˝ኦዲፒ ስግብግብ የመሆንና ሁሉንም የእኛ ነው የማለት ዓይነት ዝንባሌ አሳይቷል˝

0
655

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ኮሌጅ መምህርና በፌደራሊዝምና ሰብኣዊ መብቶች ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። ትውልዳቸው ራያ፣ አላማጣ ሲሆን በልጅነታቸው ቤተሰባቸውን በእረኝነት አገልግለዋል። በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ሲከፈትም ዕድል አግኝተው ለመከታተል የቻሉ ቢሆንም፥ የትውልድ ቀያቸው በደርግና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከለ በተካሔደው ፍልሚያ የጦር ዓውድማ በመሆኑ ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ እክል ፈጥሯል። የኋላ ኋላም ጦርነቱ በሕወሓት አሸናፊነት በመጠናቁ አካባቢያቸው ሙሉ ለሙሉ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ይወድቃል። ወቅቱ ኹለት አማራጭ ማለትም ደርግን ወይም ትግሉን መቀላለቀል እንዳቀረበላቸው የሚናገሩት ሲሳይ፥ በ1981 ክረምት ላይ የኢትትጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢሕዴን) በመቀላቀል ፖለቲካዊና ወታደራዊና ሥልጠና በመውሰድ የሕዝብ አደረጃጀት ወይም ክፍለ ሕዝብ በሚባለው መዋቅር ውስጥ ተሳትፈዋል።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (አአዩ)፣ የማስትርስ ዲግሪዎች በፈደራሊዝምና አካባቢ አስተዳደር ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በሰብኣዊ መብቶች ሕግ ከአአዩ በተመሳሳይ ጊዜ አግኝተዋል። በ2010 የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሰብኣዊ መብቶች ሕግ ከአአዩ አግኝተዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊነት እስከ የክልሉ የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የሕግ ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨረሲቲ በመምህርነት እንዲሁም ከ2004 ጀምሮ በአአዩ በመምህርነትና በተመራማሪነት በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

ባሕር ዳር በሚያስተምሩበት ወቅት ከፖለቲካ ተሳትፎ የታቀቡት ሲሳይ፥ በ2005 ከዓለሙ ካሳ ጋር ‘የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄና የማዕከላዊ መንግሥት ምላሽ፥ ከአፄ ዩሐንስ እስከ ኢሕአዴግ’ የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል።

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ሲሳይ፥ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ በተለይ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዓት አተገባበርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሲሳይ መንግሥቴ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የፌደራሊዝም ስርዓት እንደኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ብሔረሰቦችና ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሉበት አገር ተመራጭ ነው ይባላል። በርግጥ ኢትዮጵያ ከዚህ ፌደራል ስርዓተ አወቃቀር ተጠቅማለች ማለት ይቻላል?
ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ካየን በኢትዮጵያ ያልተማከለ አስተዳደር የነበረበት ሁኔታ ነበር። ማዕከል ላይ ንጉሠ ነገሥት፥ በየአካባቢው ደግሞ ነገሥታት ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት መልኩን ቀይሮ ያልተማከለ ወይም ፌደራላዊ ስርዓት የሚመስል ነበር።

ጠንከር ያሉ ንጉሶች ሲኖሩ ማዕከሉ የሚዳከምበት፤ ጠንካራ ንጉሠ ነገሥት በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ የአካባቢ ነገሥታት የሚዳከሙበት ሁኔታ እንደነበር እናስታውሳለን።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሥያሜ ደረጃ የፌደራል ስርዓት ተብሎ በሥራ ላይ ውሎ የነበረው የኢትዮ ኤርትራ የፌደራል ግንኙነት ነበር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ምክንያት የኢትዮጵያ አንድ አካል ተደርጋ እንድትታይ አድርጓት ነበር።

ነገር ግን በመካከል በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሥር ቆይታ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሐድ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ አማካኝነት የመተዳደሪያ ሕግ አዘጋጅቶላት ኤርትራ ራሷን እንድታስተዳድርና ከኢትየጵያ ጋር በፌደራላዊ ግንኙነት እንድትዋሐድ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር።

አንድ ዐሥር ዓመት በዚህ ዓይነት ግንኙነት ከቀጠሉ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ 14ኛ ክፍለ አገር ብለው ኤርትራ ወደ እናት አገሯ ተቀላቀለች በሚል የኤርትራ ምክር ቤትን በሥልጣንም በገንዘብም በመደለል ወይም በማባበል የኤርትራ መንግሥት የሚለው ቀርቶ አስተዳደር እንዲባል፤ ሰንደቅ ዓላማዋ ወርዶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ እንዲውለበለብ፤ በመጨረሻም ምክር ቤቱ እንዲበተን በማድረግ በማዕከል በሚሾም የክፍለ አገር ገዢ እንዲተዳደር የተደረገበት ሁኔታ ተፈጠረ።
በወቅቱ ወጣቶችና ፖለቲከኞች ውሳኔውን ተቃውመው ወደበረሃ ወረዱ፤ በዛም ምክንያት ለ30 ዓመታት በጦርነት ውስጥ እንድንቆይ ሆኗል።

የደርግ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ በ1983 ኢሕአዴግ የመግሥትነት ሥልጣንን ሲቆጣጠር የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ቻርተር፥ ፌደራላዊ ስርዓት ወይም ያልተማከለ አስተዳደር እንዲተገበር ፈቅዷል። ከዛም በኋላ አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሰረት ክልሎች በአዲስ መልክ ተደራጁ። ይሔ የክልሎች አስተዳደር ደግሞ በዋነኛነት ቋንቋና ብሔርን መሰረት ያደረገ ስለነበር የክልሎቹም ሥያሜም ከዚሁ ጋር የሚያያዝበትን ሁኔታ እናያለን።

በሸግግር ወቅት የተጀመረው ይሔ ሒደት በ1987፣ ሕዳር 29 የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የፌደራል ስርዓት ተከታይ እንድትሆን አድርጓታል፤ የክልል አደረጃጀቶችም 9 እንዲሆኑ፣ አዲስ አበባም ራሷን የምታስተዳድር ከተማ እንድትሆን ተደርጓል። ድሬ ዳዋን በተመለከተ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ʻለእኔʼ ትገባለች በሚል አለመግባባት ምክንያት ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ እንድትሆን ተደርጓል። በነገራችን ላይ ድሬ ዳዋ የሕገ መንግሥት እውቅና የላትም። በኋላ ላይ ፓርላማው በቻርተር እንድትተዳደር አድርጓል።

ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትን ተግባራዊ በማድረጓ ምንድን ነው የተጠቀመችው የሚለውን ለመመለስ፥ ቀደም ሲል ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ የተሞከረው መልካም ጅማሮ ነበር፤ ምንም እንኳን ንጉሠ ነገሥቱ መጨረሻ ላይ መልሰው ቢያበለሹትም። በዛው በፌደራል ግንኙነት ቢቀጠል ኖሮ የ30 ዓመቱ ጦርነት ከመቀረቱም ባሻገር ኤርትራ ራሷን ችላ አገር አትሆንም ነበር።

ላለፉት 26 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገውን ፌደራላዊ ስርዓት በተመለከተ፥ አንደኛው በተለያዩ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ ለመገንጠል በብሔር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ያደርጉት የነበረውን ሙከራ ገትቷል። ይህ ማለት ኢትዮጵያን ከመበታተን ሥጋት አድኗል ማለት ይቻላል።

ሌላው ብሔር፣ ብሔረሰቦች በሕግ ዕውቀና የተሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል አግኝተዋል። ራስን በራስ በማስተዳደር ሒደት ውስጥ ደግሞ ባሕላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ታሪካቸውን እንዲያሳድጉና ሌሎች እንዲያውቁላቸው፣ የእኩልነት መብታቸውም አንዲረጋገጥ የሚያደርጉ ሕጋዊ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።

ከዚህም ባሻገር አንፃራዊ ሰላም አምጥቷል። በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን የፍትሐዊነት ጥያቄ ቢኖርበትም በተለይ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል።

በተጨማሪም በፌደራል መንግሥት ደረጃ ውክልና እንዲኖር በማድረግ ረገድ ጅማሮ አለ፤ እንዲሁም አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖርም አድርጓል።

የፌደራል ስርዓቱ በተለይ ብሔርንና ቋንቋን መሰረት በማድረጉ አሁን በስፋት ለሚታዩት ግጭትና መፈናቀል እንዲሁም ጠርዝ ለረገጠ ብሔርተኝነት መስፋፋትም ምክንያት ሆነኗል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ። በዚህ ላይ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?
ሕገ መንግሥቱ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር መፍቀዱ፣ ለሰብኣዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የሰጠው ሽፋን ከፍተኛ መሆኑ፣ የመንግሥት ስርዓት ቅርፅና ሥልጣን በተመለከተም መርህ አስቀምጧል። ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ እንደ ትልቅ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው፥ የፌደራል ስርዓቱን ለማዋቀር የሞከረበት መንገድ ብሔር ተኮር መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ ከመግቢያው ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ ለቡድን መብቶች ትልቅ ሽፋን ይሰጣል።

በየትኛውም አገር በሌለ መልኩ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ˝እኛ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች˝ ብሎ ይጀምራል። ይህ በመሆኑም እያንዳንዱ ነገር በብሔረሰብ ዓይን እንዲሰላ አደርጓል።

ለምሳሌ አንቀጽ 8ʼን ብናይ ሉዓላዊ ሥልጣን የተሰጠው ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው። ለኢትትጵያ ሕዝብ በጥቅል የተሰጠ ሥልጣን የለም።

አንቀጽ 39ʼን ስናይ ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ብቻ ሳይሆን መገንጠል ይችላሉ ይላል። በነገራችን ላይ መገንጠል የሚችሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦች ናቸው።

ስለዚህ ሁሉንም ነገሮች ለብሔር፣ ብሔረሰቦች የመስጠቱ ጉዳይ የፌደራል አደረጃጀቱንም መልክ እንዲቃኝ አድርጎታል። ሕገ መንግሥቱ የአሸናፊዎች ሕገ መንግሥት በመሆኑ የአሸናፊዎቹን ፍላጎት፣ ስሜትና ፕሮግራም እንዲያንፀባርቅ ተደርጓል። አሸናፊዎቹ ደግሞ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ናቸው።

ሕገ መንግሥቱ ቀደም ብለው ይነሱ የነበሩትን የማንነትና እራስን በራስ ማስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሞከረ ቢሆንም አዳዲስ ፍላጎቶች፣ ማንነቶች፣ ጥያቄዎች በመምጣታቸው የፌደራል ስርዓቱ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጎታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ድኅነት ወይም የሀብት ውስንነት ባለበት ሁኔታ ከማንነት ጋር በተያያዘ የወረዳ መሆን፣ የዞን መሆን እና የክልል መሆን ጥያቄዎች በሰፊው ይነሳሉ። እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ማስተናገድ ይቻላል? ጥያቄዎቹስ መቼ ያበቃሉ?

ሕገ መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ የማንነት ጥያቄዎች መቋጫ አይኖራቸውም። አንቀጽ 39 ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መገንጠል ይችላል ይላል። ስለዚህ እራስን በራስ ማስተዳደር ትንሹ መብት ሲሆን የሚያሳዝነው ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ለመገንጠል መሆኑ ነው። ይህ ማለት ሕገ መንግሥቱ ለመብት ሳይሆን ቅድሚያ የሰጠው ለመገንጠል ነው። ስለዚህ አንቀጽ 39 ለመብት ቅድሚያ የሚሰጥ ሆኖ መስተካከል ወይም መሻሻል አለበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም።

አንቀጽ 47 (2) በማንኛውም ክልል ወይም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል ማቋቋም ይችላሉ ይላል። ለምሳሌ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሲዳማ ክልል ለመሆን ለረጅም ጊዜ ሲታገል ቆይቶ በቅርቡ የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄውን ተቀብሎታል፤ ሕዝበ ውሳኔ ብቻ ነው የሚጠበቀው።

የሲዳማን ጥያቄ ተከትሎ ግን ወደ ዐሥር የሚጠጉ ብሔረሰቦች የክልልነት ጥያቄ አንስተዋል። ይሔም ብቻ አይደለም፥ በአማራ ክልል ውስጥ አገው ጥያቄ አንስቷል። ስለዚህ ማንኛውም ብሔር ትልቅም ይሁን ትንሽ በማንኛውም ጊዜ ክልል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት ስላለው ይሔንን ጥያቄ ይዞ ቢመጣና ወደፊት የሚገፋበት ምከንያት የለውም። ስለዚህ አንቀጽ 40 (2) መሻሻል አለበት፤ ቢያንስ ክልል፣ ዞን ወይም ወረዳ ለመሆን መስፈርት ሊቀመጥ ይገባል።

በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ነገር ግን ይፋ ያልወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ200 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰብ መኖራቸውን ያመለክታሉ። በዚህ ሁኔታ ከተሔደ ከ200 በላይ ክልሎች ሊኖሩ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱን መበታተን ነው የሚሆነው።

በአንዳንድ ክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ስንመለከት በአንድ ፌደራላዊ ስርዓት የሚተዳደሩ ሳይሆን እንደጎረቤት አገራት የመተያየት አዝማሚያዎች ይስተዋላል፤ የአገራዊ ሥሜት መደብዘዝም እንዲሁ ይታያል። የፌደራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት እንዲሁም የክልል መንግሥታትም በመካከላቸው ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት?

ሕገ መንግሥቱ ከቀረጻ ጀምሮ ችግር እንዳለበት ከላይ ጠቅሻለው፥ ሌላው መታየት ያለበት ደግሞ አተገባበሩ ነው። የፌደራል ስርዓት በባሕሪው እውነተኛ ዴሞክራሲን ይፈልጋል፤ ያለ ዴሞክራሲ መርኅ፣ ባሕል ፌደራላዊ ስርዓት ሥራ ላይ ማዋል አይቻልም። ስለዚህም ነው በአለማችን ካሉ የፌደራላዊ ስርዓት ከሚከተሉ አገሮች ይልቅ አኀዳዊ ስርዓት ኖሯቸው ዴሞክራሲዊ የሆኑ አገሮች ለራስ በራስ ማስተዳደርና ሰብኣዊ መብቶች ትልቅ ቦታ የሰጡ አሉ። ለምሳሌ እንግሊዝና ጣሊያን በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው። ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ኹለት ዓይነት ችግሮች ይኖራሉ።

በዚህ ነው የፌደራል ስርዓት ከሥምና ሕግ ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ በዋናነት ኹለት ችግሮች ያስከትላል። እነዚህ ኹለት ችግሮች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተዋል።

መጀመሪያ ላይ የተማከለ ጠንካራ የፌደራል ስርዓት ነው የነበረው። ሁሉንም ነገር ከማዕከል ከኢሕአዴግ በተለይ ከሕወሓት በሚመጣ ትዕዛዝ የሚፈፀም ነበር። በመሆኑም የክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደር እንኳን ጥያቄ ውስጥ የገባ ነበር፥ ምክንያቱም ዴሞክራሲ ስላልነበረ። በአንድ ስልክ ጥሪ ወይም ትዕዛዝ ክልሎች ለፌደራል መንግሥት ታዛዥ ነበር የሆኑት። ከዚህም ባሻገር የሞግዚት አስተዳደር በሚመስል መልኩ አማካሪዎች እየተባሉ ሚመደቡ ሰዎች ነበሩ።

በኋላ ላይ ደግሞ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ፌደራል መንግሥቱ እየተዳከመ መጥቷል። የተወሰኑ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን እያወቁ ሲመጡ መገዳደር ጀመሩ። ከዚህ ሁሉ ሒደት በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ሶማሌ ክልሎች ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ በአንድ በኩል ለፌደራል ስርዓት አለመታዘዝ ፍላጎትና ሥሜት መጣ በሌላ በኩል በጎረቤታሞች መካከል የʻእኔ እበልጥ፥ እኔ እበልጥʼ ፋላጎትና ፍጥጫ መጣ። በዚህምክንያ ሕዝቦች ተፈናቅለዋል፣ አሁንም ፍጥጫው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
አገራዊ ስሜቱን በተመለከተ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት በወጥነት የተሠራበት አንዱ መጥፎ ነገር ለብሔር ማንነት ቅድሚያ የሰጠና ልዩነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። የጋራ እሴቶችን፣ የጋራ ሀብቶችን አገራዊ ስሜት በሚፈጥር መልኩ፣ ኢትዮጵያዊነትን ወደልብ በሚመጣ መልኩ አልተሠራም። በመሆኑም የአሁኑ የወጣት ኢትዮጵያ ስሜቱ ደካማ ነው።
የጋራ ከሚያስብሉን መካከል ቋንቋ አንዱ ሲሆን በተለያዩ ክልሎች (ለምሳሌ በትግራይና ኦሮሞ) የመማር ፍላጎትም ሆነ የሚሰጠው ትኩረት ደካማ ነው።

ሌላው አንድ የሚያደርገን የአድዋ ድል ነው። ይሁንና የጋራ መግባቢያ እንዳይሆን ተደርጓል። ለምሳሌ የትግራይና የኦሮሞ ልኺቃን ምኒሊክ ላይ አንድ ዓይነት የጥላቻ፣ እንደ አጥፊ የመቁጠርና ጨቋኝ ናቸው የሚል አቋም አላቸው።

አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጢያ ድንጋይ፣ የጅማውን የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት የመሳሰሉት ወደ መሐል አምጥቶ አገራዊ ሥሜት እንዲፈጠር መሠራት ይገባ ነበር።

ሰንደቅ ዓላማ የጋራ መገለጫ መሆን ነበረበት ግን ʻጨርቅʼ ነው ስለተባለ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ማንም የሚጥለውና ክብር የማይሰጠው ነበር።

ባለፉት 27 ዓመታት አንዱ መሰረታዊ ስህተት ለአገራዊ እሴቶች፣ ለብሔራዊ ተቋማት ተገቢ ትኩረት ያለመስጠት ነበር። በዚህ ምክንያት ኢዮጵያዊነት እየደከመ፣ የአካባቢ ወይም የብሔር ማንነት እየገነነ እንዲሔድ ተደርጓል። በመሆኑም የርስ በርስ ግንኙነታችን እየላላ መጥቷል። የዚህ ጦስ ውጤት አሁን በአማራና ትግራይ እንዲሁም ቀደም ሲል ደግሞ በሱማሌና ኦሮሚያ መካከል ያለው ፍጥጫ ነው።

በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የብሔር ፖለቲካ ኃይሎች ሚዛን ካደላ የመበታተን አደጋ እንደ ሥጋት ይነሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የኃይል ሚዛኑ ወደ አንድነት ጎራ ካጋደለ ማዕከላዊነትም እንደ ሥጋት ይገለፃል። የተሻለ የሚሆነው ምን ቢደረግ ነው?

ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀድ ተገቢ ነው፤ ተፈጥሯዊም ነው። ይሔ ሳይሆን ሲቀር ችግር ይፈጠራል። ነገር ግን ራስን በራስ ማስተዳደር ብቻ መወሰን የለበትም። በማዕከላዊው መንግሥት ላይ የሚኖራቸው ሚና በዛው ልክ ጠንካራ መሆን መቻል አለበት። ስለዚህ አገር የሚመሩት ክልሎች ወይም ብሔር፣ ብሔረሰቦች ወክለው የሚልኳቸው ሰዎች ጭምር ናቸው። ስለዚህ ይሔ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረግ ይጠበቃል።

አንደኛ ሕዝቦች ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀድ ግድ ነው። ይህም የፌደራል ስርዓት አንዱ መለያ ባሕሪይ ተደርጎ ይወስዳል። ኹለተኛው ክልሎችን ወይም ሕዝቦችን ወክለው ወደ ፌደራል የሚመጡትና የፌደራል መንግሥትን የሚመሩት አካላት ያንን መነሻ መርሳት ወይም መዘንጋት የለባቸውም። ስለዚህ ኹለቱን ነገር ማጣጣም ይጠይቃል።
ሌላው የፖለቲካ አደረጃጀቶች በተቻለ መጠን ብሔር ተኮር ከሚሆኑ ኅብረ ብሔራዊ መልክ ኖሯቸው፥ ሁሉንም ዜጋ በማያሳትፍ መልኩ የሚደራጁበት ሁኔታ ቢኖር ጥሩ ነው።

ችግሩን ከሥረ መሰረቱ ለመፍታት በመጀመሪያ መደረግ ያለበት ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ዝግጁ መሆን ይጠይቃል። ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል ብዙ ለውጥ እንዲመጣ አይጠበቅም። አንዳንዶች የፖለቲካ ኃይሎችን ጨምሮ ሕገ መንግሥቱ እንዳይሻሻል የሚፈልጉ ሲሆን ብዙዎቹ ግን እንዲሻሻል ይፈልጋሉ። ይሔ ማለት ግን ሕገ መንግሥቱን እንዳለ ማስወገድ ሳይሆን፥ ያሉትን መልካም ነገሮች እንደ መነሻ ወስዶ ችግሮችን ብቻ ነቅሶ በማውጣት በጥሩ አንቀፆች መተካት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲናገሩ እንደሰማኋቸው ኢሕአዴግ እንደ ውሕድ ፓርቲ ለማቋቋም በአባል ድርጅቶች መካከል ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል። ይሁንና በተግባር መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ካሰብክ ሕወሓት ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት እንኳን ትተህ ከአዴፓ ጋር ያለውን ብቻ ብትወስድ እንዲሁም አዴፓ ከኦዴፓ ጋር ያለውን ፍጥጫ ስትመለከት ወደ አንድ እንመጣለን የሚለው ለመቀበል ያስቸግራል። ምናልባት ሕወሓትን አግልሎ ሌሎቹ ሊዋሐዱ ግን ይችላሉ።

በአሁኑ አያያዝ የሚካሔደው የለውጥ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያሸጋግራታል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ?

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በተስፋም በሥጋትም ውስጥ ነው። ተስፍውን እያሰፋን የምንሔደው፥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአደረጃጀቱ፣ ባለው ዕውቀትና ክህሎት፣ በቅርበት ይህንን የፈነጠቀ ተስፋ የበለጠ እንዲለመልም በማድረግ ነው። በተለይ ምሁራን ይህንን ነፃነት ተጠቅመው ሐሳባቸውን በመግለጽ ተጽዕኖ መፍጠር አለባቸው። ሌላው ሕዝቡ በአጠቃላይ ይሔንን ተስፋ በሚያለመልም መልኩ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። ከʻሆይ ሆይʼ ፖለቲካ መውጣት አለበት። በተለይ ደግሞ ወጣቱ ነገሮችን በሚዛን እየለካ ሰከን ብሎ ጉዳቱንም ጥቅሙንም ማየት ይጠበቅበታል።

በነገራችን ላይ እንደ ዶ/ር ዐቢይ ዕድለኛ መሪ በዚህች አገር ነበረ ብሎ ማስቀመጥ ይከብዳል። መጀመሪያ ላይ ምንም ሳይሠሩ በቃላቸው ብቻ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተቀባይነት አግኝተዋል። ውጪ አገራትም የነበረው የሕዝቡ አቀባበል የሚገርም ነበር። ይህንን የሕዝብ ድጋፍ በአግባቡ ይዞ በማሳደግ የተወሰነ ጥሩ ሔዱና፥ ከግማሽ ዓመት በኋላ ክፍተቶች ታይተዋል።
አንደኛ በየመድረኩ የሚናገሯቸውን ንግግሮች የተወሰነ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሚያስቆጡ፣ የሚያስከፉ፣ ከመሪ የማይጠበቁ ዓይነት ሆነው የተገኙበት ሁኔታ አለ።

ኹለተኛው እሳቸው የሚመሩት ድርጅት ኦዲፒ ስግብግብ የመሆንና ሁሉንም የእኛ ነው የማለት ዓይነት ዝንባሌ አሳቷል። ይህንን በእርግጥ የተማሩት ከሕወሓት ነው። ሕወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሁሉንም ነገር የራሱ የማድረግ ትግበራ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን፣ ወታደራዊውን፣ ደኅንነቱንም የራሱ ሰዎች እንዲቆጣተሩት አድርጎ ነበር። በመሆኑም ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ ግንኙነት፣ አምባገነንነት ነግሶ ነበር። አሁን ኦዲፒ እየደገመ ያለው የሕወሓት የድሮ አካሔድ ይመስላል። ይሔ ደግሞ በተለይ የአዲስ አበባንና አማራን ሕዝቦች ሥጋት ላይ ጥሏል።

ኢንጅነር ታከለ ዑማን ከኦሮሚያ አምጥቶ የአዲስ አበባ ከንቲባ አደረገ፣ ታከለ ዑማ ደግሞ ኦሮሞ መሰብሰብ ጀመሩ የሚል ከሐሜት የዘለለ በተግባር የተፈጠሩ ችግሮች አሉ። ከዛም አልፎ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ኦሮሞዎች የከተማዋ ኗሪ ለማድረግና የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እየተሠራ ነው በሚል በግልጽ[የኦዲፒ ባለሥልጣናት] የተናገሩበት ሁኔታ አለ። ይሔ በመሰረቱ ወንጀል ነው። ከተሜነት በራሱ ተፈጠሯዊ ሒደት የሚካሔድ እንጂ ሰው አምጥቶ ለማስፈር መሞከር ስህተት ነው። ሕዝቡ አስቦበትና አቅዶበት አዲስ አበባ ለመኖር ካልመጣ በስተቀር መሬት ቢታደለው፣ ኮንዶሚኒየም ቢሰጠው ሸጥቶት ተመልሶ መሔዱ አይቀርም።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አዲስ አበባ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ራሷን በራሷ የምታስተዳድርና ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ከተማ ነው። አሁን ግን እየገሆነ ያለው አዲስ አበባን ልክ እንደ ማንኛውም የኦሮሚያ ከተማ የመቁጠር አዝማሚያ ይታያል።

ሐሳቤን በኹለት ምሳሌዎች ላሳይህ። የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እያከፍፈልን ነው። ለአዲስ አበባም 6 ሺሕ ኮታ ደርሷታል፤ ቤት እንዲገነባለቸው ተደርጓል ተብሏል። ይሐሔ ለምን ተደረገ የሚል ጥያቄ አለኝ። አዲስ አበባ እኮ የኦሮሚያ ክፍል አይደለችም። እነሱ ፌደራል መነግሥቱን ስለሚመሩ፣ ከንቲባውም አሮሞ ስለሆኑ ነው እንጂ ከንቲባው የሌላ ብሔር ቢሆን ለምን ብሎ ይጠይቅ ነበር። ሱማማዎች፣ አማራዎች፣ ትግሬዎች ለምን መጥተው አዲስ አበባ ላይ ይስፈሩ አልተባለም። ሕወሓት እንካን ያላደረገውን ነው እየሠሩ ያሉት።

ይሔ በጣም አሳሳቢ ነገር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሥጋትንም ከሚፈጥሩ ነገሮች ይመደባል።
ሌላ በግልጽ በሚዲያ ሲነገር የሰማሁት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሆስፒታሎችን ለመገንባት የኦሮሚያ መንግሥት ዕቅደ ይዟል። ለዚህ ፕሮጀክት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሎ፥ አዲስ አበባ 1 ቢሊዮን ብር ችሏል። ʻኦሮሚያ ክልል ለሚሠራው ፕሮጀክት፥ ያውም አብዛኛው የፕሮጀክት ወጪ አዲስ አበባ በጀት የሚመድብበት ምን ምክንያት አለ? የአዲስ አበባ ምክር ቤት እና ካቢኔ አባላት ምንድን እየሠሩ ነው?ʼ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለውጡን የሚቀለብሱ ሥጋቶች ናቸው።
ይሔም ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ ታሪክና ሕዝቦች ፋላጎትና ሥጋት አንፃር ኢትዮጵያ እንደው ዝም ብላ የምትበተን ሕዝብ ወይም አገር አይደለም። በርግጥ አሁን ያለው የፌደራል አደረጃጀት ለዚህ ክፍተት ፈጥሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here