“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
በልጅነቴ ከሴቶች ጓድኞቼ ጋር መልካም የሚባሉ ግዜያቶች ነበሩኝ፤ ሆኖም ግን ዕድሜዬ ሲጨምር ከየት መጣ የሚባል ውድድር ተጀመረ። እንደ ብዙዎቻችን “የሴት ጓደኛ አይኑርሽ” ተብዬ ካደጉት ውስጥ ነኝ። አልፈርድባቸውም! ብዙኃን መገናኛ ላይ የተቀረፀው በሴቶች መካከል ያለ ግንኙነት እንዴት አስፈሪ ነው? ሰው የሚያወራውስ ቢሆን? የሴት ጓደኝነት፣ ስስ፣ በሐሜት የተሞላ፣ ቅናት ያለበት፣ የውድድር ወይም የመበላለጥ፣ የፍርድ፣ የማስመሰል እና የተንኮል ተደርጎ ይቀርባል። “ቀንታብሽ ነው” “አንቺ እኮ እንደ ሌላ ሴት አይደለሽም” “የሴት ጓደኛ የሚባል የላትም” ሲባል የሚሰማን ትንሽ ደስታም አለ። ይኼ ለምን ሆነ? ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ አናሳ በመሆኑ ያንን ቦታ ለማግኘት እርስ በርሳችን ስለምንወዳደር፣ ለጓደኝነትም ቢሆን፣ “ሴት ተጠያቂ (ተፈላጊ) እንጂ ጠያቂ (ፈላጊ) አይደለችም” በሚል ተራ ምክንያት ከሴቶች መካከል ራሳችንን ተፈላጊ ለማድረግ ከሴት እህቶቻችን ጋር ፍልሚያ ውስጥ ስለምንገባ፣ በራሳችን ላይ ባለን አለመተማመን ምክንያት ሌሎች ሴቶችን ያላግባቡ ስለምንተች፣ በሥራ ቦታም ‘ሴት ናት’ ተብሎ ከሚመጣ ንቀት ራሳችንን ለመጠበቅ፣ ለዚህም እና ለተለያየ ምክንያት በሴቶች መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ ነው ማለት ያዳግታል። ታድያ ይሄንን እንዴት እንቀይረው?
ሴታዊት በኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኝ የፌሚኒዝም እንቅስቃሴ ስትሆን ከምትሠራው ሥራ መካከል አንደኛው #አዶዬ ብላ የሠየመችው ነው። አዶዬ ወጣት ሴቶችን ለማበረታታት እና ለመጠበቅ የተቋቋመ ትውፊታዊ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ስርዓት ነው። ሴታዊትም ይኼንን ቃል እና ሐሳብ በመውሰድ በባሕላችን የሚገኙትን ጥሩ ግንኙነቶች በማጉላት፣ ሴቶች የእህታማማችነትን ፅንሰ ሐሳብ እንዲረዱት እና እንዲኖሩበት በመደገፍ፣ ለሴቶች አመቺ የሆኑ የንግግር መድረኮች በመፍጠር፣ ብዙኃን መገናኛዎች መልካም ግንኙነቶችን እንዲቀርፁ በማበረታታት በሴቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ትሠራለች።
በባሕላችን ዕድር፣ ዕቁብ፣ ሲቄ፣ አዶዬን ጨምሮ ብዙ እህታማማችነትን የሚያሳዩ ባሕሎች አሉን። እህታማማችነት የሴት ጓደኛን ከማፍራት ያለፈ ፅንሰ ሐሳብ ነው። መንገድ ላይ ስትለከፍ ከመሳቅ ይልቅ ከርሷ አጠገብ ከመቆም ጀምሮ፣ ስለሴቶች የሚወሩ አግባብ ያልሆኑ ወሬዎችን ባለመደገፍ፣ ከእኛ በመልክ፣ በዕውቀት፣ በገንዘብ የተሻሉ ሴቶችን ከማጣጣል ይልቅ በማበረታታት፣ ሴቶችን በምንተችበት ግዜ ከማፍረስ ይልቅ ገንቢ የሆነ ምክርን በመለገስ፣ ‘አያልቅብንም’ በሚል መርሕ ሴቶችን ማበረታታት ከምንደርስበት ቦታ እንደማያግደን በመረዳት፣ ሴቶች ላይ በአለባበሳቸውም ላይ ሆነ በሁኔታቸው ባለመፍረድና ባለማጣጣል፣ ሴቶች ላይ ጥቃት ሲደርስ ዝም እስካለማለት ድረስ የሚሔድ ነው።
ከሴቶች ጋር ያለን ጓደኝነት ጎጂ ከሆነ ወይንም ራሳችን ሌሎች ሴቶችን የምንጎዳ ከሆነ፣ ቆም ብለን ማሰብ እና አስቀድመን ራሳችን ላይ መሥራት ይገባናል። “ጓደኛህን ንገረኝ እና ማን እንደሆንክ እነግርሃለው” እንደሚባለው የምንጠራው ጓደኛ ራሳችንን የሚመስል ነው። ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ ማስተካከል ይገባናል። ሰው በመሆናችን ብቻ ዋጋችን በቂ መሆኑን ልንገነዘብ እንዲሁም ከማንም እንደማናንስ ሆኖም እንደማንበልጥ ስንረዳ በራሳችን ላይ ያለን መተማመን ይጨምራል። አላስፈላጊ ውድድር እና ቅናት ከውስጣችን ይጠፋል፤ ከዚያም ይልቅ ራሳችንን እኩል አድርጎ ከማሰብ እና ከመውደድ የተነሳ ሌሎችን በዛው መንገድ ማየትን እንማራለን።
ወደ ቤት የምሔድበት መንገድ ጨለምለም ያለ በመሆኑ እኔ እና ሌሎች ኹለት የማንተዋወቅ ሴቶች በመገናኘት መንገዱን ስንጓዝ ይሄንኑ ሐሳብ አስታወሰኝ፤ በእህታማማችነት ውስጥ ኀይል መኖሩን። አንድ ላይ የቆመን ለመጣል ከባድ ስለሆነ የምንታገልለትን እኩልነት ለማምጣት አንድነታችንን ማጠንከር አለብን። የእህታማማችነት እና የሴት ጓደኝነት ጥቅም የሚካድ አይደለም። በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ በሴቶች ያገኘነው ድጋፍ ቸል የማይባል ነው። በወሊድ ግዜ አብረውን የቆዩ ሴቶችን፣ ባዘንን ግዜ ያፅናኑንን፣ በተጎዳን ግዜ የቆሙልንን፣ የተሻለ ቦታ እንድንደርስ ምሣሌ የሆኑንን፣ በምክር እና በጥበብ ያገዙንን እናስብ። ያለነው ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነውና በይበልጥ ልንረዳዳ እንችላለን። ለዚህም ከግለሰብ እስከ ብዙኃን መገናኛዎች ድረስ የአዶዬን ፅንሰ ሐሳብ በመረዳት አስቀድሞ ያጠናከርነውን ትውፊት በድጋሚ ልንጽፈው ይገባል።
ልዩ እትም ስለ ሴቶች ብቻ