እንስታዊነት

0
1048

“ሴቶች ሰብኣዊ ፍጡራን ናቸው ብሎ የማመን ፅንፈኛ ፍልስፍና”

‘እንስታዊነት’ (‘ፌሚኒዝም’) ሴቶች ከወንዶች እኩል የተጠበቁ መብቶች እና ዕድሎች እንዲያገኙ የሚደረግ የፖለቲካ ንቅናቄ ነው። ቤተልሔም ነጋሽ ለዚህ ጽሑፍ በንዑስ ርዕስነት የተጠቀሙት “እንስታዊነት ሴቶች ሰብኣዊ ፍጡራን ናቸው ብሎ የሚያምን ፅንፈኛ አስተሳሰብ ነው” (“Feminism is the radical notion that women are human beings”) ከሚለው የክሪስ ክራማሬ ተጠቃሽ ንግግር ነው። በዚህ መነሻነት፣ ስለ’ፌሚኒዝም’ የሚከተለውን መጣጥፍ ያስነብቡናል።

 

‘ፌሚኒዝም’ በተሳሳተ መልኩ ትርጓሜና አሉታዊ ግምት ከተሰጣቸው ፅንሰ ሐሳቦች አንዱ ነው። ይህ የስድብ ሥም በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ሳይሆን ዓለም ዐቀፋዊም ነው። ሥያሜውን ማጠልሸት ፍልስፍናውን የመቃወም አንድ ስልት እስኪመስል አብዛኛው ሰው እንስታዊነትን የሚረዳው ፀረ ወንድ፣ ፀረ ትዳር፣ ፀረ ባሕል አድርጎ ነው። ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ “ትውፊታዊዎቹ” የሚል ሥያሜ እስከተሰጣቸው መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ‘ፌሚኒዝም’ የሚለው ሥም ሲጠራ ከድጋፍ ይልቅ ነቀፋና ተቃውሞ፣ ከሥሙ የመሸሽ ደፍረው ሥያሜውን የያዙትንም ጠንካራ ትችትና ስድብ ማከናነብ የተለመደ ነው።

በአብዛኛው “እንስታዊነት” ተብሎ የተተረጎመው እንግሊዝኛው ‘ፌሚኒዝም’ የሚለው እንቅስቃሴ ወይም ፍልስፍና በኢትዮጵያ እንዴትና በእነማን ተጀመረ የሚለው ጥያቄ በጉዳዩ ላይ ከተደረገው መጠይቅ ውስንነት ይሁን ፅንሰ ሐሳቡን በሚገባ ባለመረዳት በአግባቡ ያልተጠና እና መረጃ ከማይገኝባቸው ርዕሰ ጉዳዩችም አንዱ ነው። ራሴን ጨምሮ በአብዛኛው ራሳችንን በይፋ ሥሙን ከተቀበሉት መካከል የምናገኘው ሰዎች ግን ጭቆናንና እንደሁለተኛ ዜጋ መታየትን እምቢ ማለት፣ ያለው ስርዓት የእኔን ድምፅና ፍላጎት አላካተተም ይቀየር ማለት በእኛ አልተጀመረም ባዮች ነን። በታሪካችን ከምናውቃቸው የቃቄ ወርዶወት እና ንግሥት ፉራ እንዲሁም ሌሎች አንግበው የተነሱለት ትግል በዚህ አይሠየም እንጂ ድሮም የነበረ ነው።

ነገሩን አቃለሽ አየሽው ባትሉኝ በይፋና በተደራጀ መልኩ በተለያየ ጊዜ የሴቶችን መብቶች ለማረጋገጥ የተደረገው እንቅስቃሴ በተለምዶ “የሴቶች ጥያቄ” ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነሳበትና የዘውድ አገዛዝን ከገረሰሰው የተማሪዎች አብዮት “የመብት ትንሽ የለውም” ብሎ ከጓዳ እስከ አደባባይ ያሉ ሴቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለማንሳት እስከሚሞክረው የአሁኑ ዘመን እንቅስቃሴ ለዘብም ጠንከርም ብሎ የሚደረገው ሁሉ እንስታዊነት ሊባል የሚችል ነው። ሒደቱና ትኩረቱ ቢለያይም የመጨረሻ ግቡ የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ ነውና።

ምናልባት ቀደም ባለው ጊዜ ሳይቀር የነበሩት ‘ፌሚኒስት’ ነሽ ወይ? ተብለው ቢጠየቁ ነኝ ባይሉም እንዲህ ከሚለው ጋር ይመሳሰል ይሆናል፦
“እኔ ራሴ ‘ፌሚኒዝም’ ምን ማለት ነው ለሚለው መልስ በትክክል ማስቀመጥ በፍፁም አልቻልኩም። እንደ በር ላይ ምንጣፍ እንረማመድብሽ፣ መብትሽን ጣዪ የሚሉኝን እምቢ የሚል ነገር ባነሳሁ ቁጥር ግን ‘ፌሚኒስት’ ብለው ሲጠሩኝ አውቃለሁ” ሬቤካ ዌስት
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በኢትዮጵያ ‘ፌሚኒዝም’ እንዴትና በማን ተጀመረ? ኢትዮጵያዊው ‘ፌሚኒዝም’ (የሚባል ካለ) ምንድን ነው? ለሚለው በጥናት የተደገፈ መልስ/ጥያቄ በጣም ጥቂት ነው። ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ስፈልግ ካገኘኋቸው በቀጥታ በርዕሱ ላይ ከተደረጉ ጥቂት ጥናቶች መካከል አንደኛውና ጠቃሚ ሆኖ ያገኘሁት መስከረም 2011 በወጣው ዓለም ዐቀፍ የሶሲዮሎጂና አንትሮፖሎጂ ጆርናል ቅፅ 10 ቁጥር 6 ላይ በኹለት ኢትዮጵያዊ ምሁራን ቀርቦ የታተመው “የሊብራል ‘ፌሚኒዝም’ በኢትዮጵያ ተሥማሚነት እና አተገባበር (Liberal feminism: Assessing its compatibility and applicability in Ethiopia context) የተሰኘ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው። አጥኚዎቹ ቢምር እያዩ እና ዓለምነህ ጌታነህ ሲሆኑ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ፆታ እና ልማት ጥናት የትምህርት ክፍል ባልደረቦች ናቸው።

የአጥኚዎቹ ጽሑፍ የሚጀምረው ‘ፌሚኒዝም’ን በጥቅሉ፣ እንዲሁም ሊተነትኑት ያሰቡትን “ሊበራል ‘ፌሚኒዝም’” በተለየ በመተርጎም ነው። ትርጉሞቻቸው ከዚህ የሚከተሉትን ይመስላሉ።

“‘ፌሚኒዝም’ በሴቶች የሕይወት ልምድ በተለይም በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበታችነታቸው ላይ የሚመሠረት የተለያዩ፣ አንዳንዴ እርስ በእርስ የሚወዳደሩ፣ ሌላ ጊዜ የሚቃረኑ ማኅበራዊ ፅንሰ ሐሳቦች፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና የሞራል ፍልስፍናዎች ስብስብ ነው። የሴቶች ንቅናቄ ሲሆን ዋና ትኩረቱም ሴቶችን ነጻ ማውጣት ነው።”

“ሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ የፆታ መበላለጥ ወይም የሴቶች እኩልነት መታጣት የመጣው ሴቶችና ልጃገረዶችን ሲቪል መብቶች በመንፈግ፣ የትምህርትና የሥራ ዕድል እንዳያገኙ በማድረግ ነው የሚል ዕሳቤ ያለው ፍልስፍና ሲሆን፥ ይህ ሐሳብ በዋናነት የሚከወነው ይህ በወንዳዊ አስተሳሰብ በተቀረፀውና ማኅበራዊ ስርዓቱ ባነፀው በኹለቱ ፆታዎች መካከል እኩልነትን በሚያጠፋው አስተሳሰብ አማካይነት ነው ብሎ ያምናል። ሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ አነሳሱ ሁሉን ዐቀፍ መብት፣ እኩል ዜግነት እና ዲሞክራሲ በሚሉት ሐሳቦች ላይ ከሚያጠነጥነው የአብርኆት ዘመን “enlightenment period” ሊበራል ፖለቲካዊ ፍልስፍና ነው። የሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ ዋና ሐሳብ በሴቶችና በወንዶች ተመሳሳይና እኩል ትምህርት የማግኘትና ሥራ የመቀጠር መብት ሊኖራቸው ይገባል፣ የባዮሎጂ ወይም የመውለድ ያለመውለድ ልዩነት በእነኝህ መብቶች ላይ ልዩነት ሊፈጥር አይገባም የሚል ነው።”

ጥናታዊ ጽሑፉ ሴቶች በኢትዮጵያ ዝቅተኛው ደረጃ የያዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን አትቶ በውሳኔ ሰጪነትም ደረጃ “የእነሱ ነው” በሚባለው ጓዳ እና የቤት ውስጥ ኑሮ ሳይቀር ተሳትፎ እንደሌላቸው ይገልጻል። ሴቶች ሰብኣዊ መብቶቻቸው እንደሚጣሱ፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንደማያገኙና በብዙ ድህነትና እጦት ውስጥ እንደሚኖሩም አስቀምጧል።

የተነሳበትን መጠይቅ ማለትም የሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ ለኢትዮጵያ ይበጃታል አይበጃትም ለሚለው ሐሳብ መልስ ሲሰጥም የሴቶች እኩልነትን ለማምጣት በመንግሥት የሚተገበሩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ጨምሮ የሲቪል ማኅበረሰቡ ንቅናቄ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው ይላል። በአብዛኛው ተሥማሚ ነው፣ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እየሠራም ነው ሲል አንዳንድ የሊበራል ‘ፌሚኒዝም’ ዕሳቤዎች የተተዉ ወይንም ከኢትዮጵያ ሕግ ጋር ጭምር የማይሔዱ በመሆናቸው አይበጁንም ብሏል።

የ“ኢትዮጵያ” የሚባል እንስታዊነት (‘ፌሚኒዝም’) አለ?
በኢትዮጵያ በ’ፌሚኒዝም’ ዙሪያ ትርጉም ያለው መጠይቅ ያደረጉ ሰዎች የሚሥማሙት የተቀናጀና ማዕከላዊ አመራር የነበረው፣ ራሱን እንዲህ ብሎ የጠራ የ’ፌሚኒዝም’ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ነው። በዘመኑም ቢሆን ‘ፌሚኒዝም’ የተሻለ ተቀባይነትና ተከታይ እያገኘ ባለበት በማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴም ይሁን እንደ ሴታዊት ባሉ ተቋማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉን ያካተቱ፣ “የኢትዮጵያ ‘ፌሚኒዝም’” ሥያሜ ለመውሰድ የሚችሉ አለመሆናቸው ነው። ምናልባትም ይኼ ሁሉን ያለማካተት ጥያቄ የሚቀርቡባቸው ትችቶች አንድ ምንጭ ሊሆኑ ይችላል።

በአንፃሩ አሁን ምናልባትም ቀደም ሲል ጀምሮ ፍልስፍናውን አውቀውና ወደው ለሴቶች እኩልነት ለማምጣት ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለው የተከተሉትም የሚደርስባቸውን ወቀሳና ትችት፣ አለፍ ሲልም ስድብና ማዋረድ ዕለት ዕለት የሚዋጉ ከዚህም ጋር አብሮ ሴቶችን ነጻ የማውጣት አጀንዳን ለማስቀጠል የሚሮጡ፣ ባለው አሉታዊ ድባብና ጥላቻ ሥራቸው የበለጠ የሚከብድባቸው፥ ይህም ወደ ኋላ የሚጎትታቸው ናቸው።

ኢትዮጵያዊ የሚባል ‘ፌሚኒዝም’ የለም ብንልም በመግቢያዬ ላይ ለማየት እንደሞከርኩት ‘ፌሚኒዝም’ ሊባል የሚችል የሴቶች መብት ጥያቄና እንቅስቃሴ ነበር። ምናልባት የ’ፌሚኒዝም’ ታሪክ በኢትዮጵያ ምን ይመስላል ስንል ለዛሬው በይፋ ሥሙን ይዞ ለሚሔደው ንቅናቄ መምጣት ዋጋ የከፈሉና መንገድ የጠረጉ፣ መሠረት የጣሉ የመጀመሪዎቹ “ ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው፣ ልጆች የመውለድ የተፈጥሮ ፀጋ ስለታደሉ ይህ ትልቅ የከበረ ዓላማ እንደ ማነስ ተቆጥሮ ወደኋላ ሊጎትታቸው፣ ቤት ቅሩ፣ ሕልም አይኑራችሁ፣ አደባባይ አትውጡ ሊባሉ አይገባም” ብለው በሃይማኖትና በሕግ ጭምር ድጋፍ የነበረውን ለወንዶች ያደላ አኗኗርና ዓለም ተቃውመው የወጡ ሴቶች ታሪክ ሊነሳ የግድ ይላል። ስለ’ፌሚኒዝም’ በኢትዮጵያ ስናወራም እነኝህን ሴቶች ሳናነሳ ማለፍ አንችልም። በየወቅቱ ያነሷቸውን ጥያቄዎችና የሴቶች እኩልነትና ተሳትፎ ጥያቄ በመንግሥትና በሕዝብ እንዴት ይታይ ነበር የሚለውንም አብሮ ማየት የግድ ይላል።

የዓለም ዐቀፉ የሴቶች ጥናት (Journal of International Women’s Studies) ጆርናል ቅፅ 14 ቁጥር 3፣ የሐምሌ 2005 እትም ላይ የወጣውና “የተደበቀው ታሪክ፣ የሴቶች የመብት ጥያቄ በኢትዮጵያ” የተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ የተሻለ ታሪኩን ተንትኖታል ብዬ ስላሰብኩ ከታች ለተዘረዘሩት የሴቶች መብቶች እንቅስቃሴ ዋና ዋና ክስተቶች በማጣቀሻነት ተጠቅሜዋለሁ።

የሴቶች ጥያቄና የ1966ቱ የተማሪዎች አመፅ
የኢትዮጵያ ሴቶች ከ1930ዎቹ ጀምሮ ለተለያዩ ዓላማዎች መደራጀትና መሰባሰብ እንደጀመሩ ጸሐፍት ይነግሩናል። ዐፄ ኃይለስላሴን ከሥልጣን ያስወገደው የተማሪዎች አመፅ የሴቶች እኩልነት ጥያቄ አንዱ እንደነበር በወቅቱ የንቅናቄው ተሳታፊ የነበሩ፣ በኋላ የሴቶች ጥያቄ እንደ አዲስ እንዲቀሰቀስ ያደረጉ እንደ ታደለች ኃይለሚካኤል ያሉ ዕውቅና ቀደምት የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ። በወቅቱ ተማሪዎች አንግበው የተነሱት ጥያቄ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የትምህርት ዕድል አለማግኘታቸውን፣ በመንግሥት ሥልጣንና ሥራም እጅግ ጥቂት ከሚባሉ ከፊውዳል ወገን ከሆኑት በስተቀር ተሳታፊ አይደሉም። ገሸሽ ተደርገዋል የሚሉ ነበሩ።

ሶሻሊዝምና የአብዮታዊት ኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበር
የተማሪዎች አመፅና የፊውዳሉን ስርዓት ለመጣል የነበረው ትግል ስርዓቱን ካስወገደ በኋላ በደርግ ተሞጭልፎ ወታደራዊ መንግሥት ሲመጣ፥ የሴቶች ጥያቄ በሶሻሊዝም አንፃር ተቃኘ። ቢያንስ የሴቶችን ጥያቄ በተወሰነ መልኩ በሕገ መንግሥት ውስጥ አካቷል የተባለው ደርግ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበር (አኢሴማ)ን ሲያቋቁም ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን ለየብቻ የሚያደራጅ ወወክማ እና ወሴክማ የተሰኙ ድርጅቶች አብረው የተቋቋሙ ቢሆንም ታች ድረስ ወርዶ ሴቶችን በሙሉ የሚያካትት የማደራጀት ሥራ እንዲሠራ ኃላፊነት የተሰጠው ግን አኢሴማ ነበር። ይህም ትልቅ የመንግሥት አካል የነበረ ሲሆን ሴቶችን በእጅ ሥራ እንዲሠለጥኑ የኅብረትና የችርቻሮ ሱቆችንና የወፍጮ ቤቶችን እንዲያቋቁሙ፣ የመዋዕለ ሕፃናት በማሥፋፋት “አብዮታዊ ሞራል ያለው ትውልድ የመፍጠር” ራዕይ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር። ደርግ ሴቶችን በተለያየ መልኩና በሶሻሊዝም መርሕ በኩል ከጓዳ ከማውጣቱም በላይ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ባስደረገው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ እንዲካፈሉ ማድረጉም በአዎንታዊ መልኩ ይነሳል። ነገር ግን ከዋናውና ከመደበኛው የፖለቲካ ሕይወት የለያቸው በመሆኑ ወቀሳው አልቀረለትም።

ደርግን ለመጣል በተካሔደው የትጥቅ ትግል የሴቶች ተሳትፎ
ቀድሞም በዐፄው ስርዓት ደስተኛ ባልነበረው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ደርግ የተማሪዎችን አመፅ ነጥቆ ወታደራዊ መንግሥትና አምባገነንነት ማምጣቱ በግልጽ ሲታወቅ በ1967 አካባቢ በኋላ ደርግን ጥሎ ለተመሠረተው ኢሕአዴግ መሠረት የጣለው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ተመሠረተ። በትጥቅ ትግሉ ወቅት አስቸጋሪ በነበረው ሁኔታ በርካታ ሴቶች መሳተፋቸው ሲገለጽ በ1983 ደርግን ካስወገደው የኢሕአዴግ ጦር አንድ ሦስተኛ ያህሉ ማለትም 40 ሺሕ ታጋይ ወታደሮች ሴቶች ነበሩ። በትጥቅ ትግል ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ እንደነበራቸው ሥማቸው የገነነ ታሪክ የሠሩና መስዋዕትነት የከፈሉ ሴቶችም እንደነበሩበት በተለያዩ መጽሐፍቶች ተጠቅሷል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መምጣትና የሴቶች ሕጋዊ መብቶች መሻሻል
ደርግ ወድቆ የሽግግር መንግሥት ሲታወጅ በአገሪቱ የነበረው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ከባቢ መቀየር አዲስ አስተሳሰብና አሠራር መተዋወቅ ጀመረ። በበርካታ ሴቶች ትግልና የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የመጣው መንግሥት ካስተዋወቃቸው ጉዳዮች አንዱ “የሴቶች ጉዳይ ቢሮ” የሚባል ክፍል በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና በኋላም በየክልሎች እንዲመሠረት ማድረጉ ነው። ነገር ግን ልክ እንደ አኢሴማ ሁሉ በሴቶች መብት ተሟጋቾች ዘንድ አደረግን ለማለት እንጂ ለውጥ ለማምጣት ያለመ እንዳልነበርና ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማምጣቱም ይነሳል።

ሕጎች ተሻሽለው ሲቪል ማኅበረሰብና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲመሠረቱ በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም አብረው መጥተዋል። በሴቶች ላይ የሚደርሰውን መገለል፣ ተሳትፎ መከልከልና ጥቃት ጨምሮ በርካታ ጉዳዮቻቸውን ወደ አደባባይ ያወጡ ድርጅቶች ነበሩ። በኋላ መንግሥት እንደ ጠላት ማየት ጀምሮ በርካቶች ከመዳከም እስከ መዘጋት እስኪደርሱ ተገፉ። ከእነኝህ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን መጥቀስ የግድ ይላል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር
ይህ ማኅበር ዛሬም ድረስ ለሴቶች መብት መረጋገጥ የሚሠራ በተለይ በሕግ በኩል ሴቶች መብቶች ላይ የነበረው አድልዎና ልዩነት እንዲቀር በብርቱ የታገለና ውጤታማ የሆነ ድርጅት ነው። የሴቶችን መብት በተመለከተ ዋነኛና ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ ብቸኛ ድርጅት ነው ቢባል አይበዛበትም። ጥናት በማስጠናት፣ የሴቶችን መብት በማስጠበቅና ከጥቃት በመጠበቅ ረገድ የነበሩት ሕጎች ክፍተት እንዳለባቸውና አገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም ዐቀፍና አሕጉር ዐቀፍ ሥምምነቶች እንዲሁም ግዴታዎች የሚቃረኑም መሆናቸውን በማሳየት እንደ የቤተሰብ ሕግ፣ ወንጀለኛ መቅጫ፣ የጡረታ፣ የዜግነት ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ በአስገድዶ መድፈር ላይ የነበረው ቅጣት እንዲሻሻልና ሌሎችን በጎ ለውጦች እንዲካተቱ ተሟግቶ ተሳክቶለታል።

ይህን ሁሉ ሲያደርግ ተቃውሞ አልነበረበትም፣ መንገዱ የተስተካከለ ነበር ለማለት ግን አይቻልም። በሰዎች “ትዳር አፋችዎች፣ ባል ያጡ የአሮጊቶች ስብስብ” ከመባል በመንግሥት እስከ መዘጋት የደረሰ ፈተና ማሳለፉም ይወሳል። በዚህ ሁሉ ፈተና መካከል ግን አባላቱም ሆነ ድርጅቱ በነጻ አገልግሎት መስጠታቸውን ለሴቶች መብት ጠንካራ ተሟጋችና ድምፅ መሆናቸውን አላቆሙም ነበር።

ከዚህ በኋላ ያለው ታሪክ የዘመናችን የሚባልና የምናየው ሲሆን በአብዛኛው እዚህ ከባቢ ውስጥ በመቆየት በልምድና በትዝብት ያገኘሁት ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያ ማበብ፦
ሴታዊት፣ ቢጫው ንቅናቄ እና ሌሎች የፌሚኒስቶች ድምፆች
እንደዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ምናልባትም ማኅበራዊ ሚዲያ ካመጣቸው በጎ ለውጦችና አዳዲስ ነገሮች መካከል ተመሳሳይ ሐሳብና ዓላማ ያላቸውን ሴቶች ማሰባሰብና በ’ፌሚኒዝም’ ዙሪያ ተከታታይ አዎንታዊ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ መሞከር አንዱ ይመስለኛል። ራሳቸውን ‘ፌሚኒስት’ ብለው ለመጥራት ችግር የሌለባቸውና ያለውን ጅምላ ፍረጃና ጥላቻ ተቋቁመው አንዳቸው ለሌላቸው ድጋፍ ሆነው በጉዳት ላይ ያሉ ሴቶችን ለመርዳት ሳይቀር የሚችሉትን ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት የማይባሉ ወጣት ፌሚኒስቶች መታየታቸውና በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ በይፋም ይሁን የየራሳቸውን መሰባሰቢያ ቡድኖችና ገፆች ተጠቅመው የሴቶች እኩልነት ጥያቄንና ዕለት ተዕለት የሚያጋጥሟቸውን መድልዖና ትክክል ያልሆኑ ድርጊቶች በማውጣት መወያየታቸው፣ ማጋለጣቸው፣ ትናንሽም ቢሆኑ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረጋቸው ተስፋ ሰጪ ነው።

ከፌስቡክ ባሻገር በቴሌግራም እንደ “ፌሚኒስታስ ዩናይት” ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች የተሰባሰቡባቸው ገፆች ከጉዳዩ ጋር የተገናኙ መረጃዎች የሚለዋወጡባቸው ጥቃት የደረሰባቸውንና ድጋፍ የሚሹ ሴቶችን በሚመለከት ውይይትና ገንዘብና ቁሳቁስ የማሰባሰብ ዘመቻዎች የሚደረጉባቸዉም ጭምር ናቸው።

ሌላዋ ምሣሌያችን “ሴታዊት” የሴቶችን መብት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ የምትሠራ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሷን በይፋ “የፌሚኒስት ንቅናቄ” ብላ የጠራች ድርጅት ስትሆን ስሒን ተፈራ (ዶ/ር) እና ፌሚኒስት ባልደረባዋ የመሠረቷት ናት። ከተመሠረተች 5 ዓመት የሚጠጋት ሲሆን ፌሚኒስቶችን በማሰባሰብና በማቀፍ በወር አንድ ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ ታደርጋለች። ከዚህ ሌላ በተለያዩ ከ’ፌሚኒዝም’ ጋር በተገናኙ ርዕሶች ላይ (ለምሳሌ ‘ፌሚኒዝም’ና እስልምና) ባለሙያዎችን በመጋበዝ ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት ውይይትና ክርክር እንዲካሔድ በዚህም ድሮ በአደባባይ ለማንሳት የሚከብዱ ሐሳቦች ላይ ግልጽ ውይይት እንዲደረግ፣ በተለይ ሴቶችን ወደ ኋላ ያስቀሩ ልምድና እምነቶች ላይ መጠይቅና መከራከር እንዲደረግ አስተዋፅዖ ታደርጋለች።

ከሴታዊት ሌላ እንደ አዲስ አበባ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በስርዓተ ፆታ ቢሮዎች ሥር ሆኖ ችግረኛ ሴት ተማሪዎችን በገንዘብ የሚደግፈውና ወርሐዊ የውይይት ዝግጅቶችን በፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚያዘጋጀው ‘ቢጫው ንቅናቄ’ ወይም የሎው ሙቭመንት ተጠቃሽ ሲሆን ማኅበራዊ ሚዲያንና ሌሎች መድረኮችን ተጠቅሞ ከ’ፌሚኒዝም’ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ሐሳቦችን የሚያራምድ ነው።

‘ፌሚኒዝም’ ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎችና ትችቶች
በብዙ ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎችና ተቃዋሚዎች የ’ፌሚኒዝም’ ጥላቻ መነሻ የተሳሳተ ግንዛቤና ፅንሰ ሐሳቡን በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ነው። ይህም ምናልባት ዕድልና አጋጣሚው ሲገኝ ሁልጊዜ ፅንሰ ሐሳቡን በሚገባ ባለመተንተንና ባለማስረዳት የሚመጣ፣ በፌሚኒስቶችም ጭምር በትንሹ ኃላፊነት ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሌላው ምናልባትም በቁጥር አነስ የሚለው አውቆ አጥፊ፣ በባሕልና በእምነት የሚሰበከውን ዓይነት በእርግጥ ሴቶች እኩል መሆን የለባቸውም ብሎ የሚያምን ‘ፌሚኒዝም’ ይህን ለምን ጠየቀ ብሎ የሚበሳጭ በፅኑ የሚቃወም የሚያጥላላ ሲሆን ተነጋግሮ የመግባባት ዕድል የማይኖርበትም ዓይነት ነው። ይህ ዓይነቱ “ሴቶች እናትነት እንጂ ወጥቶ ከወንድ ጋር እኩል መነጋገር አያምርባቸውም” ብሎ በይኖ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠርቶ “ሴት ለባሏ ትገዛ፣ በማኅበር አትናገር ተሸፋፍና ትኑር” የሚለው ዓይነት የ’ፌሚኒዝም’ ተቃዋሚና ተቺ ብዙ ነው።

ያለውን አባዊ ስርዓት የመሻር ውጥኑን ወንዶችን ከአደባባይ ወደ ጓዳ የሚከት የሚመስለው ብቻ ሳይሆን ነገ የገዛ ሚስቱ ፌሚኒስት ሆና፣ እሱን ጨምሮ ሁሉን ኑሮውን በትከሻዋ ተሸክማ መኖር በቃኝ ትለኛለች ብሎ የሚሰጋ በኑሮው የመጣበት የሚመስለው ዓይነት ነው።

ከሱ ሌላ ምንም እንድታስብ የማይፈልግ በአጠቃላይ ሴት ልጅ የተፈጠረችው ለወንድ ነው ባይ ነው። ይኼ ለሴት ጨቋኝ የሚባሉ ማኅበረሰቦች የሚፈልጉት ዓይነት ዓለም ሲሆን ይህ እንዲሆን ይሠራሉ። አባባሉ እንደሚለው፦
“የምታስበው ስለ ወንድ እስከሆነ ድረስ ሴት ልጅ ማሰቧን ማንም አይቃወምም” ቨርጂኒያ ዉልፍ
ሌላው ትችት በሴቶች ሳይቀር “የተማሩ አዲስ አበባ የሚኖሩ የመካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ፕሮፌሽናል ሴቶች ብቻ እንጂ ለደሃዋ ሴት ምንም የሚያደርግ አይደለም” የሚል ወቀሳ ነው። አንድ ጉዳዩ ላይ መወያየት እፈልጋለሁ ያለኝ ወጣት ለምሳሌ “እናንተ ስለ መደፈር ከምታወሩ የተደፈረች ሴት መጥታ ብታወራ፣ ስለ ሴት ጭቆና እናንተ ከምትነግሩኝ የገጠር ሴት ብትነግረኝ” ብሎኛል። የደረስንበት ለመድረስ ስንቶቻችን በብዙ መከራ እንዳለፍን፣ ምናልባትም የገጠር እና ደሃ ሴት ያሳደገችን ልንሆን እንደምንችል አይታሰብም። እንዲህ ዓይነቶቹን ሴቶች ለመወከል የደረስንበት ደረጃ ዕድል እንደሚሰጠንና ዕድሉንም እየተጠቀምንበት እንደሆነም ጭምር።

ይህ ትችትና ወቀሳ ተወቃሾቹ መልስ የሚሰጡበት ዕድል ሳይሰጥ በመደበኛው መገናኛ ብዙኀን ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሳይቀር የሚቀርብ የአንድ ወገን ጩኸትና ውንጀላ የሚቀርብበት በመሆኑ ቢያሳስብም፥ በሌሎች መገናኛ ብዙኀን ‘ፌሚኒዝም’ እንደ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ በቀጥታ ስለ ጉዳዩ በሚሠሩ ፕሮግራሞችና በሌሎችም ዘርፎች የሴቶች ውክልናና ተሳትፎን በሚመለከት ጊዜ ተሰጥቶ ውይይት፣ጥያቄና መልስ ሲካሔድበት ማየት ግን ተስፋ ሰጪ ነው።

ማጠቃለያ
እንደ ኢትዮጵያ ባለ በኋላ ቀር ባሕልና ለሴቶች ዝቅተኛ ቦታ በሚሠጥ ሃይማኖት ለተቃኘ አገር ‘ፌሚኒዝም’ ብቻ ሳይሆን እኩልነት የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ብዙ መሥራትና ንቅናቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ የሴቶች መብቶችና መሠረታዊ ጉዳዮች ለዘመናት ተረስተውና ችላ ተብለው ቆይተዋል። በወንዶች አስተሳሰብ የተቃኘው ስርዓት ለወንዶች ጉልበትና ሥልጣን ትልቅ ቦታና አብሮ የሚመጣውን “ክብር” እና ጥቅማጥቅም ሁሉ የሰጠ በመሆኑ፥ የሴቶችን መብት መጠየቅ ያንን ለማሳጣት እንደመሞከርና ለዘመናት በሴቶች ላይ ይደረግ የነበረው አድልዎና ጥቃት ወደ እናንተ ይዙር የማለት ያህል ከባድ ሆኖ ይወሰዳል። የሚፈለገው ያለው እንዲቀጥል ሴቶች በልጅ መውለድና በእናትነት ሥም ለአደባባይ ተሳትፎ የተጉ እንዳይሆኑ ያለውን መንገድ ሁሉ ተጠቅሞ የሚቻለውን ማድረግ ነው።

መብት መጠየቅና መከራከር ፍትሕ መሆኑ ቀርቶ እንደ ቅንጦትና ነውር ታይቶ ሴቶች ጠንካራ በመሆናቸውና ከቤት ወጥተው በአገሪቱ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅዖ እናበርክት በማለታቸው ወቀሳና ትችት ከማቅረብ አልፎ በየሥፍራው እንቅፋት በሚያኖር ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ልማድና ወግ ምክንያት ወደኋላ ቀርተዋል። ‘ፌሚኒስት’ ነን ባሉትም ሆነ የሴት መብት ተሟጋቾች ነን በሚሉ አልያም ሥም ሳይዙ ሥራ በሠሩ ተቋማትና ግለሰቦች ጥረት የሴቶች ሁኔታ መሻሻል አሳይቷል፤ ለውጦችም ተመዝግበዋል። ለውጦቹ ተቋማዊ ይዘት እስኪኖራቸውና ሴቶችን ማሳተፍ ችሮታ ሳይሆን ግዴታና መብት መሆኑን የሚረዳ አመራርና መሪ በሁሉም ደረጃ እስኪመጣ የተቀናጀ እንቅስቃሴ መቀጠል የግድ ይላል። ካልሆነ 100 ዓመት የፈጀው የ50/50 ካቢኔ ታች ወርዶ በሁሉም የሥልጣን ደረጃ እስኪዳረስ፣ አሁንም በሴቶች መብትና ኑሮ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እስኪመጣ ተጨማሪ 100 ዓመት መጠበቅ የግድ ሊሆን ይችላል። አዲስ ማለዳ

ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here