“እንዲህ አይደሉ እንዴ?”

0
836

የልብ_ወለድ ድርሰቶች፣ ፊልሞች፣ ቴአትሮችና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሴቶችን ንዑስ ስብእና እና አፍቃሪ ንዋይ አስመሥለው የመሣላቸው እውነታ የአደባባይ ምስጢር ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ የፈጠራ ገጸ ባሕርያት የምናውቃቸውን ሴቶች አይወክሉም የሚሉት ተዋናይት እና ጸሐፌ ተውኔት አዜብ ወርቁ፥ ገጸ ባሕርያቱ የሚያሳዩን በኪነ ጥበቡ ሴቶች የሚገለጹበት አምሣል ከአድሎዓዊው ስርዓተ አስተሳሰብ የተቀዳ መሆኑን እንጂ ነባራዊውን እውነታ አይደለም በማለት ይገልጹታል።

ከመልዕክት ተደራሽነት አኳያ ሲታይ የአንድን ማኅበረሰብ አሰተሳሰብ ለመቅረፅ እንዲሁም ባሕልና ልማድ ለማስረፅ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እና መገናኛ ብዙኀን ምቹ መሣሪያዎች ናቸው። በአገራችን የኪነ ጥበብ ሥራዎች እና መገናኛ ብዙኀን ሴቶች በምን መልኩ ተስለው ይቀርባሉ? ወክለውስ የሚጫወቷቸው ገጸ ባሕሪያት የእነማንን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ ሴት ገጸ ባሕሪያት የሚወከሉት ከሌሎች ጋር ያላቸው ግንኙነትን ወይም ማኅበረሰቡ ሴቶች መሆን አለባቸው ወይም ናቸው ብሎ የሚጠብቃቸው እናትነትን፣ ሚስትነትን፣ ፍቅረኛነትን… በሚወክል ገጸ ባሕሪን ሲሆን፥ በሙያ ደረጃም የወሳኝነት ሚና የሌላቸው ደጋፊ የሆኑ፣ በአዕምሮ ብስለት ሳይሆን በአካላዊ ውበት የሚመዘኑ፣ የሚያሳዩት ባሕሪም ፈሪ፣ አልቃሻ፣ ቀናተኛ፣ አባይ፣ አፍቃሪ ንዋይ፣ እምነት አጉዳይ… በምክንያት በተደገፈ ድርጊት ወይም ውጤት ሳይሆን በተለመደው የፆታ ፍረጃ በተገነባ ደካማ ሰብእና ይገለጻሉ። ሆኖም ግን በገሀዱ ዓለም ራሳችንን እና ዙሪያችንን ስንመለከት ደካማ እና ጠንካራ ባሕሪ፣ በሰብእና ውስጥ እንጂ በፆታ ተፈርጆ አናገኘውም።

ኢምክኒያታዊ የሆኑ የባሕሪ ፍረጃ ውክልናዎች በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ማቅረብ በገሀዱ ዓለም ኅብረተሰቡ ስለሴቶች የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖን እና የፆታ ጭቆና ያጠናክራል። ለዚህ እንደ ምሣሌ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ከቴአትር ትወና ተማሪዎች ጋር የነበረኝን አጋጣሚ ጥሩ ማሣያ ነው ብዬ ስለማምን ለመጥቀስ እወዳለሁ።

አንድ ቀን በትወና ትምህርቱ ላይ ተማሪዎች የተለያዩ ስሜቶችን መነሻ አድርገው፥ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ድንገቴ ትወና (Improvisation) እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። አንደኛው ቡድን የያዘው አርዕስት ወይም ስሜት ንዴት ሲሆን፥ የቡድኑ አባላት ኹለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ናቸው። ቡድኑ መሪ ገጸ ባሕሪውን እንዲወክል ያደረገው ወንዱን ነው።

በዚህ ውከላ ራሱ ለምን የሚለውን ጥያቄ አንስቶ፣ በፊልም እና በቴአትር ሥነ ጽሑፍ እና ትረካ ውስጥ ወሳኝነት ድርሻ አላቸው በሚባሉት የደራሲነት እና የአዘጋጅነት ሙያዎች ውስጥ የሴቶች ቁጥር መሳሳቱ፣ የወንዶቹ ቁጥር መበርከቱ፣ ታሪኮቹ ከወንድ ዕይታ ብቻ ለመሆናቸው፣ መሪ ገጸ ባሕሪዎች በወንዶች ብቻ ለመያዛቸው ያለውን አስተዋፅዖ እና የሚያዛባውን የትርክት ችግር ለሌላ ርዕስ በይደር አስቀምጠን በታዳጊነት ላይ ያሉ ባለሙያዎች ከፍ ያሉ ቦታዎች እና መሪ ገጸ ባሕሪንም ለወንዶች የመልቀቅ እና የማስለቀቅ ልማድ ለመተግበሩ ያደረገውን አስተዋፅዖ ግን ከላይ ባነሳነው ሐሳብ ማየት እንችላለን። ለዛሬ ግን ለተነሳሁበት ርዕስ ማሳያ እንዲሆነኝ በተውኔቱ ላይ ከቀረበው ቃለ ተውኔት ቀንጨብ አድርጌ ላካፍላችሁ።

ወንድ ተማሪ – [በንዴት በእግሩ መሬቱን ያጎናል]
ሴት ተማሪ 1፦ [በሁኔታው እየተጨነቀች] ምነው ምን ሆንክ?
ወንድ ተማሪ፦ [በንዴት ፀጉሩን ይነጫል]
ሴት ተማሪ 2፦ ኧረ ምን ሆነሃል? በጣም የተናደድክ ትመስላለህ?
ወንድ ተማሪ፦ ሴት ጓደኛዬ አናዳኛለች።
ሴት ተማሪ 1፦ ለምን?
ወንድ ተማሪ፦ [በንዴት እተወራጨ] ገንዘብ አይጠቅማትም፤ ሁል ጊዜ ጋብዘኝ ነው፣ ገንዘብ ስጠኝ ነው፣… ስልክ ግዛልኝ ነው…
ሴት ተማሪዎቹ ለእሱ የማዘን ግብረ መልሥ እያሳዩ አይዞህ ብለው ለማባበል ቃጥቷቸዋል። ወንዱ ተማሪ “ሴቶች ሲባሉ” እያለ ንዴቱን ገለጸ። እኔ ጥያቄ አቀረብኩ።
እኔ፦ ይኼንን ጭብጥ ያነሳው ማነው?
ወንድ ተማሪ፦ [በኩራት] እኔ!
እኔ፦ በተውኔቱ ላይ የገለጽካትን ዓይነት ሴት በገሃዱ ዓለም ታውቃለህ?
ወንድ ተማሪ፦ [ተጠራጠረ]
እኔ፦ ሴት ጓደኛህ እንዲህ ዓይነት ባሕሪ አላት?
ወንድ ተማሪ፦ ኧረ እኔ ሴት ጓደኛ የለኝም።
እኔ፦ እህትህ እንደዚህ ዓይነት ባሕሪ አላት?
ወንድ ተማሪ፦ [ኮስተር ብሎ] በጭራሽ!
እኔ፦ እናትህስ?
ወንድ ተማሪ፦ [በተደፈርኩ ስሜት] የኔ እናት? እንዴ? የኔ እናት የተከበረች ሴት ናት?
እኔ፦ ታዲያ በተውኔቱ ላይ የገለጽካትን ዓይነት ሴት ባሕሪ ከየት ቀዳኸው?
ወንድ ተማሪ፦ እንዲህ አይደሉ እንዴ?
“እንዲህ አይደሉ እንዴ?”

ከየት መጣ? ይኼ ልጅ በአካባቢው ከተሞክሮው እንዲህ ዓይነት ሴቶችን ካላየ ሁሉም የተሥማማበት የሚመሥል እንዲህ ናቸው ፍረጃን ከየት አመጣ? ይኼን እንደ ምሣሌ አነሳሁት እንጂ በመጽሐፎች፣ ፊልሞች እና ቴአትሮች ላይ ሴት መሆንን ለደካማ ስብእና በቂ ምክንያት አድርገው የሚስሉ ጸሐፊዎችን አንዳንዴ እጠይቃለሁ።

እንዲህ የሚቀናኑ፣ የሚመቀኛኙ፣ የማይታመኑ ሴቶች ታውቃላችሁ? እናታችሁ፣ እህታችሁ ጓደኞቻችሁ እንዲህ ናቸው? ብዬ እጠይቃለሁ። “አዎ፤ አውቃለሁ” የሚል ምላሽ አግኝቼ ምክንያቱም የተለያዩ ነገሮች ውጤት የሆነው የባሕሪ መለያ እንጂ የፆታ ስላለመሆኑ ተማምነን የተለመደውን የፍረጃ ትርክት ለመቀየር መሥራት እንደሚገባ ውይይት ያደረግኩባቸው አጋጣሚዎች አሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን ለጥያቄዬ የማገኘው ምላሽ በድርሰታችን ላይ የገለጽናቸውን ዓይነት ሴቶች በቅርበት አናውቅም ግን “እንዲህ ናቸው እኮ!”፣ “እንዲህ አይደሉ እንዴ?” የሚል ምላሽ ነው።

እንዲህ አይደሉ እንዴን ከየት ቀዳነው? ከመጽሐፍ? ከፊልም? ከመገናኛ ብዙኀን? ከአባባል? ከተረት? ከዘፈኖቻችን???
የኪነ ጥበብ እና መገናኛ ብዙኀን ሙያተኞች የኅብረተሰብን አሰተሳሰብ ሊቀርፅ የሚችል አቅም ያለው ሙያ ባለቤቶች እንደመሆናችን ለሰው ልጆች እኩል መብት፣ እኩል ዕድል የምንል፣ ፆታ ተኮር መድልዖን እና ጥቃትን የምንቃወም ከሆነ፥ ከባሕል፣ ከእምነት፣ ከአስተሳሰባችን ጋር የተጎናጎነውን የወንዶች የበላይነት የገነነበትን ትርክት በሥራዎቻችን በጥበብ ኩለን የምናስተጋባ፣ የምናስቀጠል እና የምናሰርፅ ላለመሆን ሥራዎቻችንን እና እውነታዎች የሚባሉትንም ጨምሮ በፆታ መነፅር ልንመርመር እና ልንፈተሽ ይገባል። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here