የዘመኑ የሴቶች ትግል ፈተና ዓልም ዐቀፍ ካፒታል

የስርዓተ ፆታን ድልድል ለማስተካከል ዘመናትን የተሻገረ ዓለም ዐቀፍ ትግል እየተካሔደ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አድሏዊው ስርዓት የትግሉን መሠረታዊ ፍሬ ነገር በማሳጣት አስቀያሽ መንገዶችን መስጠቱ የተለመደ ነው። ኤልሳቤት ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) በዚሁ ችግር ላይ ተመሥርተው የዘመኑ የሴቶች ትግል ዋነኛው ፈተና የከበርቴው ስርዓት ነው፤ የዚህም ትልቁ ተፅዕኖ የሚያርፈው በድሃ አገራት ላይ ነው ይላሉ።

ታላቋ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሊላ ፈርናንዴዝ እንደምትለው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና በያዝነው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ፣ መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (ግዙፍ ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅቶችን ጨምሮ) የቀረጿቸው ፖሊሲዎችና መርሐ ግብሮች ሴቶችን ግንባር ቀደም አጀንዳ ያደረጉ ናቸው። ዝቅተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ያላቸው ሴቶች ደግሞ የተሻለ ትኩረት ያገኙ ዘንድ ዘመቻ መሰል እንቅስቃሴውም ቀጥሏል።
ሆኖም ግን ይህ የመንግሥትና የዓለም ዐቀፍ አካላት የፖሊሲ አቅጣጫ በሴቶች ጥናትና በሴታዊነት ንድፈ ሐሳባዊ (feminist theories) ንግግሮች ላይ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ የሴቶች የእኩልነት መብት ጉዳይ አሁንም ፈተና ውስጥ ነው ስትል ትከራከራለች ሊላ ፈርናንዴዝ። በተለይ ታዳጊ ተብለው በሚጠሩት አገራት ውስጥ አሁንም በእኩልነት ሥም ሴቶች ጉልበታቸው መበዝበዙ ቀጥሏልና፥ ሴቶችን የተመለከቱ ለውጦችንና የወገንተኝነት የሚመስሉ ቃላትን በጥንቃቄ መፈተሽ አለብን።

በዚያ ላይ መዘንጋት የሌለብን ነገር የተባሉትም አዳዲስ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መርሐ ግብሮች እንዲያው ድንገት ከባዶ ሥፍራ የፈለቁ አለመሆናቸውንም ነው። የመርሐ ግብር ለውጦቹ በኹለት ትላልቅ ዐውዶች ውስጥ ነው ያደጉት። ዘመናትን ያስቆጠረውና አንዴ ብልጭ፣ አንዴ ድርግም፣ ሌላ ጊዜም ጠንከር እያለ የተጓዘው የሴቶች የፍትሕ ጥያቄና ትግል አንዱ ነው። ኹለተኛው ደግሞ በዓለማችን የተንሰራፋው የከበርቴያዊነት (capitalist) ስርዓት በታዳጊ አገራት ላይ ያለው ጫና ነው።

ይህን መንደርደሪያና የሐሳብ ማዕቀፍ ይዘን ኹለት ነገሮችን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። የሴቶች ትግል በመላው ዓለም ለዘመናት በተለያየ የታሪክ አግባብ ሲካሔድ ቢኖርም፥ ብዙዎቻችን የምናውቀው ወይም እንድናውቅ የተደረግነው የምዕራቡን ዓለም የሴቶች የእኩልነት ትግል ነው። ይህ የምዕራቡ ዓለም የሴቶች ትግል የምዕራቡን የሴቶች ፖለቲካ ቢቀይረውም፥ በዚያው በምዕራቡ አገራትም የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ አሁንም ቢሆን ከፈተና አላመለጠም። ጥያቄዎቻቸው በተለይ በዚህ በዘመነ ትራምፕ ወደ ኋላ መጎተት ብቻ ሳይሆን ለአዳዲስ ፈተናዎችም ተዳርጓል። ‘ዲሞክራሲ ትልቁ ዕሴታችን ነው’ በሚለው ምዕራቡ ዓለም ውስጥ ሴቶች በተለይ ደግሞ በንብርብር ጫና ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱቱ፥ ትግላቸውን አጠናክረው ሲገፉበት እናያለን። ‘ለምን?’ ካልን ደግሞ የምናገኘው መልስ የወንደኛው ስርዓት (patriarchy) ከከበርቴው ስርዓት (capitalism) ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ነው የሚል ይሆናል። የከበርቴው ስርዓት፣ ገበያውና ሌሎች የዕውቀት መነፅሮች ሁሉ የተገነቡት በወንዶች ዓለም ዕይታ ነው። ስለሆነም የሴቶች ትግል በዚያ አዙሪት እየተጠለፈ ስለሚገባ አንዴ ደከም እያለ፣ ጭቆናው ሲበረታበት ደግሞ በሴቶች ከፍ ያለ ድምፅ ዳግም ተግ የሚል ጉዞ ሆኗል።

ሊላ ፈርናንዴዝ እንደምትለው ብዙ መንግሥታት ሴቶችን ያስቀደሙ የሚመስሉ ፖሊሲዎችን ቢያወጡም ወይም የሴቶችን የማያቋርጥ ትግል ለማስተንፈስ እንደዚያ ለማድረግ ቢገደዱም፣ ሴቶች የየማኅረሰቡ ትልቅ አካላት ስለሆኑና የጉልበት ኃይላቸው ለካፒታል እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ፣ እንዲሁም ወንድን የበላይ ያደረገውና የሚያደርገው ስርዓት የካፒታሊዝም አንዱ አካል ስለሆነ ስርዓታቸው የሴቶችን እኩልነት በምልዓት ለመስጠት ያዳግተዋል።

ከምዕራቡ ዓለም ውጪ ያሉ አገራት የዓለም የካፒታል ጫና ይበልጥ አስከፊ በሆነ መልኩ የሚያርፍባቸው ስለሆነ ምዕራባዊ ባልሆኑት አገራት የሴቶች ጭቆና ኢሰብኣዊነቱ ወደር በማይገኝለት ሁኔታ ሲካሔድ ይታያል። ስለዚህም እንደኛ ባሉት አገራት የሴቶችን እኩልነት ጉዳይ ስናነሳ ካፒታሊዝም በኅብረተሰቡ ላይ ከሚጭነው ቀንበር ጋር አስተሳስረን ልናይ ይገባናል ማለት ነው። ያ ቀንበር ቀድሞውኑ አያሌ ጫናዎችን በተሸከሙት ሴቶች ላይ ሲጫን የሚፈጠረውን የጭቆና ልክ ካልመዘንንና ካልተወያየንበት የኢትዮጵያ ሴቶች እኩልነት ዘገባ ትርጉም ያጣል።

በኢትዮጵያ ሴቶች የወንዶችን ያህል ሥራ ማግኘት ይችላሉ? ከቻሉስ በየትኛዎቹ ዘርፎች? ዘጠና በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሴቶች በምን ሥራ ላይ ነው የተሠማሩት? ምን ያህል ደሞዝስ ነው የሚከፈላቸው? ለምን? ብለን ካልጠየቅን አደጋ ነው።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የካፒታሊዝምን እውነተኛ ባሕሪ አውቀን ‘ከነዚህ ዓለም ዐቀፋዊ ዐውዶች አንፃር በአገራችን ኢትዮጵያ ያለው የአደባባይ ንግግር ምን ይመስላል?’ ብሎ መጠየቅ ነው። እንዲያ ያለውን ጥያቄ ይዘን ሁኔታዎቻችንን ስንቃኝ ከኋላ አልፈንበት እንደመጣንበት አድካሚ አባጣ ጎርባጣ መንገድ ሁሉ የወደፊት ጉዟችንም የከባድ ከባድ እንደሚሆን እንገነዘባለን። አደባባዮቻችን የቀደሙ ትግሎችን የኋሊት በሚጎትቱና ከዜሮ በሚያስጀምሩ ትርክቶች እንደታፈኑ ነው ያሉት። የአሁኑን ትግል አስቸጋሪ የሚያደርጉት ደግሞ ሴቶችን የሚያግዙ መስለው ትግሉን የሚጎትቱ ዓለም ዐቀፍና አገር ዐቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ግለሰብ ወንዶች በትግል አጋርነት ሥም አብረው ስለሚቆሙ ወይም የቆሙ ስለሚመስሉ ነው። ሌላው ቀርቶ ብዙ ሴታዊት እንቅስቃሴዎች ትግሎቻቸውን የሚተልሙበት የሐሳብ መንገድ ታሪካዊና ማኅበራዊ ዳራዎቻችንን ከአገር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ጭቆናና የሴቶች ትግል ጋር የሚያስተሳስሩ ባለመሆናቸው የሚያመጡዋቸው ለውጦች የሚደነቁትን ያህል፥ ምልዓት ያለውን የነጻነት ጊዜ ወደ ኋላ በመጎተት (አውቀውም ሆነ ሳያውቁት) ይተባበራሉ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል
የኢትዮጵያ ሴቶች የፍትሕ ጥያቄና ትግል የቆየ ነው። ታሪካችን በኢትዮጵያ በይፋ እንዲታወቅ በሆነው (official) የታሪክ መዝገብ በጭራሽ ባይዘገብም ወይም እጅግ በጠለለና ይፋዊ ትርክቱን በማይጎዳ መልኩ ነገር ግን እልፍ የሴቶችን ታሪኮች ባገለለ ሁኔታ ቢተረክም፥ ትግላችን የቆየ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ታሪካችንን የምናገኘው ኃይለኞች ታሪክ ብለው በሚጠቅሱትና ይፋ በሚያደርጉት መዝገብ ውስጥ ሳይሆን በየዕለት ሕይወትና በየስርቻው በሚዘዋወሩ፣ በመሥመሮች፣ በቀለማት፣ በድምፆችና በምስሎች መካከል በምናደርጋቸው ጥልቅና ሒሳዊ ንባቦች ውስጥ ነው። እነዚያ ታሪኮች የሚያሳዩን ደግሞ ሴቶች ቁጭ ብለው የመጣውን ጭቆና ሁሉ ሲሸከሙ አለመኖራቸውን፣ ይልቁንም ለእኩልነት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ሥፍራዎችና ዘርፎች መታገላቸውን ነው።
መንግሥታት የሚያንፀባርቁት ታሪክ የሴቶቹን ትግል አንዴ ሲያዳፍን፣ አንዳንዴ ደግሞ ከላይኛው የኅብረተሰብ ክፍል አባል በሆኑ (እንዲሆኑ በተደረጉ) ሴት የጦር መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን ምሳሌነት የተነሳ ሲያነሳ ሲጥል ነው የኖረው። ጣይቱ ብጡል፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ አበበች ጨርቆሴ፣ ስንዱ ገብሩ እያለ እነዚህን አስደናቂ ተጋድሎ ያደረጉ ሴቶችን (ይፋዊ ታሪኩ ሊገድፋቸው ስላቃተውም) ለይስሙላም ቢሆን ሊያወሳ ሲሞክርም አስተውለናል። ነገር ግን የአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ፋይዳ እንደሌለው ተወርውሮ ወድቋል። የቅርቡን የኢትዮጵያን ተማሪዎች ንቅናቄ እንኳን እንደምሳሌ ብንወስድ የሴቶች ሚና ምን እንደነበር በወርድና በቁመናው ሳይገለጽ ቀርቷል። የታጋይ ሴቶች ታሪክ፣ እንደ ምሳሌም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ፣ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ሴቶች ትግል እና ውጣ ውረድ (በውስጥም በውጭም) ተድበስብሶ ቀርቷል።

በጣት የሚቆጠሩት የሴት ታጋዮችን ጽሑፎችና ትረካዎች ስናይም የሴቶችን ጭቆና አስከፊነትን ጥግና የትግል ፍሬዎቻቸውን ለሴቶችም መብት የቆምን ነን በሚሉት ታጋዮች ጭምር የመበላታቸውን እውነት በደንብ እንገነዘባለን። ከምንም በላይ ግን ሴቶች የሌሎችን የአዞ እንባና አጉል አዳኝነት የሚጠብቁ ሳይሆኑ ጭቆናን ፍልሚያው በተጠራበት ሜዳና ግንባር ሁሉ ሲፋለሙት የመኖራቸውን ሐቅ እናስተውላለን።

ስለዚህ የኛ የሴቶች አንደኛው ዋና ሥራ መሆን ያለበት ታሪካችንን ፈልፍሎ አውጥቶ ከኢትዮጵያ አገር ግንባታ ታሪክ ጋር ከማዛመድም በላይ ውስብስብ በሆኑ ችግሮችም መሐል በፊትም አሁንም በራሳችን ኃይል የቆምን መሆናችንን ማስረገጥ ሊሆን ይገባል። እንደማንኛውም ተገፊ ወይም አናሳ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ለእኩልነት ስንታገል የቆየን፣ አሁንም እየታገልን ያለን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደማንኛውም ግፉዕ ኅብረተሰብ ብዙ አስተዋፅዖ ያደረግን፣ ነገር ግን ገዢው ክፍል ከታሪክ ያስወጣን አንድና ትልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ነን።

የሴቶችን ትግል ተገናዊ ምልከታ
አሁን የሚታዩትን አንዳንድ የአገራችንን ሴቶች የተመለከቱ ሐሳቦችና ድርጊቶች ጥቂት እናንሳ። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነት፣ ፍትሕና ርትዕ ጥያቄዎችን አንፀባርቃለሁ የሚለውና ቀደም ቀደም ብሎ አደባባዩንና አየሩን ቅኝ የገዛው ቋንቋ ስንቶች በአገርም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታገሉለትን ጉዳይ ወደ ኋላ የሚወስድ ዓይነት ነው። “ሴት እህት ናት፤ ተንከባከባት”፣ “ሴት እናት ናት፤ አክብራት”፥ “ሴት ሚስት ናት፣…” የመሳሰሉት አዛኝ መሣይ መፈክሮች አደባባዩን አጣብበው፣ የመገናኛ ብዙኃንን አየር ሞልተው እናያለን። እነዚህ ደጋግ መስለው የሚመጡ አባባሎች “እናት መከበር” እንዳለባት ሲናገሩ ሐሳቡን የሚቃወም የለምና ሊያማልሉ ይችላሉ። ሆኖም ግን መነሻና መድረሻቸው ስለ ሴቶች ከኅብረተሰብ የወረሷቸውንና ‘ሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ አንድ ቦታ ዝንተ ዓለም ተቀርቅረው ሊቀመጡ ይገባቸዋል’ የሚለውን አስተሳሰባቸውን ያሳብቃሉ። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ተቋማዊ/ስርዓታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጓቸውን ትግሎች ሰርዘው፣ ነገሩን ሁሉ በአጉል ተገንነት (patronization) ትርክት ውስጥ ከተውት ቁጭ ይላሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ሴቶች በዋናነት መከበር ያለባቸው የተጠቀሱት የዝምድና ማንጠልጠያዎች ስላላቸው ነው ብሎ የሚያምን ካለ ያሳስባል። አንዲት ሴት ልጅ በተራ የሥነ ሕይወት አተያይ ካየናት እህትም፣ እናትም፣ ሚስትም ላትሆን ትችላለች። እነዚህ የዝምድና ሥያሜዎች በአንድ ደረጃ መልካምነትን አንግበዋል ብለን ልንወስዳቸው ብንችልም፤ መነሻና መድረሻቸው አንድ ነገር ብቻ ሲሆን፥ ይኸውም ሴት ሥያሜዎቹ ኖሯትም አልኖሯትም የምትከበረው ሰው በመሆኗ እና በሥራዎቿ ለመሆኑ ብዙ ማሰብና ማሰላሰል አያስፈልገውም። ይልቁንስ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች እንድናሰላስል የሚገፉን ከላይ የገለጽኳቸው ዓለም ዐቀፋዊ ከበርቴያዊነትና ወንደኛ ስርዓት የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ አድርገውት ሳለ እኛ ንግግሮቻችንን በዚህ ደረጃ እያካሔድን መቀጠላችንን ነው።
እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀሱት መፈክሮች ባዶና ትርጉም የለሽ አይደሉም። ለሴቶች እኩልነት ተቆርቋሪ፣ ለሴቶች የፍትሕ ትግል ወገንተኛ መሥለው ትንሽ ወደፊት ለመንቀሳቀስ የምትታትረውን ታጋይና ትግሏን ወደ ኋላ አሽቀንጥረው የሚጥሉ እንጂ። “ሴት እናት ናትና አክብራት” የሚለው ብሒል ‘የሴቶች ተቀዳሚ ተግባር ልጅ መውለድና ዘር ማስቀጠል ነው’ ከሚለው የኋሊት ተሳቢ እምነት በምን ይለያል? መላ አዋቂነት፣ ሩህሩህነት፣ ታማኝነት፣ ታጋሽነትና የመሳሰሉት ባሕሪያት ለምን የሴቶች (ብቻ) ቀንዲል፤ መገለጫ ይሆናሉ?

ከላይ እንደተባለው ያለንበት ዘመን ለሴቶች እኩልነት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያለ ይሁንታ የሰጠ ነው። ወይም ‘እንዲሰጥ’ ተገዷል። ስለዚህ ፖሊሲዎችና ዲስኩሮች በአብዛኛው ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ ይመስላሉ። ነገር ግን ጉዳዩን በትክክል ጠለቅ አድርገን ስንመረምረው ከላይ የተጠቀሰውና የአገራችንን አደባባይ ያጠነው ጥራዝ ነጠቅ ዲስኩር ይገን ዘንድ ያገዙት የካፒታሊስት ተቋማትም ናቸው። የካፒታሊስት ድርጅቶች (አንዳንዶቹም ከመንግሥት መርሐ ግብሮች በስተጀርባ በመሆን) የቀመሩት የጀግና ሴቶች ታሪክና ቋንቋ በተጨባጭ ካሉ ሐቆች ላይ ቢነሱም፥ የካፒታሊዝም የረድኤት ሰጪዎች ትርክት መነፅርን በቅርበት ስንፈትሽ ሴቶችን ተጎጂ፣ ተበዳይና ተረጂ ከማድረግ ያለፈ ዕይታ እንደሌለው ነው የምንረዳው። እንዲህ ዓይነቱ ትርክት በእጅጉ የሚበዛው የካፒታል ጫና በሚያይልባቸው ከምዕራቡ ዓለም ውጭ ባሉ አገራት ነው። ‘ለምን?’ ከተባለም እነዚህ አገራት በጣም ‘ኋላ ቀር’ ተብለው ስለሚገመቱ፣ ካፒታል ራሱን እንደ አዳኝ አድርጎ በማቅረብ ለመፈንጨት ስለሚመቸው ነው። ስለዚህ ቅፅሉም ግሱም የሚመነጭው ከበደል እና ከኋላ ቀርነት ትርክት ነው። መፍትሔ ተብሎ የሚቀርበውም ‘ማብቃት’፣ ‘ማስቻል’ ይሆናል።

በዚህ መሐል ነው የማደጎ ፖለቲካ ብቅ የሚለው። መንግሥት ራሱን እንደ አባት ቆጥሮ የደግ ወላጅ ወይም አሳዳጊን ሚና ይወስዳል። ሴቶች ደግሞ ‘ተበዳይና ኅዙናን ናቸው’ በሚለው ቀመር መንግሥት እነሱን ጠባቂና መከታ አድርጎ ራሱን ይሾማል። ሴቶች ቁልፍ የመንግሥት ቦታዎች ላይ ሲቀመጡም ቦታውን ያገኙት በዘመናት ትግላቸውና በተገቢነቱ ብሎም በችሎታቸው ሳይሆን ‘በተፈጥሯቸው አዛኝ፣ ታማኝና ከሙስና የራቁ በመሆናቸው ነው’ ተብሎ ይታመናል። ይህንን ስል ግን አሁን በአገራችን ጭራሽ አዎንታዊና ተራማጅ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የሉም፤ ተሿሚዎቹም የመንግሥት ሐሳብ ማስፈፀሚያና አስፈፃሚዎች ናቸው፤ የራሳቸው የትግል ታሪክና የውስጥ ኃይል የላቸውም ከሚል መነሻ አይደለም። እንደዚያ ማለት የሴቶችን ረቂቅ ትግል ከመካድ ይቆጠራል።

ንድፈ ሐሳባዊ መነፅርን ማስተካከል
መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የተለያዩ ተቋማት የሴቶች ተሳትፎን ለመጨመር እየሠሩ ነው። ይህ መልካም ነው። ይሁን እንጂ ‘የሴቶችን እኩልነት የምንመለከትበት ንድፈ ሐሳባዊ መነፅር ምን ቢሆን ነው ትክክለኛና ምልዓት ያለው (ስፋትና ጥልቀት ያለው) ለውጥ የሚመጣው?’ ብለን መጠየቅ አለብን። ሴቶች ስንል ሰለባነት ብቻ ከታየን መመርመሪያ መሣሪያችን ያሳየን ላይ ላዩን ነው ማለት ነው። ከዚህ የተሻለ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕይታ ይኖረን ዘንድ ሴቶች በታሪክ ውስጥ፣ ሴቶች ከመደብ አሰላለፍ አንፃር፣ ሴቶች በሥራ ክፍፍል መደቦችና የደሞዝ መጠን መዋቅሮች አኳያም ያላቸው ቦታ መመዘን አለበት። የካፒታሊዝም ጫና እነዚህን ነገሮች እንድንመረምራቸው አያበረታንም። አይፈልግምም። ነገር ግን አገር እንገነባለን፤ ከዚያም አልፎ ሴቶች የአገር ግንባታ አካል ናቸው ብለን አዳዲስ ጥያቄዎችን ካላስተናገድን የሴቶችንም ሆነ የአገር ግንባታን ጉዳይ በጥልቀት አላሰብነውም ማለት ነው።

ለምሳሌ የሥራውን ዓለም በትንሹ የቃኘን እንደሆነ በውስጠ ታዋቂነት ለሴቶች የተመደቡ የሚመስሉ የሥራ ዓይነቶችን በገፍ እናገኛለን፤ እነዚህ ሥራዎች ደግሞ በክፍያቸው ዝቅተኛና በሥራ ባሕሪያቸውም ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያመጡ ናቸው። በዚህ ረገድ በቅርብ የተስፋፉት የአበባ እርሻዎች ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው። ደሞዛቸው እዚህ ግባ የማይባል፣ ከዚያውም ብሶ በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና መታወክ የሚፈጥሩ ናቸው። ኬሚካሎችንም ስለሚጠቀሙ ጉዳታቸው ገጸ ብዙ ነው።

በአጠቃላይ ዝቅተኛ የሥራ መደቦችን ያየን እንደሆነ ለሴቶች የተተዉ ይመስላሉ። የቤት ሠራተኛነት፣ የመንገድና የሕንፃዎች ግንባታ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የመሥሪያ ቤቶችና የሆቴል ቤቶች ፅዳት አገልግሎቶች በሴቶች ላብና ጉልበት የቆሙ ናቸው። ከዚህ አኳያ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተመሣሣይ ሚና ያላቸው ድርጅቶች ከፖሊሲ ቀረፃ አንስቶ እስከ ተግባራዊነቱ ድረስ ያለውን ሒደት በአፅንዖት መመርመርና መፈተሽ አለባቸው።

የሴቶች ትግል በተለይም የአገራችን ሴቶች ትግል ብዙ ዘርፎች ያሉት፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መታየት ያለበት፣ በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈና እያለፈ ያለ ነው። የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ከአገር ግንባታ ታሪክ፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ የአገር ግንባታ ታሪክ ጋር ተያይዞ ሊታይ ይገባዋል። ማለትም ከ’ልማታዊ መንግሥት’ ኢኮኖሚ ታሪክ እንዲሁም አሁን ከሚካሔደው ከ’ነጻ ገበያ’ ታሪክ ጋር፣ በአጠቃላይ ከገዢና ተገዢ ውስብስብ ታሪክ ጋር ካልተያያዘ ትርጉም የለውም። የሴቶች ታሪክ ክጭቁን ሕዝብ ታሪክ ጋር አብሮ የተያያዘ ነውና። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here