የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ግንኙነት ዕይታዎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች

0
1126

መግቢያ

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የዲሞክራሲ ዋና መሠረቱ ሕዝቡ በነጻነት በመረጠው አካል ይተዳደር የሚል ዕሳቤ ነው። እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚህ መብት ተጠቃሚ የሆነበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ይህ መብት ዲሞክራሲያዊ መብት ብቻ አይደለም። የሚያስተዳድራቸውን የመምረጥ እና በመረጡትም የመተዳደር መብት የሁሉም መብቶች መሠረት (ራስ) የሆነው ሰዋዊ (ሰብኣዊ) መብት ነው። የሰው ልጅ ከእንሰሳ የሚለየው ይሆነኛል፣ ይጠቅመኛል የሚለውን አመዛዝኖ መምረጥ መቻሉ ነው። ስለሆነም ዜጎች በመረጡት የመተዳደር መብታቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊከበር ይገባል። ባልመረጠው አስተዳደር የሚተዳደር ሕዝብ ባልመረጠው እረኛ እንደሚጠበቅ ከብት ነውና።

በየትኛውም አከባቢ የሚኖረው የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የትግራይ፣ የጉራጌ፣ የሲዳማ፣ የከንባታ፣… ሕዝብ እያልን ብንዘረዝር በነጻነት የዚህ መብት ተጠቃሚ የሆነ አንዳችም ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ሆነ ግለሰብ አናገኝም። የአዲስ አበባ ነዋሪ ጥያቄ ይህ ከሆነ ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ተለይቶ የሚታይበት ምንም ዓይነት አግባብ የለም። አዲስ አበቤው ባልመረጠው አመራር አይተዳደርም ማለት ተገቢ ነው። ሰዋዊም ዲሞክራሲያዊም መብት ነው። በየትኛውም የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ደግሞ ነዋሪዎች የከተማቸው፣ ሲያልፍም የክልላቸው፣ ሲለጥቅም የአገራቸው ባለቤት እንደመሆናቸው አዲስ አበቤውም እንደ ነዋሪ የከተማው ባለቤት ነው።

የከተማ እና ከተሜነት መሥፋፋትን በተመለከተ
የከተሞች ማደግ እና መሥፋፋት ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን ከተሞች በሚሥፋፉበት ወቅት ከማኅበረሰቡ የተነጠለ መሬት ስለሌለ በዙሪያቸው ያለውን ማኅበረሰብ ወደ ራሳቸው በማቀፍና በማካተት ከተሜ ማድረግ ወይም ማዘመን ይኖርባቸዋል። የአዋሳ ከተማ፣ የመቀሌ ከተማ ወይም የባሕር ዳር ከተማ እና ሌሎችም የአገራችን ከተሞች መሥፋፋታቸው በዙሪያቸው ያለው ማኅበረሰብ ላይ የባሕልም ሆነ የሞራል፣ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ጫና መፍጠር በማይችልበት እንዲሁም ከተሜነት መጣልኝ እንጂ መጣብኝ በማያስብልበት መንገድ መሆን እንዳለበት መሥማማት ያስፈልጋል እንጂ እንዲሁ ዝም ተብሎ መሥፋፋቱ ተፈጥሯዊ ነው ስለተባለ ከተሞች በዙሪያቸው ባሉ ማኅበረሰቦች ማንነት ፍርስራሽ ላይ መገንባት የለባቸውም።

የአዲስ አበባ ከተማን ጉዳይ ከኹለቱም ወገን (ማለትም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ነች ከሚለውም ሆነ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነች ከሚለው) ቆመን ብንመለከተው ነገሩ ተመሣሣይ ነው። ከተማዋ በክልል አስተዳደር ስር የምትገኝ በቻርተር የምትተዳደርም (Chartered City Under Regional State) ትሁን አሊያም ደግሞ እራሷን የቻለችም የከተማ ክልል (City State) ወይም የፌደራል ቀጠና (Federal District) ማደጓም ሆነ መሥፋፋቷ በዙሪያዋ ባሉ ማኅበረሰቦች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ካለ መቼም ቢሆን የመሥፋፋትዋ እና የማደጓ ጉዳይ አደጋ ላይ ይወድቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ በዕቅድ (planned) አሊያም ደግሞ ያለ ዕቅድ (unplanned) በምታደርገው የጎንዮሽ መሥፋፋት (horizontal expansion) በከተማዋ ዙሪያ ባሉ ገበሬዎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና የማኅበራዊ ቀውስ አድርሳለች። የዚህ ቀውስ ዋነኛው ምንጭ ነው ተብሎ የሚታሰበው በሕግ ያልታገዘ እና በወሰን ያልተገደበ የከተማ መሥፋፋት ነው። ፊደል የቆጠረ ብቻም ሳይሆን ማሰብ የሚችል የሰው ፍጡር ሊረዳው የሚችለው የከተማ ውስጥ እና ዙሪያ ባለመሬት ገበሬዎችን ማካተት ያልቻለ እና የገበሬዎችን መፈናቀልን ዒላማ ያደረገ መሥፋፋት ያስከተለው ሁሉን ዐቀፍ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ነው። በመሬት ወረራ ቢሆን ከተማዋ በተሥፋፋችባቸው አቅጣጫዎች ባሉ ገበሬዎች ላይ የተደረገውን ግፍ አስከፊነት ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “በአርሶ አደሩ ላይ የተሠራው ግፍ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው” ይላሉ።

በቅርቡ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሥዩም ተሾመ “ነጻ ውይይት” መድረክ ላይ “የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለው የባለቤትነት እና የልዩ ጥቅም ጥያቄ” በውይይቱ በአንድ ወገንም ቢሆን ሰፊ ዳሰሳ ተደርጎበታል። በቃለ መጠይቁ ላይ እስክንድር እንደሚለው “የመቀሌ በከፍተኛ ደረጃ መሥፋፋት እንደርታን የልዩ ጥቅም ተጠቃሚ እንደማያደርጋት ሁሉ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ተጠቃሚ የምትሆንበት ምንም አግባብ የለም። ስለሆነም በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሚያ ክልል የባለቤትነትም ሆነ የልዩ ጥቅም የሚባል ነገር የለም” ይላል።

ይህ አመለካከት በመቀሌ እና በእንደርታ መካከል ያለው ክልላዊ አንድነት አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉት የኦሮሚያ ከተሞች ጋር ካላት ክልላዊ ግንኙነት ተመሳሳይ ነው ከሚል ዕሳቤ የተነሳ ከሆነ በሁሉም ኦሮሞ ዘንድ ቅቡል የሆነ አስተሳሰብ ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር ያላት ግንኙነት መቀሌ ከእንደርታ ጋር ካላት ግንኙነት ለይቶ እየተመለከቱ የመቀሌ በዙሪያዋ እንደምታደርገው ዓይነት መሥፋፋት ከአዲስ አበባ መጠበቅ ፍፁም ስህተት ብቻም ሳይሆን በቃለ መጠይቁ ላይ ሥዩም እንዳለው ጭፍን እና ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ያላስገባ ፅንፈኝነት ነው። እዚህ ላይ መቀበል ያልተፈለገው እና ማንም በቀላሉ ተነስቶ ሊቀይራቸው የማይችሉ ኹለት ነባራዊ ሁኔታዎች ሲኖሩ አንደኛውና ቀዳሚው “በአዲስ አበባ ዙሪያ” የሚገኘውን የኦሮሚያ ክልል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ባጠቃላይ አገሪቷ ውስጥ ካሉ ክልሎች በተለየ በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ጋር ያላትን የሕልውናዋ መሠረት የጠበቀ ሁሉን ዐቀፍ ግንኙነት ነው።

የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም”
አዲስ አበባ የተፈጥሮ ሀብት (በተለይም የመሥፋፊያ መሬት፣ የግንባታ ጥሬ ዕቃ እና የመጠጥ ውሃ) ፍላጎቷን ለማሟላት በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ላይ ጥገኛ የሆነች ከተማ ነች። የኦሮሚያ አዲስ አበባ ግንኙነትን የተፈጥሮ ሀብትን መሠረት አድርገን ከተመለከትነው አዲስ አበባም ሆነች ኦሮሚያ እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት ከሌሎች ክልሎች ጋር ካላቸው የተናጥል ግንኙነት በእጅጉ የተለየ ነው። ለከተማው ነዋሪ በቀን ከ300,000 ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የሚያቀርብ እንዲሁም 850,000 ቶን በላይ የከተማዋን ቆሻሻ ተረክቦ የሚያስወግድ ብሎም በከተሜነት መሥፋፋት ሥም የገበሬውን ኑሮ በማይቀይር ክፍያ በማታለል ሳይሆን ሲቀርም በማሥፈራራት እና በማፈናቀል የከተማዋን ያልተገደበ የመሬት ፍላጎት በተለየ ሁኔታ የሚያሟላ ክልል ኦሮሚያ ብቻና ብቻ ነው።

አንዳንዶች “ሲንጋፖር አብዛኛውን ውሃ የምታገኘው ከማሌዢያ እና ከኢንዶኔዢያ ቢሆንም እነዚህ አገሮች በሲንጋፖር ላይ ልዩ ጥቅም የላቸውም” የሚለውን ይዘው የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የልዩ ጥቅም ጥያቄን ውድቅ ለማድረግ ሲዳክሩ ይስተዋላል። ይህ በኹለት መንገድ ስህተት ነው። አንደኛው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ መልከዓ ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ግንኙነት ከላይ በቀረበው ደረጃ የሚራራቅ አለመሆኑና ሌላኛው ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት አገራት ጥቅማቸው እስካልተጠበቀ ድረስ ለሲንጋፖር አንዲት ጠብታ ውሃ የማቅረብ ግዴታ እንደሌለባቸው አለመገንዘባቸው ነው። የትግራይ መሥፋፋት ወደ አማራ ክልል ግዛት ሊሻገር እንደማይችለው እንዲሁም የአማራ ክልል መስፋፋት ወደ ኦሮሚያ ክልል እንደማይሻገረው ሳይሆን አዲስ አበባ ከተማ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተስፋፊ መሆኗ ሁኔታውን ከየትኛውም ክልል የተለየ ያደርገዋል።

የኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ግንኙነትን እንደ እንደ ማንኛውም የንግድ ግንኙነት አድርጎ መመልከትም ሲጀምር ስህተት ሲሆን፥ ሲቀጥል ደግሞ አደጋ ነው። የንግድ ግንኙነት በክልሎች መካከል ወይም ደግሞ በከተሞች መካከል ሊኖር ይችላል። ይህ የንግድ ግንኙነት ተመጣጣኝነት ከሌለው እና የጋራ ተጠቃሚነት ከሌለበት ሁልጊዜም የግጭት እና አለመግባባት መነሻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች ግንኙነት ልዩነቱ እስከማይታወቅበት ድረስ የጠበበ እና የጠበቀ ነው። ይህ ግንኙነት እንደ ከተማ የአዲስ አበባ ከተማን ሕልውና የሚያስጠብቅ ግንኙነት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን አንዳንድ ሰዎች በተንሸዋረረ መንገድ ሲመለከቱት ይስተዋላል። በእኔ ዕይታ የልዩ ጥቅም ጥያቄ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማለት ደግሞ እኩል ተጠቃሚነት ማለት ሳይሆን ሁሉም እንዳበረከተው አስተዋፅዖ ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሠራር ነው። የዚህ ጥያቄ መሠረት ደግሞ አዲስ አበባ በኦሮሚያ የተከበበች በመሆኗ ብቻ ሳይሆን የኦሮሚያና የአዲስ አበባ የተለየ ግንኙነትን መሠረት ያደረገም ጭምር ነው። ይህ ግንኙነት የአዲስ አበባ እስትንፋስ የሆነ ግንኙነት ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ ላይ አዲስ አበባ የምንላት ከተማ በማንነቴ ላይ የተገነባች ከተማ ስለሆነች ከአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ያስፈልገኛል ሲል፥ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ እንዳልሆነም ሊታወቅ እና ሊሠመርበት ይገባል። ላለፉት ኹለት ዐሥርተ ዓመታት ብቻ የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያን ግንኙነት ብንወስድ የከተማዋ አጎራባች የሆኑ የክልሉ ከተሞች የአዲስ አባባ የቆሻሻ ቅርጫት ከመሆን የዘለለ እንዲሁም ኦሮሚያም እንደ ክልል መሬት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿ ባለቤት እንደሌለው በከተማዋ መሥፋፋት ሥም መንግሥታዊ ዝርፊያ ሲፈፀምባቸው ከማየት የዘለለ አንዳችም ልዩ ጥቅም አላገኙም። የከተማዋ መሥፋፋት ተፈጥሯዊ ነው ተብሎ እንኳ ቢወሰድ የኦሮሞ ገበሬዎችን ከቀያቸው እያበረረች የምታደርገው ገፊ ልማት መፍትሔ እና እርማት ሊበጅለት ይገባል። በእኔ አስተሳሰብ በአዲስ አበባ የከተሜነት መደርጀት እና የመሥፋፋት ሒደት ውስጥ የኦሮሞ ገበሬዎች ሚናና መስዋዕትነትን መካድ ሰዋዊ ባሕሪ ነው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ።

የዋና ከተሞች አወቃቀር ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሦስት ዓይነት የዋና ከተሞች አወቃቀር አሉ። እነዚህም ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር የሆነ የፌዴራል ቀጠና አወቃቀር (Federal District Model)፣ ራሱን የቻለ የከተማ ክልል አወቃቀር (City State Model) እና በክልል አስተዳደር ሥር የሚገኝ ከተማ አወቃቀር (City Under Regional State Model) ናቸው። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዘርዘር አድርገን እነዚህን አወቃቀሮች እንመልከት፦
የፌደራል ከተማ አወቃቀር (Federal District Model)
በእንዲህ ዓይነቱ የዋና ከተማ አወቃቀር የፌደራል መንግሥቱ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። ከሌሎቹ በተሻለ በዋና ከተማዋ ላይ የፌደራል መንግሥቱን ፍላጎት የሚያሟላ አወቃቀር ነው። ይህ አወቃቀር አዲስ ለሚመሠረቱ ከተሞች ተሥማሚ የሆነ አወቃቀር ነው። ለምሳሌ የአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲን፣ የናይጄሪያዋን አቡጃን፣ የቬንዙዌላዋን ካራካስ እና የፓኪስታኗን ኢስላማባድ እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል። የዚህ ዓይነት አወቃቀር መሠረታዊ ችግሩ የፌደራል መንግሥቱ በከተማው ነዋሪዎች ላይ ያልተገደበ ቁጥጥር ያደርጋል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት አካሔድ አይኖራቸውም። በእንደዚህ ዓይነት አወቃቀር ውስጥ የከተማዋ ነዋሪዎች በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ መቀመጫ አይኖራቸውም። ይህ አወቃቀር አብዛኛውን ጊዜ የፌደራል መንግሥቱ እና በዙሪያው ካለው የክልል መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ይከተዋል። ይህም ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ከተሞች በባሕሪያቸው ባላቸው የመስፋፋት ፀባይ ጋር ተያይዞ ይከሰታል።

የከተማ ክልል አወቃቀር
ከተማው የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ቢሆንም ከፌደራል መንግሥቱም ሆነ ከሌላ ክልል ተፅዕኖ ነጻ ሆኖ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት አወቃቀር ሲሆን ብዙ ጊዜ በእንደዚህ ደረጃ የሚዋቀሩ ከተሞች የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆኑ ትልቅ የቆዳ ስፋት ያላቸው ከተሞች ናቸው። ለምሳሌ፦ የኦስትሪያዋ ቬና፣ የጀርመኗ በርሊን (ከ1990 ጀምሮ)፣ የቤልጄየሟ ብራሰልስ እና የሩሲያዋ ሞስኮ ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የዚህ ዓይነት የዋና ከተማ አወቃቀር ችግር የፌደራል መንግሥቱ በመቀመጫው ከተማ ላይ የመወሰን ሥልጣኑን ሙሉ ለሙሉ በማሳጣት የፌደራል መንግሥቱ በከተማው ውስጥ ለሚሠራው ማንኛውም ሥራ የከተማ አስተዳደሩን ፈቃድ ይጠይቃል። አንዳንዴ ደግሞ ከተማው ሲዋቀር ትልቅ ካልነበረ የከተማው መሥፋፋት ከአጎራባች ክልል ወይም ክልሎች ጋር ወደ ግጭት እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ የብራሰልስ ነዋሪዎች በከተማው መጨናነቅ ምክንያት ወደ ፍሌሚሾች ክልል እንዲሁም የበርሊን ከተማ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት የብራንደንብርግ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሰት በጎረቤት ከተሞች ላይ ጫና ይፈጥራል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት አገራት የወሰን መሥፋፋቱን ሕጋዊ ለማድረግ እስከ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የዘለቀ እርምጃ እንዲወስዱ ይገደዳሉ።

በክልል አስተዳደር ሥር የሚገኝ ዋና ከተማ አወቃቀር
የፌደራል መንግሥቱ በእንደዚህ ዓይነት የከተሞች አወቃቀር ላይ ሥልጣን አይኖረውም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በተዋቀሩ ዋና ከተሞች ውስጥ የዋና ከተማው መሥፋፋት ችግር አይሆንም። ያለምንም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የክልሉ መንግሥት የከተማውን ወሰን ሊያስፋፋው ይችላል። ለምሳሌ የስፔኗ ማድሪድ፣ የማሌዢያዋ ኳላላምፑር፣ የካናዳዋ ኦታዋ፣ የሲዊዘርላንዷ በርን የደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቷ አቡ ዳቢን መጥቀስ ይቻላል።

ዋና ከተሞች የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ በመሆናቸው የአገር አንድነት ምልክት ተደርገው ቢወሰዱም የፌደራል መንግሥቱ በፈለገው መንገድ ከተማዋን የማልማት ሥልጣን አይኖረውም። ከተማዋን የሚያስተዳድረው ክልል ቋንቋ፣ ወግ እና ባሕል ከተማዋ ላይ በበላይነት ስለሚንፀባረቅ የከተማዋን የሁሉም ሕዝብ ውክልና ሥሜቷን ያሳጣታል። የዚህ ዓይነቱ አወቃቀር ሌላኛው ችግር ከቋንቋ ጋር ይያያዛል። ለምሳሌ በሲዊዘርላንድ አራት ብሔራዊ ቋንቋዎች (ጀርመንኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ሮማንሽ) አሉ። ዋና ከተማዋ የምትተዳደረው በጀርመንኛ ተናጋሪዎች ግዛት ሥር ነው። በግዛቱ ሰሜናዊ ክፍል እና በዋናው ከተማ ጥቂት ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ይኖራሉ። እነዚህ ነዋሪዎች ቋንቋቸውን ተጠቅመው አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ ለመስጠት ችግር ሲገጥማቸው ይስተዋላል። የመንገድ ላይ ምልክቶች ሳይቀሩ በጀርመንኛ ናቸው። ሁሉም ነገር በክልሉ መንግሥት እንደመወሰኑ የክልሉ መንግሥት ከተማዋን እንደማንኛውም የክልሉ ከተማ በክልሉ ሕግ ሊያስተዳድራት ወይም በቻርተር ሊያስተዳድራት የሚችልበት ሲሆን የከተማው ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊሰጣቸውም ወይ ሊነፍጋቸው ይችላል።

የችግሩ ምንጭ እና የመፍትሔ አቅጣጫ
በአዲስ አበባ መሥፋፋት እና ለኦሮሞ ገበሬዎች መፈናቀል ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገው በክልሉ እና በከተማው መካከል ያሉ ግንኙነቶችን በግልጽ ቋንቋ ማስቀመጥ ያልቻለው ሕገ መንግሥቱ ነው። አገራችን አሁን እየተዳደረች ያለበት የብሔር ፌደራሊዝም ዋነኛ መነሻ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር መሠረቱ የብሔር ጭቆና ነው” የሚል ዕሳቤ ይመስለኛል። ስለዚህም ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ብሎ ያመጣው ክልሎችን በብሔር ወይም በማንነት ማደራጀትን ነው። ይህ ማንነቶችን ለጭቆና እንዳይዳረጉ ይከላከላል ተብሎ የታቀደው ዕቅድ አገሪቱን ለለየለት ብሔር ግጭት አጋልጧታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላለው የማንነት እና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ዋነኛው መሠረት ይህ የአገሪቱን ፖለቲካ አቅጣጫ ያስቀየረ ውሳኔ ያለ በቂ ጥናት፣ በበቂ ሁኔታ ሕዝብ ሳይመክርበት እና የጥቂቶችን ፖለቲከኞች የፖለቲካ ፍላጎት፣ አመለካከት እና ጥቅም መሠረት አድርጎ የተደረገው የመሬት ክፍፍል ነው። ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለበት ዕለት እንዲሁም ያዋቀራቸው የክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ሥራ ከጀመሩበት ወቅት ጀምሮ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ መሠራት የነበረባቸው የክልሎች እና የከተማ መስተዳደሮችን አስተዳደራዊ ወሰን ማካለል አለመከናወኑ አሁን ለሚስተዋሉ ችግሮች ለምሳሌ በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አከባቢዎች የሚስተዋለው ችግር፣ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች የሚስተዋለው ችግር፣ በድሬደዋ የሚስተዋለው ችግር፣ በጋምቤላ (በኑዌር እና አኙዋክ ጎሳዎች መካከል) የሚስተዋለው ችግር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አከባቢዎች የሚስተዋለው ችግር እንዲሁም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ የሆነው በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል የሚስተዋለው ችግር ዋነኛ መሠረት ሕገ መንግሥቱ ነው ለማለት ያስደፍራል። ይህም የሆነው በሕዝቦች መካከል ሥምምነት የተደረገበት ሕገ መንግሥታዊ የፌደራል ስርዓት መገንባት ሳይቻል ቀርቶ ሳይሆን ስርዓቱ እንደ ፖለቲካ መሳሪያነት ሆን ብሎ ሲጠቀምበት የነበረው በሕዝቦች መካከል ግጭትን፣ አለመተማመንን እና አለመሥማማትን በመፍጠር ዘለቄታዊ የሥልጣን ባለቤት የመሆን ስትራቴጂ ስለነበር ነው። ስለሆነም ይህ ሕገ መንግሥት እና የፌደራሊዝም አወቃቀሩ ሕዝቦችን ባሳተፈ መንገድ ዳግም ሊታይ ይገባል እላለሁ።

በስተመጨረሻም ማለት የምፈልገው በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለውን ግንኙነት በሠለጠነ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ብቸኛው መፍትሔ ውይይት እና ውይይት ብቻ ነው። በውይይት የማይፈታ ችግር የለም። ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥያቄ ምንን መሠረት ያደረገ ነው? ልዩ ጥቅም ማለት ምን ማለት ነው? የኦሮሚያ ክልል ጥያቄን ከአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መብት ጋር በማይጋጭበት መንገድ እንዴት መመለስ ይቻላል? እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሥርም ቢሆን አዲስ አበባ ራሷን በራሷ በቻርተር የምታስተዳድርበት ማዕቀፍ መፍጠር በሚቻልበት ዙሪያ መነጋገር፣ መወያየት እና መከራከር ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ውጪ የሆነ መፍትሔ ለየትኛውም ወገን ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here