እኔም ሴት እሆናለሁ!

ሴት ለመሆንና ሴት ስለመሆን በሚደረግ ትግል መካከል ያለው ልዩነት

በከተማ ያሉ ሴቶች ሴት በመሆናቸው ምክንያት ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ሲተነትኑ ለከፋና ከለከፋ የሚመነጩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ያነሣሉ፤ ሥራ ለመቀጠር ሲሔዱ ከቀጣሪዎች ስለሚቀርቡላቸው ወሲባዊ ጥያቄዎች ይዘግባሉ፤ በቤት ውስጥ ብሎም በሥራ ቦታ ስለሚሰጣቸው ከወንዶች ያነሰ ሚና ያነሳሳሉ። ወደድኩሽ በሚል ሰበብ ስለሚደርስባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖዎች ያወራሉ። በፊልምና በማስታወቅያ ሥራ ላይ የሚተውኑ ሴት ገጸ ባሕሪያት ስለሚሳሉባቸው አሉታዊ ተግባራትና ስለሚሰጣቸው አሉታዊ ሚና ይተርካሉ። የቤት ውስጥና የአደባባይ ጥቃት ይቆም ዘንድ ይታገላሉ። በባሎች ስለሚደርስባቸው ተፅዕኖ ያማርራሉ። ባሎቻቸው በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ እንደማይሳተፉ ያወራሉ፤ ያማርራሉ። በመዝናኛ ቦታዎች ብቻቸውን መዝናናት እንዳልቻሉና ወንዶች እንደሚተናኮሏቸው ያወሳሉ። በቤት ውስጥ የቤት ሥራ ጫና እንዳለባቸው ይናገራሉ፤ ያማርራሉ። በትምህርት ቤት ስለሚደርስባቸው ወሲባዊ ትንኮሳ ይናገራሉ። በሕክምና ቦታዎች ላይም በወንድ ሐኪሞች ስለሚደርስባቸው ወሲባዊ ትንኮሳ ያነሳሉ፤ ላቅ ሲልም ስለ ሥም አጠራራቸው ያወጋሉ።

ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ ተመልካች ነኝ፤ ግን ሴት ነኝ። መለከፍ ለኔ ሴት መሆኔን ማረጋገጫ ነው። ብለከፍ ተለከፍኩ ብዬ እስቃለሁ፤ እናደዳለሁ፣ ወይም መግቢያ መውጫ አጣለሁ። ከዛ ስለ መለከፍና ጣጣዎቹ አወራለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ። ያኔ ከቤቴ ወጥቻለሁ፣ መንገዱ እንደፈለኩት ያመላልሰኛል፤ ይመቸኛል። ሠው ሲያየኝ ከንፈር አይመጥም። ስለዚህ ለከፋን እሻለሁ፤ ያኔ ስለለከፋ አነሳለሁ፤ አማርራለሁ። ወንዶችን እረግማለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።
ደግሞም ሥራ ለመቀጠር ስሔድ ቀጣሪ አግኝቼ የወሲብ ጥያቄ ቢያቀርብልኝ እመርጣለሁ፤ ምክንያቱም ያኔ ጥበቃውንና መግቢያውን አልፌ ወደ ቢሮ መግባት ችያለሁ። የሚሰማኝ ሰው አግኝቻለሁ፤ ‘አትችይም’ ከመባል ድኛለሁ። ስለቀጣሪው ዋልጌነትም እዘግባለሁ፤ እተነትናለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።
ደግሞም በቤት ውስጥ ብሎም በሥራ ቦታ ከወንዶች ያነሰ ሚናን እሻለሁ፤ ያ ማለት ቤት ኖሮኛል። ሥራም እሠራለሁ፣ ሚናም ኖሮኛል። እናም ስለኔ ከወንድ ያነሰ ሚና መኖር አነሳሳለሁ። ያኔ ሴትነትን እቀዳጃለሁ።

ደግሞም ወደድኩሽ፣ አፈቀርኩሽ በሚል ሰበብ የሚደርስ ተፅዕኖን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ያኔ የሴትነት ወጉ ይደርሠኛል። አሳዛኝ ቅርፊቴን ፈንቅዬ ወጥቼ ስለሚያፈቅሩኝና ስለሚያስቸግሩኝ ወንዶች አወራለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።

ደግሞም በፊልሞችና በማስታወቅያ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተግባርና ሚና እንዲሠጠኝ እፈልጋለሁ፣ ምክንያቱም ያኔ እተውናለሁ። ስለሚሰጠኝ አሉታዊ ሚናም እተርካለሁ። ያኔ ሴት፣ እንዲሁም ተዋናይ እሆናለሁ።

ደግሞም ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባታል መባል እፈልጋለሁ፤ ያኔ እኔም ወሲብ የሚመለከተኝ ፍጥረት መሆኔን፣ ሰው ያውቅልኛል። “እርሷን ማን ይነካታል” ከመባል እድናለሁ፤ አለመታመኔ ይቆማል። ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥቃቶቼም ይፋ ይወጣሉ። እናም የ‘ፆታዊ ጥቃት ይቁም!’ ትግሉን እቀላቀላለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።

ደግሞም በባሌ ተፅዕኖ እንዲደርስብኝ እፈልጋለሁ። ያኔ ባል እንዳለኝ ይታወቅልኛል፤ ያኔ ሴት መሆኔ ይታወሳል። ያኔ ስለ ባሌ ተፅዕኖ አማርራለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።

ደግሞም ባሌ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ እንዳይሳተፍ እፈልጋለሁ። ያኔ ሥነ ተዋልዶ እንደሚመለከተኝ ይታወቅልኛል፤ ያኔ አወራለሁ፤ አማርራለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።

ደግሞም በመዝናኛ ቦታዎች ላይ ወንዶች እንዲተናኮሉኝ እሻለሁ። ያኔ መዝናናት እንደሚያስፈልገኝ እና እንደምችል ሰዎች ያውቃሉ። ወደ መዝናኛ ቦታዎች ያለምንም እርዳታ እደርሳለሁ። ያኔ ሴት ብቻ ሳይሆን ሰው እሆናለሁ። ስለተንኳሾቼ ለማውሳትና ለማማረር እበቃለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።
ደግሞም የቤት ውስጥ የሥራ ጫና እንዲኖርብኝ እፈልጋለሁ። ያኔ ሥራ እንደምሠራና መሥራት እንደምችል ሰዎች ያውቃሉ፤ እናም ስለጫና አወራለሁ፤ አማርራለሁ። ያኔ ሴት ብሎም ሰው እሆናለሁ።

ደግሞም በትምህርት ቤት ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲደርስብኝ እፈልጋለሁ። ሰዎች በትምህርት ቤት መገኘቴን ዕውቅና ይሰጡታል። ወደ ክፍሌ እንዳሻኝ እገባለሁ፤ የላይብረሪ በሩን አልፌ በማንበብያ ወንበር ላይ እራሴን ማግኘት እችላለሁ። ከክፍል ላይብረሪ ከላይብረሪ መፀዳጃ ቤት፣ ከመፀዳጃ ቤት ምግብ ቤት፣ ብሎም መዝናኛ ቦታ “ምፅ” የሚለውን ድምፅ ሳልሰማ ለመድረስ ችያለሁ። ስለዚህ ተማሪ ሆኛለሁ እናም ወንዶች ትንኮሳ ያደርሱብኛል፤ ስለነሱም አምርሬ እናገራለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ።

ደግሞም ሐኪሞች ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲያደርሱብኝ እሻለሁ፤ ያ ማለት የሆስፒታሉን ቅጥር ግቢ አልፌ ያለማንም ዕርዳታ ሐኪሙ ጋር መድረስ ችያለሁ። ሐኪሙ አካላዊ ጉዳቴን አልፎ ሴትነቴን አይቷል፤ መንገዴ ላይ ያገኘኋቸው ነርሶችና አሳላፊዎች “ምፅ… ምፅ” እያሉ በሐዘናቸው አጅበው ሊያስተናግዱኝ አልሞከሩም። ሚስጥሬን ባደባባይ አልዘሩትም፤ ለሥነ ተዋልዶ ሕክምና ሔጄ አካል ጉዳተኛ መሆኔን በማየት ብቻ ወደ አካላዊ ማገገምያ ክፍል አልመሩኝም፤ ያ ማለት ሴት የመሆንን ፈተና አልፌያለው። ያኔ ፆታዊ ትንኮሳ ስላደረሰብኝ ሐኪም አነሳለሁ፤ አማርራለሁ እናም ሴት እሆናለሁ።
ደግሞም ወይዘሮ፣ ወይዘሪት የመባል ወጉ እንዲደርሰኝ እፈልጋለሁ። ሰዎች ቅጥያ እንዲሰጡኝ እሻለሁ። ያኔ ስለ ሥም አጠራሬ እጨነቃለሁ፤ የመጠርያ ቅጥያ አልፈልግም፣ አይበጀኝም እላለሁ። ያኔ ሴት እሆናለሁ። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here