መኢአድ ከግንቦት 7 ወረራና ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው ሲል ከሰሰ

0
703

• ግንቦት 7 ክሱን መሰረተ ቢስ ብሎታል

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከግንቦት ሰባት ፓርቲና አመራሮች ወረራና ጥቃት እየተፈጸመበት መሆኑን መጋቢት 23/2011 በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ግንቦት 7 ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብና ይቅርታ እንዲጠይቅም መግለጫው አሳስቧል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአርበኞች ግንቦት 7 የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኤፍሬም ማዴቦ ክሱን መሰረተ ቢስ መሆኑን ጠቅሰው መኢአድ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ጥናት አድርጎ ከጨረሰ በኋላ እኛን ይቅርታ መጠየቅ የሚኖርበት እሱ ነው ሲሉ የመኢአድʼን ክስ አስተባብለዋል።

መኢአድ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ እንደገና አደረጃጀቱን እያጠናከረ፣ አባላቱንም በመላው አገሪቱ እያሰባሰበና ቢሮ እየከፈተ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከድርጅታችን ጋር ውሕደት መፈፀሙንና አብሮ ለመሥራት መስማማቱን በሚዲያ ማሳወቁን ሰምተናል፤ የሚለው መግለጫው ይህም ተፈፀመ የተባለው ውሕደት ድርጅታችን የማያውቀውና በድርጅታችንም ላይ የተከፈተ አደገኛ አባላቶቻችንንና ደጋፊዎቻችንን የመከፋፈልና የተነሳንለትን አገርንና ሕዝብን ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማሸጋገር ዓላማ የሚያደናቅፍ፣ ሕገ ወጥና ፀረ ዲሞክራሲያዊ አካሔድ በመሆኑ መኢአድ በፅኑ ያወግዘዋል ሲል ተቃውሟል።

የመኢአድን ክስ የሚቃወሙት ኤፍሬም በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው አርበኞች ግንቦት 7 ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ከመኢአድ ጋር አብሮ ለመሥራት በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማድረግ ጀምሮ ስለነበር፣ ያንን ለመግለጽ ከመሞከር ባለፈ ከመኢአድ ጋር ውሕደት ፈጽመናል ብለን አንድም ቀን ተናግረን አናውቅም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ ከግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝተን ፈርሰን እነሱን እንደማናቋቋምና እነሱ ሕጋዊ ፓርቲ ከሆኑ በኋላ በግንባር አብረን የምንሠራ መሆኑን አቋማችንን በግልፅ ካሳወቅናቸው በኋላ፣ በተሳሳተ መንገድ በመላው አገሪቱ አብረን ነው የምንሠራው በማለት አባሎቻችንን የማታለል ሥራ ሆን ብለው ቀጥለውበታል ይላል የመኢአድ መግለጫ። ከስህተታቸው እንዲታረሙ ብለን በተደጋጋሚ በቃል ብንነግራቸውም ሊታረሙ ባለመቻላቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ ለማድረግ ተገደናል ሲል መኢአድ በመግለጫው ገልጿል።

በቅርብ ቀን የፈረምነውን የመግባቢያ ሰነድ ወደኋላ በመተው በአባሎቶቻችንንና በደጋፊዎቻችንን ላይ የሚያደርሱትን መከፋፈልና እንዲሁም መኢአድን የማጥላላትና የማፍረስ ሙከራ በተደጋጋሚ እያደረጉ ይገኛሉ ሲልም የግንቦት 7ʼን አካሔድ በመግለጫው ተችቷል።

በመሆኑም ግንቦት 7 በየዞንና በየወረዳው ለሠራው አባሎቶቻችንንና ደጋፊዎቻችንን የመከፋፈል ፖለቲካዊ ሴራ በግልፅ መኢአድን ይቅርታ እንዲጠይቅና የጥፋት እጁን እንዲሰበስብ እንጠይቃለን ሲሉም አመራሮቹ በመግለጫቸው አክለዋል።
ከተመሰረተ 26 ዓመታት የሆነው መኢአድ እስከ 1997 ድረስ አንድ ሚሊየን አባላት ነበሩት። በሌላ በኩል የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የተመሰረተው ግንቦት 7 ከአምስት ብሔራዊና ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ጋር በውሕደት ሒደት ላይ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here