አይ ሺብሬ!

0
287

አግብቼ ከእናት ከአባቴ ቤት በወጣሁ ከአራት ዓመታት በኋላ ይኼ ሆነ።
ሁሌ እሁድ እሁድ ከሰዓት እንደማደርገው የኹለት ዓመት ተኩል ልጄን፣ ማክዳን ይዤ እኔ ወደ እናት አባቴ፣ እሷ ደግሞ ወደ አያቶቿ ቤት ገባን።
ቆይታችን እንደ ሁሌው ነበር። አባዬ ማክዳን ጉልበቱ ላይ አሳፍሮ ይወዘወዝታል። ትስቃለች። እማዬ ለአምስት ሰው እንዲበቃ አድርጋ የሠራችውን ምግብ ብቻዬን ጥርግ አድርጌ ስላልበላሁ ትነጫነጫለች። እኔ ደግሞ አንዴ ቲቪ ላይ የምታወራውን ራኬብን፣ አንዴ ደግሞ በሳቅ የምትንፈቀፈቀውን ልጄን በስስትና በፍቅር አያለሁ።

ዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ሲሆን እንደተለመደው ቡና ቀራረበና ቤቱ መጫጫስ ጀመረ። በእናቴ “እንዲህ አድርጊ… እሱን እጠቢ… ያኛውን አምጪ… ይኼንን ውሰጂ” ታጅባ ቡናውን የምታፈላው ሠራተኛችን ቴሌቪዥንኑን፣ ጀበና እና ስኒዎቿን አፈራርቃ እያየች በዝምታ ተቀምጣለች። ማክዳ እንቅልፍ ጥሏት የአባዬን ጋቢ ለብሳ ሶፋው ላይ ለጥ ብላለች።

ከዚያ፣ ልክ እንደ ሁሌውም፣ እማዬ እና አባዬ የሳምንቱን አዳዲስ ወሬ በቡና እያወራረዱ ያቀርቡልኝ ጀመር።
“ይኼ ሰፈር አሁንስ መላ ቅጡ ጠፋ! በቃ…! እንደሌላው ሰው ጨክነን ሸጠን መውጣት አለብን…” አለ አባዬ።
አባዬ በቀድሞው ሰላማዊ ሰፈራችን “መበላሸት” መማረሩ አዲስ አይደለም። ይኼ ወሬ አግብቼ ከመውጣቴ በፊት አንስቶ በየቡናው የሚነሳ እና የሚጣል ነው።
በመሰላቸት መታኘክ የማይፈልገውን ፈንዲሻዬን እንደማስቲካ አኝካለሁ። ቡናዬን ፉት እላለሁ።
“አሁንማ ለየለት እንጂ! ጭራሽ በራችን ላይ መቆም ጀመሩ እኮ!” አለች እማዬ።

ይኼም የተለመደ ነገር ነው። የእማዬ እና የአባዬ ወሬ ልክ በካሴት ተቀርፆ ተደጋግሞ እንደሚሰማ ሁሉ ከጥቂት ዓረፍተ ነገሮች መቀዳደም ውጪ ሁሌም መገመት የሚችል፣ ሁሌም አንድ ነው።

በመታከት በወጉ ያልፈኩ ፈንዲሻዎችን ከሰሀኑ ላይ አፍሼ በጥርሴ ለመስበር እታገላለሁ። በመቀዝቀዝ ላይ ያ ቡናዬን ፉት እላለሁ።
“ሸጠን መሔድ አለብን ዝናሽ… በቀኝ ማሳጅ ቤት፣ በግራ መጠጥ ቤት ጎረቤት አድርገን እስከመቼ እንኖራለን?… መሸጥ አለብን…!” አባዬ ቀጠለ።
ቀዝቃዛ ቡናዬን ጭልጥ አድርጌ ጨረስኩና ስኒውን ለልጅቱ ወሰድኩላት። ደንገጥ ብላ ብድግ አለችና ተቀብላኝ፣
“ሦስተኛ ትጠጫለሽ?” አለችኝ።
“አይ… በቃኝ…” አልኩና ቦታዬ ተመልሼ ተቀመጥኩ።
“እስቲ ሄለንዬ፣ ደኅና ደላላ ፈልጊ…” አለ አባዬ ቁጭ ከማለቴ።
“አይ አባ…” አልኩና ዝም አልኩ።
“ምንድነው አይ አባ?” ቆጣ ብሎ መለሰልኝ።

“የእናንተ ነገር… እንሸጣለን ስትሉ ስንት ጊዜያችሁ… እኔም ዳግምም ስንት ደላላ አመጣንላችሁ… ዝም ብላችሁ ነው…” አልኩኝ ሶፋዬ ላይ እየተመቻቸሁ።
“አይ…! አሁንስ በቅቶናል ሄለንዬ… ትላንት የሆነውን ባየሽ ታምኚን ነበር!” አለች እማዬ ስኒዋን ለልጅቱ እየመለሰች።
“ትላንት ደግሞ ምን ተፈጠረ?” አልኩኝ ብዙም ሳልጓጓ።
***
ጡረተኞቹ እናት እና አባቴ ትንሹን ትልቅ፣ ኮረብታውን ራስ ዳሸን፣ የሰፈር ጅረትን አባይ አድርገው የማየት አባዜ አለባቸው። “መቼ ዕለት በራችን ላይ ትልቅ የመኪና አደጋ ተፈጥሮ” ካሉ ኹለት ቪትዞች ተነካክተው ነበር ማለት ነው። ‘አጎትሽ ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ላይ ነው’ ካሉ ሐኪም ቤት ውሎ ቤቱ ገብቷል ማለት ነው።
እማዬ ሠራተኛችንን አየት አደረገቻት።
ሒጂ ማለቷ ነው። ምስጢር ልናወራ ስለሆነ ዕቃሽን ሰብስበሽ ሒጂ ማለቷ ነው።
ልጅቱ የሰው በማይመስል ፍጥነት ዕቃዎቹን ሁሉ ሰባስባ ወጣች።
አሁን ጓጓሁ።
“እ… ምን ተፈጠረ?” አልኩ ደግሜ።
እማዬ የሚያጓጓ ወሬ ልትናገር ስትል እንደምትቀመጠው ሰውነቷን ሁሉ ሶፋው ጫፍ ላይ ሰብስባ ተቀመጠችና ድምፅዋን ዝቅ አድርጋ፣
“ማታ ማታ እዚህ ዋናው መግቢያችን… አስፋልት ዳር የሚቆሙት ሴቶች የሉም?” አለችኝ።
“እ…” አልኩ ጉጉቴ እየናረ።
“ትላንት ማታ አምሽተን ስንመጣ ሺብሬን አየናት!”
አባዬ ጭንቅላቱን ቀስ እያለ ግራና ቀኝ ወዘወዘ። ሲያዝን የሚያደርገው ነው።
“ሺብሬ… ሺብሬ የኛ?” አልኩኝ ማመን እየተሳነኝ።
“እህስ!.. ራሷ ናት። መኪናችንን ስታይ አወቀችን መሰለኝ ሸሽታ ብትሔድም በደንብ አይቻታለሁ!” አለች እማዬ ከበፊቱ ጮክ ብላ።
“ከዚህ ከወጣች ወዲህ ከእንግዲህ ሰው ቤት በቃኝ ብላ መሸታ ቤት እንደምትሠራ ሰምተን ነበር፤ ግን እንዲህ ለይቶላታል ብዬ አላሰብኩም ነበር… አቤት አቤት!” እማዬ ወደ ጣራ እያየች ተናገረች። ፈጣሪን ማየቷ ነው።
“ለነገሩ እንደዛ እንደ ልጃችን አድርገን ስናያት የሠራችን ሥራ ያየ ሰው መጨረሻዋ እንደዚህ ቢሆን አይደንቀውም…! ያሳዝናል ብቻ…” አለ አባዬ።
ደነዘዝኩ።

ሺብሬ መጨረሻዋ እንዲህ ሆነ?
በቅፅበት ስምንት ዓመት ወደኋላ ሄጄ የሆነውን ሁሉ አስታወስኩ።
ሞላሌ ከሚባል አገር መጥታ እኛ ቤት በሠራተኛነት ስትቀጠር ከዐሥራ አምስት ዓመት አትበልጥም ነበር። እኔ ደግሞ ዐሥራ ስምንት ሞልቶኝ ነበር። ፍልቅልቅ እና ደስተኛ፣ ገራገር እና ታዛዥ ልጅ ነበረች። ከእኛ ቤት በፊት ሠራተኛ ሆና አታውቅም ሲሉ ትዝ ይለኛል። የተባለችውን ነገር በፍጥነት እና በጥራት ትሠራ ስለነበር እናቴ ለእኔ በሚቀርብ መጠን ትወዳት ነበር።
እኔ የተውኳቸው ልብስና ጫማዎች ይሰጧታል።
ለዓመት በዓል ለእኔ አምስት ነገር ከተገዛ ለእሷ ደግሞ አንድ ነገር ይገዛላታል።
የቤተሰብ ሽር ሽር ስንሔድ ሳይቀር ከእኔ እና ከወንድሜ ዳግም ጋር መኪና ውስጥ ቦታ ይኖራታል።
እንወዳት ነበር።
እወዳት ነበር። ታናሼ ብትሆንም የምበላውን ሠርታ ስለምታቀርብልኝ፣ የምለብሰው አጥባ ስለምትተኩስልኝ፣ የምተኛበትን አንጥፋ ስለምታሰናዳልኝ፣ የምወዳት እና የምትንከባከበኝ ታላቅ እህቴ ትመስለኝ ያህል እወዳት ነበር።
ለዘልዓለም እኛ ቤት የምትኖር ይመስለን ነበር። እንደዚያ ግን አልሆነም። ለምን?
ሺብሬ እኛ ቤት በገባች በዓመት ከምናምኑ አባዬ ለእማዬ ለኻያኛ የጋብቻ በዓላቸው የገዛላት እና ድግሱ ላይ መዓት ሰው ፊት የሰጣት የውሻ ማሰሪያ የሚያህል የወርቅ ሐብል ጠፋ። በዚያ ጊዜ እንኳን ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ብር የፈጀ ሐብል ነበር።
እማዬ አቅሏን ሳተች። አበደች። አባዬ ብስጭቱ ከልክ አለፈ።
እኔ እና ዳግም ቃላችንን ሰጠን። በፊትም በጨዋነት ያሳደጓቸውና እስከዛሬ አንዲትም ዕቃ ንክች አድርገው የማያውቁት ጎረምሳ ልጆቻቸው በዚህ እንደማይጠረጠሩ የሚያውቁት እማዬ እና አባዬ ዓይናቸውን ማን ላይ ጣሉ? ያቺ መከረኛ ሺብሬ ላይ።
“ካንቺ ውጪ ማን ወሰደው ይባላል? እያዳፋሁ ፖሊስ ጣቢያ ወስጄ ሳላስገርፍሽ ሐብሉን ውለጂ!” ብለው አዋከቧት።
እምባዋ እስከዛሬ ትዝ ይለኛል። ከአንድ ሰው ዓይኖች በዚያ ፍጥነት ያ ሁሉ እምባ ሲወርድ እስከዛም ድረስ እስከዛሬም አላየሁም። ከማልቀስ ብዛት አይኖቿ ሽንቁር ያወጡ ይመስሉ ነበር።
በአገሯ ታቦቶች ሁሉ ማለች፣ ተገዘተች። ግን ማንም አላመናትም።
ክሯን ይዛ፣ “ከዋሸሁ ሦስቱ ሥላሴዎች እዚሁ ሦስት ቦታ ይቆራርጡኝ” ብላ ማለች። ግን ማንም የሰማት አልነበረም።
ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ ባሰብኩት ቁጥር እንደ አዲስ ያመኛል። ከስምንት ዓመት በኋላም እንደ ትኩስ ቁስል ይመዘምዘኛል። እረፍት ይነሳኛል።
እማዬ እና አባዬ እያካለቧት፣ በእንግድነት የመጣው ዘመዳችን በእርግጫ እየመታት፣ ወንድሜ ዳግም ሌባ ብሎ እየጮኸባት ፖሊስ ጣቢያ ብለው ይዘዋት ሄዱ።
ቤቱ ውስጥ ብቻዬን ስሆን መኝታ ቤቴ ገባሁና አርቄ ፍራሼ ሥር የደበቅኩትን የእማዬን የወርቅ ሐብል አውጥቼ ያዝኩትና ያለ ገደብ አነባሁ። አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ብር ልሸጠውና ከዚያ ጊዜ ቦይፍሬንዴ ቃልአብ ጋር “ልጫጫስበት” የሰረቅኩትን የእማዬን የወርቅ ሐብል ይዤ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።
“ሺብሬ አይደለችም… እኔ ነኝ የሰረቅኩት” ብዬ ለመናገር ብዙ ዕድል ነበረኝ።
ዘመዳችን ስንት ጊዜ ጎኗን በእርግጫ ሲያጎነው ልነግራቸው እችል ነበር።
ዳግም ሌባ እያለ ሲያንባርቀረባት ልነግራቸው እችል ነበር።
ማተቧን ይዛ እያለቀሰች ስትገዘት፣ እማዬን አባዬ በመጠየፍ ሲመለከቷት “እሷ አይደለችም… እኔ ነኝ የሰረቅኩት” ብዬ ልነግራቸው እችል ነበር። ላድናት፣ ልታደጋት፣ ነጻ ላወጣት እችል ነበር። ግን አላደረግኩትም።
…እና ዛሬ ሌባዋ እና ውሸታሟ ልጅ የሞቀ ትዳር መሥርቼ ስኖር፣ ያቺ ምስኪን እና ሐቀኛ ልጅ ግን ሴት አዳሪ ሆና በልታ ለማደር መንገድ ዳር ወንድ ትጠብቃለች። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here