወት ዘርፍ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ታግለን ነው የምናስተካክለው፤ እየታገልንም ነው። ነገር ግን ሁሌም በዚህ ትግል የሚባክነው ጉልበት ቁጭት እረፍት ይነሳኛል።

በነዚህ ዘርፎች ሁሉ አለመወከላችን ገርሞኝ ሳያበቃ ስንወከልም ደግሞ የምንወከልበት የተሳሳተ ምሥል መሆኑ ያሳስበኛል። ይህ ስጋት እንደው ስጋት ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳይ አንድ አጋጣሚ ልጥቀስ፣ በአገራችን ካሉ ትልልቅ የመንግሥት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች በአንዱ ውስጥ በትልቅ ኀላፊነት ቦታ ላይ የምታገለግል የነበረች ወዳጄ በአንድ ወቅት መሥሪያ ቤቷ በየክፍለ አገሩ በሥሩ ያሉት ንዕስ ክፍሎችን በኃላፊነት ለመምራት (‘ሱፐርቫይዝ’) ለማድረግ ወደ የተለያዩ ከተሞች ትሔዳለች። በሔደችባቸው አብዛኞቹ ክልል መሥሪያ ቤቶች ያሉ ኀላፊዎች ማንነቷን ከመናገሯ ቀድመው አለቆችሽ የት አሉ? ማን ልኮሽ ነው? ምን ፈልገሽ ነው? የአረብ አገር ጉዳይ በዚህኛው መስኮት ነው እና የመሣሠሉትን ንግግሮች ይናገሯት እንደነበር፥ የሚጠብቁት ኀላፊ እሷ መሆኗን ባወቁ ግዜም መደበቅ የማይችሉት ከፍተኛ ድንጋጤ እና መገረም ይነበብባቸው እንደነበር አጫውታኛለች። አንዲት ሴት የሆነ ዓይነት አለባበስ ስለለበሰች እና አንድ የእምነት ተቋም ውስጥ የሚያጠቃልል ምልክቶች ስለታዩባት ብቻ ማንነቷን በተወሰነ አጥር ውስጥ የመፍረድ ያህል አንድ አገር እየኖርን አንተዋወቅም ወይ ብዬ ሳስብ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን ይገባኛል።

የፍትሕ እጦት ሮሮዎች
በአገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዙ ጊዜ ሂጃብ ለብሳችሁ መማር እና መፈተን እንዲሁም በተቋማቱ ግቢዎች ውስጥ መስገድ ክልክል ነው እና የመሣሠሉት ሕግጋቶች ይወጣሉ። ይህ ሲሆን ተማሪዎች ማንነታቸው ከተገነባበት እምነት እና ለሕይወታቸው እጅግ ጠቃሚ ከሆነው ትምህርት መሐል ለመምረጥ ይገደዳሉ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሕግጋቶች የሚወጡት የፈተና መዳረሻ ወቅቶች ላይ ነው። በውጤቱም ብዙኀኑ ተማሪ ትምህርቱን አቋርጦ፣ ጥናቱን ትቶ ተቃውሞ እና አድማ ለማስተባበር ይገደዳል፤ ግማሹ ተማሪ በአገሬው ሰው ቤት ተጠግቶ ተበታትኖ ይቆያል። ጥቂቶች በትምህርት ላይ ተስፋ ቆርጠው ላይመለሱ ወደ ቤተሰቦቻቸው ይሔዳሉ።

እነዚህን ታሪኮች የሚሰሙ ሙስሊም ቤተሰቦችም ሴት ልጆቻቸውን በቀጣይ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለመላክ ያመነታሉ። ይህን ሁሉ ተቋቁመው ለመማር የሚወስኑት ተማሪዎችም ቢሆኑ በላሸቀ ሞራል፣ በመገፋት ስሜት እና ተሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ሆነው፣ የአገር ፍቅር እና ባለቤትነት ስሜታቸውን ተነጥቀው ይቀጥላሉ። በውጤቱም እንደተለመደው የተማሩ እና በሲቪል ሰርቪሱ ዙሪያ የሚያገለግሉ ሙስሊሞችን እና ሙስሊም ሴቶች እጥረት ይኖራል። አዙሪቱ ይቀጥላል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የተመሠረተው ባለ ዘጠኝ አባላት “የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ችግሮች ጥናት በማድረግ መፍትሔ ለማቅረብ የተቋቋመ ኮሚቴ” በሚል ሥም የሚታወቀው አካል በቅርቡ በፌስቡክ ገጹ የሴቶች ዳይሬክቶሬት የተባለ የኢትዮጵያውያን ሙስሊም ሴቶችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የሚሠራ አካል አስተዋውቆ ነበር። ገጹ ለዚህ ጽሑፍ ማጀቢያነት የተጠቀመው ምስል በድሬዳዋ ከተማ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ዩኒፎርምን የለበሱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን ነበር። ተማሪዎቹ ተመሳሳይ ቀለም ያለው በተለምዶ ጅልባብ ተብሎ የሚጠራ እና ፀጉርን እና ሰውነትን የሚሸፍን አለባበስ ነበር የለበሱት። በጽሑፉ ሥር ከተሰጡ አስተያየቶች መሐከል ተደጋጋሚነት የነበራቸውና ውስጤን የነኩት፣ እንደዚ ሆኖ መማር ከተቻለማ በቃ ከስደት ስመለስ እማራለው የሚል መልዕክት ያዘሉ ነበሩ።

ይህንን አስተያየት የሰጡ ልጆች ብዙኀኑ በአረብ አገራት ሥራ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የአገሪቷን አከባቢዎች ኢኮኖሚ እና ቤተሰባዊ ሕይወት ቀጥ አድርገው የያዙ እንስቶች ናቸው። በነሱ ብርታት ብዙ ማኅበረሰባዊ ቀውስን ያስቀሩ ጀግኖችም ናቸው። ብዙኀኑ ከአገር ወቶ ለመሥራት የተገደዱት ማንነተቻውን ማመቻመች በከበደው የትምህርት ስርዓት፣ የቅጥር ሁኔታ፣ የሚዲያ ትርክት እና የመሣሠለው ኢፍትሐዊነት ነው። ይህ ኢፍትሐዊነት ደሞ የሙስሊሟን ሴት ሕይወት በማክበድ ብቻም አይመለስም። በመንግሥት ኦፊሴላዊ ቆጠራ መሠረት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአገሪቷን 1/3 ይሸፍናሉ፤ ስለዚህም እነዚህ አግላይ አካሔዶች 1/6ኛውን የአገሪቷን ዜጋ በቀጥታ፣ የተቀረውን 1/3 ደግሞ በተዘዋዋሪ ይገፋል። አገራዊ ስሜቱን ይነጥቃል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ችግሩ እዚጋ አይቆምም። 1/3 ሕዝቧን ሳታካትት የምትጓዝ አገር መቼም አታድግም። ሙስሊሟ ሴት ላይ የሚፈፀመው የውክልና እጥረት፣ ኢፍትሐዊነት እና መሠሉ ተግባር ነገን አሻግሮ ማየት ለቻለ ሰው አገር ላይ የተነጣጠረ አደጋ ነው። ይህን አደጋ ለመሻገር ከልጅነት ጀምሮ ገፊ የሆኑ እና አገራዊ ስሜትን የሚሸረሽሩ የትምህርት ስርዓቱ ህፀፆችን ማረም፣ ሚድያው፣ መዝናኛው እና መሠል ማኅበራዊ ዲስኮርሶች አግላይ እንዳይሆኑ መሥራት። ፆታን፣ ዘርን አልያም እምነትን ለይቶ ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮችን በማስወገድ እና ሁሉን ዐቀፍ የማብቃት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

ያ ሳይሆን ሲቀር ግን ወደማንወጣው እና ሁሌም ወደዞረ ድምር የሚመልሰን የአዘቅት አዙሪት ዙሪያ መሽከርከሩን እንቀጥላለን። ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊ ሴትነት በተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መገለጫ ላይ ተንጠልጥሎ ሲቀር ሌሎቻችን የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ማድመቂያ፣ አልያም የኢድ ልዩ ዝግጅት ማጀብያ ሆነን እንቀራለን። ይህም ዜጎችን በገዛ አገራቸው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ በጊዜ ሒደት የአገር አንድነትን የመሸርሸር እና ዕድገትን የማደናቀፍ አቅም አለው።

የአካታችነት ተስፋ እና ለውጥ
ሊን ኢን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና የማኬንሲ ጥናትና የቢዝነስ አማካሪ በጋራ በመሆን ‘Women In the Work Place’ በሚል ርዕስ ከ12 ሚሊየን በላይ ሰራተኞች ባሏቸው 279 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ 64 ሺሕ አካባቢ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ተሳታፊ በማድረግ የተቋማትን የብዘኀነት ባሕል፣ አካታችነት፣ የሴቶችን ተሳትፎና የሚገጥማቸውን ችግሮች በሚመለከት ጥናት አድርገዋል። በጥናቱ መሠረት አሁንም የተቋማት ብዝኀነትና የአካታችነት ባሕል ብዙ የሚቀረው መሆኑን በመደምደም ስድስት የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

የመፍትሄ ሐሳቦቹም የሚከተሉት ናቸው። ብዝኀነትን የሚቀበልና አካታች ስርዓትን መፍጠር የዜጎችን ሰብኣዊ መብቶች ማክበር መሆኑን በመረዳት ይህንኑ ለማሳካት እቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ሪፖርት ማድረግ፣ የተቋማት የቅጥር ሒደትን ፍትሐዊነት ማላበስ፣ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮችን የብዘኀነት አቀንቃኞች ማድረግ፣ አካታችና በመከባበር የተመሠረተ ተቋማዊ ባሕል ማዳበር፣ የሴቶችን ተግዳሮቶችና የሚደርሳባቸውን ትንኮሳዎች መቀነስ እንዲሁም ለዜጎች ሥራቸው ከማኅበራዊ ሕይታቸው ጋር ግብቡ የሚሆንበት ተጨባጭ መፍጠር የሚሉት ናቸው። ማኪኒስ የጥናትና የቢዝነስ አማካሪ በዚህና መሠል በርካታ ጥናቶቹ ብዝኀነትን ማስተናገድና አካታችነትን ከሰብኣዊ መብቶች መከበር አጀንዳነት ባለፈ የተቋማት ብሎም የአገራት ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ብልፅግና መሠረት መሆኑን ይሞግታል።

በሴቶች የትምህርትና የሙያ ተሳትፎ፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የንብረት ባለቤትነት መብት፣ የጤና ጉዳይን ጨምሮ በሌሎች የሕይወት ዘርፎች የውሳኔ ነጻነት፣ የሕግ ከለላና የማኅበራዊ ተጠቃሚነት፤ በተቋምና በከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን እርከን ውክልና ወዘተ. የዓለም ሪፖርትን ስንመለከት የአገራችን ሴቶች ፈተናዎች ባለ ብዙ ደርዞች መሆኑን እንረዳለን። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የሙስሊም ሴቶች ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ የከፋ ነው። በርግጥ አገራችን ኢትዮጵያ በወቅቱ እያለፈችበት ካለው የለውጥ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እንደማንኛውም የአገሪቱ ዜጎች ሙስሊም ሴቶችም በአንፃራዊነት የተሻለ ውክልና እያገኙ ነው። ለውጡ እና መሻሻሎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው። የአካታችነት ጉድለት አንድ አካልን ብቻ አቁስሎ የሚነቀል ቀስት አይደለም፤ በዚህ ድርብርብ ደርዝ ባለው ችግር ውስጥ የብዙ አለመወከሎች መደብ አቋራጭ (‘ኢንተርሴክሽን’) የሆኑት የኢትዮጵያ ሙስሊም ሴቶችን እውነት ለመቀየር ከተጀመረው በላይ ሥራ ያሻል።

ይህን ዜጎችን የሚገፋ እውነታችንን መቀየር ካልቻልን ተተኪው ትውልድም እንዳለፉት ሁሉ ይህን ሁሉ ፈተና አልፋ የበቃች ሙስሊም ሴት ሲያይ ከየት መጣች ብሎ መቀበል ይከብደዋል። በቅርቡ እንኳን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቢኔያቸውን 50% ሴቶች አድርገው በመረጡበት ወቅት ከዐሥሩ ሴቶች 2ቱ ብቻ ሙስሊም ሴቶች የሆኑ ቢሆንም፥ ማኅበረሰባዊ ሚድያው ላይ ግን ሙስሊሞቹ ለምን በዙ የሚል ማጉረምረምን ሰምተናል። ሙስሊሟን ሴት ከሕይወት የተነጠለች በብዙ ኢትዮጵያዊ እርከኖች ላይ ታይታ የማትታወቅ እና ሚና የሌላት አድርጎ መሳሉ፣ ስዕሉም እውን ይሆን ዘንድ ተፅዕኖ ማሳደሩ ከዲሞክራሲ መሠረቶች አንዱ የሆነው የዜጎች ውክልናን ይፃረራል።

ታዋቂው የቋንቋና ሥነ ጥበብ ሊቅ ኤድዋርድ ሰይድ ስለ ‘ኦርየንታሊዝም’ በሚያወጋበት መጽሐፉ የ‘ኦርየንታሊዝም’ ወይንም ወደ አንድ ሕዝብ ላይ የተቃጣ የተሳሳተ አመለካከት ትልቁ ጉዳቱ ያልሆነውን ነው መባላችን ሳይሆን፥ የሆነውን ውብ ነገሮች ልናሳይበት የምንችለውን ጊዜ እና ጉልበትን ያልሆነውን በመከላከል እንድንፈጅ ማድረጉ ነው ይላል። የኛም ታሪክ ይኸው ነው። በቀላል ምሣሌ – በሙስሊም ሴቶች ዙርያ ይህ የተሳሳተ አመለካከት እና የውክልና ችግር ባይኖር እኔ እዚህ አምድ ላይ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ስለማረም በመጻፍ ያሳለፍኩትን ጊዜ ሌላ ነገር ላይ አውዬው ከዚህ የተለየ ጽሑፍ ይዤ በመጣሁ ነበር። የውክልና ማጣት ክፋቱ ቀጥይ እርምጃን ተራምደው ማራመድ የሚችሉ ሰዎችን ጊዜ እና ጉልበት በውክልና ጥያቄ ውትወታ እንዲያልቅ ማድረጉ ነው። አገርን የሚቀይር ተሰጥኦ የተዛባውን ምሥል በማስተካከል እንዲባክን ያደርጋል፤ የኔን ዓለም ውበት ባካፍል የሚገኘውን ጥቅም ያሳጣል። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here