“መደመር” እና የነገዋ ኢትዮጵያ

0
858

የለውጥ ተስፋ ከዚያ የመከነ የለውጥ ዕድል ትዝታ ታሪኳን ደጋግሞ የሚጎበኛት ኢትዮጵያ አሁንም የለውጥ ጎዳና ላይ ነች ማለት ይቻላል። ይነገር ጌታቸው ይህንን በማጤን የአሁኑ ለውጥ እና የመደመር ፍልስፍናው አዲስ ሳይሆን ደግመን እየደገምነው ያለነው ታሪካችን ነው በሚል የላኩልንን መጣጥፍ ክፍል አንድ እነኾ!

ወደብ አልባው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬም እየቀዘፈ ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አምስት የለውጥ ዕድሎችን ቢያበላሽም አሁንም በቃኝ አላለም። ደግሞ ስድስተኛውን ተስፋ አድርጎ ጉዞወን ቀጥሏል። ከተጀመረ 12 ወራት ያስቆጠረው ወቅታዊው የለውጥ እንቅስቃሴ ከጀመረ ወዲህ የለውጥ ሾተላይ በተጠናወታት አገር ውስጥ መካሔዱ ሥጋት ሲያጭር ወዲያ ከታሪክ ተምረንስ ቢሆን የሚለው ሐሳብ ተስፋ ይለግሳል። ይህ ደግሞ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መራሹን የፖለቲካ ዝመና ከታሪክና ከአሁናው ገጽታዎች አንፃር እንድንመለከተው ያስገድደናል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ከአንድ እጅ የጣት ቁጥር የሚስተካከሉ የለውጥ አጋጣሚዎችን አምክናለች። 1953 መነሻ አድርገን፣ 1966 አስታውሰን፣ 1983 ደጃፍ ደርሰን፣ የሕወሓትን መሰነጣጠቅ ዘክረን ምርጫ ዘጠና ሰባትን ብናወሳ “የኢትዮጵያ ማሕፀን ለምለምነት” ለውጥን ያካተተ እንደሆነ እንረዳለን። ግን በዚች አገር ለውጥ አይበረክትም። ተነሳ ሲባል ይሞታል። ሞተ ሲባል ይነሳል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት እንደ ሰማይ ቅርብ ቢመሥልም ጉዞው ሲጀመር ግን ወገቤን ማለት ይመጣል። ዛሬ የጀመርነው የለውጥ እንቅስቃሴ አሮጌም አዲስም የሚባል ነው። አሮጌነቱ ካነገበው ጥያቄና ከሔደበት መንገድ ይመነጫል። መደመር የሚል ሥም የተሰጠው የአሁኑ ለውጥ ጅምር መሠረታዊ ግቡ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲን ማስፈን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደጋግመው ነግረውናል። ይህ ደግሞ የመደመር ፖለቲካዊ ስሌት አንድም የተለመደው የኢሕአዴግ አስተሳሰብ ነፀብራቅ መሆኑን ሲያሳይ አንድም ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያልተመለሰውን የአገሪቱን ፖለቲካ ሙግት ዕልባት ለመስጠት መወሰኑን ያስገንዝባል።

ትላንትን የመሠለ ዛሬ
የመደመር ፖለቲካ ግብን ብቻ ሳይሆን ሐዲዱንም የተዋሰው ከትናንት ነው። ለዚህ ደግሞ በርካታ ማሣያዎች ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል። ለአብነት ያህል ከ1983 የለውጥ ጅምር ጋር ያለውን ተመሳስሎ እንጠቀስ። ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት የአሜሪካ ሸሪክ ሁኖ ነበር። በዚህ የተነሳም ልዕለ ኃያሏ አገር ባዶ ካዘና ለተረከበው ኢሕአዴግ የቢልዮን ዶላር ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ አድርጋለች። የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤትም የምኒልክን ቤተ መንግሥት በረጀም ገመድ አስሮ መከታተል ጀምሮ ነበር። በዚህ ሒደት ኢሕአዴግ ምዕራባዊ ዲሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባት ሞከረ። በወታደራዊ ድሉ ሳይኩራራ ጊዜያዊ መንግሥት ሳይሆን የሽግግር መንግሥት መሠረተ። ለደርግ ውደቀት ምንም አስተዋፅዖ ያልነበረው የፖለቲካ ኃይል ሁሉ በለውጡ ሥልጣንን እንደ ጅብ ቆዳ ለመቀራመት አኮበኮበ።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በደርግ ወቅት የተፈፀሙ ዘግናኝ ታሪኮችን እያስታወሰ የሕዝቡን ተስፋ ከትናንት የባሰ አይመጣም በሚል ትርክት አፀና። በደርግ ፕሮፖጋንዳ ተሰላችቶ ኢቲቪን ዓይንህን ለአፈር ብሎ የኖረ ሁሉ ጣቢያው የእውነት ምንጭ ነው ብሎ ይሟገት ያዘ። እስከ ደርግ የውደቀት ዋዜማ 2000 ወታደር የነበረው ኦነግም ራሱን ዋና ተፎካካሪ አድርጎ ከሌሎች የተሻለ ሥልጣንን ለማግኘት በቃ። ሕወሓት ለድል ከበቃባቸው መንገዶች አንዱ የሆነውን የፕሮፖጋንዳ ሥራ ለኦነግ አምኖ አስረከበ። ከማስታወቂያ ሚንስትርነት በተጨማሪም የግብርናና ትምህርት ሚንስተርነት ቦታዎች ለኦነገ ሰዎች ተላለፉ። ይህ የሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ የመደመር ስሌት ግን በተለያዩ አለመግባባቶች በጊዜ ሒደት መናጋት ጀመረ። በመድብለ ፓርቲ ስርዓት የተጀመረው የኢሕአዴግ አገዛዝም ወደ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ከዛም ወደ አንድ ግለሰብ አመራር ተንደረደረ። ብልጭ ያለው የዴሞክራሲ ብርሃን እንደ ጠዋት ጤዛ ረገፈ። አምባገነናዊነት ነገሰ።

ዛሬ የተያያዝነው የለውጥ እንቅስቃሴ ጅማሮ ከኹለት ዐሥርት በፊት ከነበረው ጋር የሚያመሣስለው ነገር ብዙ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ በጣም ፈጣን የሚባሉ ለውጦችን ለማምጣት ጥረዋል። የድኅረ 83 ፖለቲካ ላይ እንደተስተዋለው የተራቆተውን የአገሪቱ የዶላር ክምችት ለማስተካከል የምዕራቡን ዓለም ደጅ ጠንተዋል። ተሳክቶላቸውም የቢሊዮን ዶላር ቀጥጠኛ የበጀት ድጋፍን ከዓለም ባንክ አግኝተዋል። በእጃቸው በገባው ሥልጣን ሳይኩራሩም የተቃዋሚውን ጎራ ወደ አገሩ ገብቶ ተፎካካሪ እንዲሆን የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። የሽግግር መንግሥትን ሳይሆን የሽግግር ፖለቲካን እንደሚመራ ሰው በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች በመንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይ ለማሳተፍ ጥረዋል። በሽግግር መንግሥቱ ወቅት እንደታየው ሁሉ የመንግሥት የፕሮፖጋዳ ተቋማትን በየበላይነት እንዲመሩ የተቃውሞን ጎራ አባላት ሹመዋል። መረራ ጉዲናን (ዶ/ር) የኢቢሲ ቦርድ አባል፣ አሕመዲን ጀበል የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሐን የቦርድ አባል እንዲሆኑ አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንትሩ ተፎካካሪ ያሏቸውን ወገኖች ወደ ሚኒስትርነት ቦታው ባያስጠጉም ዝም ብለው ግን አላለፏቸውም። በየነ ጴጥሮስን (ፕ/ር) የኮተቤ ዩኒቨርስቲ ቦርድ አባል፣ ልደቱ አያሌውን የመንግሥት ፕራቬታይዜሽን ቦርድ አባል በማድረግ አሳትፈዋል። 2010 ከ1983 የተማረው ግን ይህን ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በቀደመው አመራር ተፈፀሙ የተባሉ ግፎችን እያነፈነፈ ለሕዝብ በማድረስ የአዲሱን ስርዓት መሠረት ትናንትን በመፍራት ላይ እንዲቆም ደፋ ቀና ብሏል።

የዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ በከፊል የትናንት ምሮከኛ ነው። ነገር ግን የራሱ መልክም እንዳለው ሊዘነጋ አይገባም። በዚህ ምክንያትም ስለነገዋ ኢትዮጵያ ስናወራ የመደመር ፖለቲካ ምን የተለየነ ነገር አለው የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል። ትናንት ካመለጡን ዕድሎችስ ምን ተምሮ ይሆን ያስብለናል። በጥቅሉም ከታሪካዊና አሁናዊ ሁነቶች በመነሳት መዳረሻችን የት ነው የሚለውን መገመትም ይገባል።

ድንበር አልባው “መደመር ”
ኢትዮጵያ ባለፉት ዐሥራ ኹለት ወራት እያካሔደች ያለችው የፖለቲካ ዝመና ተሐድሶና ሽግግር የሚሉ ቃለትን እያፈራረቀ የሚጠቀም ነው። የቀድሞው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሽፈራው ሽጉጤ የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግንባሩ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ፓርቲው የጀመረው የመታደስ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ተናግረው ነበር። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም ከሥልጣን የመልቀቃቸው ምስጢር የተሐድሶው አካል መሆኑን አብራርተዋል። በዚህ ሒደት ሥልጣነ መንበሩን የተቆናጠጡት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግን የእሳቸው ወደ አመራርነት መምጣት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መሆኑን ለመናገር አፍታ አልወሰደባቸውም። ከእንደራሴ ምክር ቤቱ ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኝተው ባሰሙት ንግግርም ዛሬ በአገራችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍን ከፍተናል። ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርንም አድርገናል ብለዋል። ከዚህ በኋላም ተሐድሶ የሚለውን ቃል እርም ብለው እሳቸው የሚመሩት መንግሥት አሸጋጋሪ መሆኑን ሰብከዋል። በአሜሪካ አገር በነበራቸው ቆይታ ለተነሳላችው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም የሽግግር መንግሥት የሚለውን ሐሳብ እርሱት እኔ አሸጋጋርችኋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ ያለፈው መጋቢት የተጀመረው የፖለቲካ ዝመና ተሐድሶ ነው ወይንስ ሽግግር የሚባለው እንድንል ያደርገናል።

መሐመድ ሳልህ “Expanding Ethiopian’s Democratic Space: Aspirations, Oppourtunities, Choices” በተባለ ጥናታቸው የፖለቲካ ተሐድሶ ማለት ስርዓትን ከመቀየር ይልቅ ስርዓትን ማደስ መሆኑን ያብራራሉ። ከዚህ በተቃራኒው ግን የፖለቲካ ሽግግር የስርዓት ለውጥን ተክትሎ የሚስተዋል ነው ይላሉ። ከፊውዳል ወደ ወታደራዊ፣ ከወታደራዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ የሚደረግ ለውጥም ሽግግር እንደሚባል ይተነትናሉ። የአንድ አገር ፖለቲካ በዜጎችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማዘመን መጣሩና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ማሥፋቱ ግን ለውጥ/ሽግግር ሳይሆን ተሐድሶ ይባላል ሲሉም ይጠቅሳሉ።

ይህ የሳልህ ሐሳብ ለሌላው የፖለቲካ ልኂቅ ሕዝቅኤል ጋቢሳ (ፕ/ር) የሚዋጥ አይመስልም። የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካ “Managing Poltitical Transition in Ethiopia: The choice Factor” በተባለ ጽሑፋቸው በሥፋት የተመለከቱት እኒህ የታሪክ ምሁር ባለፈው መጋቢት የተጀመረው የፖለቲካ ዝመና ሽግግር እንደሆነ ያትታሉ። ይሁን እንጅ ዘርፈ ብዙ በሚባለው የዓለም የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ኢትዮጵያ የተያያዘቸው መንገድ ከዚህ በፊት ከተስተዋሉት ጋር እንደማይገጥም ይጠቅሳሉ። የፖለቲካ ሽግግር ከራሱ ሥልጣን ከያዘው ፓርቲ፣ ከተቃዋሚዎች አልያም ሙሉ በሙል ስርዓትን ከሚገረስሱ ወገኖች እንደሚመጣ የሚገልጹት ሕዝቅኤል “መደመር” ግን ከእነዚህ ውስጥ ከአንዱም ጋር የሚሰምር አይደልም ይላሉ።

ባለፈው መጋቢት የተጀመረው የአገራችን የለውጥ እንቅስቃሴ የተሐድሶና የሽግግርን ድንበር የሚያፈርስ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ተካሔደው ከከሸፉት የተለየ ነው። በዚህ ምክንያትም ዛሬ የተያያዝነው ለውጥ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ በተሐድሶ አልያም በሽግግር የሚወከል ሳይሆን ዝንቅ ባሕሪ ያለው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ተሐድሷዊ ሽግግር ሊባልም ይችላል። በኢትዮጵያ አሁን እየተቀነቀነ ያለው የመደመር ፖለቲካዊ “ፍልስፍና” በነባር ስርዓት ላይ የሚደርግ ጥገና ብቻ ሳይሆን ነባር ስርዓትንም የሚያፈርስ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የተጀመረው ለውጥ ለመሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለታዛቢዎችም አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የመደመር ፖለቲካ ግን የሚለየው ከላይ በተጠቀሰው ዝንቅ ባሕሪው ብቻ አይደለም። ይልቁኑም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድና ብሔራቸው በአገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ አዲስ የሚቆጠር ነው።

የዛሬው ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በድኅረ እውናዊነት (post truth politics) የሚዘወር ነው። ምሥራቅ አፍሪካን የሚያተራምሰው የፖለቲካ ንግድ በአንድ በኩል በማኅበራዊ ድረገጾች የሚዘወረው አክራሪ ብሔርተኝነት በሌላ በኩል የአራት ኪሎን የሰርክ ሕይወት አናግተውታል። ጆን ማርካኪስ እንደሚለው ደግሞ አማራና ትግራይ የተፈራረቁበትን የምኒልክ ቤተ መንግሥት አሁን ኦሮሞ ባለተራ ሁኖበታል። አንዱ ሲመራ ሥልጣን ያጡት ኹለቱ ብሔሮች የሚያኮርፉበት የአገራችን ፖለቲካም ተራው ደርሶ ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር አማራና ትግራይን ተቀናቃኝ አድርጓል። ስለመደመርና የነገዋ ኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል ስናወራ እነዚህ አሁናዊ ሁነቶች የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል።
(ሳምንት ይቀጥላል)

ቅጽ 1 ቁጥር 22 የመጋቢት 28 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here