ኢትዮጵያን ከብቸኛ አውራ ከተማ ባለቤትነት ማላቀቅ

0
1143

ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የልዩ ጥቅምና ባለቤትነት ጥያቄ መነሻ በማድረግ ጉዳዮን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አጠቃላይ የከተሞች ዕድገት ጋር ያቆራኙት ሳምሶን ኃይሉ፥ መፍትሔው በርካታዎቹ ትናንሽ ከተሞች ያላቸውን እምቅ ሀብት መሰረት በማድረግ ወደ ሰፋፊ ከተማነት ማሳደግ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

 

ዘግይቶ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጋዜጠኞች ጋር የነበራቸው ቆይታ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መብት ተሟጓቾች በአዲስ አበባ ላይ እያነሱት ያለውን የልዩ ጥቅምና ቀስ በቀስም እያደገ የመጣው የከተማዋ ባለቤትነት ይገባናል ሙግት፥ በከፊልም ቢሆንም ምላሽ የሰጠ ይመስላል። ሥልጣን ከጨበጡ ከጥቂት ወራት በኋላ አሜሪካ ሔደው የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ባወያዩበት መድረክ ጥያቄው ተነስቶላቸው እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ በቂ ምላሽ አለመስጠታቸው አጠያያቂ ቢሆንም ምላሻቸው የፖለቲካውን ትኩሳት ለማርገብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አያጠያይቅም።

የልዩ ጥቅም ጥያቂው በአብዛኛው ማኅረሰብም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት ያለው ሐሰብ ነው። አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መካከል መገኘቷ የማይካድ ሐቅ ነው። ስለሆነም ከተማዋ የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ከክልሉ እንደምታገኝ ይታወቃል። በተጨማሪም ለመሰረተ ልማት የሚሆኑ እንደ አሸዋና ድንጋይ የመሳሰሉ የጥሬ እቃ አቅርቦት የሚገኘውም ከኦሮሚያ ነው። በተቃራኒ ደግሞ ከአዲስ አበባ የሚወጣው ደረቅ ቆሻሻ በአብዛኟው የሚወገደው ወደ ኦሮሚያ ክልል በማጓጓዝ ነው። ስለሆነም ክልሉ የካሳ ጉዳይ ቢያነሳ የሚያስገርም አይሆንም። በማናቸውም ተጎራባች ከተሞች መካከል ሊኖር እንደሚገባ ግንኙነት፥ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የሚገባቸውን ካሳ ሊነፋጉ አይገባም።

ይህንንም እውነታ መሰረት አድርጎ ሕገ መንግሥቱ ላይ በአንቀጽ 49 እንደተደነገገው፥ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጥቅም የማግኘት መብት አላት። ነገር ግን ይህን ለማስፈጸም ተጨማሪ አዋጆችን ማጽደቅ ይጠይቃል። ይህም ተግባር አገሪቷ በአጭር ጊዜ ዕቅዷ አካታ ለጉዳዩ መፍትሔ መስጠት የሚገባት ይሆናል።

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው ጉዳይ በአጭር ጊዜ ሊፈታ ቢችልም አዲስ አበባ ብቸኛ አውራ ከተማ (primate city) ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላይ ከሚያንዣብበውና ወደፊት ከፍተኟ አደጋ ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳይ ማምለጥ ይቻላል ማለት አይደለም። እንደአለመታደል ሆኖ አዲስ አበባ ብቸኛዋ የከፍተኛ ምጣኔ ሀብት፣ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የመዋዕለ ንዋይ ሆነ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ነች። ይህ የአንድ አውራ ከተማ ብቻ መኖር (urban primacy) ከባለፉትና አሁን ካለው መንግሥታት ካራመዱት የዘገየና የተዛባ የከተሞች እቅድና የዕድገት ፖሊሲ የሚመነጭ ቢሆንም ካልተስተካከለ ወደፊት ሊያመጣው የሚችለው አደጋ ግዙፍ ይሆናል። የአገሪቱ ሀብት ወደ አንድ አቅጣጫ በብዛት እንዲፈስ ሲደረግ ከከተማዋ ውጭና በርቀት የሚኖሩ ዜጎች አዲስ አበባን ብቻ እንዲያበለጽጉ ይፈርድባቸዋል። ነገር ግን አዲስ አበባ ከምታመነጨው ሀብት ተጠቃሚ አይሆኑም። ከሚፈጠረውም የሥራ ዕድል ተቋዳሽ አይሆኑም። ይህም ወደፊት ጎልቶ ለሚወጣው የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄና ተዛማጅ ችግሮች መሰረት እያደላደለ ይሔዳል። ነገሮችም በዚህ ከቀጠሉ ብዙም ባልራቀ ጊዚ በቅርቡ ካየነው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ አረንቋ ውስጥ ይከተናል። ስለዚህም ጊዜው ሳይረፍድ መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ብቸኛው መፍትሔ ከአሁኑ ሚዛናዊነት ያለውና የተሰባጠረ የከተሞች ዕድገት የሚያመጣ ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው። በዓለም ላይ የተሰባጠረ (non-primacy) የከተሞች እድገት በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ መጥቷል። በአፍሪካ የሚገኙ አገራት ሳይቀር የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የከተሞቻቸውን ቁጥር በተሰባጠረ መልኩ ለመጨመር በመጣር ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌም እንደ ኢትዮጵያ በተንጽጽር ብዙ የሕዝብ ብዛት ያላቸው እንደ ናይጀሪያና ግብጽ የመሳሰሉ አገራት ሊጠቀሱ ይችላል።

በአሁኑ ወቅት ናይጀሪያ አራት ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖሩባችው ከተሞች አሏት። ትልቁ ከተማ ሌጎስ ሲሆን ከስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ይኖሩበታል። በካኑ፣ አብዳን እና ቤኒን በተባሉ ከተሞችም ከሦስት እስከ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ። በተመሳሳይ ግብጽ እንደ ካይሮ፣ አሊክሳንድሪያ እና ጊዛኧ ያሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች አሏት። ከእነዚህም በተጨማሪ የግብጽ መንግሥት ሌላ ትልቅ ከተማ በመገንባት ላይ የገኛል። ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ አገራት እንኳን ሳይቀሩ የአንድ አውራ ከተማ ብቻ መኖር ከሚያስከትለው መዘዝ ለመትረፍ እየተጉ መሆኑን ነው።

ከአንድ በላይ ከተማ መኖር በራሱ ከችግር አያድንም። ከተሞች ሲገነቡ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጣቸውና በመካከላቸው የሚኖረው ርቀት ሚዛናዊነት ሊኖረው ይገባል።` ከተሞች ተጠጋግተው ከተቀመጡ አብዛኛው የአገሪቱ መዋዕለ ነዋይ ወደ እነርሱ ስለሚፈስ በርቀት የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከተጠቃሚነት ያገላል። ይህም ቀስ በቀስ እየጋለ ለሚሔድ የሕዝብ አመጽ መሰረት ይሆናል።

በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት እየተተገበረ የሚገኙው የከተማ ልማት ፖሊሲ ለመገንዘብ የሚቻለው ግን እነናይጀሪያና ግብጽ እየሔዱበት ካለው መንገድ በተቃራኒ አቅጣጫ እየሔደች መሆኑን ነው። ከሦስት ዓመት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ሐተታ ይህንን ግምት ያጠናክረዋል። እንደ ዘገባው ከሆነ አዲስ አበባ እስከ 2017 ድረስ 20 ፐርሰንት ዓመታዊ ዕድገት ታስመዘግባለች።

የአሁኑ የከተማ ልማት ፖሊሲ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው በብዙ መንገድ ይለያል። የድሮው ፖሊሲ በዋናነት ከተሞች ቧሏቸው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የተመሰረተ ነበረ። እንደ ሀዋሳ፣ ሆሳህና፣ አርባ ምንጭ እና ዲላ የመሳሰሉት ከተሞች በዚህ አቅጣጫ ነበር የተቋረቋሩት።

በአሁን ጊዜ ግን ዋነኛው የከተሞች ዕድገት ማምጭያ መሣሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ነው። በኢትዮጵያ ወደ ዐሥር የሚጠጉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ። በተናጥልም 2 ነጠብ 5 እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ ፈሶባቸዋል። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም ቁጥሩ በእጥፍ እንደሚጨምር ይገመታል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃጨርቅ ምርቶችን አምርተው ወደ ውጭ ለሚልኩ ፋብሪካዎችን ታሳቢ ተደርጎ የተገነቡ ናቸው።

የከተሞች አመሰራረት እና ዕድገትን ከዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ጋራ ማስተሳሰር የተለመደ ስልት ነው። ለምሳሌ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅና ዋና ከተሞች የሚገኙት በባሕር ዳርቻወች አካባቢ ነው። ይህም የሚያሳየው የከተሞቹ ኅልውና ወደ ውጪ ከሚላኩት እና ወደ ውስጥ ከሚገቡት ዕቃዋች ጋር የተሳሰረ መሆኑን ነው።

በተመሳሳይ መንገድ በኢትዮጵያ በተለይም ከጅቡቲ ወደብ ቀረብ ባሉ አካባቢዋች የከተሞችን ዕድገት ማፋጠን ይቻላል። ይህ አቅጣጫ ኹለት ጥቅም አለው። በአንድ በኩል ለፋብሪካዋቹ በአካባቢው ጥሬ እቃ ማግኘት ባይቻል እንኳን ከውጭ ለማስመጣት ቀላል ይሆናል። ከወደብ ያላቸው ርቀት ከሌሎች ቦታዋች በአንጻራዊነት ትንሽ ስለሆነ የጥሬ ዕቃ ወጪ ለመቀነስም ይረዳል። በተዘዋዋሪ መንገድ ይህ አካሔድ ፋብሪካዋችን ጠቅላላ የምርት ወጪን በመቀነስ ትርፋማ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ፋብሪካዎች የሚመረቱ ምርቶችን በቀላሉ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል። እስከ ወደብ ያለው የማጓጓዣ ወጪ በንጽጽር ስለሚቀንስ የምርቶቹ በዓለም ገበያ ላይ የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት ይጨምራል።

የከተማ እቅድ እና ልማት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ግን የሁሉም ከተሞች ዕድገት ከዓለም ዐቀፋዊው ንግድ ጋር ብቻ ሊተሳሰር አይገባውም። የከተማ ምጣኔ ሀብት (urban economics) እንደሚያስረዳው የተለያዩ የከተሞችን ዕድገት የሚወስኑ ምክንያቶች አሉ። ለምሳል እያደጉ ባሉ አገሮች የሚገኙ እንደ ባሊ (እንዶኔዥያ)፣ ጁሀንስበርግና (ደቡብ አፍሪካ)፣ ካዛብላንካ (ሞሮኮ) የመሳሰሉ ከተሞች የቱሪዝም ሀብቶቻቸውን ተጠቅመው ለማደግ ችለዋል።

ይህ አካሔድ ግን በኢትዮጵያ አይስተዋልም። ምንም እንኳን እንደ ባሕር ዳር፣ ጎንደርና አክሱም የመሳሰሉ ከተሞች ትልቅ አቅም ቢኖራቸውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ብቻ ባማከለ ዕድገት ብቻ እንዲወሰኑ ተገደዋል። ከተሞች ባላቸው የቱሪዝም ሀብት ባማከለ መልኩ አደጉ ማለት ምንም ዓይነት ፋብሪካዎች በውስጣቸው አይኖርም ማለት አይደለም። በተቃራኒው ለጎብኚዋች ሊሸጡ የሚችሉ ዕቃዋችን የሚያመርቱ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ፋብሪካዋች በመገንባት የከተሞቹንም ሆነ የአካባቢው ሰወችን መጥቀም ይቻላል።

ሌላው እምቅ ሀብት የከተሞችን ዕድገት በኢትዮጵያ ለማምጣት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው ደግሞ የማዕድን ሀብት ነው። ለምሳሌ በሰሜን ትግራይ፣ በአሶሳ እና ወለጋ አካባቢ ትልቅ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ክምችት ይገኛል። እነዚህን ሀብቶች በመጠቀም የከተሞችን ዕድገት በእነዚህ አካባቢዎች ማፋጠን ቢገባም መንግሥት ግን አንድ ዓይነት አካሔድ በመላው አገሪቱ ውስጥ መከተል መርጧል። በእኔ እምነት በፍጥነት እንደዚህ ካለ አካሔድ ተላቆ፥ ያሉንን ትናንሽ ከተሞች ባላቸው እምቅ ሀብት መሰረት እንዲያድጉ ካልተደረገ አንድ አውራ ከተማ ብቻ ከመኖር ጋር ተያይዞ ለሚመጡት ችግሮች ዋለም አደረም አገረቷ መጋለጧ አይቀርም።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here