ትምህርት፣ አገርና ዕድገት

0
512

በኢትዮጵያ ያሉ ፖለቲካዊ ቀውሶችን በተመለከተ የትምህርት ፖሊሲው በተጣመመ ስርዓት የቀረጻቸው ትውልዶች ማንነታቸውን እና ትውፊታቸውን በመዘንጋታቸው የተፈጠረ ነው የሚሉት መላኩ አዳል፥ ለአገር ዕድገት እና ለዜጎች ደኅንነት ተሥማሚ የትምህርት ስርዓት መገንባት ጠቃሚ ነው ይላሉ።

 

የትምህርት ዋናው ዓላማ የአገርን ወግና ትውፊት፣ ባሕልና ታሪክ፣ በመመርመር መስተካከል ያለባቸውን አንዲስተካከሉ የሚያሰፈልገውን መንገድ የሚጠቁም፣ ጠንካራ ጎኖች ደግሞ የሚቀጥሉበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። የዘመናዊነት ማሳያ የሆኑትን የጥሩ ፖለቲካዊ አስተዳደር መንገዶችን፣ የውጭ ግንኙነትን፣ ሕግና ደንብን፣ የግል ነጻነትን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየትን፣ የሐሳብ ብዝኀነትን፣ የፆታ እኩልነትን፣ የአገር ሀብትን እንዴት ማልማትና መጠቀም እንደሚቻል ማሳወቅንና ማጥናትን ያካትታል። በተጨምሪም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተካነ፣ የአዲስ ሐሳቦችና የፈጠራ ባሕሉ ያደረገ ትውልድ መፍጠርንና ለቀጣይነት ማበረታታትን ያጠቃልላል። ይህም ማለት የትምህርት ዓላማ አንድ ኅብረተስብ የተሟላ ዕውቀትና ክኅሎት እንዲኖረው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመልካም ሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ ዕሴቶች የተገነባና በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ተፈላጊ ውጤት ማምጣት የሚችልና ከተፈጥሮ ጋር ተሥማምቶ በአመክንዮ መኖር የሚችል ኅብረተስብ መፍጠር ነው።
ዘመናዊነት የሰውን ልጅ ማዕከል ባደረጉ ዕውቀቶች የበለፀገና በፍልስፍና የተካነ የባሕል መሠረት ያለው ኅብረተሰብን ይጠይቃል። በአገራችን የዘመናዊነት የትምህርት ስርዓት ከኛነታችን ተለይቶ፣ የአገርን ወግና ትውፊት፣ ባሕልና ታሪክ፣ ከመመርመርና መስተካከል ያለባቸውን እንዲስተካከሉ ከማድረግ፣ ጠንካራ ጎኖች የሚቀጥሉበትን መንገድ ከማሳየት ወጥቶ ሁሉንም ማንነቶቻችን አራግፈን ትተን የምዕራባውያን ሥልጣኔ ብቻ ናፋቂዎች እንድንሆን አድርጎናል። በተለይም በሥነ ሰብ (‘በሁማኒቲ’) የትምህርት ዘርፎች (ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብ) የተደረገው ዘመቻ፣ ማንነቱን የማያውቅ፣ በሌሎቹ ሐሳብና ፈጠራ ብቻ የሚመራ፣ የራሱ የማሰቢያ መንገድ (ፍልስፍና) የሌለውና በአገሩ ጉዳይ ፊት ላይ ለመሆን የሚፈራ ትውልድ ፈጥሯል። ይህ ደገሞ የትምህርትን በራስ ላይ የባሕሪ ለውጥ ማምጣትን፣ አሳቢ ኅብረተሰብን የመፍጠርን፣ በኅብረተስቡ ውስጥ ደካማ ባሕልና ልምድን በመተው፣ ጥሩ የሆኑትን የባሕልና የልምድ እሴቶቻችን ወደ ዘመናዊ የባሕል መሠረት በማዋሐድ ለሕዝብ ሥልጣኔና ለአገር ዕድገት ማዋልን አደናቅፏል። የዐፄ ኃይለሥላሴ የዘመናዊ ትምህርት ትውፊትንና ባሕልን እንዲያካትት ቢታሰብም የነበሩት መምህራን የውጭ በመሆናቸው በታለመለት መንገድ ሊጓዝ አልቻለም። በተጨማሪም ውጭ ተምረው የሚመለሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ባሕልና ልምድ የራቁ ነበሩ። ይህም ምንም እንኳን የጠያቂነትን ባሕል ቢያጎለብትም የማንነት ጥያቄን ያልመለሰ እንዲያውም የምዕራቡ ዓለም ጥገኞች እንድንሆን አድርጎናል። የተማሩ ዜጎቻችንንም በኅብረተሰቡ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲቀንስ አድርጓል። ስለዚህም የአገርን ጉዳይና የአገር በቀል ዕውቀትን ያካተተ፣ ከራስ ማንነት የተነሳ የትምህርት ስርዓት መንደፍ ይጠበቅብናል።

የትምህርት ፖሊስ ቀረፃ
ማንኛውም የትምህርት ስርዓትና ፖሊሲ የኅብረተሰቡን ችግር ነቅሶ አውጥቶ ለመፍትሔ የሚሠራ መሆን አለበት። በዝግጅት ጊዜ የአተገባበርን፣ ምዘናን፣ የሰው ኀይልና የመምህራን ጥራትን፣ የምርምር ልምድን፣ የገንዘብ አቅምን፣ ከተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ያለውን ትሥሥር፣ ተደራሽነትን ያገናዘበ መሆን አለበት። የትምህርት ስርዓታችን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥኑ የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ መሆን አለበት። በተለይም የሒሳብ ትምህርት በማንኛውም ደረጃና ትምህርት ክፍል በተገቢ መልኩ መስጠት ይኖርበታል። ይህም የሚያስፈልገውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ በቀላሉ እንዲገባን ብሎም ፈጣሪዎች እንድንሆን ያግዘናል። የፖለቲካ ውሳኔ የሚጠይቁ የመማሪያ የቋንቋ፣ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዕርዳታ ስለተገኘ ብቻ የሚተገበሩ ፕሮገራሞች፣ የመምህራን ነጻነትና የደሞዝ ሁኔታ፣ በየዩኒቨርስቲዎቹ ለመምህሩ ጥቅም ብቻ ያለ በቂ ሰው ኀይልና የአስፈላጊነት ጥናት የሚከፈቱ ፕሮግራሞች፣ የ70፡30 ጉዳይ፣ ዩኒቨርስቲዎች የሚከፈቱበት መሥፈርት ለፖለቲካ ፍጆታ ወይስ ስለሚያስፈልጉ መሆኑን መጠየቅ ይገባል። በተጨማሪም የትምህርት ሥርዓቱ በሙሉ ሀገሪቱ ከመተግበሩ በፊት የፓይለት ፕሮገራም ቢኖር ይመረጣል።

የምንከተለው የትምህርት ስርዓት፣ ማንነቱን የማያውቅ፣ ወደ ውስጥ ሳይሆን ወደ ውጭ የሚያይ፣ ለስደት የተዘጋጀ ዜጋ ፈጥሯል። ፖለቲከኞቻችን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ሲኖርባቸው፣ ከባዕድ ባገኙት ወይም ራሳቸው በፈጠሩት የፈጠራ ትርክቶች፣ የአገራችንን ታሪክ በጎ ጎኖችን በመተው መጥፎ ጎኖች ብቻ ላይ በማተኮር፣ ሕዝብን በማሳሳት አገርንና የአገር አንድነትን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው። ለዚህ ትርክቶች ይረዳቸው ዘንድ፣ የነበረውን የመደብ ጭቆና ወደ ጎን በመተው፣ ያልነበረን የብሔር ጭቆና በማቀንቀን፣ በዘር መሠረት የተዋቀረ ፌዴራሊዝም አቋቁመው አገራችንን አደጋ ላያ ጥለዋታል። ይህም ብሔር ብሔረሰብ የተባለ የመንጋ ፖለቲከኞችና የወንጀለኞች መሸሸጊያ ዋሻ ፈጥሯል። ይህ ቡድን አመክንዮ የማያውቅ በደመነፍስ የሚጓዝ፣ አገር የሚል ሐሳብ የማይታየው፣ መገንጠል ቀላል የሚመስለውና የሚያደርገው ድርጊት በነገ እሱና አገሩ ላይ የሚያመጣውን መዘዝ የማያውቅ፣ ከመገንጠል ተያየዞ የሚመጣው ችግርና ጦርነትና እልቂት የማይታየው፣ በመሰሪ ፖለቲከኞች በተቆፈረለት ቦይ ያለ ምክንያት እንደ ውሃ የሚፈስ፣ ባልተማሩ ወይም ለሰርትፍኬት በኮሌጆች ወይም ዩኒቨርስቲዎች ባለፉ ሰዎች የሚመራ የደመነፍሶች ቡድን ፈጥሯል።

ስለዚህም ለረጂም ጊዜ በምን መንገድ የትምህርት ስርዓቱን በማሻሻል፣ ብቁና ለአገር የሚያስብና የሚሠራ ዜጋ መፍጠር እንደሚቻል አጥንቶ መሠረታዊ መሻሻል መደረግ አለበት። ለዚህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በመሆኑም በፖለቲካው መሻሻል ላይ ቅድሚያ መሥራት ያስፈልጋል። ለአጭር ጊዜ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የፓርቲዎች አደረጃጀት በዘር እንዳይሆን በመከልከል በርዕዮተ ዓለም ብቻ እንዲሆን ማድረግ፣ የፌደራል አወቃቀሩን ከዘር ይልቅ የሕዝብ ፍላጎትን፣ አሠፋፈርን፣ የኢኮኖሚ ትሥሥርን፣ የአስተዳደር አመችነትን፣ ታሪክና ባሕልን፣ እንዲሁም ቋንቋን ባካተተ መልኩ እንዲሆን ማድረግ፣ ነጻ የምርጫ ቦርድ እንዲኖርና የምርጫ ሕጎች በፓርቲዎች ሥምምነት ማርቀቅ፣ በኢሕአዴግ ድርጅቶች ያለውን አለመግባባት መፍታት፣ የሕግ መጣስና የሕዝብ ደኅንነት መጓደልን ማስተካከል፣ የፓርቲ መሪዎች ደኅንነትን መጠበቅ፣ ከሕግ ውጭ ሆኖ የሥም የመቀየርና የታሪክ ሽሚያን መከላከል፣ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር የገቡት ለሰላማዊ ትግል መሆኑን ማረጋገጥ፣ የፓርቲና የመንግሥት ልዩነትን ማወቅና መተግበር፣ የነዳጅና ማዕድን ብሎም ሌሎች ሀብቶችን በተጠናና የአካባቢውን ሕዝብ በአሳተፈና በሚጠቅም መንገድ ለአገር ጥቅም ማዋል፣ የውጭ ግንኙነት ላይ ማንንም ጠላት ባላደረገ መልኩ አገርን በሚጠቅም መንገድ መንቀሳቀስና በተጠናና በጠራ ርዕዮተ ዓለም መምራት ይጠይቀናል።

ለዚህም ለጊዜው የሚመጥን ከብሔር ይልቅ ለሁሉም ዜጋ የሚጠቅም አስተሳሰብን፣ ከስሜት ወጥቶ በምክንያት በመመርኮዝ እንዴት ከፈለግነው ደረጃ እንደምንደርስ ማሰብና የተጠና ርዕዮተ ዓለም፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ማዘጋጀትና በተገቢው መንገድ ወደ ተግባር መተርጎም መቻል ያስፈልጋል። ይህም ለአገር ዕድገትና ለዜጎች መጠቀም ዋስትና ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here